እስራኤል በአየር ኃይል ወታደሮቿ ላይ የጉዞ እገዳ ጣለች

እሥራኤል በአየር ኃይል ወታደሮቿ ላይ የጉዞ እገዳ ጣለች፡፡ ከ10 ወራት በፊት ሐማስ በእስራኤል ምድር ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነበር በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡ አንድ ሺህ 200 ሰዎች በሐማስ ጥቃት ተገድለውብኛል ያለችው እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት የድርጅቱ የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎችን ገድላለች።

በጋዛ የተጀመረው ይህ ጦርነት በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ወደ ሊባኖስ እና የመን እየተስፋፋ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ በሌሎች አካባቢዎችን ሊሰፋ እንደሚችል ስጋት አይሏል፡፡

በተለይም በኢራን ተመራጩ ፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት ወደ ቴህራን ያመሩት የሐማሱ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ መገደል ተጨማሪ ውጥረት ፈጥሯል፡፡

ግድያው በግዛቷ የተፈጸመባት ኢራን እሥራኤልን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን እሥራኤል መቀጣት እንዳለባት እና ርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች፡፡

እሥራኤል ከኢራን፣ ሂዝቦላህ እና በሌሎች ሀገራት የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች አማካኝነት ጥቃት ይደርስብኛል በሚል በተጠንቀቅ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡

ግብፅ እና ጆርዳንን ጨምሮ ሌሎችም ሀገራት ወደ እሥራኤል የሚተኮሱ የአየር ላይ ጥቃቶችን እንደሚያከሽፉ አስቀድመው አስጠንቅቀዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ እሥራኤል የአየር ኃይል ወታደሮቿ ወደ ውጪ ሀገራት እንዳይጓዙ ያስጠነቀቀች ሲሆን ወታደሮቹ በኢራን እና አጋሮቿ ዒላማ ሊዳረጉ እንደሚችሉ በመስጋት ነው፡፡

አሜሪካ በበኩሏ እስራኤልን ከጥቃት ለመጠበቅ ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎችን አስቀድማ ወደ ስፍራው የላከች ሲሆን ተጨማሪ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች እንዲላኩም መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ባሳለፍነው ሳምንት ኢራን እና አጋሮቿ በእሥራኤል ላይ የተቀናጀ ጥቃታቸውን በሦብት ቀናት ውስጥ እንደሚያደርሱ አስጠንቅቆ ነበር፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You