የሚያጋጥሙን የሕይወት ፈተናዎች መማሪያ ወይም ለመውደቂያችን ምክንያት ይሆናሉ። ከችግር ተምሮ የራስን ቀጣይ ኑሮ የተሻለ ለማድረግ መጣር ስኬት የመሆኑን ያህል፤ ካለፈው ትምህርት በመውሰድ ሌሎች በዚህ መንገድ እንዳያልፉ ትምህርት መስጠት እና አርአያ መሆን የስኬቶች ሁሉ ቁንጮ ነው።
አንዳንዴ ለችግር መጋለጣችን ሌሎች ምክንያት እንደሚሆኑት ሁሉ፤ ለሰው መድኃኒቱ ሰው ነው እንዲሉ፤ ከችግር ለመውጣታችን፣ ለስኬት የመብቃታችን የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ሰዎችም አይጠፉም።
እነዚህን በተቸገርንበት ጊዜ እጃቸውን የዘረጉልንን ቅኖች ለመርዳት የግድ እነሱ እስኪቸገሩ መጠበቅ ላይኖርብን ይችላል። ሌሎች እኛ ካሳለፍናቸው ሁኔታዎች ጋር እየታገሉ ያሉ ብዙ ነፍሶች አሉና እነዚህን ተመልሶ መርዳት የሚያስመሰግን ተግባር ነው።
በዚህ ደግሞ አንዱ የምንረዳበት መንገድ ያሳለፍነውን ወጣ ውረድ ለሌሎች ብርታት እንዲሆን በመንገር ነው። ይህን መርህ በተግባር ማሳየት ከቻሉ ሴቶች መሀል ደግሞ የዛሬዋ ባለታሪካችን አንዷ ናት።
የዛሬዋ ባለታሪካችን የተለያዩ የሕይወት ፈተናዎች ርሃብን፣ ጥሙን እና የሚደርስባትን ጥቃት ተቋቁማ ማለፍ የቻለች እናት ናት። እነዚህ ችግሮች ሳይበግሯት ሁለት ልጆችን ከጎዳና አንስታ አሳድጋለች። ያጋጠሟትን ችግሮች በምትጋፈጥበት ወቅት የአካባቢው እና የወረዳው ድጋፍ አልተለያትም ነበር። የተደረገላትን ውለታ ሳትረሳ አሁን ለበርካቶች ድጋፍ በማድረግ እየረዳች ትገኛለች።
በሰራችው በጎ ሥራዎች የተለያዩ ዋንጫዎች፤ ሜዳሊያዎች፣ የምስክር ወረቀት ተሸልማለች። በተጨማሪም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሽልማት ተበርክቶላታል። ይህቺ በጎ አድራጊ ጌጤነሽ ኃይሌ ትባላለች። በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በበጎ ፈቃድ ሥራ እና ማስተባበር ለ11 ዓመታት እያገለገለች የምትገኝ ሴት ናት። ትውልዷ በኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ ሲሆን፤ ትምህርቷን እስከ ስምንተኛ ክፍል ነበር የተማረችው።
‹‹ትምህርቴን የተከታተልኩት በአዲስ አበባ ከተማ ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት ነው። የተማርኩት እስከ ስምንተኛ ክፍል ነው›› ስትል ትገልጻለች። አንዳንዴ ያልጠበቅነው እና ያላሰብነው ነገር ወደ ሕይወታችን ይመጣና የሕይወት አቅጣጫችንን እንድንቀይር ያስገድደናል። ባለታሪካችን ከነበረችበት የሕይወት መንገድ አቅጣጫዋን ለመቀየር የሚያስገድድ ነገር አጋጠማት።
‹‹ትምህርቴን ስምንተኛ ክፍል እየተማርኩ ሳለ እናቴ በድንገት ስትሞትብኝ ትምህርቴን መቀጠል አልቻልኩም። ምክንያቱም ሊያስተምረኝ የሚችል ዘመድ ስላልነበረኝ ለሥራ ወደ ሌላ ክልል ሄድኩ››ስትል ታስረዳለች።ለሥራ በሄደችበት በአጋጣሚ ከባለቤቷ ጋር ተዋውቀው ትዳር መስርተው አምስት ልጆችን ወልደዋል። ‹‹አሁን ሁሉም ልጆቼ ቦታ ቦታ ይዘውልኛል›› ትላለች።
ጌጤነሽ ትዳር መስርታ አምስት ልጆችን ብትወልድም፤ ከባለቤቷ ጋር በገጠማት ተደጋጋሚ አለመግባባት ምክንያት አብረው ሊዘልቁ አልቻሉም።
ጌጤነሽ ሰውን ለመርዳት ድህነት ያልበገራት እናት ናት። አምጣ ከወለደቻቸው ልጆች ውጭ፤ ለሌሎች ልጆችም እናት ለመሆን በቅታለች። ባለታሪኳ ያሳደገችው አምስት ልጆች ብቻ ሳይሆን፤ ሌሎች ሁለት ልጆችን ከጎዳና አንስታ ለወግ ለማዕረግ አብቅታለች።
ሁለቱን ልጆች ከጎዳና አንስታ ልታሳድግበት የቻለችበትን አጋጣሚ ጌጤነሽ ስትናገር ‹‹ ልጆቹ ጎዳና ላይ ብርድና ፀሀይ ሲፈራረቅባቸው በተደጋጋሚ እመለከት ነበር›› ስትል ታስረዳለች።‹‹በተለይ አንደኛው ልጅ ከደቡብ ክልል ነበር የመጣው በጣም ነበር የሚያሳዝነው። ወስጄ አሳድጌው እስከ ዘጠነኛ ክፍል አስተምሬው ነበር። ነገር ግን እኔ ሳላውቅ በመከላከያ ተመዝግቦ ሄዶ ሞተ።››ትላለች።
ከጎዳና ወስዳ ካሳደገቻቸው ልጆች አንደኛውን በሞት ብትነጠቅም፤ በአንደኛው የተካሰች ትመስላለች። አንዱ ያሳደገችው ልጅ በህክምና ትምህርት ተመርቆ እየሰራ እንደሚገኝ ትናገራለች።‹‹አሁንም ቢሆን እንደዚህ ጎዳና ላይ የወጡ ልጆችን ስመለከት ዝም ብዬ አላልፍም።ከየት ነው የመጣቹት? ከገጠር ያመጣችሁ ምንድን ነው?›› በማለት እጠይቃለሁ ትላለች።
ጌጤነሽ ያሳደገቻቸውን ሁለት ልጆች ከጎዳና ወስዳ ለማሳደግ የነበራት ኢኮኖሚ ጠንካራ የሚባል አልነበረም። ራሷን ለማስተዳደር በአንድ ፋብሪካ ተቀጥራ የምትሰራ ሲሆን፤ ከጎዳና ያነሳቻቸውን ልጆች ለማሳደግ ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራት ትሞክራለች።
‹‹ቀን ቀን በበጎ ፈቃድ ማስተባበር ሥራ ወረዳ እሰራለሁ፤ ከዛ በኋላ ማታ 12 ሰዓት ወደምሰራበት የፋብሪካ ድርጅት እሄዳለሁ። እዛ ስሰራ አድሬ ጠዋት ነው የምወጣው›› ትላለች። ‹‹ያለኝ የገንዘብ አቅም ዝቅተኛ ቢሆንም፤ ሌሎችን ስረዳ የተመለከቱ የሰፈር ሰዎች፤ “እሷ እኮ ከራሷ አልፋ ሌሎችን የምትረዳ ናት” እያሉ ይደግፉኛል። በተጨማሪም ወረዳዬም ያግዘኛል ››ስትል ትገልጻለች።
ጌጤነሽ በተሰማራችበት የበጎ ፈቃድ ሥራ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርታ ድጋፍ ትሰጣለች። የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት ችግር ላይ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን መለወጥ እንዲችሉም ታስተምራለች። ጌጤነሽ እንደምትናገረው ጎዳና ላይ ለወጡ ሴቶችና ሕፃናት ሕይወታቸውን መቀየር እንዲችሉ እና ሰርተው እንዲለወጡ ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት ትምህርት ትሰጣለች። ‹‹ጥቃትም የደረሰባት ሴት ካለች እምባዋን አብሼላት እስከ ፍርድ ቤት ድረስ እወስዳታለሁ ስትል›› ታስረዳለች።
ጥቃት ለደረሰባቸው በምን መልኩ ወደ ህግ እንደሚሄዱ የምታስረዳው ወ/ሮ ጌጤነሽ፤ ከህግ አወሳሰን ጋር በተያያዘ ለምሳሌ፤ አንዲት ሴት ላይ የመደፈር ጥቃት ተፈጽሞ ጥቃት አድራሹ ላይ ስድስት ዓመት ብቻ የሚፈረድበት ከሆነ ይግባኝ በማለት አብራ ከተጠቂዋ ጋር እንደምትቆም ታስረዳለች ።
ይህንንም ስራ ስትሰራ ከአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ታስረዳለች። አስፈላጊ ሲሆንም ጠበቃ በነጻ ሊቆምላቸው እንደሚችል ትናገራለች። ‹‹አንዳንንድ ጊዜም ራሴ የምሄድባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ። ፍርድ ቤት ላይ በሴቶች ጥቃት ላይ የሚሰሩ አካላት ስልካቸው አለኝ። የደረሰውን ጥቃት በዝርዝር እነግራቸው እና ወደ ማጣራት ስራ እንዲገቡ አደርጋለሁ›› ትላለች።
‹‹ለምሳሌ ባለፈው አንድ አባት ልጁ ላይ የመድፈር ጥቃት ፈጸመ። ከዛን ከህግ አካላት ጋር በመሆን ወደ ቦታው ሄደን በማጣራት፤ ልጅቷን መጠለያ ስላለን ወደ መጠለያ አስገባናት፤ ሰውየው በፖሊስ እንዲያዝ ተደርጎ ክስ ተመሰረተባቸው›› ስትል በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በምን መልኩ እንደሚከላከሉ ታስረዳለች።
በሌላ በኩል ደግሞ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሲያጋጥማት ቀስ ብላ በመጠጋት፤ ደላላው እየወሰዳቸው ካሉ ሰዎች ጋር በመቀላቀል እና አብራ የምትሄድ በመምሰል በማጣራት፤ ለህግ አካላት ችግሩን በመጠቆም መፍትሄ ለማግኘት ትሞክራለች።
ጌጤነሽ በምትሰራቸው ስራዎች ምንም አይነት የገንዘብ ክፍያ አይከፈላትም። የበጎ ፈቃድ ስራዎች እንዳይቋረጥ ምሽት ከሚሰሩት ስራ በተጨማሪ ወደ ሀብታም ቤት በመሄድ የተለያዩ ስራዎችን ትሰራለች።‹‹ጠዋት ከስራዬ ወጥቼ ወደ ወረዳ እስከምመጣ ድረስ ሁለት መኪናዎችን አጥባለሁ። ከዛ በኋላ ወረዳ መጥቼ የሚሰራ ስራ ካለ ቶሎ እጨርስና ወደ ቀታና እሄዳለሁ›› ትላለች።
‹‹ልጆች ይዤ በርካታ የርሃብ እና የችግር ግዜያትን አሳልፌያለሁ›› የምትለው ጌጤነሽ፤ የምትሰራቸው ስራዎች ከችግር እንዳላቀቋት ትናገራለች። ስራዎቹ በሴት ያልተለመዱ ቢሆንም፤ ስለለመድኳቸው አይከብደኝም በማለት ትናገራለች።
ጌጤነሽ ሌሎች ሴቶችን በመጨመር ድግስ ባለባቸው ቤቶችም ሄዳ ትሰራለች። ስራ አጥተው እቤት ቁጭ ካሉ ሴቶች አንድ ወይ ሁለት ሴቶችን ከእኔ ጋር በመያዝ ሄጄ በመስራት ሁላችንም ተጠቃሚ እንድንሆን አደርጋለሁ ስትል ታስረዳለች።
ወደ በጎ ፈቃድ ስራ ከአስር ዓመት በላይ እንደሆናት የምትናገረው ጌጤነሽ፤ በሰራቻቸው የበጎ ፈቃድ ስራዎች በከተማ ደረጃ በተከታታይ አንደኛ በመውጣት ትታወቃለች። በአጠቃላይም ሶስት ዋንጫ እና ሜዳሊያዎችን ተሸልማለች። ‹‹በአንድ ወቅት ባለቤቴ ጥቃት እያደረሰብኝ ስለተቸገርኩ፤ዋንጫዎቹን እያነሳ እየወረወረብኝ ብዙ ፈተና ስላየሁኝ፤ ወንድሜ ጋር እንዲቀመጡ አደረኩ›› የምትለው ጌጤነሽ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተንቀሳቃሽ ስልክ መሸለሟን ትናገራለች።
ጌጤነሽ በኑሮዋ ደካማ መሆኗን በመረዳት አሁን የምትኖርበትን ቤት ወረዳው ነው ሰርቶ የሰጣት። እሷም በተራዋ አቅም የሌላቸውን ሰዎች በመለየት ቤት እንዲሰራላቸው በመጠቆም የተከፈላትን ውለታ መልሳ ለመክፈል እየጣረች ነው።
‹‹ሰዎችን ለመርዳት ጊዜ አልወስድም። ጉዳይ ቢኖርብኝ እንኳን ከበጎ አድራጎት በላይ የማስቀድመው ነገር አይኖረኝም›› የምትለው ጌጤነሽ፤ የበጎ ስራ በምትሰራበት ወቅት ሰዎች እየደወሉ እንዳያስቸግሯት ስልኳን ጭምር እንደምታጠፋ ትናገራለች።
የበጎ ፈቃድ ስራው ከጌጤነሽ አልፎ ልጆቿ ጋር ጭምር እንደገባ ትናገራለች። ለበጎ ፍቃድ ስራ ልጆቿ ጭምር ስሱ ልብ እንዳላቸው ታስረዳለች። ‹‹ትልቋ ልጄ ጤና ጣቢያ ነው የምትሰራው፤ ከስራ አድራ ስትመጣ ያለውን ስራ ትሰራለች፤ እሷ ስትሄድ ደግሞ ሌሎች ልጆቼ ወደ ቤት ስለሚመለሱ የቤት ውስጥ ስራውን እየተጋገዙ ይሰራሉ፤በዚህም ህይወትን እየተጋገዝን እንመራታለን ››ትላለች።
የጌጤነሽ የልጅነት ህልም የተቸገሩትን ሰብስቦ መርዳት ነበር። ለሰዎች ጥሩ ማሰብ፣ የተቸገሩን ማንሳት ነበር ።ይኸው ምኞት አሁን እውን መሆኑ እንዳስደሰታት ትናገራለች። ‹‹ለሰው ልጅ ቅድሚያ እሰጣለሁ፤ ተቸግረው ወደ ወረዳ እያለቀሱ ሲመጡ አብሬ አልቅሼ፣ የተራቡትንና የተጠሙትን ባለኝ አቅም አብልቼ አጠጥቼ ሌላ ችግር ካለባቸውም በተቻለኝ አቅም ደግፌ ከጎናቸው እቆማለሁ›› የምትለው ጌጤነሽ፤ ይህን ስታደርግ የውስጥ እርካታ እንደሚሰማት ትናገራለች።
ጌጤነሽ እንደምትለው በጎ ስራ እርካታ ይሰጣል። ያለንን ነገር ለሌሎች ማካፈል ትልቅ ደስታ ያጎናጽፋል።‹‹ ድሮ እኔ ልብስ አልነበረኝም የዚህ የወረዳው አመራሮች ናቸው ያለበሱኝ ›› ስል ያለፈችበትን ችግር ታስታውሳለች።‹‹ዛሬ እኔ ባለ ልብስ መሆን ችያለሁ። ስለዚህ እንደኔ ለተቸገረች ሴት ካለኝ አንድ ቀሚስ ብሰጣት ለእኔ እረፍት ነው። ሌሎችን ሳስተምር፤ ድሮ እኔ እንዲሁ ነበርኩ ነው የምለው። ስለዚህ ያጣም ያገኛል፤ ያገኘም ያጣል ›› ስል ታስረዳለች።
ባለታሪኳ እንደምትናገረው፤ ወደ ወረዳ ተቸግረው እያለቀሱ የሚመጡ ሴቶች ሲኖሩ፤‹‹ ወደ ጌጤነሽ ሂዱ››ይባላሉ። እሷ ጋር ሂዱና ተሞክሮ ውሰዱ በማለት ወደ እሷ ይላካሉ። ‹‹እኔ ጋር ሲመጡ አጽናናቸዋለሁ፤ ከዚህ በፊት እኔም በርካታ ችግሮችን እንዳለፍኩ አስረዳቸዋለሁ። እናም በችግር ውስጥ ላሉት የማስተላልፈው በትግስት ሁሉም ያልፋል በርቱ የሚል ነው›› ስትል ትናገራለች።
የጌጤነሽን ምክር በመስማት አሁን ላይ ሰርተው ማደር እና ለሌሎችም ድጋፍ ማድረግ የጀመሩ መኖራቸውን ታስረዳለች። እናም በቀጣይ ባላት አቅም የተቸገሩትን ለመርዳት ትልቅ ፍላጎት እንዳላትና ከራሷም ተሞክሮ በመነሳት ሴቶች ወድቀው እንዳይቀሩ የበኩሏን እገዛ እንደምታደርግ በመናገር ሃሳቧን ቋጭታለች።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም