መንግሥት ከሰሞኑ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን አስመልክቶ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል። ይህንኑ መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱን አሻሽሏል። ባንኩ፣ ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮም ሥራ ላይ ያዋለው ማሻሻያ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ወደሆነውና በገበያ ላይ ወደተመሰረተው የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት እንደሚያሸጋግራት አመላክቷል። በኢኮኖሚ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና መዛባት እንደሚሻሻልም ይታመንበታል ሲል አስረድቷል። የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሰረት የሚተገበር እንደሚሆንም አብራርቷል።
ኢትዮጵያ፣ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጓን ተከትሎ ሰሞኑን ባንኮችም አዲሱ የምንዛሬ ተመንን መተግበር ጀምረዋል። ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓቱ ተግባራዊ ከመሆኑ አስቀድሞ የአንድ ዶላር ዋጋ 58 ብር አካባቢ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ሥርዓቱ ተግባራዊ በመሆኑ ይህ አኃዝ ወደ 100 ብርና ከዚያ በላይ ማሻቀቡ የሚታወቅ ነው። በጥቁር ገበያው ሲቸበቸብ ከነበረው ዋጋ ጋርም ያለው ልዩነት እየጠበበ መምጣቱም የአደባባይ ምስጢር ነው።
ይሁንና መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ከማድረጉ ጋር ተያይዞ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ በመሆኑ የብር የመግዛት አቅም ተዳክሟል። ይህን ተከትሎም ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ቀደም ሲል የነበራቸውን ሸቀጥ በመሰወራቸው የሸቀጥ ዋጋ መናሩ እየተነገረ ይገኛል፤ ነገር ግን መንግሥት ደግሞ ሸቀጥ በሚሰውሩና ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ በግልጽ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል።
ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ዋጋ እንዲካሄድ መወሰኑ ጠቀሜታው ምንድን ነው? አስፈላጊነቱስ ምን ይመስላል? የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መዝለቅስ ይቻል ይሆን? ለሚሉ ጥያቄዎች በዘርፉ የዳበረ ልምድ ያላቸው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከሸገር ኤፍ.ኤም 102 ነጥብ አንድ ሬዲዮ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስና የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) ለሪፖርተር ጋዜጣ ያጋሩትን ሃሳብ ለጽሑፋችን በዋቢነት ተጠቅመናል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ መንግሥት ሰሞኑን ይፋ ያደረገው ውሳኔ እንዲያውም የዘገየ ነው ባይ ናቸው። ለሁለት አስርት ዓመታት በዚህ ፖሊሲ ዙሪያ ሲናገሩ መቆየታቸውን ደጋግመው የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ “የእኛ ሀገር ኢኮኖሚ እያንዳንዱ ሴሉ በካንሰር ተይዟል። ካንሰር ማለት ደግሞ ከአንድ እስከ አራት ድረስ የተለያዩ ደረጃዎች አሉት። ከአራተኛ ደረጃ ቀጥሎ ይገድላል። እኛም ልክ በኢኮኖሚያችን ያለፉት አስራ አምስትና ሃያ ዓመት ውስጥ ከደረጃ አንድ ካንሰር በሒደት ደረጃ አራት ካንሰር ውስጥ ገብተናል። ስለዚህም በጽኑ ታመናል፤ ለምን ቢባል በተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት ነው። አሁን ግን መድኃኒቱ ተገኝቷል ” ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሁን መታከም አለብን። ሕክምናው ደግሞ ያማል። የካንሰር ሕክምና ደግሞ መርዝ ነው። የካንሰር ሴሎችን የሚገድል ነው። ነገር ግን ደግሞ ለይቶ መግደል አይችልም። መድኃኒቱን ፈርተን አንወስድም ማለት ግን የሚያስከትለው ሞት ነው። ስለዚህ በረጅም ጊዜ የመጣ ችግር ዝም ብለን ምንም ሳይሰማን የምናልፈው ነገር አይደለም። ግን ደግሞ መሆን አለበት። ይሁንና በተለይ አቅም የሌለው ሕዝብ እንዳይጎዳ ድጎማ አስፈላጊ ነው። በቂ ነው ወይ ከተባለ ግን አይደለም። ለግሽበቱ መድኃኒት የሚሆነው ኢንቨስትመትና የገበያ ዓርዓት መስተካከል ሲችል ነው። አሁን የተወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማስታገሻ ሳይሆን መሰረታዊ መድኃኒቱ ነው።
የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት የፖሊሲው ተግባራዊ መሆን ትክክለኛ ጊዜው ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ ከዚህ ሊያልፍ የሚያስችል ጊዜ ግን የለንም ይላሉ። ለተግባራዊነቱ ሌላ ቀጠሮ መያዝ እንደማይቻልም ይናገራሉ። ባለፈው ዓመት አንድ ዶላር በጥቁር ገበያ 95 ብር እየተመነዘረ ባለበት ሰዓት ገበያውን ነፃ እናድርገው ሲባል ‘እስኪ ይቆይ!’ ተብሎ ምንም ለውጥ ሳይደረግ አንድ ዶላር 120 ብር ገባ። አሁንም ገበያውን ሳናስተካክል 140 ብር ይገባል። ስለዚህ ቁጭ ብሎ በመጠበቅ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም ሲሉ ይናገራሉ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ (ዶ/ር) እንደ አቶ ኤርሚያስ ሁሉ ፖሊሲው ተግባራዊ ሲደረግ ሕመም እንዳለው ያመለክታሉ። የገንዘብ ምንዛሪን በገበያ ዋጋ ማድረግ ሊያስከትል የሚችለው ሕመም አንዱ መገለጫ ነጋዴው ሸቀጥ መደበቁና የዋጋ ንረቱ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ። በምርት መሸሸግ ምክንያት በተወሰነ ደረጃ ገበያውን ሊረብሹ የሚችሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። አንዱ መፍትሔ መንግሥት ያወጣውን ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ እስኪሆን መሥራት ነው ሲሉ ያብራራሉ። በዚህ ረገድ ምንም ማወላወል ሳያደርግ በፖሊሲው መሠረት በአግባቡ ሥራዎች መሠራታቸውን መከታተልና መቆጣጠር ተገቢ ነው ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የተወሰደው ርምጃ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው። የውጭ ምንዛሪ ገበያው የተበላሸ ስለነበር መስተካከል ነበረበት። አሁን የተወሰደው ርምጃ ይህን ብልሽት የነበረበትን የውጭ ምንዛሪ ገበያችንን የሚያስተካክል ነው። ነገር ግን ችግሩ ሥር የሰደደ ስለነበር ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል የተባለው ርምጃ ሲወሰድና ሲስተካከል ሕመም አለው። ይሁንና ሕመምን ይዞ መቀመጥ አይቻልም። ሕመሙን በማለፍ ማስተካከል የግድ ነው ሲሉ የአቶ ኤርሚያስን ሃሳብ ያጸናሉ።
ለምሳሌ አንድ ሰው ከባድ ሕመም ላይ ሆኖ ቀዶ ሕክምና ቢያስፈልገው ቀዶ ሕክምናው የሚያመጣበትን ሕመም ፈርቶ ህክምና ሳያደርግ አይቀርም። አሁን የተወሰደውን ርምጃ የማየው እንደዚያ ነው። ቀዶ ሕክምናው ሕመምተኛውን ለጊዜው ከአልጋ እንዳይነሳ ያደርገዋል። ዋናው ነገር ከሕክምናው በኋላ መንቀሳቀስ መቻሉን ማስጠበቅ ነው። ገበያው የሚሠራበትን መንገድ ከፍቷል። ገበያው ጤናማ ሆኖ እንዲሠራ ማስቀጠል ይጠበቅበታል። የተወሰደው ዕርምጃ ከዚህ አኳያ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ የመሆኑን ያህል ብቸኛው ጉዳይ ተደርጎ ግን መወሰድ የለበትም።
መንግሥት ያወጣውን አዋጅ ላነበበ ሰው አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት፣ አራት… ተብለው በደንብ የተቀመጡ ነገሮች አሉ የሚሉት ደግሞ አቶ ኤርሚያስ ናቸው። አሁን ባንኮች ዘንድ ሲስተም ውስጥ የሌሉ ዶላሮች ከአሁን በኋላ መግባት እየጀመሩ ነው። ይህ ማለት አሁን አዋጁ ላይ ቁጭ ያለ ነገር አለ ማለት ነው፤ ቀደም ሲል መንግሥት ከባንኮች ከሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶ ይወስድ ነበር። አሁን ግን ‘አልወስደውም፤ ይቀመጥ፤’ አለ፤ ይህ ስንት ዶላር ነው ቢባል በግርድፍ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ነው። መንግሥት ከሁሉም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ በገባ ቁጥር 50 በመቶ የሚወስደው ማለት ነው። መንግሥት ይህንን ‘ትቼላችኋለሁ’ አለ። ከመቼ ጀምሮ ከተባለ ጉዳዩ ይፋ ከሆነበት ዕለት ጀምሮ ማለት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ነጋዴዎቹም እምብዛም ስላልገባቸው ይጨምራል በሚል ግምት ዶላሩን ይዘዋል። በተመሳሳይ ባንኮቹም ካለማወቅ የተነሳ ይዘውታል። ነገር ግን በቀጣዮቹ 12 ወራት ውስጥ ባንኮች ጋ ገብቶ ብሔራዊ ባንክ ይወስደው የነበረውን ሦስት ቢሊዮን ዶላር አሁን ባንኮች ጋ ይቀራል። ይህ በፖሊሲ ለውጥ ብቻ የመጣ ነገር ነው። ፖሊሲ የመጨረሻ ከባድ መሳሪያ ነው። ምክንያቱም በአንድ ፊርማ በፊት ወደ መንግሥት ይሔድ የነበረ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አሁን ባንኮች ጋ ሊቀር ነው። ያ ማለት ደግሞ አሁን ሦስት ቢሊዮን ዶላር ከጥቁር ገበያ ወጣ ማለት ነው። ይህ አንዱ ጉዳይ ነው ይላሉ።
አቶ ኤርሚያስ እንደሚናገሩት፤ ሌላው ቢቀር ይህ ፖሊሲ ባንክ ሔደን የዶላር አካውንት እንድንከፍት ይፈቀድልናል። ስለዚህ ከውጭ ሀገር ዶላር ቢላክልን በዶላር ይቀመጥልኝ፤ አይመንዘር ማለት ይቻላል። ይህ በራሱ ወደጥቁር ገበያ ሊገባ የሚችልን ከውጭ የተላከ ገንዘብ (Remittance) ወደባንክ ሊያመጣ ይችላል። ወደ ባንክ ሲስተሙ ገባ ማለት ለሚፈልግ ሰው ተደራሽ የሚሆን ነው ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ለሕክምና ውጭ ሀገር መሄድ ፈልጎ መቶ ሺ ዶላር አስፈልጎት ባንክ ጠየቀ እንበል፤ ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ ውሰድ ይባላል፤ በስንት ይላል አሁን ለጊዜው 74 ነው ይባላል። ሌላውም እንዲያ ቢል ብሩ እስካለ ድረስ መልሱ ትችላለህ ነው።
አሁን የሚሰጥ ከተገኘ ማንም ሰው የውጭ ብድር መውሰድ ይችላል። አሁን ደንበኛው ሔዶ ባንኮችን ዶላር ስጡኝ ልመና ይቀርና ባንኮች መጥተው እባካችሁ ከእኔ ግዙ ማለታቸው አይቀሬ ነው።
አቶ ኤርሚያስ፤ አሁን ዶላር መግባት እየጀመረ ነው፤ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ደግሞ በደንብ መጉረፍ ይጀምራል። ያኔ ዶላሩን ይዞ መቀመጥ አስቸጋሪ ነው። ዶላር የሚፈልግን አካል ማሳደድ የግድ ይሆናል ይላሉ። እንዲያውም እርሳቸው እንደሚሉት፤ ማስታወቂያ ሁሉ ሊጀመር ይችላል ነው። “አሁን በእኛ አውድ የውድድር ሜዳው ተከፍቷል›› ሲሉ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ያመለክታሉ።
ጥቁር ገበያ በአንድ ምሽት ሊጠፋ አይችልም የሚሉት ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ (ዶ/ር) ሲሆኑ፤ በባንኮችና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ ከመጣ፣ ቀስ በቀስ የጥቁር ገበያ እንቅስቃሴ በጣም ይቀንሳል ይላሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ጥቁር ገበያው ስላለ በገበያ ዋጋ መገበያየት አልሠራም ማለት አይደለም። ጥቁር ገበያ የትም ሀገር ውስጥ አይቀርም። እንቅስቃሴ እስካለ ድረስ ይኖራል። ዋናው ነገር ጥቁር ገበያው መኖሩ ሳይሆን በጥቁር ገበያው ያለው እንቅስቃሴ ምን ያህል ተፈላጊነቱ ይቀንሳል የሚለው ነው። ይህ እንዲሆን ግን በባንክና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የምንዛሪ ዋጋ በጣም መቀራረብ አለባቸው። የዋጋ ተመኑ ካልተቀራረበ ኤክስፖርተሮችና ከውጭ ገንዘብ የሚልኩ ሰዎች በቀጣይም ጥቁር ገበያውን እየተጠቀሙ ይቀጥላሉ ማለት ነው። ወደ ትክክለኛው የምንዛሪ ቦታ የሚመጡት ተመኑ ሲቀራረብ ብቻ ነው። የባንክ የምንዛሪው ተመን ወደ ጥቁር ገበያው ዋጋ መጠጋት አለበት። ባንኮች በራሳቸው ተመን ማውጣት ስለተፈቀደላቸው እነሱም የዶላር እጥረት ስላለባቸው ዶላር ወደነሱ የሚያመጡትን ለማበረታታት ገበያው ወደሚከፍለው ጠጋ ማለታቸው አይቀርም ሲሉ ያብራራሉ።
ዋናው በበጎ የሚታይበት ጉዳይ ግን ገበያውን ያስተካክላል ተብሎ ስለሚታመን ነው የሚሉት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው፤ በተለይ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ወይም በወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ነጋዴዎች ትክክለኛ ዋጋቸውን እንዲያገኙ ያስችላል ሲሉ ይጠቅሳሉ። በአንድ ዶላር 58 ብር ሲያገኙ የነበሩ ምንዛሪው ዋጋ 100 ብር የሚገባ ከሆነ የቡና፣ ሰሊጥ ላኪዎች የተሻለ ዋጋ ያገኛሉ። ይህ አንዱ በጎ ጎኑ መሆኑን አመልክተው፤ ሌሎች ጠቀሜታዎችም እንዳሉት ይገልጻሉ። ገበያው ለሁሉም እኩል በሆነ የመሮጫ ሜዳ ውስጥ እንዲሆን ያደርጋል ሲሉም የአቶ ኤርሚያስን ሃሳብ ያጠናክራሉ።
ከዚህ በፊት የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ሲያገኙ የነበሩት መንግሥትና ጥቂት ባለሀብቶች ብቻ ናቸው ሲሉም አስታውሰው፤ አሁን ግን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ሁሉም ሰው ያገኛል እንደ ማለት ነው ብለዋል። አሉታዊ ተብሎ የሚጠቀሰው ደግሞ ኢምፖርት የሚደረጉ ዕቃዎች ዋጋ የሚወደድ በመሆኑ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ እየተረጋጋ የነበረውን የዋጋ ንረት መልሶ እንዲወጣ ያደርጋል የሚል ሥጋት አለ ሲሉ ስጋታቸውን ይጠቁማሉ። ይህ ደግሞ በተለይ ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚጎዳ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ኤርሚያስ አባባል፤ የመርካቶ ነጋዴ አፍኖ ያስቀመጠውን እቃ ቢበዛ ከአራት ወራት በኋላ ለምኖ የሚሸጥበት ጊዜ ይሆናል። አሁን ዳኛው ገበያው ነው፤ ፖሊሲው ደግሞ ተቆጣጣሪው ነው። ከገበያው ፍላጎት ጋር መሄድ ነው፡። በተቃራኒ ከሄድን እንጠፋለን፤ ስለዚህ ዶላር አሁን እጥረት አይኖርም፤ ይህ እውቀትና ግንዛቤ አልባ አካሔድ ከሁለትና አራት ወር ድረስ ሊፈነጭ ይችላል። በኋላ ግን የሚከስም ነው። ውድድር እየመጣ ነው። የምንዛሪ እጥረት እየጠፋ ነው።
ማሻሻያውን ተከትሎ የውጪዎችም እንደሚመጡ ጠቁመው፤ በቀጣዩ ዓመት የምናየው ሌላ ሜዳ ነው ሲሉ አመልክተዋል። እርሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ያሉ ተጫዋቾች ይህን ተገንዝበው መነቃቃት አለባቸው። ንግድ ባንክን መከተል ትተው የራሳቸውን እቅድ አውጥተው መሯሯጥ አለባቸው። አሁን የመጣው ፖሊሲ ያመቻቸው ሜዳ ቢኖር ይህንን ነው። በአጠቃላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አዕምሮና የደም ዝውውር ሊኖረው ነው ብለዋል።
ምሁራኑ እንደሚሉት፤ ማሻሻያውን ተከትለው የሚመጡ ሕመሞች የሚያሰቃዩት ለጥቂት ጊዜ ነው። ግፋ ቢል የተወሰደው መድኃኒት እስኪሰራ ድረስ ነው፤ መድኃኒቱን ባለመጠቀም በዚህ ሕመም ውስጥ ሆኖ መዝለቅ ግን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሞት ነውና ጊዜያዊ የሆነውን ሕመም በመታገስ ጤናማ የሆነ መስመር ላይ መሆን አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። ስለዚህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የበለጠ ተነቃቅቶ እንዲጓዝ መንግሥት ያወጣውን ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ እስኪሆን መሥራት የግድ ነው።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም