ግብርናው ቴክኖሎጂን አሟጦ መጠቀምና ገበያ ማፈላለግን ይጠይቃል

በግብርናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባሮች ምርትና ምርታማነት በየአመቱ እያደገ ይገኛል፡፡ ይህ እድገት ግን ካለው እምቅ አቅምና ሀገሪቱ ከምትፈልገው የግብርና ምርት አኳያ ሲታይ አሁንም ምርትና ምርታማነቱ ማደግ እንዳለበት ይታመናል፡፡

በሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የኢትዮጵያ መንግሥት የምንጊዜም ሥራ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ግብርና አሁንም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ የያዘ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለቀጣዩ የኢንዱስትሪም ሆነ ሌሎች ልማቶች አንዱ አቅም የሚገኘው ከዚሁ ከግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ ለእዚህም ነው በዘርፉ ኩታ ገጠም እርሻን፣ ሜካናይዜሽንን፣ የበጋ መስኖ ልማትን ፣ ወዘተ ለማስፋፋት በትኩረት እየተሠራ ያለው፡፡

ሰሞኑን የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ በዘርፉ ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን ያቀረቡት የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች እንዳስታወቁትም፤ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲያስችሉ ሥራ ላይ በዋሉት እንደ ኩታ ገጠም እርሻ፣ ሜካናይዜሽን ፣ወዘተ ባሉት ለውጦችን ማስመዝገብ እየታቸለ ነው፤ የበለጠ ለውጥ ለማስመዝገብ ግን አሁን በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ የግል ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ደምስ ጫንያለው ፤ ግብርናው በተለይ በእርሻው አካባቢ ለውጦች እንደሚታዩ ጠቅሰው፣ ለውጡ የምንፈለገውን ያህል አይደለም ይላሉ። ይህም የሆነው ከታች ከመሬት ጉዳይ ጀምሮ ከዘር፣ ማዳበሪያ አቅርቦት በተለይ ከስርጭት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል።

ዶክተር ደምስ እንዳሉት፤ ኩታገጠም እርሻዎች ላይ ያለው ለውጥ በጣም ትልቅ ነው። ከሶስት አራት ዓመታት በፊት የነበረው ዜሮ ነጥብ ስድስት ሄክታር በኩታገጠም ይታረስ የነበረው መሬት አሁን ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል። ምርማነቱም ጥሩ ነው።

የተገኘውን ምርት ወደ ሸማቹ ወይም ገበያ ለማድረስ ከመጋዘን አቅርቦት፣ ከማጓጓዝ ጀምሮ ችግሮች ስለመኖራቸው በስፋት እንደሚሰማም ጠቁመዋል። ምርታማነቱ ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ ምርቱ ጥሩ ዋጋ ማግኘት አለበት ይላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ጥሩ ለውጥ እንዳለም ጠቅሰው፣ ተያይዘው የተከሰቱ ችግሮች መኖራቸውን አመላክተዋል።

አማካሪው እንደገለፁት፤ በግብርናው ዘርፍ ከማምረት፣ የማምረቻ መሬት ከማስፋት፣ ከመጠቀም እና ምርታማነትን ከመጨመር በእያንዳንዱ አካባቢ በጥራት ከማቅረብ አንፃር ሥራዎች ተሠርተዋል። ይሁንና አርሶ አደሩ በኢንተርፕሩነርሺፕ ራሱን አሻሽሎ በምርታማነት ማደግ የሚያስፈልገውን ከማግኘት አንፃር ገና ብዙ መሰራት ይኖርበታል፡፡

እስካሁንም በግብርናው በተለይ በእርሻው ክፍል ውስጥ የመዋቅር ለውጥ ለማምጣት የተጀመረ ሥራ የለም ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህን አንቆ የያዘው አንደኛው የመሬት ጉዳይ ነው ብለዋል። አሁንም ቢሆን በቅርቡ ማሻሻያ አድርገናል፤ ብዙ መሥራት ግን ይኖርብናል። መሬትን ወደ ግል ከመቀየር ውጪ ግን በማሰባሰብ ሊያድጉ የሚችሉ ገበሬዎች ከእርሻው ውስጥ እንዳይወጡ ማድረግ መቻል አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።

ሁለት ሄክታር ይዞ ጥሩ አፕል ሲያመርት የነበረ አንድ ገበሬ፣ ከሁለት ሄክታር ያገኘውን ገንዘብ ይዞ ከተማ ገብቶ ቤት ወይም ወፍጮ ለመሥራት ከመሄድ ይልቅ እዛው ሆኖ እርሻውን የሚያስፋፋበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ዘለቄታዊ ለውጥ ለማምጣት የዚህ አይነት የስትራቴጂ አስተሳሰብ ያለው አሠራር መቅረጽ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

በስንዴው የጀመርነውን በሌላውም በተመሳሳይ መስራት አለብን ሲሉም ጠቁመው፣ የተፈጥሮ ሀብት በበቂ ያለን በመሆኑ በዚህ ላይ መሥራት አለብን ሲሉ አማካሪው ገልጸዋል።

የግብርና ኢኮኖሚክስ ባለሙያና ተመራማሪ ዶክተር ዳዊት ዓለሙ በበኩላቸው እንደሚገልፁት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥራት ያለው የግብርና ግብዓት ያስፈልጋል። ለምግብ አምራቾች እንዲሁም ለውጭ ገበያው የሚላከውን ጥራት ያለው ምርት ለማምረት የሚያስችል የግብርና ግብዓት ያስፈልጋል። ከዚህ ውስጥ ትልቁ የዘር ሥርዓት፣ የማዳበሪያ አቅርቦት እና ኬሚካል አቅርቦት ጉልህ ድርሻ አላቸው። ከዚህ በተጨማሪም ችሎታ ያላቸው የሰው ኃይል እንዲሁም የግብርና ማሽነሪዎችም ወሳኝ ናቸው። ሌሎችም መሰል ግብዓቶች አሉ።

የግብርና ግብዓች እንደየግብዓቱ ዓይነት የራሳቸው ጥንካሬ እና ደካማ ጎን አላቸው። የዘር ሥርዓቱ ብዙ የግል ሀብቶች የሚሳተፉበት ቢሆንም ብዙ በመንግሥት ድርጅቶች የሚመራ ነው። ይሄም ብዙውን ወደተወሰኑ ሰብሎች ላይ ያተኮረ ነው። ወደ 80 በመቶ የተረጋገጠ ዘር የሚመረተው ለስንዴ እና ለበቆሎ ነው። ለስንዴም ለበቆሎም ሆኖ ለጥቂት ዝርያዎች ነው። ሀገር ውስጥ ከሚመረቱት አኳያ አዳዲስ ዝርያዎች ወደ ምርት አይገቡም። በሥራ ላይ ያሉት ዝርያዎች አማካኝ እድሜያቸው ወደ 15 ዓመት ይሆናል፤ ነገር ግን መሆን ያለበት በ 15 ዓመቱ አዳዲስ ዝርያዎች እየተኩ እንዲሄዱ ነው።

ለዚህም ዋናው ችግሩ መነሻው ጠንካራ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓት የለንም በየጊዜው መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የአስተዳደር ሥርዓቱ ይቀያየራል። ያ ደግሞ የነበሩ ደካማና ጠንካራ ጎኖችን አይቶ ለማሻሻል የሚያስችለውን አሠራር ለመተግበር ትልቅ ችግር ያለ በመሆኑ በዚህ ላይ አተኩሮ መሥራት ያስፈልጋል።

አሁን መስከረም ላይ የፀደቀው አዲሱ የዘር አዋጅ ከላይ የተገለጹትን ችግሮች ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞም አዳዲስ መመሪያዎችና ደንቦች ማውጣት የሚጠበቅ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የአትክልት ዘርን በተመለከተ ፕሬዚደንቱ እንደገለፁት በጣም ወሳኝ በሆነ ደረጃ ከውጭ ጥገኛ ነን። ይህም የዘር ሉዓላዊነት ችግርን ያመጣል። የዛሬ ሶስት ዓመት ህንድ የሽኩርት ዘርን ጨምሮ የተለያዩ የአትክልት ዘር ወደ ውጭ መላክን ስትከለክል የዘር አቅርቦት በጣም ችግር ውስጥ ገባ። በመሆኑም አሁን የአትክልቶች የዘር ሥርዓት በቅመማቅመም ማስፋት ያስፈልጋል። ለእንደዚህ ዓይነት ሰብሎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል። ይህ በአጠቃላይ የመንግሥት እና የግል ተሳታፊዎችን ሚና ለይቶ ማን ምን ይደግፍ የሚለው ታይቶ ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል።

የአግሮ ኬሚካል ግብይትን በመተለከተ የአሠራር ሥርዓት እና ሕጎች አሉ ያንንን የማስፈፀም ተገቢ ነው ሲሉም ነገር ግን ትልቁ ችግር አሁን ያለው የአግሮኬሚካል ግብይት ሁሉም አርሶአደር ስለበሸታውም ሆነ ስለኬሚካሉ እውቀት አለው ብሎ ያስባል። ነገር ግን በሚጠበቀው ልክ ላይሆን ይችላል። በመሆኑም በእውቀት ላይ የተመረኮዘ አጠቃቀም እንዲኖር የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ይሄም ወደ አገልግሎት አቅርቦት የመሄድ የተማሩ ሰዎች ወደዛ ቢዝነስ የሚገቡበት እና በሽታውን ለይተው የትኛው ኬሚካል መቼ ይረጭ፣ ምን ያህል ይረጭ የሚለውን ሁሉ የሚለዩ መሆን አለባቸው። ምክንያቱም ሀገር ውስጥ ለምንመገበው ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ ለሚላከውም የኬሚካል አቅርቦቱ ወሳኝ በመሆኑ ወደ ቢዝነስ መር አገልግሎት መውሰድ የግድ መሆኑን አመላክተዋል።

የኬሚካል ማዳበሪያ አስመልክተው ፕሬዚደንቱ ሲገልጹም ሙሉ በሙሉ ከውጭ የሚመጣ ነው። አንዳንድ ካምፓኒዎች ፍቃድ ወሰዱ ይሄንን ያህል ኢንቨስት አደረጉ ሲባል ይደመጣል። አሁን የድሬዳዋውን የማዳበሪያ ኩባንያ በ2023 የተፈራረሙ ቢሆንም እስካሁን ምንም አልታየም ነገር ግን አንደኛው የሀገር ውስጥ ምርት የሚመረትበትን ማመቻቸት ነው። ሁለተኛው ግን አሁን ወደ ሀገር ውስጥ ስናስገባ ብቁ እንድንሆን የሚያደርግ ነው። ዓለምአቀፍ መስፈርት ለማሟላት እና አቅም የመገንባት ሥራ ነው። በመሆኑም በዚህ ደረጃ አቅም መፍጠር ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ 400 በላይ ኬሚካሎች በምርምር ተጠንተው ውጤታማነታቸው ተመዝግበዋል። በዚህ ዓመትም በሚቀጥለው ዓመትም ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል። ውጤታማነቱም ምርምሩ ላይ የተሞከረው ይሁን አይሁን የሚፈተሽበት የለም ደረጃውን ብቻ ነው የምናየው። በመሆኑም ይሄንን አቅም ማሳደግ ያስፈልጋል። ይህም የራሱ ትልቅ ክፍተት የሚፈጥር ነው።

በመሆኑም ግብርና ኬሚካል ላይ የሚቆጣጠረው የተፈለገው ደረጃ መኖሩን ብቻ ነው። በመሆኑም በብዙ ግፊት የተደረገው እና የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን እንዲቋቋም የተደረገው በኬሚካልም በዘርም የቁጥጥር አቅም በራሱ ችሎ መሰራት አለበት። ነገር ግን ያ አቅም ስለመፈጠሩ እና አለመፈጠሩ ወደ ፊት በጋራ የሚታይ መሆኑን አመላክተዋል።

የመሣሪያዎች አቅርቦቱም በተመሳሳይ ሙያዊ በሆነ መልኩ የሚመራበት መንገድ መፈጠር አለበት፤ የዓለም አቀፍ የማዳበሪያ ንግድ ዓለም አቀፍ ፖለቲካ አለበት፣ ግፊት አለበት። በመሆኑም ይሄንን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አቅም መፍጠር ያስፈልገናል። በባለሙያ ብቻ ሳይሆን በብዙ ተዋናዮች ሊሠራ የሚገባው ነው ነገር ግን ይህም ሆኖ ከገባ በኋላ በቂ ሥርጭት ያስፈልገዋል።

መንግሥት ከወደብ ወደ ማዕከላዊ መጋዘን አስገብቶ ከዚያም ወደ ማዕከላት በማስገባት የሚያሰራጨው ሁኔታ የተሻለ ውጤታማ አሠራር ነው። አሁን ግን ይህ አሠራር እየተዳከመ ስርጭቱም ወደ አልተገባ የንግድ ጥቅም እየገባ መሆኑን ጠቁመዋል።

‹‹ገበያ ማለት የሚገዛ ኃይል ማለት ነው። ሁልጊዜ የሚገዛው ኃይል የሚያመርተውን ኃይል ይመራዋል።›› የሚሉት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚከስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚደንት ዶክተር እንደሻው ሀብቴ፣ ምርት መመረቱ ብቻ በራሱ በቂ አይሆንም፤ ምክንያቱም ስርጭት መታየት መቻል አለበት ሲሉ ይገልጻሉ።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ስርጭት ደግሞ ከገበያው ጋር ይገናኛል። ከአቅርቦት ጋር ይገናኛል፤ መንገድ፣ የገበያ መረጃ ሥርዓት መኖር አለባቸው። ሰዎች ምርት የት እንደ ተመረተ፣ መቼ እንደሚመረት፣ አምራቹም ደግሞ ገበያው የት እንዳለ ማወቅ መቻል አለባቸው፡፡

እነዚህን በሚገባ ሥርዓት ማስያዝ ከተቻለ፣ ቢያንስ አሁን ያለውን የምግብ ሥርዓት ማስያዝ ቢቻል፣ ቢያንስ አሁን ያለውን የምግብ እጥረት ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ባይቻል ትርጉም ባለው ደረጃ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ተብሎ የሚታመን መሆኑን ገልፀዋል።

በሀገራችን ካሉ ለውጦች አንፃርም ዝግጁነቱ መኖር እንዳለበት ያስረዳሉ። ለምሳሌ የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር ተያይዞ የምግብ ፍላጎትም በተመሳሳይ ያድጋል ሲሉም የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጠቁመው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ዝግጁነት መኖር እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ግብርናውን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር አያይዘው ሲገልጹም የካፒታል አቅርቦት መኖር እንዳለበት አስገንዝበዋል። የማህበሩ ፕሬዚዳንት አምራቹ ኃይል በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መደራጀት መቻል አለበት ሲሉም አመልክተዋል።

ከገበያም ሆነ ከምርት አኳያ እንደ ህብረት ሥራ ማህበራት ያሉትን፣ በተለይ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትን ኩታገጠም እርሻ ተብሎ የተጀመረው ትልቅ ተነሳሽነት መኖራቸውን በአዎንታዊነት ጠቅሰዋል። ይህም በበሬ እና በሰው ኃይል ከማረስ ቴክኖሎጂን፣ ትራክተሮችን የመሳሰሉትን ለመጠቀም እና ለሌሎች የተቀናጀ ሥራዎች አስቻይ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ዶክተር እንዳሻው እንዳብራሩት፤ ከመሬት፣ ከእውቀት፣ ከቴክኖሎጂ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያሉትን ሁኔታዎች ማሻሻል ከተቻለ ገበያው ይሄንን ማቀላጠፍ ይችላል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂም ለመጠቀም አርሶአደሩም የተሻለ እድል ይኖረዋል። ገበያ ሲባል የብድር አገልግሎትንም ጨምሮ ሰዎች ገንዘብ ሲፈልጉ መበደር መቻልም አለባቸው። ያንንም የሚያቀርብ ገበያ መኖር አለበት።

የኤክስቴንሽን አገልግሎቱም እውቀትን በአግባቡ ማቅረብ አለበት ሲሉም ጠቅሰው፣ የዘር ስርጭቱም ወይም ሌሎች የሜካናይዜሽን ሥራዎች በአግባቡ ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You