
ዜና ሀተታ
የመዲናዋ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት የ 70 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረ እና በቀን በአማካይ 600 ሺህ ነዋሪዎችን እያጓጓዘ ይገኛል።
የአውቶብስ አገልግሎቱ የክፍያ ታሪፍ ከሌሎች አማራጭ የትራንስፖርት አይነቶች ያነሰ በመሆኑ በብዙሃኑ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ነዋሪዎች ዘንድ ይዘወተራል። በአነስተኛ ክፍያ በአንድ ጉዞ ረጅም ኪ.ሜ የሚያጓጉዝ በመሆኑም ከተጠቃሚዎች ዘንድ “ባለውለታ” ተብሎም ይጠራል።
የከተማ አውቶብስ አገልግሎት የከተማዋና አጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች ለረጅም ዓመታት የተገለገሉበት፣ ዛሬም የብዙኃኑ ምርጫ መሆኑ እሙን ሆኖ ሳለ፣ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ግን ቅሬታ ይነሳበታል። ተጠቃሚዎች ሊሻሻሉ ይገባል የሚሏቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ።
የከተማ አውቶብስ ተጠቃሚ ወ/ሮ አበራሽ ዋሲሁን፣ ጠዋት ወደ ሥራ ለመውጣትም ሆነ ከሥራ ለመመለስ አውቶብስ እንደሚመርጡ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፣ አውቶብሱን ፈልገው ቢጠቀሙም ብዙ ጊዜ ረጅም ሰዓት ቆመው ለመጠበቅ ይገደዳሉ። አውቶብስ ቆሞ መጠበቅ ደግሞ በተለይም ቀን በሥራ ለደከመና ለአቅመ ደካሞች በጣም አድካሚና አሰልቺ ይሆናል።
ከዚሁ ጋር አያይዘው፣ አውቶቡሶች ረጅም ሰዓት ቆይተው ሲመጡ የተሳፋሪው ቁጥር ከመብዛቱ የተነሳ ባሶች ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሰው ጠቅጥቀው እንደሚጓዙ አንስተው፣ ይህም ለሌብነትና ሴቶችን ለወሲባዊ ትንኮሳ እያጋለጠ ነው ብለዋል።
የአውቶብስ ተጠቃሚው በሰላም ወጥቶ እንዲገባ አውቶብሶች በተገቢው ሰዓት ምልልስ እንዲያደርጉ መሥራት እና የአውቶቡሶችን ቁጥር በመጨመር ሰው ያለልክ ተጠቅጥቆ የሚጓዝበትን ሁኔታ ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አቶ ገዛኸኝ ይሁኔም የከተማ አውቶብስ የረጅም ዓመት ደንበኛ ናቸው። ለዓመታት በመጠነኛ ዋጋ ለከተማዋ ነዋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠቱ በእርሳቸውም ሆነ በአብዛኛው ነዋሪ ዘንድ የአውቶብስ አገልግሎት ተመራጭ መሆኑን ይናገራሉ።
ሶስትና አራት ታክሲ የሚፈልጉ ረጅም ርቀቶችን በአንድ ጉዞ መድረስ መቻሉም አውቶብስን በብዙሃን ዘንድ ተመራጭ አድርጎታል ይላሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን፣ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት በርካታ ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን ያነሳሉ።
እርሳቸው ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የአውቶቡሶች ንጽህና ጉዳይ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ውስጥና ውጪያቸው በጣም የቆሸሹ አውቶቡሶች እንደሚገጥሟቸው ይናገራሉ።
አውቶቡሶቹ በርካታ ሰዎችን ረጅም ርቀት የሚጓጉዙ በመሆናቸው ለመቆሸሽ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ይታወቃል ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ ድርጅቱ ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አውቶቡሶቹ ንጹህ ሆነው አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ቢያመቻች የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።
አቶ ገዛኸኝ “ድርጅቱ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ማስተካከል ያለበት ችግር ነው” ብለው ያነሱት በአንዳንድ የአውቶብስ አሽከርካሪዎችና ቲኬት ቆራጮች ላይ የሚታየውን የሥነ ምግባር ጉድለት ነው። እርሳቸው እንዳሉት፣ በአግባቡ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ሹፌሮችና ቲኬት ቆራጮች እንዳሉ ሆነው፣ ከዚህ በተቃራኒ የሆኑና ተሳፋሪውን በእኩል ዓይን የማያስተናግዱ፣ ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ከተሳፋሪ ጋር ስድብ የሚመላለሱ፣ ቆመው ሰው መጫን የሚገባቸውን ፌርማታ የሚያሳልፉ፣ ተሳፋሪውን ፌርማታ አሳልፈው የሚያወርዱ ሹፌሮችና ቲኬት ቆራጮች በብዛት እንደሚስተዋሉ አንስተዋል።
ድርጅቱ እንዲህ ያሉ ሥነ ምግባር የጎደላቸውን ሠራተኞቹን በአግባቡ ሊቆጣጠር ይገባል ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ ድርጅቱ ሠራተኞቹ በምን መልኩ አገልግሎት እየሠጡ እንዳሉ የሚያውቅበት መንገድ ቢያመቻች የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ያግዘዋል በማለት መክረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አካሉ አሰፋ፣ የሰዓት አጠቃቀምና ሰዎች ፌርማታ ላይ ረጅም ሰዓት ይቆማሉ በሚል የቀረበውን ቅሬታ አስመልክተው ሥራ አስፈጻሚው በባስ ፌርማታዎች ላይ አውቶብሱ ከመምጣቱ ቀደም ብሎ የመጣ ሰው ረጅም ጊዜ የሚቆይበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ያነሳሉ።
የዚህንም ምክንያት ሲያስረዱ እንዳሉት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይሆን ከከተማ ውጪም ዜጎችን ያጓጉዛል። ከዚህ ረጅም ጉዞ በኋላ ሰው በሚጠብቅበት ፌርማታ ላይ እስኪደርስ ድረስ ጊዜ ይወስድበታል።
መንገድ በሚዘጋጋበት ጊዜ ደግሞ ይህ ሰው አውቶቡሱን የሚጠብቅበት ጊዜ ይረዝማል። ይህ ሁኔታ ወደፊት የአውቶብስ አቅርቦት እየተሻሻለ ሲመጣ የሚቀረፍ ይሆናል ሲሉ ያስረዳሉ።
አውቶቡሶች ከአቅም በላይ ከመጫን ጋር ተያይዞ የተነሳውን ቅሬታ በተመለከተም ሥራ አስፈጻሚው “በየትኛው ሀገር ቢሆን አውቶቡሶች አገልግሎት ሲሰጡ ወንበር ያገኘው ቁጭ ብሎ ወንበር ያላገኘ ሰው ደግሞ ቆሞ የሚሔድበት ሁኔታ ይኖራል።
በሀገራችን ያሉ ባሶች የወንበር ቁጥራቸው 42 እና 45 ሲሆን፣ ቆሞ የሚሄደውን ጨምሮ እስከ 70 ሰው ይጭናሉ። ካለው የተሳፋሪ ፍላጎት አኳያ፣ ሰው መንገድ ላይ ቆሞ ከሚቀር አውቶቡሶች እስከቻሉት ድረስ ቆመው መሄድ የሚፈልጉ ሰዎችን ይጭናሉ” በማለት ያስረዳሉ።
ይህ አይነቱ ጉዞ ለሌብነትና ለአላስፈላጊ ድርጊት የሚያጋልጥበት ሁኔታ ይስተዋልል የሚባለው እውነት ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ አውቶቡሶቻችን ውስጥ ፖሊስ የምናቆምበት አሠራር የለም ይላሉ።
ነገር ግን አውቶቡሶቻችን ሌብነትንና አላስፈላጊ ተግባራትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ 4 እና 5 ካሜራ የተገጠመላቸው ዘመናዊ አውቶቡሶች ናቸው ብለዋል። በአውቶቡሶች ካሜራ አማካኝነት እስካሁን ድረስ በርካታ ሌቦችን መያዝና ለፀጥታ አካላት ማስረከብ መቻሉንም አንስተዋል።
ከዚህ በበለጠ ግን እኛ ሕዝባችንን የምንመክረው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሲከሰት አድራጊውን በማጋለጥና እርስ በእራሱም በመከባበር ጤናማ ጉዞ እንዲያደርግ ነው ብለዋል።
ከሥነ ምግባር ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር አስመልክቶ ችግሮች መኖራቸውን አንስተው እነዚህን ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ጥናት መሠረት ሪፎም ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
በሪፎርሙ ከህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ከንጽህና ጋር ተያይዞ ከተጠቃሚው የቀረበውን ቅሬታ የከተማዋ ነዋሪ የትራንስፖርት ፍላጎት ከድርጅቱ የአውቶብስ አቅርቦት በላይ በመሆኑ ድርጅቱ በአለው አቅም ነዋሪውን ለማገልገል ሲል አውቶቡሶቹ ከማለዳ እስከ ምሽት አገልግሎት እንደሚሰጡ ያነሳሉ። ከዚህ የተነሳ አውቶቡሶቹን በየቀኑ ለማጽዳት አስቸጋሪ ይሆናል ይላሉ።
ሆኖም አውቶብሶቹ ቢያንስ በሳምንት ሁለቴ እንዲታጠቡ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ ከሥራው ባሕሪና ከአየር ጠባያችን አንጻር ግን፣ አውቶብሶች ጠዋት ታጥበው ማታ ሊቆሽሹ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።
አውቶቡሶቻችን በየቀኑ ቢጸዱ እኛም ደስ ይለናል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ ለወደፊቱ ለሕዝባችን ከዚህ የተሻለ ክብር ሰጥተን ጽዱ በሆኑ አውቶቡሶች ማገልገል ስላለብን፣ የጽዳት ማሽኖቸቻንን ቁጥር በመጨመርና የጽዳት አገልግሎት አሠራርን በመቀየር በተቻለ አቅም የአውቶቡሶችን ንጽህና በየቀኑ ለመጠበቅ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ ሥራ አስፈጻሚው፣ ህብረተሰቡ የራሱን ንብረት በአግባቡ ተንከባክቦ ጠብቆ በደረሰበት ሁሉ ክትትል እያደረገ ጉድለትም ሲያይ ጥቆማ እየሰጠ አግባብ ያለው አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ትብብሩን ጠይቀዋል።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም