ከ24 ዓመት በኋላ ወደ ቤቱ የተመለሰው የኦሊምፒክ ማራቶን ድል

የምን ጊዜም የዓለም ምርጡ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በክብር እንግድነት ተገኝቶ ባስጀመረው የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አሳክታለች። በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ የወንዶች ማራቶን ታሪክ 5ኛውን ድል በማስመዝገብ ጀግናው አትሌት ታምራት ቶላ ትልቅ ታሪክ ፅፏል። ከ24 ዓመታት በኋላ የተመዘገበው ይህ ድል ዛሬ 33ኛ ዓመት የልደት በአሉን ለሚያከብረው አትሌት ታምራት ቶላ ከሁለት ጊዜ አሸናፊው አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ እና ገዛኸኝ አበራ ተርታ እንዲቀመጥ አድርጎታል።

በወጥ አቋምና አስደናቂ ብቃት ሩጫውን በበላይነት ያጠናቀቀው ታምራት የኦሊምፒክ የማራቶን ክብረወሰንን በ6 ሰከንድ በማሻሻል ጭምር ነው ድሉን ያጣጣመው። የቀድሞ የርቀቱ የኦሊምፒክ ክብረወሰን እአአ በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሊምፒክ በኬንያዊው አትሌት ሳሙኤል ዋንጂሩ የተመዘገበ ሲሆን፤ ታምራት ትናንት በድንቅ አሯሯጥ ክብረወሰኑን ተረክቧል። ኢትዮጵያ ከሮም እስከ ፓሪስ ማራቶን 5 የወርቅ፣ 1 የብር እና 3 የነሃስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን በማግኘትም በመድረኩ የዓለም መሪነቷን አጠናክራ ማስቀጠል ችላለች።

ውድድሩ የተካሄደበት የሴን ወንዝ ዳርቻ በአብዛኛው ዳገታማ መሆኑ አብዛኛዎቹን አትሌቶች የፈተነ ቢሆንም በከፍተኛ ቦታዎች ላይ ልምምዳቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያውያን ፈተናውን በድል ተወጥተዋል። ባለድሉ አትሌት ታምራት ከ30ኛው ኪሎ ሜትር አስቀድሞ ከቡድኑ ተነጥሎ በመውጣት በመሪነት ረጅም ርቀት ሸፍኗል። ከፍተኛ ጽናትን እንዲሁም ትዕግስትን በሚጠይቀው ማራቶን በብቃት ከዓለም ቀዳሚ አትሌቶች መካከል አንዱ መሆኑን ያስመሰከረው ታምራት ርቀቱን ለመሸፈን የፈጀበት 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ ብቻ ነበር። በዚህ ድልም በውጤት መራቅ ተከፍቶ የቆየውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማስደሰት ባለፈ ዛሬ ለሚደረገው የሴቶች ማራቶንም ከፍተኛ ሞራል የሚሰጥ ሆኗል።

አብዛኛውን የሩጫ ክፍል ከፊት በመሆን ሲቆጣጠር የቆየው የዓለም ቻምፒዮኑ ታምራት ቶላ፤ በዚህ ኦሊምፒክ በተጠባባቂነት ከተያዘ በኋላ በሲሳይ ለማ ቦታ ተተክቶ ነበር ወደ ፓሪስ የተጓዘው። ታምራት በዩጂን የዓለም ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት በርቀቱ ያለውን ብቃት ያስመሰከረ ሲሆን፤ በቀጣዩ የቡዳፔስት ቻምፒዮና ወቅት በህመም ምክንያት መጨረስ ባይችልም በዚያው ዓመት የለንደን ማራቶን የነሃስ፣ በኒውዮርክ ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ነበር። በኦሊምፒክ ተሳትፎ ይሄ ሁለተኛው ሲሆን እአአ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምክ በ10ሺህ ሜትር ተሳትፎው የነሃስ ሜዳሊያ በማግኘት ሀገሩን ማስጠራት ችሏል። በርቀቱ እአአ 2021 አምስተርዳም ላይ የገባበት 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ39 ሰከንድ የሆነ ሰዓት የግሉ ፈጣን ሰዓቱ ሲሆን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሩን በወከለበት የኦሊምፒክ ማራቶን እጅግ አስደሳች ውጤትን ሊያስመዘግብ ችሏል። ቤልጂየማዊው በሽር አብዲ 21 ሰከንዶችን ዘግይቶ ውድድሩን በሁለተኛነት ሲያጠናቅቅ፤ ኬንያዊው ቤንሰን ኪፕሩቶ ደግሞ በአንድ ደቂቃ ልዩነት የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ደሬሳ ገለታ በሰከንዶች ልዩነት በቅርብ ርቀት ታምራትን በመከተል ፉክክሩን አጠናክሮት ቢቆይም በመጨረሻዎቹ ኪሎ ሜትሮች በመቀደሙ ለተጨማሪ ሜዳሊያ ያደረገው ተሳትፎ ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህ ውድድርም ርቀቱን የሸፈነው 2 ሰዓት ከ 07 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ሲሆን፤ 5ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቋል። ወጣቱ አትሌት ደሬሳ በተያዘው ዓመት በተደረገው የሴቪሌ ማራቶንን ያሸነፈው 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ በመግባት ሲሆን፤ ይኸውም የቦታው ክብረወሰን ነበር። በማራቶን 20ኛው ፈጣን አትሌት ባለፈው ዓመት የቤጂንግ እና ልጎስ ማራቶኖች አሸናፊም ነበር።

ከ12 ዓመታት በኋላ ሀገሩን በኩራት ባስጠራበት ኦሊምፒክ ዳግም የተመለሰው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የውድድሩ ድምቀትና ተጠባቂ ነበር። በዓለም ሶስተኛው የርቀቱ ፈጣን አትሌት የሆነው ቀነኒሳ ከመም እስከ ጎዳና ከዘለቀው የምንጊዜም ተፎካካሪው ኬንያዊ አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ ጋር በታላቁ ውድድር መገናኘታቸው ደግሞ አጋጣሚውን ታሪካዊ አድርጎታል። በ42 ዓመቱ የመጨረሻውን የኦሊምፒክ ተሳትፎ ያደረገው ቀነኒሳ 39ኛ ደረጃን በመያዝም ውድድሩን ፈጽሟል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You