ታሪካዊው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የጀመረው የኢትዮጵያ የ5ሺ ሜትር የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በሚሊዮን ወልዴ እና በቀነኒሳ በቀለ አንድ ወርቅና አንድ ነሐስ ቀጥሎ ኢትዮጵያን የርቀቱ ፈርጥ አድርጓታል። ፊጣ ባይሳ፣ ደጀን ገብረመስቀል እና ሐጎስ ገብረሕይወት ደግሞ የብርና ነሐስ ሜዳሊያዎቹን ያጠለቁ አትሌቶች ናቸው። ያለፉትን ዓመታት በጉዳት ምክንያት ከውድድር ርቆ የቆየው ሐጎስ ዳግም ወደ መድረኩ መመለሱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ዘንድሮ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ በርቀቱ ዳግም የሜዳሊያ ሽሚያ ውስጥ እንደምትገባ ይጠበቃል።
ዛሬ ምሽት በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዘንድ እጅግ ተጠባቂ ከሆኑ የፍጻሜ ውድድሮች መካከል አንዱ 5ሺ ሜትር የወንዶች ውድድር ሲሆን የ10ሺ ሜትር ባለድሉ ዑጋንዳዊው አትሌት ጆሽዋ ቺፕቴጌና የሀገሩ ልጅ ጃኮብ ኪፕሊሞ ከፉክክሩ መውጣታቸውን ተከትሎ ማን ያሸንፋል የሚለው ጉዳይ አጓጊ ሆናል።
ኢትዮጵያ ከሜዳሊያ ውጪ በነበረችበት ያለፈው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረው ጆሹዋ ቺፕቴጊ ዘንድሮም የድል ባለቤት ይሆኗል የሚል ቅድመ ግምት አግኝቶ ነበር። ይሁን እንጂ አትሌቱ የኦሊምፒክ ክብረወሰን ባስመዘገበበትና ፈጣን በነበረው ከ10ሺ ሜትር ውድድሩ ድካም ባለማገገሙ ምክንያት የ5ሺ ሜትር ተሳትፎውን ለመሰረዝ ተገዷል። በመሆኑም ሁለተኛው የርቀቱ ፈጣን አትሌት ሐጎስ የወርቅ ሜዳሊያውን የግሉ የማድረግ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሞስኮ እና ቤጂንግ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ ስኬታማ በሆነበት 5ሺ ሜትር የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለው ሐጎስ፤ እአአ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክም የነሐስ ሜዳሊያ አጥልቋል። ከሁለት ዓመት በኋላ በ3ሺ ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ቢሆንም ከዚያ በኋላ ያሉትን ዓመታት በጉዳት ምክንያት በሚጠበቀው ተወዳዳሪነቱ መቆየት አልቻለም ነበር። ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ባለፈው ዓመት ሲመለስም ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የጎዳና ሻምፒዮና ላይ በ5 ኪሎ ሜትር አሸናፊ በመሆንም ነበር። በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ተሳትፎ ራሱን በማጠናከር ወደቀደመ አቋሙ በመመለስም በአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ሃገሩን ወክሎ በድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። በተያዘው ዓመትም የኦስሎ ዳመንድ ሊግን 12:36.73 በሆነ ሰዓት በመሮጥ በርቀቱ ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።
ይህ ሰዓት ከክብረወሰኑ በአንድ ሰከንድ ብቻ የዘገየ መሆኑ ደግሞ አትሌቱን በኦሊምፒክ አስደናቂ ብቃታቸውን ያሳያሉ በሚል ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዱ አድርጎታል። በርቀቱ ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ሜዳሊያ ለመመለስ የሚያስችል ዝግጅት በሙሉ ጤንነት ሲያደርግ መቆየቱን ከውድድሩ አስቀድሞ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግሯል። ‹‹ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ፤ በጉዳቴ ምክንያት የቶኪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ በሌሎች ውድድሮች ላይ ከውጤት ርቄ ነው የቆየሁት። አሁን ባለሁበት ሁኔታም ሁሉም ሃገሩን ለማስቀደም በሚፎካከርበት ኦሊምፒክ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በጥንቃቄ እንሮጣለን፤ እንደ ቀነኒሳ በቀለ ካሉ ታላላቅ አትሌቶች ያገኘነውን ምክርም ተግባራዊ እናደርጋለን። የተቻለንን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈልም ውጤት ለማስመዝገብ እንሮጣለን›› በማለትም ሐጎስ ወደ ፓሪስ ከማቅናቱ በፊት ተናግሯል።
ሐጎስ አሰልጣኝ ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ በበኩላቸው፣ ውድድሩ ከመላው ዓለም ጋር እንደ መሆኑ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል ዝግጅት ላለፉት ሦስት ወራት ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ። በርቀቱ የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ አትሌቶችን በመለየትና በምን መልኩ በመሮጥ ሜዳሊያ ማግኘት ይቻላል በሚለው ላይ አስቀድመው መዘጋጀታቸውንም አመላክተዋል።
ከሐጎስ ባለፈ ኢትዮጵያን የሚወክሉት ወጣቶቹ አትሌቶች አዲሱ ይሁኔ እና ቢኒያም መሐሪ ናቸው። 12:49.65 የሆነ ፈጣን ሰዓት ያለው አዲሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃገሩን በወከለበት የ2022ቱ የወጣቶች ሻምፒዮና በዚህ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችሏል። በተያዘው ዓመት በዚመን እና ኦስሎ ዳይመንድ ሊጎች ተሳትፎውም አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። በመሆኑም በምሽቱ ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የዘንድሮ ዓመት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሸናፊ የነበረው ታዳጊው አትሌት ቢኒያም ይህ ኦሊምፒክ ሃገሩን ለሁለተኛ ጊዜ የሚወክልበት ነው። በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ1ሺ500 ሜትር እስከ ፍጻሜ የተጓዘው አትሌቱ በሌሎች ርቀቶችም ተሳትፎውን ሲያሳድግ ቆይቷል። በ5ሺ ሜትር 12:54.10 የሆነ ሰዓት ያለው ሲሆን በርቀቱ ልምድ ካላቸው አትሌቶች ጋር ለሜዳሊያ ይፋለማል።
የዑጋንዳውያኑን አትሌቶች በውድድሩ ላይ አለመሳተፍ ተከትሎ ፍልሚያው የሚቀል ቢመስልም የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮናው ኖርዌዢያዊው ጃኮብ ኢንግብሪስተን መኖሩ ውድድሩን ለኢትዮ ጵያውያን ፈታኝ ያደርገዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በርቀቱ በኦሊምፒክ የሚሳተፈው አትሌቱ ከቀናት በፊት በ1ሺ500 ሜትር 4ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው።
ብርሃን ፈይሳ
-የኦሊምፒክ ማራቶንን ድል ለመመለስ የሚደረግ ትንቅንቅ
ኢትዮጵያ የኦሊምፒክ መድረክ ማራቶን የድል ጉዞ የሚጀምረው እአአ በ1960 ሮም ላይ በፈርቀዳጁ አትሌት ሻምባል አበበ ቢቂላ የባዶ እግር ገድል ነው። በአበበ የተጀመረው የድል ጉዞ በትውልድ ቅብብሎሽ በአስደናቂና አይረሴ ታሪካዊ ድሎች ታጅቦ ኢትዮጵያን በፓሪስ ሰማይ ስር ዳግም ድል እንድትጠበቅ አድርጓታል።
በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ የወንዶች ማራቶን ዛሬ የሴቶች ደግሞ ነገ ይካሄዳል። በዓለም አቀፍ ውድድሮች በርካታ ድሎችን መቀዳጀት የቻሉ ታላላቅ አትሌቶች እንዲሁም ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ለበርካታ ዓመታት የራቀውን የማራቶን ውጤት ለማስመለስ ተዘጋጅተዋል።
በጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ፊታውራሪነት የሚመራው የኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን በአትሌት ደሬሳ ገለታ እና አትሌት ታምራት ቶላ ጥምረት ለድሉ ከምንጊዜውም በላይ ተዘጋጅተል። አትሌቶቹ ወርቁን ለመውሰድና ታሪክን ለማደስ ከኬንያውያንና ከሌሎች የርቀቱ ጠንካራ አትሌቶች ከባድ ፍልሚያ እንደሚገጥማቸውም ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በመድረኩ በዚህ ርቀት በሜዳሊያ ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛ የምትገኝ ሲሆን 4 ወርቅ፣ 1 የብርና 3 ነሐስ በጥቅሉ 8 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ኬንያን፣ አሜሪካን እና ፈረንሳይን አስከትላ ደረጃውን ትመራለች። ኢትዮጵያ በዚህ ርቀት ለመጨረሻ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያን ያጠለቀችው በ2000ው የሲድኒ ኦሊምፒክ በአትሌት ገዛኸኝ አበራ አማካኝነት ሲሆን፤ ለመጨረሻ ጊዜ ሜዳሊያ ውስጥ በመግባት ያጠናቀቀችው ደግሞ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ ነው። ከ2008ቱ የቤጂንግ ኦሊምፒክ ጀምሮ የኬንያውያን የበላይነት የነገሠበትን የወንዶች ማራቶን ፉክክርን ለመቀልበስ የተዘጋጀው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጥምረት ወርቁን ለማስመለስ ዛሬ ከባድ ትግል ያካሂዳል።
በርቀቱ የሁለት ጊዜ ባለድል ኬንያዊ አትሌት ኤሉድ ኪፕቾጌ እና የቀድሞው ኦሊምፒክ 10 እና 5ሺ ሜትር ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ በቀለ መካከል የሚደረገው ትንቅንቅም ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ቀነኒሳ ለፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ተሳትፎ የወርቅ ሜዳሊያውን ለማጥለቅ ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። የ42 ዓመቱ አንጋፋ አትሌት ለድሉ ከቀድሞ የትራክ ባላንጣው ጋር አሁን ደግሞ በጎዳና ውድድር ለትልቁ ክብር እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ የሚያደርግ ይሆናል።
ቀነኒሳ ከብዙ የትራክ ላይ ድሎች በኋላ ፊቱን ወደ ጎዳና ውድድሮች በማዞር በትልልቅ የማራቶን ውድድሮች አመርቂ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። በጎዳና ውድድሮች የመጀመሪያውን ተሳትፎ ማድረግ የቻለው እአአ በ2014 የፓሪስ ማራቶን ሲሆን 2፡05፡04 በሆነ የውድድሩ ክብረወሰን ማሸነፍ ችሎ ነበር። በ2016ቱ የበርሊን ማራቶን 2፡03፡03 የሆነ ሰዓት ሮጦ የራሱ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል። በቫሌንሺያ የማራቶን ውድድር 2፡04፡19 በመሮጥ አራተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ከወራት በኋላ በለንደን ማራቶን 2፡04፡15 የሆነ ሰዓት በመሮጥ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቆ የአንጋፋ አትሌቶችን ክብረወሰን መጨበጥ ችሏል።
በሪዮና ቶኪዮ ኦሊምፒኮች የወርቅ ሜዳሊያን መውሰድ የቻለው ኪፕቾጌ ቶኪዮ ላይ የሮጠው 2፡08፡38 ሰዓት የተሻለው የኦሊምፒክ ሰዓቱ ሆኖ ሲመዘገብለት ከአበበ ቢቂላ በኋላ በኦሊምፒክ ለሁለት ተከታታይ ዓመት ያሸነፈ አትሌት ለመባል በቅቶ ነበር። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዛሬው ውድድር ከረጅም ዓመት በኋላ ወርቁን ለማስመለስ ብቻም ሳይሆን ታሪክንም ለማስጠበቅ ጭምር ይሮጣሉ።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ቡድኑ ለማሸነፍ የሚያስችለውን ተገቢ ዝግጅት ማድረጉን ከፓሪስ ጉዞው አስቀድሞ ገልጿል። ቀነኒሳ ከቡድኑ አባላት ጋር በቅንጅትና በትብብር በመሥራት ጥሩ ውጤት እንደሚመዘገብ እምነቱ ነው። የኦሊምፒክ ውድድር ትልልቅና ውጤታማ አትሌቶች ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚሳተፉበት የመሆኑን ያህል ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለማሸነፍ እንደሚሰለፉም ይገልጻል። እስከ አሁን ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ መድረክ ወክሎ ያስመዘገበው ውጤት ከፍተኛ ቢሆንም ለእሱ በቂ እንዳልሆነና ጠንክሮ መሥራት እንደሚፈልግም ጠቅሷል።
አትሌት ደሬሳ ገለታ ሌላው በርቀቱ ሜዳሊያን ለማስመዝገብ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን ከኬንያውያን የሚገጥመውን ፉክክር ለማሸነፍ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎም ይጠበቃል። አትሌቱ በጥቅምት ወር በቤጂንግ ማራቶን 2፡07፡41 የሆነ ሰዓትን በመሮጥ አሸንፏል። የቡድኑ ተጠባባቂና ጠንካራው አትሌት ታምራት ቶላም እንዲሁ ከኬንያዊው አትሌት ኪፕቾጌና ከሌሎች ሀገራት አትሌቶች ጋር ተፎካክሮ ወርቁን ለማስጠበቅ ከቀነኒሳና ደሬሳ ጎን ይሰለፋል።
ዓለማየሁ ግዛው
– በ1ሺ500 ሜትር ለሜዳሊያ የሚጠበቁት እንስቶች
በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ዛሬ ምሽት ከሚካሄዱ የፍጻሜ ውድድሮች መካከል አንዱ የሴቶች 1ሺ500 ሜትር ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በርቀቱ ለሜዳሊያ ይፎካከራሉ። በማጣሪያና በግማሽ ፍጻሜው ፉክክር በማድረግ ለሜዳሊያ ፍልሚያው የበቁት አትሌቶች ደግሞ ጉዳፍ ፀጋይ እና ድርቤ ወልተጂ ናቸው።
በዚህ ርቀት ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ በአትሌት አበባ አረጋዊ የነሐስ እንዲሁም በገንዘቤ ዲባባ የብር ሜዳሊያ ከማስመዝገብ የዘለለ ውጤት የላትም። ሊጠናቀቅ አንድ ቀን ብቻ በቀረው የፓሪስ ኦሊምፒክ ግን ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን የማግኘት ተስፋ አላት። ይሁን እንጂ በ5ሺ ሜትር የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ከነበሩ አትሌቶች በዚህ ርቀትም መሳተፋቸው ውድድሩን ፈታኝ ማድረጉ የማይቀር ነው።
ከተጠባቂ አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው በርቀቱ የቤት ውስጥ ክብረወሰን ባለቤቷ (3:53.09) ጉዳፍ ናት። እአአ በ2022 የቤልግሬድ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አሸናፊዋ አትሌት፣ በዩጂን ዓለም ሻምፒዮናም በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች። ከ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ስኬቷ የተመጣጠነ ውጤት በርቀቱ ስታስመዘግብ የዳይመንድ ሊግ ተሳትፎዎቿም ይህንኑ ያረጋግጣሉ። በተያዘው ዓመት ያስመዘገበችው 3:50.30 የሆነ ሰዓትም የግሏ ፈጣን ሲሆን፤ በርቀቱ በቀዳሚነት ሦስተኛውን ደረጃ ይዟል። ጉዳፍ በ10ሺ ሜትር ተሳትፋ 24 ሰዓት ባልሞላ ልዩነት ይህን ውድድር የምታደርግ ቢሆንም ለሜዳሊያ የምታደርገው ትንቅንቅ አጓጊ ነው።
በቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና ባልተጠበቀ ሁኔታ የብር ሜዳሊያ በማጥለቅ የስፖርት ቤተሰቡን ያስደሰተችው ወጣት አትሌት ድርቤ ወልተጂ በተለይም በግማሽ ፍፃሜው ማጣሪያ ባሳየችው ድንቅ ብቃት ዛሬ በፍፃሜው ጠንካራ ተፎካካሪ እንደምትሆን ተስፋ እንዲጣልባት አድርጋል። ወጣቷ አትሌት በዓለም የጎዳና ላይ ሻምፒዮና በአንድ ማይል አሸናፊ ስትሆን፤ በተያዘው ዓመት የግላስኮ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ግን 5ኛ ደረጃን ነበር ይዛ ያጠናቀቀችው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም