የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ በሀገሪቱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ትልቅ አቅም በመሆን ይታወቃል፡፡ ከሀገሪቱ ካፒታል በጀት አብዛኛው የሚውለው ለመሠረተ ልማትና ለመሳሰሉት ግንባታ የሚውል እንደመሆኑም ይህን ሀብት በማንቀሳቀስ በኩል ትልቅ ኃላፊነትም አለበት፡፡
ዘርፉ በሀገር ምጣኔ ሀብት እድገትና በሥራ እድል ፈጠራ ከግብርናው ዘርፍ ቀጥሎ ይጠቀሳል፡፡ በከተማና ገጠር መሠረተ ልማት ግንባታ ዋናው ተዋናይ የሆነው ይህ ዘርፍ ሀገሪቱ በቀጣይ የምታካሂዳቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች በመዳፉ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከዘርፉ ብዙ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ከቴክኖሎጂና እውቀት ውስንነት፣ በግዥ ሂደት ከሚያጋጥሙ ችግሮች፣ ከውጭ ምንዛሬ አጥረት፣ ከፋይናንስ አቅርቦት እጥረት፣ ከፕሮጀክት አስተዳደር እና ከመሳሰሉት አኳያ ባሉበት ውስንነቶች የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ሳይችል እንደቀረ በተለያዩ መድረኮች ይገለጻል፡፡
በተለይ ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የሚታይበት ውስንነት ተወዳዳሪ እንዳይሆን እንዲሁም ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እንዳይችል ሲያደርገው ቆይቷል፡፡ ቴክኖሎጂንና እውቀትን ከውጭ ለማምጣትም ሆነ ከሀገር ውስጥ ለመግዛት ወሳኝ የሆነው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ደግሞ ትልቁ ፈተና እንደሆነበት ይገለጻል፡፡
ለግንባታው ዘርፍ የሚያስፈልጉ እንደ ማጠናቀቂያ ግብዓቶች ያሉት ምርቶች፣ ማሽነሪዎች ወዘተ ከውጭ የሚመጡ መሆናቸውና ለእዚህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ የግድ ማስፈለጉ ዘርፉ በሚጠበቅበት ልክ እንዳይጓዝ ካደረጉት ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ለፕሮጀክቶች በወቅቱ አለመጠናቀቅ፣ ተወዳዳሪ ላለመሆን በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ቢችሉም የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከዋናዎቹ መካከል ስለመሆኑ በተለያዩ መድረኮች ይገለጻል፡፡
ሀገሪቱ በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ ያስገባቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና እሱን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ የወጣው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ የኮንስትራክሽን ዘርፉን በአጠቃላይ በተለይ በቤቶች ልማት ወይም በሪል ስቴት ልማት ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች እየተገለጹ ናቸው፡፡ በተለይ የውጭ ምንዛሬ ግብይቱ በገበያ እንዲመራ መደረጉ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚቻልበትን እድል እንደሚከፍትም እየተጠቆሙ ይገኛሉ፡፡
የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ሀብተማሪያም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኮንስትራክሸን ኢንዱስትሪው ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል። ማሻሻያው በዘርፉ ያጋጥሙ የነበሩትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የደረቅ ክሬዲት ወይም የኮንስትራክሽን ኤልሲ ምንዛሪ የማግኘት ችግርን ይፈታል ሲሉም ተናግረው፣ በሀገር ውስጥ ለሚመረቱ የግንባታ ምርቶች የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎችን ማግኘት እንደሚያስችልም አስታውቀዋል።
ከውጭ የሚገቡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በተለያዩ አስመጪ ድርጅቶችና ኩባንያዎች በብዛት ብቻ ሳይሆን በጥራትም ጭምር ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እንደሚያስችል፣ በዚህም ከጥራት እና ከእጥረት አንፃር ያለውን የኮንስትራክሽን ግብዓት ችግር ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የተወሰኑ አስመጪዎች በበላይነት ይዘውት የነበረውን የኮንስትራክሽን ግብዓት ከውጭ የማምጣት ሥራ ሌሎች አቅሙ ያላቸው ዜጎች እንዲሰማሩበትና ውድድሩ ከፍ እንዲል ያደርጋል። በዚህ በኩል የሚመለከተው የጥራት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ቁጥጥር በማድረግ በሀገሪቱ የግንባታ ሕግና ደንብ ላይ ለውጥ ይደረጋል ተብሎ ይታሰባል።
አተገባበር ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ግድፈቶችንም አብሮ ማየት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትንና በሀገር ውስጥ የሚመረቱትን የግንባታ ግብዓቶች ዋጋን በአግባቡ መቆጣጠር እንደሚገባም መክረዋል፡፡ ይህ ካልሆነ የኑሮ ውድነት ይባባሳል። የሚመለከተው ባለሥልጣን አሰራር ቀይሶ ቁጥጥሩ ላይ መሥራት አለበት ሲሉም ያስገነዝባሉ።
ኢንጂነር ግርማ ‹‹የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ባለድርሻ እንደመሆናችን ማሻሻያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እንዲሆን ከፍ ያለ ፍላጎት አለን ያሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፣ ለዚህ ምክንያት ያሉትም በሀገሪቱ በርካታ ፕሮጀክቶች በማጠናቀቂያ እቃዎች እና በውጭ ምንዛሬ ችግር ምክንያት የቆሙበትን ሁኔታ ነው፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በጣም ውድ የኤሌክትሮ መካኒካል፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የኤሌክትሪክ እቃዎች እና ሌሎችም ቴክኖሎጂን የሚጠይቁ እቃዎች ሳይገቡ ቀርተው ብዙ ፕሮጀክቶች ቆመዋል። እነዚህ ብዙ ሀብት የፈሰሰባቸው ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ተግባር እንዲገቡ ማድረግ ይገባል። የግንባታውን ዘርፍ ከባሕላዊ እና ልማዳዊ አሰራር ወደ ቴክኖሎጂ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰው፣ በዚህ በኩል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የማህበሩ ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል።
የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ ሆኖ ከሀገር አልፎ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የመሄድ ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው፣ ይሁንና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሀገር ውስጥ ያለውን የግንባታ ዘርፍ ችግር በማይፈታበት ደረጃ ላይ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ማሻሻያው በአተገባበር ብዙ ፈተናዎች ሊያጋጥሙት ይችላሉ ሲሉም ስጋታቸውን ጠቁመው፣ በዚህ ዓይነት አሰራር ለጉዳት የተዳረጉ ሀገሮች ዓይነት ችግር እንዳያጋጥመን በትግበራው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች አቅም አለመገንባት እና እየተዳከመ መምጣት በርካታ የውጭ ኮንትራክተሮች የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን ቦታ እንዲይዙ የሚያስገድድበት ሁኔታ ይፈጥራል ሲሉም አመልክተው፣ ይህ ለሀገራችን የግንባታ ዘርፍ ተወዳዳሪነት ፈታኝ የሆነ ሌላ አጀንዳ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
“የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ሥራ በጥራት አይጨርሱም፤ የውጭዎቹ በጥራት ይጨርሳሉ” ሲባል እንደሚሰማም ጠቅሰው፣ በቂ ድጋፍ ከተደረገላቸው የኢትዮጵያ ተቋራጮችም የውጭዎቹ የሚሰሩትን ለመሥራት የሚያስችል አቅም አላቸው ሲሉ ገልጸዋል። በቅርቡም አንዳንድ ኮንትራክተሮች የውጭ ሥራ ተቋራጮች ከሚሰራቸው ጥራት በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርተው ያስረከቡበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡
የኮንስትራክሽን፣ ዲዛይን እና ሪልስቴት ዘርፎች አማካሪው ኢንጂነር ደሳለኝ ከበደ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አቅም ያላቸው የውጭ ባለሀብቶችን፣ ባለሙያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ለመሳብ እገዛ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ።
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቴክኖሎጂያቸውን ይዘው መጥተው በመሸጥ፤ ትርፋቸውንም ይዘው መሄድ የሚችሉበት እድል እንደተፈጠረላቸው አስታውቀዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም በተመቻቸው የውጭ ምንዛሪ ገበያ በመጠቀም በሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ በየትኛውም የዓለም ክፍል ያለውን ቴክኖሎጂ ይዘው መምጣት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ይላሉ።
የሀገሪቱ ባለሀብቶች ለግንባታው ዘርፍ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከውጭ እንደሚያስመጡ ጠቅሰው፣ በርካታ የሀገር ውስጥ የብረት ፋብሪካዎች ማምረት ከሚገባቸው አቅም በታች እያመረቱ ባለበት ሁኔታ አብዛኛው የብረት ምርት ከውጭ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ የተነሳም አዳዲስ የብረት እና የኮንስትራክሽን እቃ ግብዓቶች ወደ ዘርፉ ገብተው ሥራ አልጀመሩም። በኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት ይሄ ችግር ከተፈታ አዳዲስ የግንባታ ግብዓት አምራች ፋብሪካዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። መለዋወጫ ለማሟላት የውጭ ምንዛሪ ይጠባበቁ የነበሩ ማሽኖች መለዋወጫው ተገዝቶላቸው እንደ አዲስ ይነሳሉ። በግንባታ ላይ ያሉም ይጠናቀቃሉ። በዚህ ሀገር የሌለ ከውጭ መምጣት ያለበት ቴክኖሎጂም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ ይሰፋል። ከውጭ የሚመጣውን የግንባታ ግብዓት የሚተኩ ምርቶች በሀገር ውስጥ ሊመረቱ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኮንስትራክሽን በቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘ ነው የሚሉት ኢንጂነር ደሳለኝ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም በርካታ የኮንስትራክሸን ቴክኖሎጂ ችግሮችን ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
በሀገሪቱ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት ይስተዋላል፤ የዚህ ምክንያቱ በተለመደው የግንባታ ዘይቤ እየተሰራ በመሆኑ ነው ሲሉ አመልክተው፣ ዓለም የቤት ችግሩን የፈታው እኛ አሁን በምንሰራው አካሄድ አይደለም፤ በቴክኖሎጂ ነው›› ይላሉ፡፡
የተገጣጣሚ ሕንፃዎች ቴክኖሎጂ በዓለም ጥቅም ላይ ከዋለ መቆየቱን ጠቅሰው፣ በዚህ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ቴክኖሎጂዎቹን ገዝቶ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን እንደሚጠይቅም እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ገዝቶ ብዙ ቤቶችን መገንባት እንደሚቻልም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በ1978 ዓ.ም አካባቢ የተቋቋመ የተገጣጣሚ ሕንፃ ማምረቻ ፋብሪካ ነበር። በወቅቱም በቴክኖሎጂው በርካታ ቤቶችን መገንባት ተችሏል ይላሉ፡፡
ኢንጂነር ደሳለኝ እንዳሉት፤ አሁን በዓለም ሀገራት የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ናቸው፤ እነዚህን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት በርካታ የግንባታ ግብዓቶችን እንዲሁም ሕንፃዎችን ማምረት ይቻላል። ቢም፣ ኮለን፣ ስላቭ በፋብሪካ ደረጃ በማምረት አጓጉዞ ለመግጠምም ቴክኖሎጂን ይፈልጋል። ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገር ውሰጥ በስፋት እንዲገባ ለማድረግ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጥሩ አማራጭ ይሆናል ሲሉም ጠቅሰው፣ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮችም ችግራቸውን ለመፍታት በዚህ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመላክተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወደ ትግበራ የገባው በቅርቡ ነው፤ እሱን ተከትሎ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት መለቀቅ የጀመረው የገንዘብ ድጋፍ ገና ወደ ጥቅም አልተቀየረም ሲሉም ጠቅሰው፣ ድጋፉ ፋይዳው እየታየ እንደሚሄድ እና አዎንታዊ ውጤት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ችግርን በመፍታት ላይ ማተኮሩ እየታየ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ይሄንን ተከትለው የሚወጡ ቀጣይ ፖሊሲዎች ይኖራሉ ብለው እንደሚጠበቁም አመልክተዋል።
ማሻሻያው የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ተወዳዳሪ ከማድረግ አንፃርም የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ኢንጂነር ደሳለኝም አመልክተዋል። ማሻሻያው ላደጉት ሀገራት ጭምር ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ ጠቅሰው፣ እነዚህ ሀገሮች ግንባታቸውን ጨርሰዋል፤ የገንዘብ አቅም ግን አላቸው፤ በሀገራችን ደግሞ ከፍተኛ የግንባታ ፍላጎት አለ ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ 130 ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብ አለ። ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግርም አለ። ከሕዝቡ 70 በመቶው ወጣት ነው፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ጉልበትም አለ። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሚያመጣው መልካም እድል ወጣቱ የሥራ እድል ተጠቃሚ ሲሆን ፣ ቤተሰቡንም ኑሮውንም ሊያሻሻል ይችላል። መኪና፣ ብስክሌት የመሳሰሉትን መግዛት፣ ኢኮኖሚውን ማሻሻል ይችላል፡፡
በርካታ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ይጀምራሉ፤ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ይመጣሉ፤ የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ይደረጋል። ባደጉት ሀገሮች የሰው ጉልበት ውድ ነው፤ በአንፃራዊነት በኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ጉልበት ሰላለ ይህን ፍለጋ ባለሀብቶች ወደዚህ ይመጣሉ።
አሁን በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ብቻ ግን ለውጥ አይጠበቅም ሲሉም ኢንጂነር ደሳለኝ አስገንዝበዋል፡፡ እሳቸው በሪል እስቴት ዘርፍ በብዛት እንደሚሳተፉ ጠቁመው፣ ይህም የዘርፉን ዋና ዋና ችግሮች እንዲመለከቱ በር እንደከፈተላቸው ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ የመጀመሪያው የብድር ገደብ አለ። ለቤት ገዢም የተመቻቸ የብድር አቅርቦት የለም።
ማሻሻያው ውጤታማ እንዲሆን በቀጣይ ብዙ ፖሊሲዎች አብረው ሊወጡ እንደሚገባም ነው አማካሪው የጠቆሙት፡፡ ኢንጂነሩ ያስፈልጋሉ ካሏቸው ፖሊሲዎች መካከል አንዱ የሪልስቴት ግብይትን የሚመለከት ነው፤ የሪል ስቴት ግብይቱ በመንግሥት ደረጃ የሚመራ መመረት እንዳለበት ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ማሻሻያው ወደ ሥራ መግባቱ ማምረት አቁመው የነበሩ የብረት ፋብሪካዎች ጥሬ እቃ የሚያገኙበት እና ብዙም ሊያመርቱ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። ማሻሻያውን ተከትሎ ሲሚንቶ 100 እና 200 ብር አካባቢ ጨምሯል፤ ምርቱ የሀገር ውስጥ ስለሆነ ወደፊትም ብዙ ይጨምራል ተብሎ አይገመትም። ብዙ ሲሚንቶ የሚያመርት ፋብሪካ ከሶስት ወር በኋላ ወደ ሥራ ይገባል። በዚህ ጊዜም ብዙ ምርት ይኖራል ሲሉ ያብራራሉ።
በኮንትሮባንድ እያስገቡ የሚሸጡ እንዳሉም ጠቅሰው፣ ይህን ኮንትሮባንድ ማስቆም ከተቻለ እና ፋብሪካዎቹም በጥሩ አቅም ካመረቱና በቂ አቅርቦት ከተሰጣቸው በርግጠኝነት የብረት ዋጋም በነበረበት ይጸናል ሲሉም አስታውቀዋል። የኮንስትራክሽን ዋጋ ጭማሪ መሠረት የሚያደርገው በግንባታ ግብዓቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በዶላር ምንዛሪ ዋጋ ጭማሪ ላይም መሆኑን ኢንጂነር ደሳለኝ ተናግረዋል።
በኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት ከአይ ኤም ኤፍ እና ከዓለም አቀፍ ረጂ ሀገራት የተሰጠው ድጋፍ ኢኮኖሚው እንዲንቀሳቀስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህ ሰዓት የቆሙ መንግሥት በባለቤትነት የያዛቸው ፋብሪካዎች አሉ። በሰላምም፣ በፋይናንስ ችግርም የቆመ የመንገድ ፕሮጀክት አለ፤ እነዚህ ሁሉ እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
ቤትም ሀገርን ኢኮኖሚን ያንቀሳቅሳል። ይህ እንዲንቀሳቀስ ድጋፉ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል። ፋብሪካ የሚቆም ከሆነ መብራት፣ ውሃ መንገድ እንዲሁም ሌሎች መሠረተ ልማቶችም ይጎዳሉ ሲሉም ጠቅሰው፣ ድጋፉ በትክክል ከተመራ የቆመ መኪና እንደማስነሳት በሁሉም ዘርፍ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያነቃንቅ የመጣ ነው ሲሉም ይገልፃሉ።
ዓለም አቀፍ ደጋፊዎች ገንዘብ ሲሰጡም የራሳቸውን ፍላጎት ጨምረው ነው ያሉት ኢንጂነር ደሳለኝ፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይ የኮንስትራክሸኑ ዘርፍ ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ይበልጥ ክፍት እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡መንግሥትም ሀገራዊ ጥቅሙን ያስጠብቃል ብለዋል።
የውጭ ተቋራጮች ወደ ሀገሪቱ መጥተው በኮንስትራክሽን ዘርፉ ሲሰማሩ የሚያመጡት ትሩፋት እንዳለም ጠቅሰው፣ የዚያኑ ያህልም በሀገር ውስጥ ያሉትን ኮንትራክተሮች ሥራ እንዳይሻሙና ከገበያ ውጭ እንዳያደርጓቸው በፖሊሲ አቅርቦት አሰራር መደገፍ እንደሚያስፈልግና ለእዚህም መንግሥት እንዲያስብበት አመላክተዋል። ብሔራዊ ባንክ የዶላር ጨረታ ለባንኮች ማውጣቱን ጥሩ ሲሉ ጠቅሰው፣ በዚህ መልኩ ጣልቃ በመግባት የውጭ ምንዛሬ ግብይቱን ወደ ሥርዓት ማስገባት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ማሻሻያው ወደ ቀደመው አሰራር ተመልሶ እንዲገባ የሚፈልጉ አካላትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል መንግሥት ማስተካከያ ማድረግ አለበት የሚል እምነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። መደበኛ አቅጣጫ በሚሰጥበት ጊዜ መደበኛ ያልሆነው አሰራር ሁልጊዜ ወደኋላ ይጎትታል ሲሉ አስገንዝበው፣ ተገቢ የቁጥጥር አሰራር ሊበጅ እንደሚገባም ይመክራሉ።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም