ከቢሊየነሩ ኢላን መስክ ጋር በአደባባይ የቃላት ምልልስ ውስጥ የገቡት የቬኒዙዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ኤክስን ለ10 ቀናት አገዱ።
የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ባለቤት የሆነው ኢላን መስክ ፕሬዚዳንቱን “አምባገነን” እንዲሁም “ቁምነገር አልባ” ሲል ከመወረፍ አልፎ የፕሬዚዳንቱን የማሰላሰል አቅም ከአህያ ጋር አነጻጽሯል።
ፕሬዚዳንቱ በምላሹ መስክን፤ ‘ፋሽስት’ እንዲሁም በቬኒዙዌላ “ጥላቻ የሚዘራ እና የእርስ በእርስ ጦርነት የሚቀሰቅስ” ሲሉ ወርፈውታል።
የሁለቱ ግለሰቦች ውዝግብ የጀመረው አወዛጋቢው የቬኔዙዌላን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኒኮላስ ማዱሮ ማሸነፋቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተደረገው ምርጫ በብዙ የምርጫ ታዛቢዎች ዴሞክራሲያዊ አልነበረም ተብሏል።
ከአንድ ወር በፊት የተደረገውን የምርጫ ውጤት ያልተቀበሉ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ጸረ-መንግሥት የሆኑ የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲው ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ምርጫውን ማሸነፋቸውን የሚያሳይ ማስረጃ አለን ሲሉ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ማዱሮ የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ወቅት የሳይበር ጥቃት ደርሶበት ነበር ካሉ በኋላ፤ ኢላን መስክ ዳግም እንዳልመረጥ የሳይበር ጥቃት አስከፍቶብኛል ብለዋል።
በቬኔዙዌላ መንግሥት ምርጫውን እንዲታዘብ ወደ ሀገሪቱ የገባው የካርተር ማዕከል ግን በምርጫ ቦርዱ ላይ የሳይበር ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳይ ምንም አይነት ምልክት አልታየም ብሏል።
ማዱሮ በቴሌቪዥን መስኮት በቀጥታ በተላለፈ ንግግራቸው ለኢላን መስክ ምላሽ ለመስጠት በሚመስል ርምጃ ኤክስ ለ10 ቀናት በቬኒዙዌላ ይታገዳል ብለዋል።
“ኢላን መስክ የኤክስ ባለቤት ነው። ሁሉንም ሕጎች ጥሷል” ብለዋል ማዱሮ።
“ጥላቻ በመንዛት፣ በፋሺዝም፣ የእርስ በእርስ ጦርነት በመቀስቀስ፣ ለቬኒዙዌላውያኖች ሞት በመመኘት ሁሉም ሕጎች ጥሷል” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው።
ከቬኒዙዌላው ምርጫ በፊት ኢላን መስክ ለዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩ ድጋፉን ገልጾ ነበር።
ከምርጫው በኋላ መስክ “በማዱሮ መንግሥት ትልቅ የምርጫ ውጤት ማጭበርበር ተከናውኗል፤ አምባገነኑ ማዱሮ አሳፋሪ ናቸው” ሲል ጽፎ ነበር።
በዚህ ያልተገደበው መስክ፤ የፕሬዚዳንት ማዱሮን የማሰላሰል አቅም ከአህያ ጋር በማመሳሰል “የቬኒዙዌላ ሕዝብ ይህን ቁም-ነገር አልባ ሰው በቃን ያሉበት ጊዜ ነው” ብሏል።
የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ማዱሮ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ይፋ ቢያደርግም የአሜሪካ፣ አርጀንቲና፣ ኡራጉዋይ እና ኢኳዶር መንግሥታት ምርጫውን ያሸነፉት ተቃዋሚው ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ ናቸው ብለዋል።
ምርጫ ታዛቢው የካርታር ማዕከል እንዲሁም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟላ አይደለም በማለት ዴሞክራሲያዊ አይደለም ሲል ደምድሟል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም