ሜክሲኮ ፕሬዚዳንት ፑቲንን እንድታስር የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ አደረገች።
በሜክሲኮ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ክላውዲያ ሼንቡአም ማሸነፋቸው ይታወሳል።
አዲሷ ተመራጭ ፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት በፈረንጆቹ ጥቅምት አንድ ቀን ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል።
በርካታ ሀገራት በፕሬዚዳንቷ በዓለ ሲመት ላይ እንዲገኙ ግብዣ የቀረበላቸው ሲሆን ፕሬዚዳንት ፑቲን ግብዣው ከቀረበላቸው መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ሩሲያ ከሜክሲኮ የቀረበላትን ግብዣ እንደተቀበለች መገለጹን ተከትሎ ዩክሬን ፕሬዚዳንት ፑቲን ወደ ሜክሲኮ እንደገቡ እንዲታሰሩ ጥያቄ አቅርባለች።
ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፑቲን በዩክሬን ላይ የዘር ማጥፋት ፈጽመዋል በሚል የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱ አይዘነጋም።
ይህን ተከትሎም ሜክሲኮ ፕሬዚዳንት ፑቲንን አስራ ለጦር ወንጀል ፍርድ ቤት እንድትሰጥ በዩክሬን በኩል ጥያቄ ቀርቦላታል።
ተሰናባቹ የሜክሲኮ ፕሬዚዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ የዩክሬንን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ “ጉዳዩ እኛን አይመለከትም” ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሜክሲኮ የዓለም አቀፉ ጦር ወንጀል ፍርድ ቤት አባል ስትሆን ሩሲያ በአንጻሩ አባል አይደለችም።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ክላውዲያ ሼንቡአም የሜክሲኮ አዲስ ፕሬዚዳንት ሆና ስትመረጥ የእንኳን ደስ አለሽ መልዕክት ካስተላለፉ የዓለም መሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በወቅቱ ሩሲያ በደቡብ አሜሪካ ካሏት ወደጅ ሀገራት መካከል ሜክሲኮ ዋነኛዋ ናት ብለው ነበር።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም