አሜሪካ በየመን የሃውቲ ቡድን ይዞታዎችን በመደብደብ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች ማውደሟን አስታወቀች። ቡድኑ ትናንት በኤደን ባሕረሰላጤ ሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦችን መምታቱን መግለጹ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሰው የአሜሪካ እዝ (ሴንትኮም) የአጸፋ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
በተፈጸመው የአየር ድብደባ ሁለት የሃውቲ ድሮኖች፣ ሦስት ጸረ ሚሳኤል ክሩዝ ሚሳኤሎች እና የመቆጣጠሪያ ጣቢያው መውደማቸውን ነው ማዕከላዊ እዙ የገለጸው። የሃውቲዎችን ጥቃት “ኃላፊነት የጎደለውና አደገኛ ነው” መሆኑን በመጥቀስም ለቀጣናው መረጋጋት ሲባል የቡድኑን ይዞታዎች መደብደቡን እንደሚቀጥልም ጠቁሟል።
ማዕከላዊ እዙ የየመኑ ቡድን በሁለት የጦር መርከቦቹ ላይ ጥቃት ስለማድረሱ ግን ማረጋገጫ አልሰጠም። የሃውቲ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ ግን የቡድኑ አየር ኃይል ድሮኖችን በማስወንጨፍ “ኮል” የተሰኘችውን የአሜሪካ የጦር መርከብን መምታቱን ገልጸዋል።
“ላቦን” የተባለችው የጦር መርከብ ደግሞ በባለስቲክ ሚሳኤል መምታቷን መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሃውቲዎች በቅርቡ በሰሜናዊ የመን ሳዳ ግዛት ተመቶ የወደቀውን ግዙፍ ሰው አልባ አውሮፕላን ስብርባሪዎች የሚያሳይ ምስል መልቀቃቸው ይታወሳል ሲል አል ዐይን ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም