በዩናይትድ ኪንግደም ዘረኝነትን የሚነቅፉ ሰልፎች ተካሄዱ

በዩናይትድ ኪንግደም ከሳምንት በፊት የተጀመረውን ስደተኞች ጠል ነውጥ የሚቃወሙ የፀረ ዘረኝነት ሰልፎች ተካሄዱ። ስደተኞች ጠል ሰልፎች ይካሄዱባቸዋል በተባሉባቸው የሰሜናዊ ለንደን፣ ብሪስትል እና ኒውካስል አካባቢዎች ነውጦቹን በመቃወም ሠላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።

ስደተኞች ጠል ነውጥን በሚቃወሙት ሰልፎች ላይ “ስደተኞች መምጣት ይችላሉ” የሚሉና ሌሎችም ዘረኝነትን የሚኮንኑ መፈክሮች ታይተዋል። ከ100 በላይ ሰልፎች ይካሄዳሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ተሰማርተዋል።

ባለፈው ወር በሳውዝፖርት ሦስት ሕጻናት ልጆችን በስለት የወጋው ሙስሊም ጥገኝነት ጠያቂ ነው የሚል የተሳሳተ ዜና ከወጣ በኋላ ነው ነውጡ የተጀመረው። መጀመሪያ ላይ ጥቃት መሰንዘር የተጀመረው ጥገኝነት ጠያቂዎች የተጠለሉባቸው ሆቴሎችና መስጊዶች ላይ ሲሆን መደብሮችም ተቃጥለዋል፤ ተዘርፈዋል።

በዕለቱም ስደተኞች ጠል ነውጦችን በመፍራት ሱቆች ተዘግተው ውለዋል። የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከቱ ሠራተኞች ያሉባቸው የሕግ ተቋማት ስም ዝርዝር ይፋ ከተደረገ በኋላ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመስጋት ከቤት እንዲሠሩ ተነግሯቸዋል። የፀረ ዘረኝነት ሰልፎቹ በአብላጫው በሠላማዊ መንገድ እንደተካሄዱ ተገልጿል። የተወሰኑ ሰዎች መታሰራቸውም ሪፖርት ተደርጓል።

ከሠላማዊ ሰልፎቹ መካከል በሊቨርፑል የተካሄደው ሰልፍ በጥገኝነት ጠያቂዎች ቢሮ አቅራቢያ ነው። ይህ መሥሪያ ቤት በስደተኞች ጠል ነውጥ ቢጎዳም የፀረ ዘረኝነት ሰልፈኞቹ ለስደተኞቹ ድጋፋቸውን ገልጸውበታል።

በለንደን በሚገኙት ዋልትማስቶው እና ኖርዝ ፊንችሊ በሺዎችን የሚቆጠሩ ሰዎች ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ ፀረ ዘረኝነት አቋማቸውን አንፀባርቀዋል። በብሪስቶል የሠራተኞች ማኅበሮች የፀረ ፋሺስት ቡድኖች እንዲሁም ጥቁሮችና እስያውያን ሠላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

በኒውካስል አንድ ሺህ የሚጠጉ በአብዛኛው ሙስሊሞች የሆኑ ሰልፈኞች ለስደተኞች አገልግሎት በሚሰጠው ቤከን ሴንተር አካባቢ ድምፃቸውን አሰምተዋል። በአክሪግንተን ለሙስሊሞች ድጋፍ የሚያደርጉ የማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄዎች ተደርገዋል።

በሳውዝሀምተን ከ300 እስከ 400 የሚሆኑ ሰዎች በገቨርነርስ ስኩዌር ተገኝተው “ዘረኞች ቤታችሁ ግቡ” “ዘረኛነት ከጎዳናችን ይጥፋ” የሚሉ መፈክሮች አሰምተዋል። 10 ስደተኞች ጠል ሰልፈኞች በቦታው ቢደርሱ ፖሊስ ሁለቱን ቡድኖች ለያይቶ ጥበቃ አድርጓል።

ባለፈው ሳምንት ከተነሳው ስደተኞች ጠል ነውጥ ጋር በተያያዘ 400 ሰዎች ታስረዋል። ከ140 በላይ ሰዎች ሲከሰሱ ከመካከላቸው ፍርድ የተላለፈባቸውም ይገኙበታል። ሳውዝፖርትና በሊቨርፑል ነውጥ ሦስት ሰዎች እስር ተፈርዶባቸዋል። ከእነዚህ እስሮች ጋር በተያያዘ በሚመስል ሁኔታ ነገሮች እየረገቡ ይመስላል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጅላ ሬይነር በሮተርዳም የሚገኘው ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚጠለሉበት ሆሊደይ ኢን ኤክስፕረስ ሆቴልን ጎብኝተዋል። ይህ ሆቴል ባለፈው እሑድ በስደተኞች ጠል ነውጠኞች ጉዳት ደርሶበታል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ነውጠኞቹ “በሕግ ይጠየቃሉ” ሲሉ ሌሎች ሰዎችም ከነውጡ “እንዲርቁ” አሳስበዋል፡፡

“ጎዳና ላይ ወጥቶ ፖሊሶች ላይ ጥቃት ማድረስ ወይም እንደዚህ ያሉ ሆቴሎችን መጉዳት ምክንያት አልባ ድርጊት ነው። በዚህ አገር ፖለቲካችንን የምናከናውንበት መንገድ አለ። ያንን የሚያፈርስ ነውጠኛና ሁከተኛ ነው” ብለዋል። አድማ በታኝ ፖሊሶች በቀጣይ ቀናትም ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም

Recommended For You