በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ቀናት ውስጥ ህፃናት በአግባቡ ካልተመገቡ ሊመለስ የማይችል አካላዊና አእምሯዊ ዕድገት መገታት ወይም መቀንጨር ሊያጋጥማቸው ይችላል።በነዚህ ቀናት የተስተካከለ አመጋገብ መከተል ደግሞ በርካታ ጥቀሞች እንደሚያስገኙ በመጥቀስ የአመጋገብ ሥርዓቱን ወላጆች እንዲከተሉ የጤና ባለሞያዎች ይመክራሉ።
ከስድስት ወር በላይ የሆናቸው ህፃናት በሚመገቧቸው ምግቦች ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን እንደምግቡ አይነትና ይዘት ይለያያል።በየትኛውም የህፃናት ምግብ ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ግን መገደብ እንዳለበትና ወላጆችም ለልጆቻቸው ጣፋጭ ምግቦችን ከመስጠት ይልቅ የአትክልት ምግቦችን የበለጠ መመገብ እንዳለባቸው በቢሲ የህፃናት ጤና ባለሞያዎች ሰሞኑን ይፋ ያደረጉትን ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የህፃናት ምግብ ማር ወይም ፍራፍሬ ከሚይዘው ጣፋጭ ውጭ ምንም አይነት ስኳር ያልተጨመረበት መሆን እንዳለበት ያስጠነቀቀው ሪፖርቱ፤ ወላጆች ለጨቅላ ህፃናት ጎምዛዛ ጣዕም ያላቸውን ምግቦች መስጠት እንዳለባቸው በተለይ የሮያል ኮሌጅ የህፃናትና የልጆች ጤና ትምህርት ክፍል ጠቁሟል።ይህም የህፃናት ጥርስን ከመበስበስ የሚያድን፣ ደካማ አመጋገብን የሚያስቀርና ቅጥ ያጣ ውፍረትን ለመቀነስ የሚረዳ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሷል።
ምክረ ሃሳቡ ሊቀርብ የቻለው በእንግሊዝ አገር የህፃናትን ጤንነት እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል በተሠራው ሪፖርት ውስጥ ሲሆን፣ የህፃናትን ውፍረት መቀነስ በሁሉም የእንግሊዝ ግዛቶች ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ በመሆኑና እ.ኤ.አ በ2030 መጠኑን ለመቀነስ ከስኮትላንድ ጋር ስምምነት የተገባበት መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል።
በእንግሊዝ እ.ኤ.አ በ2018 ጣፋጭ መጠጦችን ለመቀነስ የተጣለውን ግብር መነሻ በማድረግ መንግሥት በህፃናት ምግቦች ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለመቀነስ አስገዳጅ ገደብ ማስተዋወቅ እንዳለበትም ሪፖርቱ ጠቁሟል።በምግቦቹ ማሸጊያዎች ላይ የስኳር መጠንን የሚገልፁ ምልክቶች ቢኖሩም፣ አብዛኛዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ተፈጥሯዊና ተጨማሪ ስኳሮችን እንደሚይዙ አመልክቷል።
ሪፖርቱ እንደጠቆመው፤ ጨቅላ ህፃናት በምንም አይነት ጣፋጭነት ያላቸው መጠጦችን መውሰድ የለባቸውም።ከዚህ ይልቅ ከንፁህ ፍራፍሬዎች፣ ወተትና ካልተቀነባበሩ የወተት ተዋጽኦዎች ተፈጥሯዊ ስኳር ማግኘት ይችላሉ።
በሮያል ኮሌጅ የህፃናትና የልጆች ጤና ትምህርት ክፍል የሥነ ምግብ ባለሞያዋ ፕሮፌሰር ማሪ ፊውትሬል ህፃናት ከተወለዱ ከስደስት ወር በኋላ የሚወስዷቸው ምግቦች በአብዛኛው ከፍተኛ የፍራፍሬ መጠን ያላቸው ወይም የጣፋጭነት ይዘት ያላቸው የአትክልት ምግቦች መሆናቸውን ይገልፃሉ።
ለህፃናት ተብለው የሚዘጋጁ የፈሳሽ ይዘት ያላቸው የታሸጉ ምግቦችም ከፍተኛ የቅባትና የስኳር መጠን ያላቸው መሆናቸውን ያስረዳሉ።እንዲህ አይነቶቹን ምግቦች ህፃናት በአፋቸው በመምጠጥ ስለሚመገቧቸው በማንኪያ አልያም በራሳቸው መመግብ እንዳይችሉ የሚያደርጉ መሆናቸውንም የሥነ ምግብ ባለሞያዋ ያብራራሉ።
የህፃናት ምግቦች ከፍራፍሬ ስኳር የተሠሩ ከሆነ ‹‹ስኳር ያልተጨመረባቸው›› በሚል በማሸጊያቸው ላይ ምልዕክት ሊደረግባቸው ይችላል የሚሉት የሥነ ምግብ ባለሞያዋ፤ሁሉም የስኳር አይነቶች በህፃናት ጥርስና በምግብ መፈጨት ሂደት ላይ ተመሳሳይ የሆነ አሉታዊ ውጤት እንዳላቸው ይጠቁማሉ።ህፃናት በተፈጥሯቸው ጣፍጭነት ያላቸው ምግቦችን ለመመገብ የሚመርጡ ቢሆንም ወላጆች ይህን ማበረታታት እንደማይገባቸው ያስጠነቅቃሉ።
‹‹ህፃናት ዕድሉ ከተሰጣቸው በተፈጥሯቸው የተለያየ ጣዕም ያላቸውን ምግቦች ለመቅመስ ፍቃደኛ ናቸው›› ሲሉ የሚናገሩት የሥነ ምግብ ባለሞያዋ፣ በተለይ ህፃናት ብሮኮሊንና ስፒናች ከመሳሰሉ የመጎምዘዝ ጣዕም ካላቸው ምግቦች ጋር ምላሳቸው የሚተዋወቅ ከሆነ የስኳርነት ጣዕም ያላቸውን የምግብ አይነቶች በመቀነስ ጤንነታቸውን በቀላሉ መጠበቅ እንደሚቻል ያስገነዝባሉ።ወላጆችም ስኳር በህፃናት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ የጤና ተጽዕኖ ሊረዱ እንደሚገባ ያመለክታሉ።
ከልክ ያለፈ ስኳር ለተለመደ የልጆች የአፍ ውስጥ በሽታ በተለይም ለጥርስ መበስበስ ዋነኛው ምክንያት እንደሆነና በዚህም 23 በመቶ የሚሆኑ፣ አምስት ዓመት የሞላቸው ህፃናት እንደሚጠቁ የሥነ ምግብ ባለሞያዋ ያስረዳሉ።ከዚህ በሻገር ስኳርን በብዛት ለህፃናት መስጠት ከልክ ላለፈ ውፍረት እንደሚያጋልጥም ያሳስባሉ።
የሥነ ምግብ ሳይንስ አማካሪ ኮሚቴ እድሚያቸው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ህፃናት በቀን የሚወሰዱት የስኳር መጠን ከ5 በመቶ በላይ መሆን እንደሌለበትና እንዲውም ከዚህም ማነስ እንዳለበት ይመክራል።ይሁንና የጥናት ውጤት ሪፖርቱ አንድ ዓመት ተኩልና ሦስት ዓመት የሞላቸው ህፃናት በቀን መውሰድ ያለባቸው የስኳር መጠን 11 ነጥብ 3 ከመቶ መሆን እንዳለበት ይጠቁማል።ይህም የሥነ ምግብ ሳይንስ አማካሪ ኮሚቴው ካሰቀመጠው መጠን በእጥፍ የሚበልጥ መሆኑን ያሳያል።በሪፖርቱ የስኳር መጠኑ ከተቀመጠው መጠን እጥፍ መሆኑ የተጠቆመ ቢሆንም፣ ስኳሩ በብዛት መገኘት ያለበት ከአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች መሆኑን አመላክቷል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011