የማህፀን በር ካንስር በኢትዮጵያ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ሴቶችን የሚያጠቃ በሽታ መሆኑን ከጤና ጥበቃ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።በሽታው ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ ለመከላከል የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማካሄድና ክትባት መውሰድ አዋጭ መንገዶች መሆናቸውን የጤና ባለሞያዎች ይመክራሉ።
የማህፀን በር ካንሰርን ለመከላከል ከሚያስችሉ መንገዶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ክትባት መወሰድ ነው።ክትባቱ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ የዋለው እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ህዳር ወር አንስቶ ነው።በዚህም እድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች መሰጠት ተጀምሯል።ክትባቱ በተለይ የማህፀን በር ካንሰር ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚያስችልም ታምኖበታል።
በማህፀን በር ካንሰር ክትባት የተገኘው ዓለም አቀፍ ስኬት በቀጣይ የማህፀን በር ካንሰርን ለመከላከል ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተቀማጭነቱን በእንግሊዝ ያደረገው ጆስ ሰርቪካል ካንሰር ትረስት የተሰኘው የዕርዳታ ድርጅት በክትባቱ ዙሪያ የተለያዩ መረጃዎችን የቃኙ የሳይንስ ሊህቃንን የጥናት ውጤት ዋቢ በማድረግ ሰሞኑን ይፋ አርጓል።
ቢቢሲ ሰሞኑን ይዞት የወጣው ይህ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ 60 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችን በሸፈነው የ65 ጥናቶች ቅኝት የማህፀን በር ካንሰርና የቅድመ ካንሰር እድገት እየቀነሰ መምጣቱን አሳይቷል።ክትባቱ ከተጀመረበት ካለፈው አስር ዓመት ወዲህ የማህፀን በር ካንሰር በእጅጉ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን፣ይህም ምን አልባት የማህፀን በር ካንሰርን ከነአካቴው ለመከላከል እንደሚቻል ያመለከተ ተግባር መሆኑን ጥናቱ ተጠቁሟል።
ከ100 በላይ የሚሆኑ የማህፀን በር ካንሰር ቫይረሶች እንዳሉ በጥናቱ ቅኝት ተጠቁሟል።አብዛኛዎቹ ሴቶች በህይወት ዘመናቸው ምንም አይነት ህመም ሳይሰማቸው በማህፀን በር ካንሰር ሊጠቁ እንደሚችሉ ታውቋል።የማህፀን በር ካንሰር በአብዛኛው የሚከሰተውም በኢንፌክሽን አማካኝነት እንደሆነና ሌሎቹ የካንሰር አይነቶች ልቅ በሆነ የገብረሥጋ ግንኙነት በተለይ በወንዶች የመራቢያ አካላት ላይ በሚፈጠሩ እብጠቶች የሚከሰቱ መሆናቸው ተገልጿል።
እ.ኤ.አ ከ2008 ጀምሮ 12 እና 13 ዓመት ለሆናቸው ልጃገረዶች ሁለት ጊዜ የሚሰጠው ክትባት አራት አይነት የማህፀን በር ካንሰር ቫይረስ፣ 16 እና 18 የሚባለውንና 70 ከመቶ በላይ ከማህፀን በር ካንሰር ጋር የሚያያዘውን በሽታ ለመከላከል እንዲሁም 6 እና 11 የሚባለውንና ከ90 በመቶ በላይ በመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰተውን የካንሰር አይነት ለመከላከል ማስቻሉ በጥናቱ ተጠቁሟል።
በጥናቱ ቅኝት እንግሊዝን ጨምሮ 14 ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ላይ የተሰሩ ጥናቶችን ለመሸፈን ተችሏል:: በዚህም የማህፀን በር ካንሰር ያለበት መጠን፣ በመራቢያ አካላት ላይ የሚፈጠሩ የካንሰር አይነቶችንና በማህፀን ውስጥ ያለውን የቅድመ ካንሰር ህዋስ ደራጃ ለማየት እና የማህፀን በር ካንሰር ክትባት ከመጀመሩ በፊትና በኋላ ያለውን ደረጃ ለማወዳደር ተሞክሯል።
በማህፀን በር ካንሰር ቫይረስ 16 እና 18 አይነት የሚከሰተው የማህፀን በር ካንስር ከ15 እስከ 19 ዕድሜ ክልል ባሉ ሴቶች ላይ 83 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ ዕድሚያቸው ከ20 እስከ 24 ባሉት ሴቶች ላይ ደግሞ 66 በመቶ መቀነሱ ተረጋግጧል፡፡
በመራቢያ አካላት ላይ የሚፈጠረው የካንሰር አይነትም ከ15 እስከ 19 ዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሴቶች ላይ ወደ 67 በመቶ ዝቅ ሲል፣ ከ20 እስከ 24 የዕድሜ ክልል ባሉ ሴቶች ላይ ደግሞ በ54 በመቶ መቀነሱ ታውቋል።
ልቅ በሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በማህፀን በር ካንሰር ቫይረስ አማካኝነት በሚፈጠር ኢንፌክሽን በወንዶች ላይ ሊከሰት የሚችለው የካንሰር አይነት እድሚያቸው ከ15 እስከ 19 ባሉት ላይ በ50 በመቶ ሲቀንስ፣ በሴቶች ላይ ደግሞ 30 በመቶ መቀነሱ ተገልጿል።የክትባት ሽፋኑ ከፍተኛ በሆነባቸውና በከፍተኛ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው ክትባቱን በወሰዱባቸው አገራት ውስጥ የማህፀን በር ካንሰር መጠንም ሊቀንስ ችሏል።
የእንግሊዝ ህብረተሰብ ጤና ሃላፊው ዶክተር ዴቪድ ማሸር የማህፀን በር ካንሰር ቫይረስ መጠንና የማህፀን በሽታዎች የመቀነስ አዝማሚያ እያሳዩ መምጣቸውን ጠቅሰው፣ይህም የማህፀን በር ካንሰር ሊጠፋ እንደሚችል አመላካች መሆኑን ይጠቁማሉ።
የካናዳ ላቫል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና የጥናቱ ቅኝት መሪ ፕሮፌሰር ማርክ ብሪሰን በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የማህፀን በር ካንሰር ቫይረስ በተለይ ዕድሚያቸው ከ20 እስከ 30 ባሉት ሴቶች ላይ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ሊቀንስ የሚችልበት ፍንጭ እንዳለ ጥናቱ አሳይቷል።የክትባት ሽፋኑን ማሳደግ የሚቻል ከሆነም ከ100 ሺ ሴቶች ውስጥ በአራቱ ላይ የሚከሰተውን የማህፀን በር ካንሰር መቀነስ የሚቻልበት ዕድል ይኖራል።
ጆስ ሰርቪካል ካንሰር ትረስት የተሰኘው የዕርዳታ ድርጅት የጥናቱ ግኝት የማህፀን በር ካንሰር ክትባትን ተጽዕኖ በግልፅ አሳይቷል ያለ ሲሆን፣ በተለይ ክትባቱ አይሰራም ለሚሉ ትልቅ ማረጋገጫ የሰጠና የሚያበረታታ መሆኑን የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ሮበርት ሚዩሲክ ገልፀዋል።የማህፀን በር ካንሰር ክትባት የህብረተሰቡን አመኔታ እንደሚጨምርና ምን አልባትም የማህፀን በር ካንሰር ታሪክ ሊሆን እንደሚችል የጠቆመ መሆኑም አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011
አስናቀ ፀጋዬ