በሰሜናዊ እስራኤል በምትገኘው ሃይፋ ከተማ ከምድር በታች የሚገኘው ግዙፉ ሆስፒታል ለጦርነት ጊዜ ራሱን ማዘጋጀት ጀመረ።
ሆስፒታሉ በኮንክሪት ግንቡ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ አልጋዎችን የመያዝ አቅም አለው። ቀዶ ሕክምና ክፍሎች፣ የእናቶች ማዋለጃ ክፍል እና የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘኖች አሉት።
ለጊዜውም ቢሆን ግን ታካሚዎች የሉትም።
ራምባም ሜዲካል ማዕከል ይህን ያስገነባው እአአ ከ2006ቱ የእስራኤል-ሄዝቦላ ጦርነት በኋላ ነበር።
ይህ ከምድር በታች በርካታ ወለሎች ያሉት ግንባታ በሰላማዊ ጊዜ ለመኪና ማቆሚያነት የሚያገለግል ሲሆን፤ ግንባታው የተከናወነው አስፈላጊ በሆነ ጊዜ በሦስት ቀናት ውስጥ ወደ ሆስፒታል እንዲቀየር ተደርጎ ነው።
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ከምድር በታች ያለው ወለል ወደ ሆስፒታልነት ለመቀየር በተጠንቀቅ ላይ ሆኖ ቆይቷል።
አሁን ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት ማየሉን ተከትሎ መኪና ማቆሚያ ወደ ሆስፒታልነት እየተቀየረ ነው። ሆስፒታሉ ከሁለት ሺህ በላይ አልጋዎች አሉት።
እስራኤል መጠነ ሰፊ የሆነ ጥቃት ቢከፈትባት በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ከሚገኙ ሆስፒታሎች ታካሚዎችን ከምድር በታች ወስዶ ማከም ከመቻሉ በተጨማሪ፤ በጦርነት የሚቆስሉ ተጎጂዎችን የመርዳታ አቅም አለው።
የሐማሱ መሪ እስማኤል ሃኒያ እና የሄዝቦላ ከፍተኛ አዛዥ ፉአድ ሹክሪ ባለፈው ሳምንት መገደላቸውን ተከትሎ ኢራን እና ሄዝቦላ እስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
ይህን ተከትሎ በሃይፋ የሚገኙ ሐኪሞች ከሌባኖስ ድንበር በቅርብ ርቀት የምትገኘው ከተማቸው ጥቃት ሊፈጸምባት እንደሚችል ግምት አላቸው።
“መቼ ነው የሚፈጸመው (ጥቃቱ)? ማንም አያውቅም” የሚሉት የራምባም ሜዲካል ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አቪ ዌይስማን ናቸው።
ሃይፋ ከሌባኖስ ድንበር ያላት ቅርበት ለሄዝቦላ ሮኬት ተጋላጭ ያደርጋታል። ለዚህም ይመስላል የከተማዋ ነዋሪዎች በጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ዶ/ር አቪ የሚናገሩት።
ተማሪዎች ሳይቀሩ የከማዋ ነዋሪዎች ሊያጋጥም በሚችል የድንገተኛ ጥቃት ወቅት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተደጋጋሚ ልምምዶችን ያደርጋሉ።
የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ጥንዶች በዚህ መሰል ሰቆቃ ውስጥ መኖር ምን እንደሚመስል ስሜታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።
“የሆነ ሰዓት ላይ እንደሚፈነዳ ቦምብ ነው። በየትኛውም ሰዓት ልሞት እችላለሁ? ጥቃት ሲፈጸም ቤተሰቦቼ ጋር መድረስ እችላለሁ? እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ” ስትል ሴቷ ትናገራለች።
ወንዱ ደግሞ “ሰዎች ይፈራሉ፤ እኔ ግን መፍራት አቁሜያለሁ” ይላል።
ግለሰቡ በከተማዋ በሚገኘው ቡና መሸጫ ሱቁ ቡና እያፈላ በአካባቢው ያለውን ውጥረት በመላመዱ ፍርሃቱ መጥፋቱን ይናገራል።
የከተማዋ ከንቲባ ዮኖ ያሃቭ ግን በስጋት እንቅልፍ አጥተው እንደሚያድሩ ይናገራሉ።
እአአ 2006 በነበረው ጦርነት ከተማዋን ይመሩት የነበሩት የሃይፋ ከተማ ከንቲባ፤ ያለባቸው ኃላፊነት እረፍት እንደሚነሳቸው ይናገራሉ።
“በመካከለኛው ምሥራቅ ሰዎችን በመግደል እና በውድመት ላይ ብቻ የተጠመዱ መሪዎች አሉ” ሲሉ ከንቲባው ይናገራሉ።
ምንም እንኳ የሃይፋ ዶክተሮች ለጦርነት ጊዜ ሆስፒታላቸውን ዝግጁ በማድረግ ቢጠመዱም በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ለመቀነስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንደቀጠሉ ናቸው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም