የዴሞክራቷ እጩ ካማላ ሃሪስ አጣማሪ አድርገው የመረጧቸው ቲም ዋልዝ ማን ናቸው?

የዴሞክራቷ እጩ ካማላ ሃሪስ በ2024 ምርጫ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚያጣምሯቸውን የሜኔሶታ አስተዳዳሪ ቲም ዋልዝን መርጠዋል፡፡

ሁለቱ ተወዳዳሪዎች የህዳሩን ምርጫ አሸናፊ ይወስናሉ ከሚባሉ የፍልሚያ ግዛቶች አንዱ በሆነው የፊላዴልፊያ ግዛት ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡

በነብራስካ የተወለዱት የ60 ዓመቱ ቲም ዋልዝ ቀደም ሲል በመምህርነት እና በወታደርነት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡

ወደ ፖለቲካው ከገቡ በኋላ ከ2007 እስከ 2019 በኮንግረሱ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ሰርተዋል። በ2019 እና በ2022 የሚኒሶታ አስተዳዳሪ ሆነው ለሁለት ጊዜ መመረጥ ችለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የዴሞክራት አስተዳዳሪዎች ህብረት ሊቀመንበር ናቸው፡፡

በ17 ዓመታቸው በሀገሪቱ መከላከያ ናሽናል ጋርድ ውስጥ የተቀላቀሉት ቲም በጦሩ ውስጥ ለ24 ዓመታት አገልግለዋል። ከሚሊታሪ ህይወት ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ በአሜሪካ ደቡብ ዳኮታ እና ሚኒሶታ እንዲሁም በቻይና በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አስተምረዋል፡፡

ወደ ፖለቲካው ዓለም መሳብ የጀመሩት ማሳቹስቴት ግዛት ሴናተር ጆን ኬሪ በ2004 የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ከተቀላቀሉ በኋላ ነበር፡፡

በግዛት አስተዳዳሪነት ዘመናቸው የኮሌጅ የትምህርት ወጪን መሸፈን ለማይችሉ ተማሪዎች ድጋፍ እንዲደረግ እንዲሁም በሚኒሶታ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የቁርስ እና የምሳ ምገባ በነጻ እንዲጀመር ያስቻሉ ናቸው፡፡

በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቋማቸው የኢራቅ እና አፍጋኒስታን ጦርነት ላይ የፈንድ ድጋፍ እንዲደረግ በኮንግረሱ እና በሌሎች ማዕቀፎች ቅስቀሳ በማድረግ ይታወቃሉ፡፡

በተጨማሪም በአሁናዊው የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ለዩክሬን ድጋፍ ማድረግ የሩሲያን ተጽእኖ ለመግታት ወሳኝ ነው ብለው የሚያምኑ ሰው ናቸው።

ሃሪስ በአጣማሪነት ሊመርጧቸው እንደሚችሉ ከተዘረዘሩ ከሰባት በላይ እጩዎች ቲምን ለምን እንደመረጧቸው ተንታኞች ሲናገሩ፤ ሰውየው በመከላከያው እና በሲቪል አገልግሎት በነበራቸው አበርክቶ በዜጎች ዘንድ ተወዳጅ በመሆናቸው ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህ ባለፈም ወግ አጥባቂ ከሚባሉ ፖለቲከኞች እና መራጮች ጋር ቲም ያላቸው ወዳጅነት ዴሞክራቶችን በምርጫው ሊያግዝ የሚችል ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም የዴሞክራት እና ሪፐብሊካኖች በእኩል ቁጥር በሚገኙባት ሜኔሶታ ያለቅሬታ ማስተዳደር መቻላቸው ጥሩ የፖለቲካ ልምድ እንዲያካብቱ እንዳገዛቸውም ይነገራል፡፡

በተጨማሪም ቲም ከሰዎች ጋር ያላቸው መልካም ግንኙነት እና በንግግር የማሳመን ተጽእኗቸው በምርጫው ወሳኝ እጩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል ሲል የዘገበው አል ዓይን ነው፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You