ኢራን ቀጣናዊ ውጥረት እንዲፈጠር ባትፈልግም፣ እስራኤልን ግን “እቀጣለሁ” አለች።
ኢራን ቀጣናዊ ውጥረቱን የማባባስ ፍላጎት ባይኖራትም፣ ተጨማሪ አለመረጋጋትን ለማስቀረት እስራኤልን መቅጣት ያስፈልጋል ብለው እንደሚያምኑ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ይህን ያሉት የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ እስራኤል ሳታደርሰው አትቀርም በተባለው ጥቃት በኢራን ዋና ከተማ መገደሉን ተከትሎ ነው።
“ኢራን በቀጣናው መረጋጋት እንዲፈጠር ትፈልጋለች፤ ነገር ግን ይህ የሚሳካው ተንኳሹን በመቅጣት እና ጽዮናዊው አገዛዝ ጥቃት መፈጸም እንዳይችል ማድረግ ሲቻል ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ ናሰር ከናኒ ኢራን የአጸፋ ምላሽ መስጠቷ አይቀሬ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቀጣናው መረጋጋት ማምጣት ስላልቻለ በተንኳሹ ላይ የሚደረገውን ቅጣት መደገፍ አለበት ያሉት ካናኒ፤ አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቴህራን የሚገኙትን አምባሳደር እና የተልእኮ ኃላፊ ከተጠባባቂው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ባግሪ ካኒ ጋር ተሰብስበው የኢራን ርምጃ አይቀሬነት ተነግሯቸዋል።
ከናኒ እንዳሉት፤ ኦርጋናዜሽን ኦፍ እስላሚክ ኮኦፕሬሽን በሀኒየህ ግድያ ዙሪያ ውይይት እንዲያደርግ በኢራን ጥያቄ መሰረት በመጪው ረቡዕ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሂዳል።
ኢራን እና አጋሮቿ ሀማስ እና ሄዝቦላን ጨምሮ በሀኒየህ ላይ ግድያ የፈጸመችው እስራኤል ነች የሚል ክስ እያሰሙ ናቸው።
ይህ ግድያ 11ኛ ወሩን ያስቆጠረው የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በሀማስ መሪዎች ላይ ከተፈጸሙት ግድያዎች ውስጥ አንዱ ነው።
የእስራኤል ባለስልጣናት እስካሁን ለግድያው ኃላፊነት አልወሰዱም። የኢራኑ አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት ሆሴን ሳላሚ ከትናንት በስተያ “ጊዜው ሲደርስ እስራኤል ቅጣቷን ትቀበላለች” ሲሉ ዝተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም