የሱናሚው ዋናተኛ

ስሙ ለጊዜው ይቆየን። ይኼው አንድ ስም አይጠሬ አርቲስት በዲሲ ከተማ ውስጥ ካለ አንድ አፓርታማ ላይ ተንደላቆ እንደተቀመጠ ለሌላ አንድ ወዳጁ እንዲህ ሲል አወጋለት፤ “ሀገር ቤት ሳለሁ አንድ ማታ ላይ በቀረጻ አመሸንና ሌሊት 10 ሰዓት ገደማ በቀረጻው አብረውኝ የነበሩትን አሳፍሬ በሾላ ጎዳና ላይ እየነዳሁ ነበር። ሀገር ምድሩ ጭር ብሏል። ሰማዩ ከብዶ ሃይለኛ ዝናብ ይጥላል። በዚያ ዶፍ ውስጥም በእግሩ የሚጓዝ አንድ ሰው ከርቀት ተመለከትኩ። ቀረብ ብዬ እየነዳሁ አጠገቡ ስደርስም ሰውየው ልመንህ ታደሰ ሆኖ አገኘሁት…” ከማለቱ ወዳጁ ቀጣዩን ለመስማት ጓጉቶ “እና ዝም ብለኸው አለፍክ?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም ጀብዱ የሠራ ያህል ጀነን ብሎ “አዎን ትቼው መንገዴን ቀጠልኩ” በማለት መለሰለት። ከዚህ ቀጥሎ የነበረውን ንግግሩንም ጠያቂው ለራሱ እንኳን መልሶ ለማሰብ አይፈልገውምና እኛም ባንሰማው ይሻላል።

ስለ ልመንህ ታደሰ ያወራው ነገር በርግጥም እውነት ነበር። ለነገሩ ልመንህን እንዲያ ሆኖ ከተመለከትን ከብዙዎቻችን መሀከል አንዱ እንጂ ስለጉዳዩ የሚያውቅ ብቸኛው ሰው አልነበረም። የሁላችንም ዓይን ቢመለከትም ልባችን አላምን እያለ ይሁን ብቻ ግን ግድ አልሰጠንም ነበር። ዝናቡ ባህር ሠርቶ በሱናሚው ውስጥ ሆኖ ከሕይወት ማዕበል ጋር ሲንቦራጨቅ የነበረውን ሰው አልፈነው ሄደናል። ደጉ ሳምራዊ ደግነቱን አጥቶ የሥጋ ልቡ በድንጋይ ተለውጦ ነበር። ጊዜ ግን፤ ሰው ጥሎ ሰው ቢያነሳም፣ የጊዜ ፍርድ በዚህ ሰው ግን እንደምን ያለውን ጭካኔ እንደሆን አከናንቦታል፡፡

በ1970ዎቹ መጨረሻ እና በ80ዎቹ መጀመሪያ የነበረው ሰው፣ ኖሮም ከመድረክና ከቴሌቪዥን ፊት የተጠጋ፣ ተጠግቶም ከጥበብ ማዕድ የተቋደሰ ሰው፤ ኮሜዲያን ልመንህ ታደሰን አለማወቅ አይቻለውም። የዛኔ በጥበብ ሥራዎቹ ነግሶ፣ በሕዝብ ፊት ዘውዱን የደፋበት ነበር። በሕይወት ውስጥ ጉዞ፣ በጉዞም ውስጥ መነሻ አለ። ለመነሻም አንድ ቦታ ይኖረዋል። ከዚያም ቦታ ላይ በአንዲት ነገር ጉዞ ይጀመራል። ለብዙ ሰዎች ይህቺ ቦታ ትምህርት ቤት ናት። መነሻዋም ልጅነት ነው። ያቺ አንዲት ነገርም ጥበብ ናት። መነሻው ውስጥ ልጅነት አለ። በልጅነት ውስጥም ጥበብ አለ።

ልመንህ ታደሰም ገና በልጅነት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕውቀት ብርሃን ትምህርት ቤት ሲደርስ፤ ትምህርት ቤቷም በፊተኛው አስፋው ወሰን በኋላኛውም ምስራቅ ቦሩ ነበረች። የሁሉም ነገር መጀመሪያ እዚያ እንደነበረ ባደረጋቸው ቃለመጠይቆች ተናግሮታል። አብዝቶ መቀለድ፣ ቀልዶም ማሳቅ ይወድ ነበር። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሳለም በርከት ያሉ ተማሪዎች ቀልዱን ሽተው በዙሪያው ከተኮለኮሉት አብዛኛዎቹም ጓደኞቹ ለመሆን በቁ። ባለብዙ ወዳጅ ተፈላጊና ተወዳጅ ነበር።

በዚያን ጊዜ መማር ካሉስ በእነ ልመንህ ታደሰ ክፍል ውስጥ ነው። መማሩ ካልቀረም ከልመንህ ጋር በቀኝ በግራ፣ ከኋላ ፊት ተቀምጦ ዘና እያሉ መማር ነው እንጂ ብለው የሚያስቡም አልጠፉም።

በዚያ በቀልደኛ የልጅ ጨዋታ አዋቂነቱ ተማሪው ብቻም ሳይሆን አስተማሪዎቹም ይወዱታል። በየትምህርት ክፍለ ጊዜው ከቁጥርና ፊደላቱ ጋር ላይ ታች ሲል ለቆየው አዕምሯቸው በፈገግታ ለማፍታታት ሲፈልጉ መድኃኒቱ ልመንህ ነው። የልመንህ የመታወቂያው ጅራትና ጭንቅላቱ የገዘፈው በቀልዱ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ የትምህርት ዓይነቶችም ጭምር ነበር። ከሁሉም በላቀ በሳይንስ ትምህርቱ ፊተኞቹንም የሚያስከትል ነበር። ዳቦ ሳይቆረስ ከዚህም ከዚያም የማያወጡለት ቅጽል ስሞች አልነበሩም።

በትምህርት ካገኘው፣ አይቶ ሰምቶ ከያዘውም እያፈሰ በመበተን ለመናገር ስለሚወድ ፈላስፋው፣ ሳይንቲስቱ… እያለ ተማሪው ሁሉ ይጠራዋል። ደግሞ እንደገና ከቀልዶቹና ከድርጊት ሁኔታዎቹ በመነሳት ሲልች፣ ኳሽኮር፣ ቆራጣው… የሚሉትም ያሉበትን ምክንያትም እራሳቸው ያውቁታል። ግራም ይንፈስ በቀኝ ተማሪና መምህሩ ግን ሁሌም እንደወደዱት ነበር፡፡

ጉዞ ወደ ኪነ ጥበብ… ከልጅነት ወዲያ የቀጣዩ መዳረሻው ከጥበብና ከጥበብ ልጆች መገኛ ስፍራ ላይ መታየቱ ነበር። ድሮ ድሮ ትምህርት ቤት ውስጥ ሳለ የሚቀልደው አስቦና የኮሜዲያንነት ማህተብ አስሮ አልነበረም። እንዲያው ግን ዝም ብሎ ጨዋታ ስለሚወድ ነበር። ትንሽ ቆይቶም ሰዎች በእርሱ ምክንያት እየሳቁ ሲመለከት በእርሱ ቀልድ የእነርሱን ደስታ መፍጠር መቻሉን አጤነ። መቀለዱን ይበልጥ ወደደው። ጓደኞቹና የሚያውቁት ሁሉም ኮሜዲያን እንደሆነ ሲነግሩትም ስለ ተሰጥኦው አርቆ ማሰብ ጀመረ።

የእርሱ ሕይወት የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደ ቀልድ በመጀመሪያው የቀልድ ዓለም ውስጥ ስለመሆኑ በህልሙ ተስፋ ውስጥ እየታየው ይበልጥ ርግጠኛ ሆነ። ከዚህ በኋላም ይህንን የውስጥ ህልሙን ፈቶ ዕውን የሚያደርግበትን አጋጣሚና መንገድ ማሰስ ማሰላሰል ጀመረ። በዚያን ጊዜ በጥቁርና ነጭ የቴሌቪዥን መስኮት ውስጥ በሚመለከታቸው የጥበብ ሰዎችም መሳብና እንደ እነርሱ ሆኖ የመገኘት ስሜት እያየለበት መጣ። በቲያትር፣ በኮሜዲውም ሆነ በሙዚቃው ከሚመለከታቸው ውስጥ በልቡ እየመረጠ ለአርአያነት ያሰናዳቸው ገባ። “ወጋየሁ ንጋቱና ጌጡ አየለን በጣም እወዳቸው ነበር። የጥላሁን ገሰሰ ሙዚቃዊ እንቅስቃሴም ኮሜዲ ነበር የሚመስለኝ። በጣም ይማርከኝ ነበር። ታዲያ በሰፈራችን ውስጥ የነበረው አንድ ብላክ ኤንድ ዋይት ቴሌቪዥን ብቻ ስለሆነ ሴትየዋ ማታ እንዲያስገቡን ቀን ላይ በበራቸው ጎርደድ ጎርደድ ማለት አለብን። ማታ ሄደን በሩን ስናንኳኳም ቀን ስለተላላከልኝ በማለት ይፈቅዱልናል” ሲል ነበር በአንድ ወቅት ማስታወሱ።

ከፍተኛ 16 እና ልመንህ… በአንደኛው ሰሞን በአዲስ አበባ ከተማ አልፎም በሀገር ደረጃ የተቋቋመው የከፍተኛ ኪነት ቡድኖች ውልደት ለሀገራችን ኪነ ጥበብ አምጦ ያልወለደው የጥበብ ልጅ አልነበረም። ልመንህ ታደሰም የጥበብ ውልደቱ የሚጀመረው ከከፍተኛ 16 የኪነት ቡድን ውስጥ ነው። ከዚያም ወደ ኮንስትራክሽን ሚንስቴር የኪነት ቡድን ተወሰደ። በዚያም የተሰጥኦውን ህብለ ሰረሰር ጨበጠው። ያኔ ድምጻዊ ጸጋዬ እሸቱና ኬኔዲ መንገሻም ከእርሱ ጋር አብረው በቅርበት ነበሩ። ልመንህ ለኬኔዲ መንገሻ ለጥበብ ሕይወት ጅማሬ ያደረገው ትልቅ ነበር። “ኬኔዲ ብዙም ሰው አይቀርብም ነበር። እያፏጨ ጓሮ ጓሮውን ይዞራል። አንድ ቀን ጠራሁትና ስናወራ ሙዚቃ ሞክራለሁ አለኝ። ከዚያም ወደ ኪነት ቡድኑ ወስድኩትና ለማየት በድምጽ እንዲሞክር ተደረገ። በጣም የሚያምር ቆንጆ ድምጽ ነበር” ሲል ልመንህ አስታውሶ ተናግሮታል።

ዋናተኛው ከጥበብ ቤት ባህር አካሎ ይሽከረከራል። ደግሞ በቤቷ ዙሪያ እየተንጎራደደ፣ በአራቱም ማዕዘናት እየዞረ፣ አንድ ጊዜ በአጥሩ ተንጠላጥሎ አንገቱን እያሰገገ ያያል። ሌላ ጊዜም በቀዳዳው አጮልቁ ወደ ውስጥ ይቃኛል። በድንገትም የመግባቱን ዕድል፣ መግቢያውን አገኘው። ከዚህ በኋላም ነበር ጎህ ቀዳ የፈነጠቀችለትን ሌላ አጋጣሚ የተመለከተው። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ያወጣው ማስታወቂያ ነበር። በወቅቱ የነበረውንም ሲናገርም “በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዜና አንባቢ የነበረው ጌታቸው አሰፋ የተባለ ጋዜጠኛ አንድ የህብረ ትርኢት ዝግጅት ሊያሰናዳ ልጆችን በማሰባሰብ ላይ ነበር። እንደሰማሁም ጌታቸውን አገኘሁት። በሰዓቱ እነ እንግዳዘር ነጋ፣ አለባቸው፣ ፈትለወርቅ፣ ፍቅርተ፣ ሮማን ሁሉ እዚያ ውስጥ ነበሩ። እነርሱ የማስተዋወቁንና መሰል ሥራዎችን ሲሠሩ እኔና አለባቸው ደግሞ ለሁለት በቀልድ እናዋዛው ነበር። ዝግጅቱም በሳምንት ለሁለት ቀናት ይተላለፍ ነበር። የሚከፈለን በሠራነው ልክ ተቆጥሮ ቢሆንም ለብሩ ግድ አልነበረንም። የኛ ደስታ ሥራውና ታዋቂ መሆኑ ነበር” ምኞትና ህልሙም ሳይከስም ሳይመነምን ቀረና ነገሮች ሙሉ እየሆኑለት ሄዱ። ለሁለት ውብ ትዝታ ለመፍጠር የቻለበትን መነሻ ያደረገው ከዚሁ ነበር።

ልመንህ ታደሰ ሲጠራ የአለባቸው ተካ(አለቤሾው) አቤት ይላል። አለቤ ሲጠራም ልመንህ ይወሳል። በየግላቸው ፍቅርን ከጥበብ ጋር ያስቀመጡ ቢሆኑም የሁለቱ ጥምረት ግን ከዚያም በላይ ነው። በጊዜው የተመለከታቸውና የሚያውቃቸው ከምስሎች ሁሉ ገዝፎ የሚታየው ምስል የሁለቱ ጥምረት የፈጠረውን ምስል ነው። ልመንህ በውስጥ አንድ የሥራ ሃሳብ ይመላለስ ነበር። እነ ወጋየሁና ፍቅርተ በጥምረት ሆነው ይሠሩት በነበረው ዝግጅት ላይ በእጅጉ ከመማረኩም በሌላ በኩል፣ ከአንድ ከሌላ ሰው ጋር እንዲህ ባለ መልኩ የመጣመር ፍላጎቱ ጨምሮ ሃሳቡን በጭንቅላቱ ተጣማሪውን በዓይኑ ያማትር ነበር። ትዝ ሲለው ከዚህ ቀደም የሚያውቀው አለባቸው ተካ ሁነኛው ሰው ሆኖ አገኘው። አንድ ዕለት ላይም ሁለቱ አብረው ከፒያሳ ትሪያኖቫ ቡና ቤት ውስጥ ሻይ ቡና እያሉ ሳሉ ይኼው ሃሳብ ተነሳ። ወደ ጌታቸው አሰፋ በመሄድም እቅዳቸውን አስረድተው ይሁንታን አገኘና የሚያቀርቡት መለማመዱ ጀመሩ። በኋላም ሃሳቡን በድጋሚ አዳበሩትና መልኩን ለወጥ አደረጉት። በአፍ ጨዋታ መልክ ከሚሆን ለምን አቀራረባችንን ድራማዊ አድርገን በገጸ ባህሪያት መልክ አናቀርበውም ሲሉ አዲስ ነገር ፈጥረው ይበልጥ አሳመሩት። ሥራቸውንም ከአቀራረባቸው ጋር ከሽነው የተመልካቹን ቀልብ በመሳብ ከዚህም ከዚያም እየጠሩ ያመጡት ጀመሩ። ሳያቋርጡ፣ ሳያቆራርጡ እንዳማረበትና እንዳማረባቸው ድፍን አሥር ዓመታትን አብረው ዘለቁ፡፡

አውራው ጥበብ ሳተና ስሙ የሚጠራው ከአለቤ ጋር ብቻም አልነበረም። ከታማኝ በየነም ጋር ልዩ ትውስታ አስቀምጧል። ከሀገር ፍቅር እስከ ብሔራዊ ቲያትር ባለ መድረኮች ላይ ነግሶባቸዋል። በዚያን ዘመን በአንድ ለእናቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእሁድ መዝናኛ መስኮት ውስጥ የእርሱ ቀልዶች ከእነ ምስሉ ዐሻራ ተቀርጾበታል። በተለይ ደግሞ “ህብረ ትርኢት” የሚለው ዝግጅት ገና ሊጀምር ልመንህ ብቅ ብሎ ሲታይ ድምጹን ሰምተን ሳይሆን እንዲሁ ምስሉን አይተን ብቻ እንዲሁ ሳቅ ሳቅ ይለን ነበር። የእርሱ የኮሜዲያንነት ገጸ በረከቱ በዓይነት በዓይነቱና በተለየ ቅርጽ የተሽሞነሞነ ነበር። ድምጹን እየለዋወጠ በቅምጥል ሴት፣ ሲያሻው በአሮጊት፣ ደግሞም በሕፃንና በአባወራ ድምጸት እንዳሻው ሲያወፍር ሲያቀጥን ያንበለብለዋል። በቀልዶቹ እየዋኘ አድማጭ ተመልካቹን የፈገግታና የሳቅ ሱናሚ ያስነሳበታል። ብዙዎች የማያውቁለት ሌላ አንድ ተሰጥኦም አለው። ይኼውም ከኮሜዲያኑ ሁሉ እርሱን ለየት የሚያደርገውን አዝናኝና ፈገግ የሚያስብሉ ስዕሎችንም ጭምር ይስል ነበር። ኮሜዲነቱ በቃላትና ድርጊት ሳይገታ በብሩሽና በቀለማት ላይ ሁሉ ይረብብ ነበር፡፡

ከሱናሚው ቀደም ብሎ ሁሉም ነገር ደህና፣ ሁሉም ሰላም ነበር። ልመንህ በአሜሪካን ሀገር ትዳሩን መስርቶ፣ ሁለት ልጆችንም አፍርቶ ሲኖርም ነበር። ቀለበታማው የሕይወት ሱናሚ ግን አዙሪት ውስጥ ስትርመሰመስ የማትገባበት፣ ገብታም በማዕበል የማታሰምጥበት ጉድጓድ የለም። በአሳቻ ይዛ አደፈቀችው። ከላይ ንፋስ፣ በግራ ቀኝ አውሎ ንፋስ፣ ከሕይወት ውስጥ በታፈነ እስትንፋስ መአትን ታዘንባለች። ራስን ለማዳን ቢችሉም ባይችሉም በዋና መንቦራጨቅ አይቀርም። ቢሆንም ግን አለሁ ብሎ ፈጥኖ ደራሽ፣ ባለታንኳ ጀልባ ይዞ የሚደርስ የነብስ አድን የለምና የጣረ ሞት ባንዲራ ከሩቅ ሲውለበለብ ብቻ ይታያል። ይወደኛል ብለው የተጋቡት ኑሮ መልሶ ዓይጥ እንደተመለከተ ድመት በአባሮሽ ያሳድዳል። እግሬ አውጪኝ ሲሉ የገቡበት የአሳቻ ጉድጓድ መውጫውም ይጠፋና ቢጮሁም ሰሚ ይጠፋል። የሰማና ያየም እግዜር ይሁን እያለ ምንም ለማድረግ እንደማይችል እያጉተሞተመ ይሄዳል። የሕይወቱን የጨለማ ዘመን ቀን መቁጠሪያ አንገቱ ላይ ሲሰቅልለት ልመንህ ከሀገር ወጥቶ ባህር ማዶ ተሻገረ። በሕይወት ላይ ግን መሻገር ሳይሆን ከድልድዩ ላይ ተንሸራቶ ወደ ገደሉ እንደ መውደቅ ነበር። ኑሮው በአሜሪካ እንደ ክረምቱ ጭቃ የቦካ ሆነበት። ሳቅን በገፍ በገፍ ሲያድል ኖሮ ከእናት ሀገሩ ተሰዶ የተጠጋት አሜሪካ የሚሰጠውን ቀርቶ ለራሱ የሚሆነውን እንኳን ሳታስቀር መንትፋ ወሰደችበት። ጤናውም እየራቀው ከአካሉ ላይ እንደጉም ጢስ እየተነነ መሄድ ጀመረ።

ከቀን ወደ ቀን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለበት አዕምሮውም ታወከ። እርሷን ተማምኖ የሄደባት አሜሪካም የራሴን ልጆች ትቼ አንተን እሹሩሩ እያልኩና እያስታመምኩ የማባክነው ሽርፍራፊ ጊዜ የለኝምና እዚያው ከሀገርህ ሄደህ እንደ ፍጥርጥርህ ሁን ስትል መለሰችው። ከሳምራዊው ልብ የነሱ ኢትዮጵያውያን ተረባርበው፣ ጓዙን አሸክፈው ወደ ሀገሩ ሰደዱት፡፡

ተመልካች አልባ ስብራት… በወገሼ አልባ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ወደቀ። አይዞኝ የለሽ ህመሙን አዝሎ፣ ከርታታውን ባይተዋርነቱን ታቀፈ። ተሰጥኦና ችሎታውን በጥበብ አቁማዳ እያደረገ የጥበብን ቤት ይሞላታል ሲባል፤ ከየጎዳናው የቱቦና የቆሻሻ መጣያ ውስጥ ፌስታሉን እየለቃቀመ በእጅና በጆንያው ይሞላ ጀመረ። ሽቅብ ሲመለከቱት ቁልቁል ወርዶ ተፈጠፈጠ። የሕይወትን ሽልማት ሳይሆን የጥቁር ሞትን ብስባሽና ርጋፊ ተሸከመ። ከዋሽንግተን ዲሲ ተደንድሮ፣ በአንድ ጊዜ ሲምዘገዘግ “የት ትደርሳለች ያሏትን ዛፍ ቀበሌ ቆረጣት”…

ያ የቀይ ዳማ ፊቱ ጠቋቁሯል። ሰውነቱ ገርጥቶ አጥንቱ መለመሉን ቀርቷል። በላዩ ላይ የተሰፋች ያህል እስክትመስል የማይቀይራትን ጥቁር ሰማያዊ ሱፍ ወይባ እንደነተበች ሁሌም ለብሷት ይታያል። ቀለም የጠማው የቆዳ ጫማው ወደ ቁርበትነት ሊለወጥ ሆኗል። ከእጁ ላይ ቡጭቅጫቂ ወረቀቶች አይጠፉም። የቦርሳውን ዘለበት በአንገቱ አጥልቆ፣ እንዳነገታት እያልጎመጎመ በለሆሳስ ለራሱ ብቻ ሲያወራ አንዱን መንገድ ተከትሎ ይሄዳል። በየአደባባዩ ላይ ቆሞ አሊያም ከየቆሻሻው ገንዳ ውስጥ አርቲ ቡርቲውን ሲለቅም ይታያል። “ምን ፈልገህ ነው? ራበህ? ወይንስ ጠማህ?” የሚለው ግን አንድም የለም። ከዚያ ይልቅ ሕፃናቱ እንኳን እየተመለከቱ ያፌዙበታል። አዋቂዎቹም “አያድርስ ነው የተማረ እብድ…” ሲሉ ያልፉታል። የሚያውቁትም የማያውቁትም በጨረፍታ እያዩ ከመገረም ውጭ ግድ የሚሰጠው አልነበረም።

በደንብ የሚያውቁት እንኳን “ልመንህ! በአደባባይ ላይቭ መሥራት ጀመርክ እንዴ…ኧረ አለባቸው ይጠራሃል…” ፌዝ… ቀልድ… ቅንጣት ርህራሄ አልባ ቀቢጸ ተስፋነት ነበር።

ከአምስት ዓመታት በፊት ኮሜዲያን ደረጀ ኃይሌ ልመንህን በአንድ የቴሌቪዥን የበዓል ዝግጅት ላይ ይዞት ቀረበ። ደረጀ እንዲህ ሲል ጠየቀው “አንዳንድ ሰዎች ሲያገኙህ ልመንህ አሞታል ምናም ይላሉ፤ አንተስ ምን ትላለህ እውነት ነው?” ልመንህም “እኔ በሕይወቴ ምንም ደዌ የለብኝም። ትንሽ ራስ ምታት…ምናልባትም ሰው ወጣ ያለ ባህሪዬን ተመልክቶ ይሆናል። ደግሞም አያውቀኝም” በማመንና ባለማመን፣ በመከፋትን ባለመከፋት፣ በባህር ሱናሚና በየብስ መሀከል ሆነበት። በልመንህ የጨለማ ዘመናት ውስጥ ወድቆ እንዳይቀር በጭላንጭል ብርሃንም ቢሆን ከተከተሉት ጥቂት ሰዎች መሀከል አንደኛው ኮሜዲያን ደረጀ ኃይሌ ነበር።

ባለሀብቱ ኢንጂነር ተክለብርሃን አምባዬምና ሌሎችም “አይዞህ!” እያሉት ወደ መቆም ጀመረ። ለ20 ያህል ዓመታት የሳቅን ሱናሚ ሲያስነሳ ቆይቶ ለ15 ዓመታት ያህል ደግሞ በኑሮ የጨለማ ሱናሚ የወደቀ አሳዛኝ ሰው… አሳዛኝ ሕይወት ነበር። ምናልባትም ሲያገግም አንድ ቀን…

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You