አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ዜጎቻቸው በአስቸኳይ ከሊባኖስ እንዲወጡ አሳሰቡ

በመካከለኛው ምሥራቅ አይቀሬ የተባለ ሰፊ ጦርነት ማንዣበቡን ተከትሎ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳ ዜጎቻቸው ከሊባኖስ በአስቸኳይ እንዲወጡ አሳሰቡ። በቤይሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎች “በተገኘው ቲኬት” ከሊባኖስ በአስቸኳይ እንዲወጡ አሳስቧል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ እንዲሁ በቀጣናው ያለው ሁኔታ በፍጥነት ሊቀያየር ስለሚችል ዜጎች ከሊባኖስ እንዲወጡ አሳስበዋል። እስራኤል የሐማስ የፖለቲካ መሪ የነበሩትን እስማኤል ሃኒያ በኢራን ከገደለች በኋላ ኢራን “ከባድ” የአጸፋ ምላሽ እሰጣለሁ ብላለች።

ከሃኒያ ግድያ በፊት ደግሞ እስራኤል መቀመጫውን ሊባኖስ ያደረገው የሄዝቦላ ከፍተኛ አዛዥ የነበረውን ፉአድ ሹከር ቤይሩት ውስጥ መግደሏ ይታወሳል። ኢራን የሐማሱ መሪ በቴህራን መገደላቸው እንዲሁም የምታስታጥቀው የሄዝቦላ መሪ ቤይሩት ውስጥ መገደሉ አስቆጥቷታል።

ከጥቂት ወራት በፊት እስራኤል በሶሪያ የሚገኘውን የኢራንን ቆንስላ በቦምብ ካጋየች በኋላ ቴህራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል መተኮሷ ይታወሳል። ብዙዎች መሰል የበቀል እርምጃ ከኢራን የሚወሰድ ከሆነ ሰፊ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል ይላሉ። ሄዝቦላም እንዲሁ እስራኤል ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት የሚከፍት ከሆነ እስራኤል በምላሹ ሙሉ ወታደራዊ አቅሟን ልትጠቀም ትችላለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ ሄዝቦላ ወደ እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን አስወንጭፏል። ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የእስራኤል የአየር መከላከያ ሰርዓት ‘አይረን ዶም’ ወደ እስራኤሏ ቤይት ከተማ የተተኮሱ ሮኬቶችን አየር ላይ ሲመታ አሳይተዋል። ሮኬቶቹ በሰው ላይ ያደረሱት ጉዳት ስለመኖሩ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ከአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግድም በተጨማሪ የዮርዳኖስ እና የካናዳ መንግሥታት ዜጎቻቸው ከሊባኖስ እንዲወጡ እንዲሁም ወደ ሊባኖስ ጉዞ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው ማሳሰቢያ ላይ ከሊባኖስ የማይወጡ ዜጎቹ ዘለግ ላለ ጊዜ እራሳቸውን ከልለው ማቆየት የሚችሉበት ሁኔታን እንዲያመቻቹ አሳስቧል።

ይህ ማሳሰቢያ የወጣው በርካታ አየር መንገዶች ወደ ሊባኖስ የሚያደርጉትን በረራ እየሰረዙ ባሉበት ወቅት ነው። ዩናይትድ ኪንግደም ዜጎችን ከሊባኖስ ለማስወጣት ተጨማሪ የሠራዊት አባላትን የሚጨመር የባለሙያዎች ቡድን ወደ ቀጣናው እንደላከች አስታውቃለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ተፈናቃዮችን አስጠልሎ በነበረ ትምህርት ቤት ላይ የእስራኤል ጦር በፈጸመውን የአየር ጥቃት 17 ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። እስራኤል ትምህርት ቤቱ የሐማስ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ሆኖ ሲያገለግል ነበር ብላለች። ቫግነር ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ማሊ ከዩክሬን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች።

ማሊ የሠራዊት አባላቷ እና የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ከዩክሬን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች። በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ የወጣው የማሊ ወታደራዊ መንግሥት በድንገተኛ ጥቃቱ የዩክሬን ባለሥልጣናት ሚና ነበራቸው ብሏል።

ባለፈው ወር ማሊ ከአልጄሪያ ከሚያዋስናት ድንበር አቅራቢያ የሀገሪቱ ጦር አባላት እና የቫግነር ተዋጊዎች፤ ቱአሬግ በሚባሉ ተገንጣይ ኃይሎች ድንገተኛ ጥቃት ተከፍቶባቸው ነበር። ለቀናት በዘለቀው ውጊያ ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው እስላማዊው ተገንጣይ ቡድን በማሊ ጦር እና በቫግነር ተዋጊዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

ከዚህ ጥቃት በኋላ የዩክሬን ጦር ደኅንነት ቃል አቀባይ አንድሪይ ዩሶቭ፤ ተገንጣይ አማጺ ቡድኑ ጥቃቱን እንዲፈጽም “አስፈላጊው መረጃ ተሰጥቶታል” ብለዋል። የማሊ ጦር ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል አብዱላዬ ማኢጋ በዚህ ጥቃት የዩክሬን ተሳትፎ ማሊን በእጅጉ ማስቆጣቱን ተናግረው፤ ኪዬቭ የባማኮን ሉዓላዊነት ጥሳለች ብለዋል።

ኮሎኔሉ ባወጡት መግለጫ፤ የዩክሬን መንግሥት “ከአሸባሪ ኃይሎች ጎን በመሆን በዚህ አሳፋሪ፣ መሰሪ እና ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ተባባሪ መሆኑን አምኗል” ብለዋል። ይህን ተከትሎ ማሊ ከዩክሬን ጋር ያላትን ግንኙነት “በአስቸኳይ ለማቋረጥ” ወስናለች ብለዋል።

የማሊ ሠራዊት እና የቫግነር ተዋጊዎች ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ ተጨማሪ ኃይል እየተጠባበቁ ሳለ ነበር ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በተገንጣይ ቡድን ድንገተኛ ጥቃት የተከፈተባቸው። ባለፈው ሳምንት የማሊ ጦር በዚህ ድንገተኛ ጥቃት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ይግለጽ እንጂ ምን ያክል አባላቱ እንደተገደሉ ያለው ነገር የለም።

በተመሳሳይ መጠሪያ ስሙን ከቫግነር ወደ ‘አፍሪካ ኮርፕስ’ የቀየረው የሩሲያው ተዋጊ ቡድን እንዲሁ በአንድ ሺህ ታጣቂዎች ድንገተኛ ጥቃት ተከፍቶበት ሄሊኮፍተሩ ተመትቶ መውደቁን እና አንድ አዛዡ መገደሉን ከመግለጽ ወጪ የደረሰበትን ዝርዝር የጉዳት መጠን አልገለጸም።

ይሁን እንጂ እስከ 80 የሚደርሱ ተዋጊዎቹ በዚህ ጥቃት ሳይገደሉ እንደማይቀር ይገመታል። ተገንጣይ ኃይሎቹ በበኩላቸው 84 የቫግነር ተዋጊዎችን እና ወደ 50 የሚጠጉ የማሊ ወታደሮችን መግደላቸውን ገልጸዋል። ይህ ቫግነር የደረሰበት ጉዳት አማጺ ኃይሎችን ለመዋጋት የማሊን መንግሥት መደገፍ ከጀመረ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ትልቁ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።

ከአስር ዓመት በፊት የማሊ ማዕከላዊ መንግሥት በቱአሬግ አማጺ ቡድን እንቅስቃሴ ምክንያት አብዛኛውን የሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ መቆጣጠር ተስኖታል። አሁን ስልጣን ላይ ያለው የማሊ ወታደራዊ መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ላይ የወጣው መንግሥት ሰሜናዊ የሀገሪቱን ክፍል መቆጣጠር ተስኖታል በሚል ምክንያት ነበር። ወታደራዊው መንግሥት ከፈረንሳይ ጋር የነበረውን ወዳጅነት በመተው ፊቱን ወደ ሩሲያ ካዞረ ሰነባብቷል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 /2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You