‹‹ስኬት በዓላማ መጽናትን ይጠይቃል›› ዲዛይነር ትዕግስት አበበ የጤና አዳም ድርጅት መሥራችና ባለቤት

ሴቶች ከፈለጉ ማሳካት የማይችሉት ጉዳይ አይኖርም፤ ከአንድ ነገር በላይ የሆኑት ተግባራትን በተመሳሳይ ሰዓት ማከናወንም አይሳናቸውም የሚል እምነት አላት። የውስጧን ጥሪ ተከትላና ጊዜ ሰጥታ በማብሰልሰል ውስጥ ለተፈጥሮ የቀረበ ማንነቷን ሊያንጸባርቅ የሚችል ለትውልድ የሚተላለፍ ሌጋሲ እንዲኖራት ምኞቷ ነበር።

በዚህም ለዓላማዋ ቁርጠኛ በመሆን ለሌሎች እውን መሆኑ የሚያጠራጥር ለእርሷ ግን የታያትን ህልሟን ወደ መሬት በማውረድ የሀገራችን ሀብት የሆነውን ቀርቀሃ በመጠቀም በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ተፈላጊ የሚባሉ ምርቶችን በማቅረብ ደንበኞችን አፍርታለች። ቀርከሃን በማስተዋወቅ መጠቀምና ለእናቶችና ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚችልና ተጠቃሚ የሚያደርግ ተቋምም መስርታለች። በዛሬው ገጻችን ብዙም ትኩረት ያልተሰጠውን ቀርከሃን በመጠቀም ከሌሎች የሀገራችን ሀብቶች ጋር በማጣመር የተለያዩ የእደ-ጥበብ ውጤቶችን፣ ጌጣጌጦችና ቦርሳዎችን በመሥራት ለብዙዎች ያስተዋወቀች እንስት የሕይወት ጉዞ እናጋራችኋለን። መልካም ንባብ፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት አበበ ትባላለች። ዲዛይነር፣ የጤና አዳም ድርጅት መሥራችና ባለቤት ናት። ትውልዷ በባህር ዳር ከተማ ሲሆን፣ እድገቷ ደግሞ በጅማ ከተማ ነው። “በጅማ ከተማ ማደጌ ዛሬ ላይ ላለው ማንነቴ አስተዋጽኦ አለው” የምትለው ትዕግስት፣ ለእደ-ጥበብ ውጤቶች ቅርብ እንድትሆንና እንድትሳብ ያደረጋት እንደነበር ታስታውሳለች። ‹‹አጎቴ የተለያዩ ማበጠሪያዎችንና ከእንጨት የሚሠሩ ወንበሮችን ይሠራ ስለነበር እንድንሞክር ያደርገን ነበር፤ በልጅነቴ ቅርጻቅርጽ መሥራትና ስዕል መሳል በጣም እወድ ነበር፡፡›› በማለት ከእደጥበብ ውጤቶች ጋር የተቆራኘውን የልጅነት ጊዜዋን ታስታውሳለች።

በልጅነቷ ጥናት ማድረግ፣ መመራመር የሚያስደስታትም ነበረች። በመሆኑም የተለያዩ ጥናቶችን ለመሥራት ያስችለኛል ያለችውን የትምህርት ክፍል ማለትም የሜዲካል ላቦራቶሪ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተቀላቀለች።

ትዕግስት በትምህርቷ ጥሩ ውጤት ነበራትና በጊዜው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሴቶች ባቀረበው የሁለተኛ ዲግሪ ነጻ የትምህርት እድል ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ መጣች። በዚህ አጋጣሚ ነበር ተማሪ ሳለች የተሳበችበትን አየር መንገድ የተቀላቀለችው። ‹‹የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ወደትምህርትቤታችን በምንሄድበት መንገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትኬት ቢሮ ነበርና በዚያ የሚሠሩ ሰዎች ሲያዩን ያላችሁ ቁመና ለአየር መንገድ ይሆናል ታውቃላችሁ ወይ? እያሉ ስለ አየር መንገድ ነግረውን ነበር፡፡›› የምትለው ትዕግስት፣ ይህንን መረጃ ይዛ የነበረች ጓደኛዋ አስቀድማ በአየር መንገድ በማመልከቷ እድሉን እንድትጠቀም መረጃውን አጋራቻት ።

ይህ መረጃ አዲስ አበባ ለመጣችው ትዕግስት ጥሩ እድል ነበርና ከትምህርቷ ጋር ጎን ለጎን ለማስኬድ የሚያስፈልጋትን የትምህርት ማስረጃ ካሟላች በኋላ ማመልከቻውን አስገብታ የተቀመጡ መስፈርቶችን ለማለፍ ቻለች። ትዕግስት አዲስ ምሩቅ በመሆኗ የትምህርት እድሉ ለሌሎች በሥራ ቆይታቸው ልምድ ላላቸው ሰዎች ተላለፎ መሰጠቱን ታስታውሳለች።

በመሆኑም ትኩረቷን አየር መንገድ ላይ አደረገች፤ በዚያም ፈተናውን በማለፏ የሶስት ወር ሥልጠና ወስዳ አየር መንገድን ተቀላቀለች። በአየር መንገድ የነበራት የሥራ ቆይታ አንድ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመርቃ ለወጣች ሴት አዲስ ዓለም እንደነበር የምታነሳው ትዕግስት በሕይወቷ ለገነባቻቸው ልምዶች አስተሳሰቦች ትልቅ ድርሻ እንዳለው ታነሳለች። ከሰዎች ጋር ለመግባባትም እንዲሁ በጅማ የነበራት አስተዳደግና የማህበራዊ ሕይወት በእጅጉ ጠቅሟታል። በአየር መንገድ ውስጥ የተለያዩ ሀገራት ላይ የመብረርና ብዙ ሀገራትን የመጎብኘት፣ አዳዲስ ሰዎችን መተዋወቅ እና ሌሎች ሀገራት ያላቸውን ሀብት የሚጠቀሙበትን መንገድ ትመለከት ነበር።

በሥራ ሕይወት ቆይታዋም ለዓለም የምትሰጠው አበርክቶ ራሷን በቀጣዩ ትውልድ የምታስጠራበት የራሷን ሌጋሲ የምታስቀጥልበት ዘርፍ መገንባት በትዕግስት ልብ ውስጥ ሁልጊዜም የሚመላለስ ሃሳብ ነበር። ‹‹ከእኔ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ዓላማ ያለው ሥራን መሥራት ለትውልድ ትቼ የማልፈው ነገር እንዲኖር ሁሌም እፈልግ ነበር። አየር መንገድ ግን እንኳን ሰራሁበት ብዬ የምኮራበት ተቋም ነው፤ ምክያንቱም ሀገሬን ወክዬ ወደ በርካታ ሀገራት ለመሔድ እድሉን አግኝቻለሁ፡፡››

ትዕግስት፣ ለመሥራት የምታስበውን ነገር በውስጧ እያብሰለሰለች ሕይወቷን ቀጠለች፤ ትዳር መሠረተች፤ የልጆች እናትም ሆነች። ይህ ሁሉ ኃላፊነት ግን ሌጋሲዋን ልትቀጥል የምትችልበትን ሃሳብ ከማውጠንጠንና ከመፈለግ አላገዳትም። ምክንያቱም በትውልድ ውስጥ ባለቤት ሆነው ሥራዋን ከሚረከቧት ውስጥ ልጆቿም ጭምር ይገኙበታልና፡፡

ትዕግስት፣ “ምን እንደሆነ ባላውቀውም ግን ጤና አዳም የሚለው ስም ሁሌም አዕምሮዬ ውስጥ ነበር፤ ምክንያቱም ሀገራችን የብዙ ተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ናት። በመሆኑም ይህንን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ከፕላስቲክ ምርቶች ጋር ያለንን ቁርኝት ትተን ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ጤናማ የሆነ ሕይወት መከተል የሚለው እሳቤ በውስጤ ነበር።›› በተጨማሪም ትዕግስት በምትበርባቸው ሀገራት ያሉ ዜጎች ሀብታቸውን የሚጠቀሙበትን መንገድና ሀገራቸውን ለማስጠራት የሚሄዱበት ርቀት ሲያስደንቃት በሀገራችን ያለው የተፈጥሮ ሀብት የሰው ኃይል እያለ በዓለም ደረጃ፣ ሀገር እንደአምራች የምትጠራባቸው ምርቶች ውስን መሆን ቁጭትን ፈጥሮባታል።

ይህንን ቁጭት ለመወጣት ትክክለኛ ሆኖ ያገኘችው ሰዓትም ሶስተኛ ልጇን ነፍሰጡር ሳለች የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለምአቀፍ ስጋት መሆኑ ተገልጾ ነበር፤ ወቅቱም ብዙ እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ የተጣለበትና ሠራተኞች ረጅም ጊዜን በቤታቸው ለማሳለፍ የተገደዱበት ጊዜ ነበር። በቤት ውስጥ ረጅም ጊዜን ስታሳልፍ የተለያዩ ልትሰራው የምታስበውን ማጥናት ጀመረች በዚህም በምታስብበት ወቅት ትኩረቷን የሳበው ቀርከሃ ነበር። ‹‹በሌሎች ሀገራት በምበርበት ጊዜ የቀርከሃ ውጤት የሆኑ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን በጥራት ተሠርተው አይቼ አውቃለሁ፡፡››

ቀርከሃ በሌሎች ሀገራት ላይ ትልቅ ቦታ ያለው ሲሆን፣ በሀገራችን ግን ሀብቱ፣ በስፋት ቦታ ያልተሰጠው መሆኑን ታነሳለች። ‹‹በአፍሪካ ከሚገኘው የቀርቀሃ ሀብት 67 በመቶ የሚሆነውን የምታበቅለው ኢትዮጵያ ስትሆን፣ ከአለም ደግሞ አስረኛ ናት፡፡›› የምትለው ትዕግስት፣ የቀርቀሃ ሀብትን እንዴት ወደሌሎች ምርቶች መቀየር ይቻላል የሚለውን ጥናት ማድረግ ጀመረች። ይህን ጊዜ የትዕግስት ለተፈጥሮ ያላት ቅርበትና ልትሠራበት የምታስበው ጉዳይ ከቀርቀሃ ጋር የተዋሀደ ሆኖ አገኘችው።

ሥራዋን ለመጀመር ከባለቤቷ ጋር ከመከረችበት በኋላም ቀርቀሃን ለማግኘት ወደትፈልገው ውጤት ለመቀየር የሚያስችላትን ሥልጠና ለመውሰድ ወደምትችልበት ድርጅት አቀናች፤ ሃሳቧን ካጋራች በኋላ በጊዜው ቀርከሃ ላይ ሥልጠና የሚሰጥ የወጣት ሴቶች ማጎልመሻ ማዕከል ውስጥ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ለመጀመርያ ጊዜ ሙከራዋን ያደረገችውም በቀርቀሃ የተሠራ የጸጉር ማበጠርያ የእጅ ጌጦች፣ የቁልፍ መያዣዎች እንዲሁም አንድ ቦርሳ ከአፍሪካ ጨርቅ ጋር በማድረግ በመሥራት ጀመረች። ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራችውን ቦርሳ ይዛው ስትወጣ ብዙዎች አድናቆትን ይቸሯት ነበር። በማዕከሉም ተከታታይ ሥልጠናዎችንም አገኘች።

ትዕግስት ይህ ሃሳብ ምንም እንኳን በውስጧ ቢኖርም በዙሪያዋ ያሉ ሰዎችን ማሳመን ይጠበቅባት ነበር። በመሆኑም ራሷን ወደ ሥራዋ ሙሉ ለሙሉ ትኩረት ለማድረግ የንግድ ፍቃዷን አውጥታ ወደ ሥራ ገባች። የድርጅቷ ስያሜም “ጤና አዳም” ሲሆን፣ ዓለምአቀፍ ብራንድ ሆኖ ኢትዮጵያን ሊያስጠራ የሚችል፣ ተፈጥሯዊ ምርቶችን የሚያስተዋውቅና ለእናቶች እና ለብዙሃን ወጣቶች ሥራ እድል መፍጠር የሚችል እንዲሆን ጤና አዳም ተመሠረተ።

ቀጣዩ ሥራ የነበረው ቀርከሃ ሀብትን ማፈላለግና ለጌጣጌጥ ሥራ እንዲውል ቀርቀሃውን መግዛት ነው፣ ከዚያ በኋላ የሚፈለገውን ደረጃ እንዲይዝ ባለሙያ ማግኘት በራሱ አንዱ ፈተና እንደነበር ትዕግስት ታስታውሳለች። በመሆኑም ቀርቀሃውን ወደሚፈለገው ቅርጽ ለማምጣት የሚያልፍበት ሒደት ድምጽ ያላቸውን ማሽኖች እንድትጠቀም የሚያደርግ በመሆኑ የመሥሪያ ቦታ ለማግኘት ተቸግራ ነበር። በዚህ ወቅትም በሥራዋ ያገዟትን ዘርፉ ላይ የነበሩ ጥቂት ባለሙያዎችን ታመሰግናለች፡፡

ከዚያም ባገኘቻቸው ባለሙያዎች የራሷን ዲዛይን በመፍጠርና እውን በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራዎቿን ይዛ የተገኘችበት ኤግዚቢሽን ላይ የቁልፍ መያዣዎች፣ ጌጣጌጦች ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገዟት የተሰማትን ደስታ አሁንም ድረስ ታስታውሰዋለች። በቀርቀሃ የተሠሩ የእደ-ጥበብ ውጤቶችን ይዛ በምትቀርብበት ወቅት ብዙ በጎ ያልሆኑ አስተያየቶች ቢገጥሟትም እሷ ግን ምርቶቹን ሊረዱ ይችላሉ በምትላቸው ሰዎች ኤግዚቢሽኖች መድረኮች፣ ኤምባሲዎች የሚያዘጋ ጇቸው ባዛሮች ላይ በመገኘት ስራዎቿን ማስተዋወቅ ጀመረች።

በአሁኑ ሰዓት የጤና አዳም ብራንድ ስር ከቀርከሃ የሚሠሩ ፋሽን ላይ ያተኮሩ ከዘመናዊ አለባበስ ጋር መሄድ የሚችሉ ጌጣጌጦች ከነሀስ ጋር በማጣመር ለወንድም ሆነ ለሴት የሚሆኑ ቦርሳዎች ከቆዳ ጋር፣ ከሽመና ጋር እንዲሁም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ የባህል አልባሳት ጋር በማጣመር ተሠርተው ወደገበያ ያቀርባሉ። ለሆቴሎችና ለድርጅቶች በብራንዳቸው የሚሠሩ ሎጎዎችን መጋረጃዎችን የቤት ውስጥ ማስዋቢያዎችን ትዕዛዝ እየተቀበሉ በሚፈልጉት ዲዛይን ይሠራል።

ብዙዎች ቀርቀሃ መሆኑን ሲያስቡ ጥንካሬው ጥያቄ ይፈጥርባቸዋል ለዚህም አንድ የማርኬቲንግ ባለሙያ ገጠመኝን ታስታውሳለች ‹‹አንድ ወደ ውጭ ሀገር የሥራ ጉዞ የነበራት ደንበኛችን ወደ ሱቃችን የኮምፒውተር መያዣ ቦርሳ መግዛት ፈልጋ ነገር ግን ጥንካሬውን ማመን አልቻለችም ነበር። ከግማሽ ሰዓት በላይ ከተወያዩ በኋላ ገዛችውና ወደ ሥራ ጉዞዋ ከሄደች በኋላ ግን ከሌሎች ዜጎች የተቀበለችው አድናቆት በሀገሯ ምርት እንድትኮራ አድርጓታል፡፡›› በማለት ገጠመኟን ታስታውሳለች። ምርቶችን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ይዞ መውጣት እንቅስቃሴዎች ያሉ ሲሆን፣ ያለው የጥራት ደረጃ ከፍ ማድረግ ተቋሙ ምንጊዜም የሚጥርበትና የሚሠራበት መሆኑን ትዕግስት ጠቅሳለች።

የቀርከሃ ምርትን ከሚበቅልበት ቦታ አንስቶ ተቆርጦ ወደሚፈለገው መጠንና የልስላሴ ደረጃ እና የቦርሳም ሆነ የጌጣጌጥ ሥራ ላይ እንዲውል በርካታ ሒደቶችን ያልፋል። ሆኖም ትዕግስት እነዚህ ደረጃዎች በጤና አዳም ስር ይሠሩ የሚል እምነት የላትም፤ ማለትም ባለሙያዎችን ማፍራት የምታተኩርበት እና ሥራን ለባለሙያው መስጠት የጤናአዳም አንዱ ዓላማ ነው። ‹‹ቀርከሃን ከመቁረጥ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እንሥራው ካልን የሚኖረው ጥራት ይቀንሳል። ስለዚህ እኔ የማምነው ዓለም ላይ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ለማምረት የሚያስችሉ ቀርቀሃውን ከማብቀል ጀምሮ ለእኛ እስከማቅረብ የሚሠሩ አምራቾችን መፍጠር ላይ ማተኮር እፈልጋለሁ፡፡››

ትላለች። በመሆኑም ጤና አዳም በሚፈልገው የጥራት ደረጃ መሥራት እንዲያስችል ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሥራት እናቶችን በዘርፉ ላይ አሠልጥኖ በማደራጀት ለመጀመር ያህል 20 እናቶችን በማሠልጠን በሥራው አሠማርቷል። እነዚህ እናቶች በጤና አዳም ተቋም ስር ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ በግላቸው አቅራቢ ሆነው ከተቋሙ ጋር የሚሠሩ ሲሆን፣ የራሳቸውን ገቢ መፍጠርና የቀርከሃ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ለሚሠሩ ሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሥራት ገቢያቸውን ማሳደግ እንዲችሉ ያደርጋል።

በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ብዙ ደንበኞችን ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ በሰዎች ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ለማግኘትም ሥራዎቹን ከእለት ተዕለት በማሻሻል ጥራት ያላቸውን ሥራዎች ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን ትዕግስት ታስረዳለች ‹‹አንዱ መለያችን ብዬ የማስበው የደንበኞቻችንን አስተያየት ተቀብለን ማስተካከል የእድገታችን አንዱ ምስጥር ነው፡፡›› ትላለች።

ትዕግስት ዲዛይኖችን የምትሠራው በራሷ ሲሆን፣ ወደ እዚህ ዘርፍ ገብታ የአዕምሮዋ ውጤት የሆኑ ዲዛይኖችን በቀርቀሃ ላይ በማሳረፍ የሠራቻቸው ሥራዎች ቀርከሀ በፋሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ በዚህ መልኩ መሠራት ይችላል የሚለውን እይታ መፍጠሯን ትገልጻለች። አሁን ላይ ወደ ዘርፉ እየተቀላቀሉ መሆኑን ጠቅሳ፤ ከዚህ በላይ በትምህርት የበቁ ወጣቶችንና ባለሙያዎችን መሳብ እንደምትፈልግ ተናግራለች። የቀርከሃ ሀብት በብዙ መንገድ ገቢ እንዲያመጣ መደረግ እንደሚችል በመግለጽ በሚበቅልባቸው የሀገራችን ክፍሎች ለምግብነት እንደሚውል አመልክታለች፡፡

ትዕግስት፣ ወደ ሌሎች ምርቶች መቀየር የሚችል በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ጠቅሳለች። ‹‹ዓለም ላይ ውዱ የሚባለው የስፖርት ልብስ ከቀርቀሃ የሚሠራ ነው፣ የቀርከሃ ውጤት የሆነው ምግብም ብዙ ንጥረነገሮች የሚይዝ ነው። በመሆኑም ፈጠራ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ወጣቶች፣ ባለሀብቶች፣ መንግሥትንም ጨምሮ ወደ ሴክተሩ ቢገቡ መልካም ነው ትላለች።

ጤና አዳም፣ ወደፊት ያለው የማምረት አቅም አሳድጎ ዓለምአቀፍ እውቅናን ያገኘ በፋሽን ኢንዱስትሪው በጉልህ የሚነሳ እና ኢትዮጵያን የሚወክል ብራንድ እንዲሆን ትዕግስት ምኞቷ ነው። በዚህም ቀጣይነት ባለው እናቶችን የማሠልጠንና ወደሥራው የማስገባት ሥራ ብዙ እናቶችን በማሳተፍ ቀርከሃ ከማብቀል ከገበሬው ጀምሮ በስፋት የቀርቀሃ ውጤቶች እናቶች መሥራት የሚችሉበና ጎብኚዎች መጥተው ይህንን የእደ-ጥበብ ውጤቶች ራሳቸው ሠርተው፣ ገዝተውና የሚያልፈውን ሒደት ጎብኝተው እንዲሄዱ የሚያስችል የቀርከሃ መንደር መገንባት የነገ ህልሟ ነው። ጤና አዳም አሁን ከሚያመርታቸው ምርቶች ባለፈ የቀርከሃ ውጤት የሆኑ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን እንዲሁ ወደገበያው ማስተዋወቅ በእቅዱ ውስጥ ያለ ነው።

አብዛኛዎቹ ሴቶች የትዳር ሕይወትን ከመሠረቱ እና የልጆች እናት ከሆኑ በኋላ ያለባቸውን ተፈጥሯዊ ኃላፊነት ለመወጣት በማሰብ አዲስ ነገርን መሞከር ይፈራሉ። ትዕግስት፣ ለዚህ መፍትሄው ‹‹ሴቶች ከፈለጉ ማድረግ የማይችሉት ነገር የለም፤ በመሆኑም የሕይወት ትልቁ መሠረት ነው ብዬ ማስበው ሚዛናዊ ማድረግ፤ ጊዜያቸውን በማመጣጠን የሚፈልጉትን ማሳካት ይችላሉ። ሌላው ዋነኛው ነገር ደግሞ ማንኛውንም ነገር ለማሳካት በዓላማችን እንስከመጨረሻው መጽናት ይኖርብናል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 /2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You