በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተው አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ምንድነው?

ከሰሞኑ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን ካደረጋቸው ማሻሻያዎች ውስጥም የገንዘብ ፖሊሲው በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ ይሆናል የሚለው ይገኝበታል። በመንግሥት በኩል በተሰጠው መግለጫም ርምጃው የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን ማዘመን ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ተብሏል።

የሦስት ዓመቱ የብሔራዊ ባንክ ስትራቴጂክ እቅድ ዝቅተኛና እና የተረጋገጠ የዋጋ ንረት መኖሩን ማረጋገጥ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ከንግድ ባንኮች ጋር በሚያደርገው የንግድ ግብይት በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት እንዲፈጠር ቅድሚያ እንደሚሰጥ በመግለጫው ላይ ተነስቷል።

ብሔራዊ ባንክም በማክሮ ኢኮኖሚና በባንክ ዘርፉ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ይህንን የፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ መጀመሩን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በማሻሻያው የተካተተውና ብሔራዊ ባንኩ እከተለዋለሁ ያለው በወለድ ተመን ላይ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሲባል ምን ማለት ነው? ኢኮኖሚው ላይ ምን አይነት ለውጦችን ያመጣል? ምንስ ጥቅም ይኖረዋል? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ከኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡት የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዘመዴ ጫሚሶ እንደገለጹት ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ከነበረው በገንዘብ አቅርቦት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ወደ በወለድ መጠን የሚመራ የገንዘብ ሥርዓት መሻገሩ ባንኩ የብሔራዊ ባንክ ሚናን እንዲወጣ የሚያደርገው ነው ።

በዚህ ፖሊሲም ብሔራዊ ባንክ በገበያ ውስጥ የሚኖርን የገንዘብ አቅርቦት ለመወሰን አቅም የሚያገኝ ሲሆን በገበያው ውስጥ በመጋጋል እንዲሁም በመቀዛቀዝ ምክንያት የሚመጣን የዋጋ ንረት የገንዘብ ዝውውሩ እንደ አመቺነቱ በመግታትና በመልቀቅ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ከበፊቱ በተሻለ ምቹ ሜዳን ያገኛል ይላሉ።

አቶ ዘመዴ ፖሊሲው በዚህ የሚመራ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን ብሔራዊ ባንክ ይህንን የማድረግ አቅም ይኖረዋል ብለው እንደማያስቡና በሂደት ግን ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ለዚህም በአሁኑ ጊዜ የኑሮ ውድነት እንዳይከሰት መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከተለያዩ አካላት እያገኘው ያለውን የገንዘብ ድጋፍ ለዋጋ ንረት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የመደጎም ሥራውን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ሌላኛው ያስቀመጡት የመፍትሔ አቅጣጫ መንግሥት ሞኒታሪና ፊስካል ፖሊሲውን አጣምሮ በመሥራት ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ እቃዎች ላይ የሚጥለውን ቀረጥ በመቀነስ የኑሮ ውድነቱን መከላከል እንደሚቻል መክረዋል።

ይህ የገንዘብ ፖሊሲም የብድር አቅርቦት ላይ የወለድ መጠኑ በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ የሚመሠረት የሚያደርግ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን በማዘመን ገበያው እራሱን በራሱ የሚመራ ስለሚያደርግ በብሔራዊ ባንክ ላይ የሚኖረውን ጫና እንደሚቀንስ አብራርተዋል።

ሌላኛው በዚህ ፖሊሲ ላይ ሀሳባቸውን ለኢፕድ ያጋሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ቆስጠንጢኖስ በርሄ ተስፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት አዲሱ የብሔራዊ ባንክ መዋለ ንዋይ ፖሊሲ ኢኮኖሚው ላይ ያለውን የገንዘብ ፍሰት ያለውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠር ወለድን ይጠቀማል።

ማዕከላዊ ባንክ ኢኮኖሚው በሚቀዘቅዝበት ጊዜ ያለውን ወለድ በጣም ዝቅተኛ በማድረግ ሰው እንዲበደር የሚያበረታታ ሲሆን ኢኮኖሚው ደግሞ በጣም ተነቃቅቶ ወደ ዋጋ ግሽበት ሲሄድ የወለድ መጠንን ከፍ በማድረግ የገንዘብ ዝውውሩን የመግታትና የኑሮ ውድነቱን መቆጣጠር ያስችለዋል።

በአሁኑ ሰዓት ብሔራዊ ባንክ ባንኮች እርስ በራሳቸው የሚበዳደሩበት የወለድ መጠን 15 በመቶ ያደረገ ሲሆን ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚያበድሩበት የወለድ መጠን ግን ራሳቸው ይወስናሉ።

ይህም ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፍሰቱ እንዲቀንስ በማድረግ የዋጋ ንረቱ ለመቆጣጠር ያግዛል ያሉ ሲሆን ለአብነትም በአሁኑ ሰዓት የዋጋ ንረቱ ከ30 በመቶ ወደ 19 በመቶ የወረደው ዋነኛ ምክንያቱ የገንዘብ ፍሰቱ በመቀነሱ መሆኑን ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ያነሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ይሄ የመዋለ ንዋይ ፖሊሲ ኢንቨስትመንቱን ያነቃቃል ያሉ ሲሆን ይህ ግን እንደ ሠላም ጉዳዮችና የጥቁር ገበያን መቆጣጠር ሲቻል መሆኑን አንስተዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You