አስገድዶ ከመድፈርም በላይ

አላዩ ዓለምነህ ከሰው ተነጥሎ የሚኖር አኩራፊ ነው:: ትምህርት ካለመማሩም በላይ በዕድሜው የሰው ልጅ የሚደርስባቸው ደረጃዎች ላይ መድረስ አልቻለም:: ይህችን ምድር ከተቀላቀለ ግማሽ ምዕተ ዓመታት ሊሞሉት ሶስት ዓመታት ብቻ የቀሩት ቢሆንም፤ ትዳር አልመሠረተም:: የተሻለ ሥራ ሠርቶ ትልቅ ገቢ ለማግኘት አልታደለም:: የሚሠራው መርካቶ አካባቢ ቢሆንም፤ ከቀን ሰራተኝነት የተሻለ ሥራ ሠርቶ አያውቅም:: አንዳንድ ጊዜ ይሸከማል:: ገቢው ከእጅ ወደ አፍ ነው::

አንድ ቀን ጥቂት መቶ ብሮችን ካገኘ እስኪጠግብ ይበላል:: በቀረው ብር እስኪ ሰክር ይጠጣል:: የራሱ ቤት የለውም:: የሚኖረው ዘመድ ቤት ተጠግቶ ነው:: ሰዎችን ሲመለከት በመላ ሰውነቱ የሚሰራጨው ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ ብቻ ነው:: ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማጣራት የአላዩ አጠቃላይ ሕይወቱን በተመለከተ ጥናት ማካሔድ ያስፈልጋል:: ከጥላቻው ብዛትም ሰው በምንም መልኩ ይፈፅመዋል ብሎ ለማሰብ የሚዘገንን ከባድ ወንጀል ፈፅሟል::

መከላከል ያቃታት ሕፃን

አላዩ በጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ገንዘብ አግኝቷል:: ጥግብ ብሎ ከበላ በኋላ እስኪሰክር ጠጥቶ እንደለመደው ያስጠጉት ዘመዶቹ ቤት ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ገባ:: የጠጣውን ለማውጣት ሽንት ቤት እየተመላለሰ አደረ:: ሲነጋለት ማለትም ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ እርሱም በሚኖርበት ግቢ ውስጥ የሚኖረው የአክስቱ ልጅ ባል ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ አየ::

ከሽንት ቤት ሲመለስ ወደ አክስቱ ልጅ ቤት ገባ:: ሳሎኑን አልፎ ወደ መኝታ ቤት ሲያመራ የ14 ዓመት ዕድሜ ያላት እና የአክስቱ ልጅ ቤት ተጠግታ የምትኖረዋን ቃልኪዳን ዘነበ ወደ ትምህርት ቤት ለመሔድ ደብተሯን እያስተካከለች አገኛት::

ቃልኪዳን አላዩን እንዳየች ደነገጠች፤ አይኑ እንደደፈረሰ ነው:: እያፈጠጠ ሲጠጋት ደብተሯን ጥላ፤ ‹‹ልትደፍረኝ ነው? ›› ብላ ጮኸች:: አላዩም፤ ‹‹አዎ›› ብሎ በሃይል በጥፊ ሲላት አልጋው ላይ ወደቀች:: ዘሎ ወጥቶባት አንገቷን አነቃት:: እንዳትጮህ በቅርብ ያለውን የልጆች ኮፍያ ሳይቀር አፏ ውስጥ ጠቀጠቀ:: በሕፃን አቅሟ ብትታገለውም የ47 ዓመት ዕድሜ ያለውን እና የቀን ሥራ የሚሰራውን ጎልማሳ ከላይዋ ላይ ማንሳት አልቻለችም::

እንደፈራችው አንገቷን እንዳነቀ ቀሚሷን ወደ ላይ ሰብስቦ የለበሰችውን ቱታ አወለቀ:: በድጋሚ ታገለችው ነገር ግን ልትቋቋመው አልቻለችም:: የራሱን ሱሪ አውልቆ በኃይል አካላቱን ሰውነቷ ውስጥ ከተተው:: በጭኖቿ መሃል ደም መፍሰስ ጀመረ:: ቃልኪዳን ገና ሕፃን ያልጠነከረች በመሆኗ መቋቋም አቃታት:: ብዙም ሳትቆይ በዛችው ቅፅበት ህይወቷ አለፈ:: ሳትኖር የሕይወትን ትርጉም በቅጡ ሳትረዳ በደረሰባት የአስገድዶ መደፈር ጥቃት እስከ ወዲያኛው አሸለበች:: አላዩ የሚፈልገውን ፈፅሞ ሱሪውን አጥልቆ ቃልኪዳንን እዛው እግሯ እንደተከፈተ አፏ ጨርቅ እንደተጠቀጠቀበት ትቷት ሮጦ ወጣ::

ቃልኪዳን ምንም እንኳ ጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል ህይወቷ ቢያልፍም፤ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት እስከሚሆን አስክሬኗን ያየ አልነበረም:: አሳዳጊዋ ትዕግስት ዘጠኝ ሰዓት ከሥራ ስትገባ ቦርሳዋን ለማስቀመጥ ወደ ጓዳዋ ስትዘልቅ አልጋ ላይ ያየችውን ማመን አልቻለችም:: የቃልኪዳንን አስክሬን ተጠግታ ለማየት ፈራች:: እደጅ ወጥታ መጮህ ጀመረች:: ሰዎች ተሰበሰቡ:: የምስኪኗ የቃልኪዳንን ገበና ሁሉም አየው:: ጎረቤት ተጯጯኸ:: ፖሊስ ተጠራ:: ያልታደለችዋ ሕፃን ቃልኪዳን አስክሬኗ የተሰበሰበው ቀኑን ውሎ ሙሉ ለሙሉ ከደረቀ በኋላ ነበር:: ጎረቤት አልገነዛትም፤ ብዙዎች ግን እምባቸውን እያፈሰሱ ነውሩን አዩ:: ፖሊስ አስክሬኗን አንስቶ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ላከ::

ምስክርነት

የቃልኪዳን አሳዳጊ ሥራዋ የሚከናወነው ከለሊት ጀምሮ በመሆኑ ማልዳ ጠዋት 12 ሰዓት ከቤት ወጥታለች:: ልጆቿን ትምህርት ቤት የሚያደርሰው ባለቤቷ ነው:: ቃልኪዳን ደግሞ አድጋለችና ወደ ትምህርት ቤት የምትሄደው ብቻዋን ነው:: መስካሪ ትዕግስት የቃልኪዳን አሳዳጊ በጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከቤት የወጣችው ልክ 12 ሰዓት ነበር:: እንደልማዷ ከቤት ወጥታ ሮጠች:: ከቤቷ ስትወጣ የምታሳድጋትን የ14 ዓመት ሕፃን ቃልኪዳን ብቻ ሳይሆን ሁለት ልጆቿ እና ባለቤቷ ቤት ነበሩ::

ዘጠኝ ሰዓት ከሥራ ስትመለስ ያጋጠማት ዱብ ዕዳ ለዘላለም አብሯት መቃብር ድረስ የሚወርድ ፀፀት ጣለባት:: ከሥራ መጥታ ወደ መኝታ ቤት ስትገባ፤ ትምህርት ቤት ትሆናለች ብላ ያሰበቻት ልጅ ቃልኪዳን አፏ ውስጥ ጨርቅ ተጠቅጥቆ አልጋ ላይ ተንጋላለች:: እግሯ ተከፍቷል:: ቀሚሷ ወደ ላይ ተሰብስቧል፤ ሱሪዋ ወልቆ መሬት ወድቋል:: በጭኖቿ መሃል የደረቀ ደም ይታያል:: ጠጋ ብላ ስታረጋግጥ የቃልኪዳን ህይወት አልፏል::

የቃልኪዳንን ሞት ያረጋገጠችው አሳዳጊ ድረሱልኝ ብላ መጮህ ጀመረች:: የአካባቢው ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ፖሊስ ተጠራ በመጨረሻም የፖሊስ የምርመራ ቡድን አስክሬኑን በጥንቃቄ አነሳ ስትል መስክራለች:: በመጨረሻም ቃሏን የሰጠችው ቃልኪዳን ከተቀበረች በኋላ ሲሆን፤ ተከሳሽ የአክስቷ ልጅ አላዩ እንዲህ ዓይነት ከባድ ወንጀል ይፈፅማል ብላ እንዳልጠረጠረች፤ ነገር ግን አላዩ ቃልኪዳን ከሞተችበት ቀን ጀምሮ መጥፋቱን እና የጠፋውም ምናልባት ድርጊቱን የፈፀመው እርሱ ይሆናል ብላ ተናግራለች::

ሕፃን ቃልኪዳንን ከመድፈር አልፎ ሕይወቷን ያጠፋው አላዩ በፖሊስ ብርቱ ክትትል በቁጥጥር ስር ዋለ:: እውነት ተደብቆ አይቀርም እና ክፉ ድርጊቱ አሳልፎ ሰጠው:: በመርማሪ ፖሊስ ፊት ቀርቦ ድርጊቱን መፈፀሙን አመነ:: ራሱ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ላይ እንደሰፈረው፤ የቀን ሠራተኛ የሆነው አላዩ ዓለምነህ ዕድሜው 47 ነው:: ትምህርቱን ያቋረጠው ገና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነበር:: አዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር 286 ከዘመዶቹ ጋር ተጠግቶ ይኖር እንደነበር ጠቁሞ፤ ድርጊቱን የፈፀመው በጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ከሰላሳ አካባቢ፤ በዛው በሚኖርበት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሽሮ ሜዳ አዲስ ተስፋ ትምህርት ቤት ወለጋ ሠፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ መሆኑን አምኗል::

የወንጀሉ ዝርዝር

ወንጀሉ የተፈፀመው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀፅ 620 (2)(ሀ)እና (3) ስር የተመላከተውን በመተላለፍ መሆኑን የጠቀሰው የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ፤ የወንጀሉን ዝርዝር ሲያስረዳ ተከሳሽ የኃይል ድርጊት በመጠቀም ከጋብቻ ውጪ የ14 ዓመት ሕፃን የሆነችውን ሟች ቃልኪዳን ዘነበ የምትኖርበት ቤት ውስጥ በመግባት በጥፊ ፊቷ ላይ በመምታት አልጋ ላይ በኃይል በመወርወር ጥሏታል:: እዛው አልጋ ላይ እንዳለች አንገቷን በሁለት እጆቹ በማነቅ ሟች ስትጮህ አንገቷን ከመጫን ባለፈ አፏ ውስጥ ጨርቅ በመጠቅጠቅ እና በማፈን በመታገል የኃይል ድርጊት በመጠቀም እራሷን እንዳትከላከል አድርጓል:: የለበሰችውን ቱታ በማውለቅ የራሱንም ሱሪ በማውለቅ ግብረስጋ ግንኙነት ፈፅሞባታል:: በፍፁም ሰው በሰው ላይ ይፈፅመዋል ተብሎ የማይገመት አስነዋሪ ድርጊት የፈፀመባት ሲሆን፤ ግፈኛነቱን እና የጨካኝነቱን በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር 286 በዛው ቤት ውስጥ ያሳየ መሆኑን በወንጀሉ ዝርዝር ላይ ተመላክቷል::

የአስክሬን የምርመራ ውጤትም ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ላብራቶሪ የቀረበ ሲሆን፤ የህክምና ማስረጃው እንደሚያሳየው ዜሮ ነጥብ አንድ ሳንቲ ሜትር ርዝመት እና በስድስት ሳንቲ ሜትር ስፋት ያለው የቆዳ መጋጥ ጉዳት ከግራ የታችኛው መንጋጋዋ መዓዘን ዝቅ ብሎ የሚገኝ የአንገት ክፍሏ ላይ ታይቷል:: ሁለተኛ ቁመቱ ዜሮ ነጥብ አምስት እና ስፋቱ ሶስት ሳንቲ ሜትር የሆነ የቆዳ መጋጥ ጉዳት በግራ መንጋጋ ማእዘን ላይ እንደደረሰባት ማረጋገጥ ተችሏል::

ሌላው የቀኝ የአይኗ ቅንድብ የታችኛው ቆብ የጠቆረ ሲሆን፤ በአይኗ እና አፍንጫዋ መካከል መበለዝ የታየ ሲሆን፤ በዛ አካባቢም ጉዳት እንደደረሰባት ለማወቅ ተችሏል:: የታችኛው ክንፈሯም በቀኝ በኩል መበለዙ እና የቀኝ ጡቷ ላይም የቆዳ መጋጥ መኖሩ ታውቋል::

ከተጠርጣሪው አላዩ የጉንጭ ህዋስ እና የምራቅ ናሙና የተወሰደ ሲሆን፤ ከሟች ቃልኪዳን ከመራቢያ አካል ተሰበሰበ ከተባለው ናሙና የተገኘው ዘረመል ሲመሳከር ሙሉ ለሙሉ ተመሳሳይ መሆኑ ተረጋግጧል:: በአጠቃላይ ይህን የወንጀል ዝርዝር አካቶ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ወንጀል ምርመራ ዲቪዥን ሞትን ያስከተለው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የክሱን ፍሬ ነገር በአጭሩ አብራርቶ ለአቃቤ ሕግ አቅርቧል::

አቃቤ ሕግም ተጠርጣሪው በጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ በዚሁ በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ክልል ልዩ ቦታው ሽሮ ሜዳ አዲስ ተስፋ ትምህርት ቤት አጠገብ መኖሪያ ቤት የምትኖረውን የ14 ዓመት ሕፃን ልጅ የሆነችውን ሟች ተማሪ ቃልኪዳን ዘነበ አንገቷን አንቆ በመያዝና በማፈን የአስገድዶ መድፈር በመፈፀም ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል በሚል የወንጀል ምርመራ ተጣርቶበታል ሲል የሰው ምስክር እና የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ ክስ መስርቶ ጥፋተኛው ላይ ተገቢው ውሳኔ እንዲተላለፍ አቅርቧል::

የሴቶችና ሕፃናት ዓቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት መዝገብ ቁጥር 008/16 በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መዝገብ ቁጥር 890/15 እና በፌዴራል አቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ አላዩ ሞገስ ደሳለኝ መካከል ሲካሔድ የነበረው ክርክር በመጨረሻም መቋጫ አግኝቷል፡፡ ተከሳሽ የተከሰሰበትን አስገድዶ የመድፈር እና ከባድ የግድያ ወንጀል መፈፀሙን ማስረጃዎች ተሰምተው በበቂ የቀረቡ በመሆናቸው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የነበረው ክርክር ሲጠናቀቅ የቀረበውን ሰው የመግደል ወንጀል በተመለከተ ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ወንጀል ፈፃሚውን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል ብሎ ባመነበት በግንቦት 09 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹ የ19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ምህረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You