ጅማ ከምትታወቅበት የቡና ምርቷ በተጨማሪ በእንጨት ሥራዎቿም ዕውቅናን አትርፋለች:: ጅማን ስናስብ ከአንድ ግንድ ተፈልፍሎ የሚሰራው ባለ ሶስት እግሩ የአባ ጅፋር በርጩማ ቀድሞ ይታወሰናል:: አለፍ ሲልም የስኒ ረከቦቶቹ /በዓይነትና በመጠን/፣ አልጋው፣ የቡና ጠረጴዛው፣ የፎቶ ማስቀመጫና ሌሎች ከእንጨት የሚሰሩ ቅርጻ ቅርጾችን ማንሳት የግድ ነው:: የእንጨት ሥራ የዕድ ጥበብ ውጤት እንደመሆኑ ጅማ ጎራ ያለ እንግዳ በሙሉ ጥበበኛ እጆች የተጠበቡባቸውን የእንጨት ውጤቶች ተመልክቶ መማረኩና የራሱ ማድረጉ የማይቀር ጉዳይ ነው::
የጅማ እንጨት ሥራ መነሻው የአባጅፋር ወንበር ሲሆን፤ ወንበራቸው በተፈጥሮ ከአንድ ግንድ ተፈልፍሎ የወጣ ባለሶስት እግር በርጩማ ነው:: ይህ በርጩማ ከአንድ የዋንዛ ግንድ ተፈልፍሎ የተሠራ ነው፤ መቀመጫው ምንም ዓይነት ዘመናዊ መሳሪያ ወይም ማሽን ያልነካውና በመጥረቢያና በእጅ ብቻ የተሰራ ዘመን ተሻጋሪ ስለመሆኑም ይነገራል:: በዚሁ መነሻነት የተጀመረው የእንጨት ሥራም አሁን ላይ ጅማ ከምትታወቅባቸው ዋና ዋና ጉዳዮቿ መካከል አንዱ መሆን ችሏል:: የእንጨት ሥራዎቿ ዛሬም ድረስ እየተሻሻሉ ቀጥለዋል:: በተለይም ባለሶስት እግር ወንበሩ ወይም በርጩማ በዘመን ተሻጋሪነቱ ይታወቃል::
የእንጨት ሥራ በስፋት በተለመደባት ጅማ አብዛኛው ወጣት እጁን የሚያፍታታውና ሥራ የሚጀምረው በእንጨት ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይደለም:: በአካባቢው እንጨት ተፈልፍሎ ተገቢውን ቅርጽ ይዞ ለተለያየ አገልግሎት ሲውል መመልከት የዕለት ተዕለት ተግባሩ ለሆነው የጅማ ወጣት የእንጨት ሥራ ሙያ በእጁ ላይ ነው ማለት ይቻላል:: አብዛኛው ወጣት የእንጨት ሥራን በቀላሉ በመልመድ የመጀመሪያው የሥራ አማራጩ የሚያደርገውም በዚሁ ምክንያት ነው::
የዕለቱ የስኬት እንግዳችንም እንደ አብዛኛዎቹ የጅማ ልጆች ለእንጨት ሥራ እንግዳ አይደለም:: ጅማ ከተማ ተወልዶ እንደማደጉ በየአካባቢው የእንጨት ሥራን እየተመለከተ አድጓል:: ከመመልከት ባለፈም ውስጣዊ ፍላጎትና ለጥበብ የተሰጠ ማንነት ያለው በመሆኑ እንጨቱን ይጠበብበታል::
‹‹የእንጨት ሥራ ዕደጥበብ ነው›› የሚለው እንግዳችን እንጨት ፈልፍሎ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችን ይሠራል:: ትናንሽ ከሚመስሉ ቅርጻ ቅርጾች በተጨማሪም ትላልቅ የሚባሉ እንደ ቁም ሳጥን፣ አልጋ፣ ወንበር ጠረጴዛ፣ በርና መስኮቶች፣ በርጩማና ሌሎችንም ይሰራል:: አጠቃላይ ከእንጨት የሚሰሩ ማናቸውንም ቁሶች በመሥራት የሚታወቀው ጥበበኛው እንግዳችን ወጣት ሙሉቀን ወንድሙ ይባላል::
ጅማ ላይ ተወልዶ ያደገው ወጣት ሙሉቀን፤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በዚያው ተምሯል:: የከፍተኛ ትምህርቱንም እንዲሁ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተከታትሎ በማኔጅመንትና በአርት (በሙዚቃ ትምህርት ክፍል) የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል::
ትምህርት የተሻለ ዕውቀት የሚሰጥ ስለመሆኑ የሚያምነው ወጣት ሙሉቀን፤ ለሚሰራው የእንጨት ሥራ አቅምና ጉልበት እንደሆነው ይናገራል:: ‹‹በተለይ አርት ሰዎች እራሳቸውን ፈልገው የሚያገኙበት መንገድ ነው›› ይላል:: ከከፍተኛ ትምህርት በኋላ እራሱን ጥበብ ውስጥ እንዳገኘው የሚናገረው ወጣት ሙሉቀን ከትምህርት በኋላ በቀጥታ ወደ እንጨት ሥራ እንደገባና የፈጠራ ችሎታውን በመጠቀም የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችን መሥራት እንደጀመረ አጫውቶናል::
እሱ እንደሚለን፤ ከከፍተኛ ትምህርት በኋላ ተቀጥሮ የመሥራት ፍላጎት አልነበረውም:: ከዛ ይልቅ በውስጡ የሚመላለሰውን የቅርፃ ቅርፅ ጥበብ ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል:: በጥረቱም ዕውቀቱንና ውስጣዊ ፍላጎቱን ብቻ መነሻ በማድረግ በወላጆቹ መኖሪያ ግቢ ውስጥ እንጨት ሰብስቦ ፈጠራ የታከለበት ሥራ መሥራት ጀምሯል:: ታዲያ ትናንሽ ከሚባሉ ቅርጻ ቅርጾች ጀምሮ ከእንጨት የሚሰሩ ትላልቅ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ለመሥራት ጊዜ አልወሰደበትም:: ምክንያቱም ይላል፤ ‹‹ምክንያቱም ማንም ሰው አሻፈረኝ ካላለ በስተቀር የጅማ ልጅ ሆኖ ለእንጨት ሥራ ባዳ የሚሆን ሰው የለም:: ፍላጎት ያለው ሁሉ የእንጨት ባለሙያ መሆን ይችላል:: ለዚህ ደግሞ ጅማ ውስጥ በብዛት ፋብሪካ አለመኖሩም ሌላው ምክንያት ነው›› ይላል::
ጅማ ውስጥ የሚፈለገውን ያህል ፋብሪካዎች ባለመኖራቸው አብዛኛው ወጣት እንጨት ሥራን እንደ አንድ አማራጭ ወስዶ ወደ ሥራው ይገባል:: የሚለው ወጣት ሙሉቀን፤ የእርሱም አጋጣሚ ከዚህ የተለየ እንዳልነበር ይናገራል:: በዚህም የተለያዩ ከእንጨት የተሰሩ የጥበብ ሥራዎች ጅማ ውስጥ ይታያሉ:: ምንም ዓይነት ማሽን ሳይጠቀሙ እንጨት ፈልፍለው በእጃቸው ብቻ ከሚሰሩት የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችና ቅርጻ ቅርጾች መካከል ቀጭኔን ጨምሮ የተለያዩ የእንስሳት ቅርጽ፣ የቡና ጠረጴዛ፣ የስኒ ረከቦት፣ ፎቶ ፍሬም፣ ዱካ፣ መቀመጫዎችና ሌሎችም ይጠቀሳሉ::
በከተማዋ ከሚታዩት የእንጨት ሥራዎች መካከል ሁሉንም ዓይነት የእንጨት ሥራዎች በሚባል ደረጃ የሚሰራው ወጣት ሙሉቀን፤ እንጨት የተባለ ሁሉ እጁ ሲገባ ሕይወት ይዘራበታል:: ሳቢና የሚያማምሩ ቅርጻ ቅርጾችን እንዲሁም የተለያዩ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ያመርትበታል:: ባጠቃላይ እንጨቱን ይጠበብበታል ብንል ማጋነን አይሆንም:: በወላጆቹ መኖሪያ ግቢ ውስጥ ብቻውን አንድ ብሎ የጀመረው የእንጨት ሥራ ዛሬ በከተማዋ አሉ ከሚባሉ እንጨት ሠራተኞች ተርታ አሰልፎታል::
ገና በልጅነቱ የእንጨት ሥራዎች ሲሰሩ እየተመለከተ ያደገው ወጣት ሙሉቀን፤ ሙያውን ለመማር ብዙ አልተቸገረም:: በቀላሉ ሰዎች ጋር ተጠግቶ በመላላክ እንዲሁም ረዳት በመሆን ነው ሙያውን የለመደው:: ይሁንና ለሙያው ጠለቅ ያለ ፍቅርና ከፍተኛ ተነሳሽነት ያዳበረውም በዚያ ምክንያት ነው:: በዚህ መነሻ በቀጥታ ወደ ሥራው በመግባትም የእንጨት ሥራዎቹን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል::
ጅማ ላይ ያለው የእንጨት ሥራ ትኩረት ቢሰጠው አሁን ላይ ካለው አበርክቶ የበለጠ ለወጣቱ ሥራ ዕድል ፈጠራ ብዙ ሊያበረክት የሚችል ነው:: የሚለው ወጣት ሙሉቀን፤ በርካታ ወጣቶች ሕይወታቸውን የለወጡበትና የተሻሻሉበት ቢሆንም የበለጠ እንዲታወቅ መንግሥት ትኩረት ቢሰጠው መልካም መሆኑን ሲያስረዳ፤ የገበያ ትስስር ተፈጥሮለት ሥራው እንዲሰፋ መንግሥትን ጨምሮ የሁሉንም ትብብር የሚፈልግ ነው:: በርካታ ወጣቶችም ሙያውን በቀላሉ መማር የሚችሉበትና መጠነኛ በሆነ መነሻ ካፒታል መሥራት የሚችሉት ሥራ ነው::
እንጨት ሥራ ጅማ ውስጥ በቀላሉ የሚጀመር ሥራ እንደመሆኑ ከፍተኛ ጥረት ሲታከልበት ውጤታማ የሚያደርግ ነው:: የወጣት ሙሉቀንም ተሞክሮ ከዚህ የተለየ አይደለም:: ቀን ከሌሊት በመሥራት ውጤታማ መሆን ችሏል:: ይህም ሲባል አሁን ላይ ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል የስኒ ረከቦት በተለያየ መጠንና ቅርጽ በስፋት አምርቶ አዲስ አበባን ጨምሮ ለክልል ከተሞች ይልካል:: የማምረት አቅሙንና የገበያ ፍላጎቱን በማጣጣም ትዕዛዝ ሲበዛ ለሌሊት ጭምር በመሥራት ወደ ስኬት እየተንደረደረ ያለ ወጣት ነው::
ለሥራ ያለውን ውስጣዊ ፍላጎትና ተነሳሽነት መሠረት በማድረግ አንድ ብቻውን ሆኖ በወላጆቹ መኖሪያ ግቢ ውስጥ የጀመረው የእንጨት ሥራ ዛሬ ላይ 24 ለሚደርሱ ወጣቶች በቋሚነት የሥራ ዕድል ፈጥሯል:: ከ24ቱ በተጨማሪም የሥራ ትዕዛዝ ሲጨምር ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ያሰራል:: የመሥሪያ ቦታውን በተመለከተም ሁለት የማምረቻ ቦታ ያለው ሲሆን፤ አንደኛውን ቦታ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘው ሲሆን፤ ሁለተኛውን ከግለሰቦች ተከራይቶ ይሰራል:: አንደኛው የማምረቻ ቦታ ትላልቅ የሚባሉ እንደ አልጋ፣ ቁምሳጥን፣ በሮች፣ መስኮቶችና የምግብ ጠረጴዛዎች የሚመረቱበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ቀለል ያሉ እንደ ስኒ ረከቦት የቡና ጠረጴዛ፣ የፎቶ ማስቀመጫ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾች ሆነው ሱቅ ላይ መሸጥ የሚችሉትን ያመርታል::
የሚያመርታቸው ምርቶች ባፈራቸው ደንበኞቹ አማካኝነት በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ከተማ ተደራሽ እንደሚሆኑ ያነሳው ወጣት ሙሉቀን፤ በተለይም አልጋ የጅማ ሕዝብ በስፋት እንደሚገዛና ወደ አዲስ አበባም እንደሚልክ ይናገራል:: ከተማ ውስጥ ከሚገኘው መሸጫ ሱቅና ከክልል ደንበኞች በተጨማሪ በማህበራዊ ሚዲያ ማለትም በቲክቶክ፣ በፌስቡክና ኤም ኤም ፈርኒቸር በሚል በቴሌግራም ምርቶቹን የማስተዋወቅና የመሸጥ ሥራ ይሰራል::
ለምርቶቹ አስፈላጊ የሆነው ጥሬ ዕቃ በዋናነት እንጨት ነው:: ይህ እንጨትም ጅማ ውስጥ በስፋት የሚገኝ ሲሆን፤ ዓይነቱም የዋንዛ እንጨት ነው:: የእንጨት ሥራዎቹ በስፋት የዋንዛ እንጨት በመጠቀም የሚመረቱ ሲሆን፤ ከእንጨት በተጨማሪ እንደ አስፈላጊነቱ ኤምዲኤፍ፣ ላሚኔት፣ ኮምቤፍአይጂትና ሌሎችም ማንኛውም እንጨት ቤት የሚገኙ ጥሬ እቃዎችን ይጠቀማል:: ለዘርፉ የጥሬ እቃ ችግር የለም:: ነገር ግን የገበያ ትስስር ባለመኖሩ አምራቹ ማምረት በሚችለው አቅም ሳይሆን ገበያው በሚጠይቀው ልክ ብቻ እያመረተ መሆኑን በመግለጽ የገበያ ትስስር አለመኖሩ አንዱ ችግር ነው ይላል::
ላለፉት 15 ዓመታት በእንጨት ሥራ ውስጥ ያሳለፈው ወጣት ሙሉቀን፤ የእንጨት ሥራ አንዱ የዕደ ጥበብ ውጤት እንደሆነ ያስረዳል። ጅማ ውስጥ ከእንጨት የሚሰሩ ውብ ሥራዎች እንዳሉና እነዚህን ውብ ሥራዎች ግን አውጥቶ የመጠቀምና የማስተዋወቅ ሥራ አልተሰራም:: ስለዚህ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መታየት ቢችል አሁን እየፈጠረ ካለው የሥራ ዕድል በበለጠ በርካታ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችል አመላክቷል:: ከሥራ ዕድል በተጨማሪም ምርቶቹ ውብ፣ ጠንካራ ዘመን ተሻጋሪ እንደመሆናቸው ከውጭ የሚገባውን ፈርኒቸር በመተካት የውጭ ምንዛሪን ማዳን እንደሚቻል አስረድቷል::
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ወጣት ሙሉቀን በአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶች ሙያዊ ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራው እንዲገቡ ያደርጋል:: በተለይም በመንግሥት በኩል ከተለያዩ ቀበሌዎች ተደራጅተው ለሚመጡ ወጣቶች የስድስት ወር ስልጠና በመስጠት የእንጨት ሥራ ሙያን ቀስመው ይወጣሉ:: በአንድ ጊዜ አምስትና አስር ወጣቶችን በማሰልጠኑም የምስክር ወረቀት አግኝቷል:: በአሁን ወቅትም አምስት ወጣት ሴቶችን ከወረዳው ተቀብሎ እያሰለጠነ ይገኛል::
በቀጣይም የእንጨት ሥራውን የማስፋትና የማዘመን ዕቅድ ያለው መሆኑን ያነሳው ወጣት ሙሉቀን፤ በተለይም ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በማምረት እንዲሁም ሥራዎቹን በስፋት ማሳየት በሚችል ትልቅ የእንጨት ሥራዎች ማሳያ የመክፈት ዕቅድ አለው:: ለዚህም ዘመናዊ ማሽኖች ሥራ የሚያቀሉ በመሆናቸው ዘመናዊ ማሽኖችን ለመጠቀም አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሰራ ስለመሆኑም አጫውቶናል::
ማንኛውንም ሥራ ሰዎች ፈልገውና ከውስጥ በመነጨ ተነሳሽነት መሥራት ከቻሉ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የሚመክረው ወጣት ሙሉቀን፤ በተለይም የጅማ ወጣቶች በቀላሉ የሚለመደውን እና በሁሉም ደጅ የሚገኘውን የእንጨት ሥራ ሙያ በመቅሰም መሥራት እንደሚችሉ ይናገራል:: ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ያምናል:: በአሁን ወቅትም የእንጨት ሥራው በርካታ ወጣቶችን የያዘ በመሆኑ የበለጠ ለመሥራት የመንግሥት ትኩረት ወሳኝ ነው ብሏል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም