
ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በሶስት ወራት ውስጥ 39 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አገኙ።
የሜታ ኩባንያ ንብረቶች የሆኑት ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ባለፉት ሶስት ወራት ከፍተኛ ገቢ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
ኢንስታግራም እና ፌስቡክ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ 39 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
ሁለቱ ኩባንያዎች ያገኙት ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ 13 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ20 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል።
ኩባንያዎቹ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀማቸው ለገቢያቸው መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተገልጿል።
በዓለማችን ካሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በሜታ ኩባንያ ስር ካሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
የድርጅቱ መሥራች እና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ እንዳስታወቀው ተወዳዳሪ ለመሆን እና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንዲረዳቸው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ 40 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያደርጉ አስታውቋል።
መሠረታቸውን አሜሪካ ያደረጉት ሜታ፣ ጎግል እና ማይክሮሶፍት ኩባንያዎች የተሻሻለ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያ ለመሥራት ፉክክር ላይ ናቸው።
70 ሺህ ሠራተኞች ያሉት ሜታ ኩባንያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት ሠራተኞችን እየቀነሰ ይገኛል።
ድርጅቱ በፈረንጆቹ 2022 ላይ በመላው ዓለም ላይ 80 ሺህ ሠራተኞች ነበሩት።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም