የቬንዝዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ቢሊየነሩ ኢለን መስክ ለመደባደብ መስማማታቸው ተነገረ፡፡
ባለፉት ጊዜያት በማህበራዊ ትስስር ገጽ እና በመገናኛ ብዙሃን ሃይለ ቃላትን ሲለዋወጡ የሰነበቱት ሁለቱ አካላት ንግግራቸውን በድብድብ ለመደምደም ተስማምተዋል፡፡
ኒኮላስ ማዱሮ ባሰለፍነው እሁድ ለሶስተኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመን ማሸነፋቸው ይፋ መደረጉን ተከትሎ በኤክስ ገጹ ላይ “አጭበርባሪ ፕሬዚዳንት” በሚል የገለጻቸው መስክ በሥልጣን መቀጠል የሌለባቸው ፕሬዚዳንት ሲል ወርፏቸዋል፡፡
ቀጥሎም የቬንዝዌላ ዜጎች የማዱሮን ሀውልት አፍርሰው የቀድሞውን የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ሁጎ ቻቬዝ ሀውልት ሲተክሉ የሚያሳይ የተቀነባበረ ተንቀሳቃሽ ምስል በገጹ ላይ ለጥፏል፡፡
ፕሬዚዳንቱ መስክ በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር አመጽ እና ብጥብጥን የመፈጥር ዓላማ ያለው ሀገራችንንም በስፔስ ሮኬቶቹ መውረር የሚፈልግ ዋነኛ ጠላታችን ነው ሲሉ ከስሰውታል፡፡
ማዱሮ ሰኞ እለት በሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው “ከኔ ጋር መጣላት ትፈልጋለህ ቦታ እና ጊዜውን መርጠህ አሳውቀኝ እኔ የቻቬዝ እና ቦሊቫር ልጅ ነኝ” ሲሉ ዝተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የፕሬዚዳንቱን የይዋጣልን ጥያቄ መቀበሉን ያስታወቀው መስክ እኔ ካሸነፍኩ ማዱሮ ከሥልጣን ላይ ይወርዳሉ ከተሸነፍኩ ደግሞ ፕሬዚዳንቱን በነጻ ወደ ማርስ የሽርሽር ጎዞ እጋብዛቸዋለሁ ብሏል፡፡
የስፔስ ኤክስ እና ቴስላ ዋና ስራ አስፈጻሚው ቢሊየነሩ ኢለን መስክ የተለያዩ ታዋቂ እና ተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በመወረፍ እና ቡጢ ቢውዳደሩ እንደሚያሸንፋቸው በመፎከር ይታወቃል፡፡
ከዚህ ቀደም የፌስቡክን መስራች ማርክ ዙክርብርግ የቡጢ ውድድር ይዘጋጅልን እና እንተያይ የሚል ጥቄ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ ደግሞ ከቬንዝዌላው ፕሬዚዳንት ጋር ተፋጥጠዋል፡፡ ሁለቱ አካላት እንዳሉት ፊት ለፊት ለመቧቀስ ይገናኛሉ ተብሎ አይጠበቅም ሆኖም ማዱሮ የሀገር መሪ ሆነው የእንቧቀስ ጥያቄ ማቅረባቸው መነጋገርያ ሆኗል፡፡
የቬንዝዌላ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ኒኮላስ ማዱሮ 51 በመቶ የመራጮችን ድምጽ በማግኘት ሀገሪቱን ለሶስተኛ ተከታታይ የሥልጣን ዘመን ማስተዳደር የሚችሉበትን ይሁንታ ማግኘታቸውን አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሰኞ ጀምሮ ምርጫ ተጭበርብሯል ያሉ የሀገሪቱ ዜጎች በአደባባይ ተቃዎሟቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም