ኢትዮጵያ በወርቅ ማዕድን ክምችቷ ትታወቃለች። ቅርብ ጊዜ የወጣ መረጃ እንዳመለከተውም፤ በሀገሪቱ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከ517 ቶን በላይ የወርቅ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል። ይህ የማዕድን ሀብት በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የሚገኝ ቢሆንም፣ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ክልል፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በስፋት እንዲለማ እየተደረገ ነው።
ይህ የወርቅ ማዕድን በአብዛኛው እየለማ ያለው ግን በባሕላዊ መንገድ ነው። የወርቅ ልማቱ በኋላ ቀር መንገድ እየተካሄደ ያለበት ሁኔታ አልሚዎችም ሆኑ ሀገሪቱ ከዚህ ማዕድን ሀብት ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማዕድኑን የማውጣቱም ሆነ የግብይቱ ሥራ በሕገወጦች ቁጥጥር ስር እየሆነ ያለበት ሁኔታ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አድርጎታል። ይህም ችግር ከወርቅ ማዕድን የሚገኘው ሀብት በአግባቡ እንዳይገኝ ተደርጓል። መንግሥት ይህን ሕገወጥ ተግባር ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሠራ ይገኛል።
ሕገወጥ ተግባሩን ከመከላከልና መቆጣጠር ጎን ለጎንም መንግሥት ሀገሪቱ ከወርቅ ማዕድኗ ምርት ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ መሥራቱን አጠናክሯል። ለእዚህም በባሕላዊ መንገድ የሚካሄደውን ወርቅ የማምረት ሥራ ለማዘመን፣ በባሕላዊ መንገድ የሚያመርቱትም ቢሆኑ በስፋት ወደ ልማቱ እንዲገቡ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል። የወርቅ ልማቱ ማዕድኑ ባለባቸው ሌሎች ክልሎችና አካባቢዎች እንዲስፋፋ ለማድረግም ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
በተለይ የወርቅ ልማቱን ለማዘመኑ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል። ልማቱ በኩባንያ ደረጃ እንዲካሄድ ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ሥራም በወርቅ ልማቱ የሚገኘውን ገቢ በብዙ እጥፍ ማሳደግ የሚያስችሉ ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ ገብተው እንዲያለሙ እየተደረገ ነው። ይህን ተከትሎም አንድና ሁለት ብቻ የነበሩት የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች ቁጥር በቅርቡ እንደሚጨምር ይጠበቃል። አዳዲስ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች በተለያዩ ክልሎች ላይ እየተገቡ ሲሆን፣ ግንባታቸውም በጥሩ ደረጃ ላይ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ‹‹ኩርሙክ›› እንዲሁም በጋምቤላ ክልል ‹‹ኢትኖማይን›› የተሰኙ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች ግንባታ እየተካሄደ ያለበት ሁኔታም የወርቅ ማዕድን ልማቱን ለማዘመንና በኩባንያ ደረጃ ለማካሄድ ለተያዘው ጥረት ማሳያ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡
በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ ተገኝተን የግንባታ ሥራውን የተመለከትነው የኢትኖማይን የወርቅ ፋብሪካ ሳይት ማናጀር ኢንጂነር ወልደገብርኤል አረጋዊ ክልሉ ትልቅ የወርቅ ሀብት ክምችት እንዳለው ይናገራሉ። ይህም በወርቅ ማዕድን ልማቱ ብዙ መሥራት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ፋብሪካው ልማቱን የሚያካሂደው በ16 ኪሎ ሜትር ስኩየር ቦታ ላይ ነው። ይህም ፋብሪካው ያረፈበት እና ወርቅ ፍለጋው የሚከናወንበት ስፍራን ያካተተ ነው ።
የማዕድን ጥሬ እቃ ወይም ወርቅ ያዘለ አለት የሚወጣበት ስፍራ በጣም ምቹ እና ትልቅ ሀብት ያለበት መሆኑን የሚገልፁት ኢንጂነር ወልደገብርኤል፤ በአሁኑ ወቅት የወርቅ ማዕድኑ የሚካሄድበት ፋብሪካ ግንባታ 90 ከመቶ በላይ ደርሷል ሲሉም አስታውቀዋል። የወርቅ አለት ያለበት ስፍራ የውስጥ ለውስጥ ግንባታም እየተከናወነ መሆኑን ተናግረው፣ ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ለመግባት ጫፍ ደርሷል ብለዋል።
በአካባቢው ያለው ወርቅ ያዘለ አለት በጣም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተፈላጊነቱም በዚያው ልክ መሆኑን ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በአካባቢው ያለው ወርቅ በአንድ ቶን አፈር ውስጥ በአማካይ 22ነጥብ7 ግራም ወርቅ ይገኝበታል፤ የፋብሪካ በአካባቢው መገንባትም ይህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ነው። ለዚህም የሚውል ለየት ያለ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ይውላል። የወርቅ ማዕድን አቅሙም ሆነ ያንን ለማውጣት የሚተከለው ፋብሪካ አቅም ለኩባንያው ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
በኢትዮጵያ የወርቅ ማዕድን በማውጣት ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት እንደ ሀገር ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፤ ይህን ለመጠቀም ደግሞ ከቴክኖሎጂ፣ እውቀትና ሳይንሳዊ አሠራር በዘለለ ሰላም ወሳኝ ነው የሚሉት ኢንጂነሩ፣ ይህን ለማረጋገጥ የሚያስችል አሠራር በክልሉ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል መዋቅር ድረስ መዘርጋቱንም ነው ያመለከቱት።
ኩባንያው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ትልቅ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ በመሆኑ ለኩባንያው በነዋሪዎች ጭምር ጥበቃ ይደረግለታል ይላሉ። ክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት አስፈላጊውን የፀጥታ ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
ፋብሪካው ለዜጎች የሥራ እድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረው፣ ግንባታው እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ለ220 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል ሲሉም ጠቅሰዋል። ግንባታው ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ ከዚህ በላቀ ደረጃ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የፋብሪካው የፕሮዳክሽን ሱፐር ቫይዘር አቶ ተስፋዬ ገብረ በበኩላቸው ኢትኖማይን የማዕድን ፋብሪካ ለኢትዮጵያ ትልቅ በረከት ይዞ መጥቷል ይላሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ፋብሪካው በሰዓት 10 ቶን የወርቅ አፈር የሚፈጭ ሲሆን፣ በዓመት ደግሞ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን አፈር ይፈጫል። በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እስካሁን በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ የማዕድን ፋብሪካዎች አዳዲስ ቴክሎጂዎችን የሚጠቀም ነው። አዲስ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም በመሆኑም የአካባቢ ብክለት እና መሰል ተያያዥ ጥያቄዎችን አያስነሳም።
የአካባቢ ብክለትን እያስከተሉ ፣ ጥሩ ስም ሳይገነቡ ብሎም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት ሳይፈጠሩ በመሥራት ዓለም አቀፍ ገበያ መውጣት አዳጋች መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘመኑም የሶሻል ሚዲያ እና ኢንፎርሜሽን ዘመን ስለሆነ በተበላሸ አሠራር እና የአካባቢ ብክለትን በማስከተል ማምረት አይቻልም ብለዋል።
በአካባቢው ያለውን ትልቅ ፀጋ ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ማህበረሰብን ያማከለ እና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆን እንዳለበት ይታመናል ሲሉም አመልክተው፣ ኩባንያውም እነዚህን የደህንነት መርሆች በመከተል እንደሚሠራ ገልጸዋል። ወርቅ ለማግኘትና ለገበያ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ወርቃማ አሠራሮችንም እንደሚከተል አስታውቀዋል።
አቶ ኡጁሉ ኦማኒ የዲማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ናቸው። እሳቸው እንደተናገሩት፤ ወረዳው በከፍተኛ የማዕድን ሀብት ታድሏል፤ ሌሎች በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችም አሉት። በአሁኑ ወቅት ወጣቶችን እና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች በሰፊው ወደ ሥራ እየገቡ ናቸው።
በወረዳው በማዕድን ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አቶ ኡጁሉ ጠቅሰው፣ አካባቢው ወርቅ ልዩ መለያው መሆኑን አመልክተዋል። በወርቅ ማዕድን ላይ በሰፊው ጥናት መሰራቱንም ገልጸው፣ ለኮንስትራክሽን የሚውሉ በርካታ ማዕድናት በወረዳው እንዳሉም ጠቁመዋል።
ይህን ታሳቢ በማድረግ በርካቶች ፍቃድ አውጥተው እየሰሩ መሆናቸው ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት በወረዳዋ ሁለት ከፍተኛ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች ፍቃድ አውጥተው በወርቅ ማዕድን ፍለጋ እና ማምረት ሥራ ላይ ተሰማርተው ትልቅ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በወረዳው በባሕላዊ መንገድ ወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ አካላት የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ግዙፍ ፋብሪካዎች ጋር የጥቅም ግጭት እንዳይከሰት ሕጋዊ አሠራር፣ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ነው። በአካባቢው ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን ቀድሞ ማስወገድና ሥጋት ለሚሆኑት ደግሞ ቀድሞ እልባት በመስጠትና ጥንቃቄ በማድረግ ሥራው እንዳይስተጓጎልም እየተሠራ ይገኛል። አካባቢው ለደቡብ ሱዳን ድንበር በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመሆኑ ወረዳው፣ ዞኑ፣ ክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው፡፡
በዲማ ወረዳ ብቻ በልዩ አነስተኛ የተሰማሩ ከ50 በላይ ፋብሪካዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉት ፋብሪካዎች ሁለት ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በአካባቢው ሀብት እና ጥናቶች ከሚያመላክቱት መረጃ አኳያ ግን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ሀብት ውስን ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በልማቱ እየተከናወነ ባለው ተግባር በቂ ሀብት እየተገኘ ነው ማለት እንደማይቻል ጠቁመው፣ አካባቢው በወርቅ ሀብት ከፍተኛ አቅም ቢኖረውም በሕገ ወጥ የወርቅ ንግድ /ኮንትሮባንድ/ ሳቢያ ግብይቱ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን አስገንዝበዋል። ይህን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያመች ሕጋዊ አሠራር መዘርጋት እንደሚገባ ገልጸዋል። ለእዚህም ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥት የተጠናከረ ሥርዓት መዘርጋት ብሎም ከአጎራባች ሀገራት ጋር መነጋገርና መስማማት ይገባል ብለዋል። በብሔራዊ ባንክ በኩልም በወርቅ ግብይት ላይ ያለውን አሠራር በማጤን ጥቁር ገበያ የሚቆመበትን ሁኔታ ለመፍጠር በተጠናከረ መንገድ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ኡመድ ኡጁሉ በበኩላቸው፤ ማዕድን በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋና የዕድገት ተኮር ዘርፍ ተብለው ከተለዩት አምስት ዘርፎች አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ የተለያዩ የማዕድን ሀብት ክምችቶች እንዳሉ ይታወቃል። በዋናነት የወርቅ ማዕድን በስፋት የሚገኝ ሲሆን፣ በክልሉ አራት ወረዳዎች (አኙዋሃ ዞን ዲማ፣ አቦቦና ጋምቤላ ወረዳዎች፤ ማጃንግ ዞን መንገሺ ወረዳ) የወርቅ ማዕድን ክምችት ይገኛል።
በዚሁ መሠረት በወርቅ ምርት እስካሁን ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የተደረገ የወርቅ መጠን አስመልክተው ሲያብራሩ እንደገለጹት፤ 2011 በጀት ዓመት 122ነጥብ24 ኪሎ ግራም፣ በ2012 በጀት ዓመት 264ነጥብ24 ኪሎ ግራም እንዲሁም በ2013 በጀት ዓመት 1212 ነጥብ 24 ኪሎ ግራም ወርቅ ገቢ ሆኗል። በ2014 በጀት ዓመት ደግሞ 1206 ነጥብ51 ኪሎ ግራም ፣ በ2015 ዓ.ም 236 ኪሎ ግራም ወርቅ ገቢ የተደረገ ሲሆን፤ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ 225 ኪሎ ግራም ወርቅ ገቢ ተደርጓል። የሚመረተውም የወርቅ ምርት በየወቅቱ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ በማድረግ ክልሉ ለሀገር ልማት የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የወርቅ ሀብት በአግባቡ በማልማት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጥቅም እንዲውል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ባሕላዊና አነስተኛ ወርቅ አምራቾች ቁጠባን መሠረት በማድረግና ዘመናዊ ማምረቻ መሣሪያዎችን በመጠቀም እንዲያመርቱ በማድረግ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ለማድረግም እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኘውን የወርቅ ማዕድን ለመጠቀም ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፣ ሀገሪቱ ያላትን የማዕድን እምቅ ሀብት በመጠቀም ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ እንዳለባት የዓለም ባንክ መረጃም ይጠቁማል። በተለይም አሳማኝና በቂ የማስተዋወቅ ሥራ አለመሠራቱ፣ ጊዜ ቆጣቢና ሥርዓትን መሠረት ያደረገ የማዕድን አወጣጥ ፍቃድ አሰጣጥ ሥርዓት አለመዳበር፣ በዘርፉ በበቂ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሙያዎች አለመኖር፣ ከመሬት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች ከወርቅ ልማቱ ፈተናዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም