የክልሉ ምክር ቤት የሕዝብን የልማት ጥያቄዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሚቀርፉ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል

አዲስ አበባ፡- የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕዝብን የልማት ጥያቄዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሚቀርፉ ጉዳዮች ላይ መወያየቱን አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋየ ገለጹ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን የተለያዩ ውሳኔዎችንና ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋየ እንደገለጹት፤ የክልሉ ምክር ቤት የሕዝብን የልማት ጥያቄዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሚቀርፉ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ጉባዔው የክልሉን ወቅታዊ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በስፋት ተመልክቷል ያሉት አፈ ጉባዔዋ፤ ምክር ቤቱ በመደበኛ ጉባዔው በተለያዩ ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገንቢ ምክክሮችን አካሂዶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳርፏል ብለዋል።

ክልሉ ለአንድ ዓመት ከዘለቀው ግጭት ወጥቶ አንጻራዊ ሰላም በበርካታ አካባቢዎች መስፈኑን ጠቅሰው፤ የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ዳር እንዲደርሱ የሚያስችሉ ምክክሮች መካሄዱን ገልጸዋል።

በክልሉ ሕዝብን ያማረሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በተለይም የፍትሕ ሥርዓቱን በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒ ለማድረግ ምክር ቤቱ ምክክሮችን እንዳደረገ በመግለጽ፤ በየደረጃው የሚገኘው የምክር ቤት አባል ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንደሚኖርበትም መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

የሕዝቡን የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በጀትን በቁጥጥርና በቁጠባ መጠቀም፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን አብራርተዋል።

በምክር ቤቱ የሕዝብን ጥያቄ እያዳመጡ በየደረጃው ምላሽ መስጠትን ጨምሮ የምክር ቤቱን የክትትልና ቁጥጥር አቅም ማጠናከር የሚሉ ጉዳዮች መነሳታቸውንም ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ጉባዔው የተለያዩ ደንቦችንና መመሪያዎችን መርምሮ ማጽደቁን የገለጹት አፈ ጉባዔ ፋንቱ፤ የክልሉን መንግሥት የ2017 በጀት መርምሮ አጽድቋልም ብለዋል።

በተጨማሪም በጀታቸው በምክር ቤት የሚጸድቅላቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የክልሉ ምክር ቤትና የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዓመታዊ በጀት ማጽደቁንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በምክር ቤቱ የክልሉን መንግሥት የ2017 በጀት 150 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ የቀረቡለት ሹመቶችንም አስመልክተው አቶ ዓለምአንተ አግደው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ ሙሉዓለም ቢያዝን ዓለሙ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አቶ መልካሙ ፀጋየ ገላው የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ እንዲሆኑ ማጽደቁን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት ለምክር ቤቱ ቀርቦ የጸደቀ ሲሆን፤ አቶ አበራ ፋንታው የሰው ሀብት አስተዳደር እና ቱሪዝም ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም እመቤት ከበደ የመንግሥት ወጪ ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸውን ማወቅ ተችሏል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You