ኢትዮጵያ በዘመናት የደመቀ የኦሊምፒክ መድረክ ውጤታማ የአትሌቲክስ ታሪክ ገናና ስም ያተረፈችው በረጅም ርቀትና በማራቶን ውድድሮች ነው:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በመካከለኛ ርቀቶችም ውጤታማ መሆን ችላለች:: የአትሌቲክሱ አንድ አካል በሆነው የእርምጃ ውድድሮች ግን እንኳን የውጤት እምብዛም የተሳትፎ ታሪክ የላትም:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ባህል እየተቀየረ መጥተል:: በኦሊምፒክ መድረክ ባይሆንም በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የተለያዩ ቻምፒዮናዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም በእርምጃ ውድድሮች ከተሳትፎ ባሻገር ውጤት ማስመዝገብም እየቻሉ ነው::
ለዚህ ትልቁ ማሳያም 2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድሮች ዛሬ ሲጀመሩ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የእርምጃ ቻምፒዮኑ አትሌት ምስጋና ዋቁማ በ20 ኪሎ ሜትር ኢትዮጵያን በብቸኝነት ወክሎ የሚፎካከር ተራማጅ ኦሊምፒያን መሆኑ ነው::
መንፈሰ ጠንካራው አትሌት ምስጋና ዋቁማ በብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶች አልፎ ዛሬ ጠዋት 2፡30 ላይ በሚጀመረው የፓሪስ ኦሊምፒክ የ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ታሪካዊ ተሳትፎውን ያደርጋል::
ኢትዮጵያዊው ተራማጅ ኦሊምፒያን እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ዋጋ ከፍሏል:: ከሆቴል አስተናጋጅነት እስከ ጽዳትና የጉልበት ሠራተኝነት ሕይወት ውስጥ አልፏል:: ለሚገጥሙት የሕይወት ፈተናዎች ሸብረክ ሳይል በጠንካራ ሥራና በሰነቀው ትልቅ ህልም ግን ዛሬ በዓለም ትልቁ የስፖርት መድረክ ሀገሩን ወክሎ ለመፎካከር በቅቷል::
በኦሮሚያ ክልል ወንጪ የተወለደው አትሌት ምስጋና እንደ በርካቶቹ ኢትዮጵያውያን ኦሊምፒያኖች በግብርና ሥራ ከሚተዳደር ቤተሰብ ነው የተገኘው:: ቴክኖሎጂ ብዙም ካልተስፋፋበትና በቀላሉ መረጃዎችን መግኘት ከማይቻልበት ስፍራ ተነስቶ እዚህ መድረሱ ጥንካሬውን አጉልቶ ያሳየ ነው:: በተወለደበት አካባቢና በትምህርት ቤት ሩጫ በመሞከር ወደ ስፖርቱ የገባው አትሌት በጊዜው ትኩረት ሰጥቶ የሚመለከተው አልነበረም:: ከትውልድ ሥፍራው ወደ አዲስ አበባ ሲያቀና የልጅነት የሩጫ ፍቅሩ አልተለየውም:: አዲስ አበባ መጥቶ ግን ከስፖርትና ሥራ ጎን ለጎን ማስኬድ ከብዶት ያቋረጠውን ትምህርቱን ከሁለት ዓመት በኋላ ጀምሮ ከልምምዱ ጋር በማጣጣም አሁን የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን እየተከታተለ በኦሊምፒክ ይወዳደራል::
አትሌቱ የእርምጃ ተወዳዳሪ ከመሆኑ በፊት በ10 እና 5ሺ ሜትር የሩጫ ውድድሮች ሲሳተፍ የቆየ ቢሆንም በአንድ እንስት አሠልጣኝ ምክር የእርምጃ ተወዳዳሪነቱን አሃዱ ብሎ እንደጀመረ በተለያዩ አጋጣሚዎች ባደረጋቸው ቃለምልልሶች ተናግሯል:: የእርምጃን ስፖርት ቴክኒክ ያስተማረችውም ይችው መካሪው አሠልጣኙ ነበረች:: ያምሆኖ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብዙም ደፍረው ሲገቡበት በማይታየው የእርምጃ ስፖርት በክለብ ለመታቀፍ ነገሮች ቀላል አልነበሩም:: ከፌዴራል ማረሚያ ክለብ ጋር ለስምንት ወራት ያክል ልምምዱን ቢሠራም የመቀጠር እድሉን ማግኘት አልቻለም ነበር:: በዚህም ተስፋ ሳይቆርጥና ሌላ አማራጭ በመፈለግ፣ ባገኘው አጋጣሚ በአዲስ አበባ ክለቦች ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ወክሎ በመወዳደር በሶስተኝነት በማጠናቀቁ በክለቡ የመታቀፍ እድል አገኘ::
አትሌት ምስጋና ክለብ ካገኘ በኋላ በ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር በሀገርና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ስኬታማነቱን ደጋግሞ አስመስክሯል:: በአህጉር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ወክሎ መሳተፍ የጀመረውም ንግድ ባክን በተቀላቀለ የመጀመሪያ ዓመቱ ሲሆን፣ ብቃቱን በማሳደግ ውጤታማ አትሌት ሆኗል::
ኢትዮጵያን ወክሎ የመጀመርያ አህጉር አቀፍ ተሳትፎውን ባደረገበት የ2022ቱ የሞሪሺስ ሴንት ፒየሪ የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና አራተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል:: በካሜሮን ያውንዴ በተካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና እና በጋና አክራ በተካሄደው 13ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ ችሏል:: እአአ በ2023 የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና በ 10 ሺ ሜትር የእርምጃ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊም ሆኗል:: በወቅቱ ባስመዘገባቸው ድሎች በ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ከዓለም 76 ደረጃን መያዝም ችሎ ነበር:: ከወራት በፊት በቱርክ አንታላይ በተካሄዳው የዓለም 20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ውድድርም 10ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል::
በአንታላይ በተካሄደው የዓለም እርምጃ ቻምፒዮና 1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ ውድድሩን ያጠናቀቀ ቢሆንም ከውድድሩ ውጪ በሆነ አትሌት ተተክቶ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ መብቃት ችሏል:: ኢትዮጵያ 15ኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋን የምታደርግበት 33ኛ የፓሪስ ኦሊምፒክ ለዚህ አትሌት ሌላ የተለየ ደማቅ ታሪክ ነው::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም