የሱዳን መንግሥት ከፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ጋር ለመደራደር ተስማማ

የሱዳን መንግሥት በአሜሪካ መንግሥት በቀረበው የድርድር ጥያቄ መሠረት ከፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ጋር ለመደራደር ተስማምቷል።

በአሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ መሪነት በሲውዘርላንድ ጄኔቫ እንዲካሄድ ለቀረበው የድርድር ጥሪ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መንግሥት ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል።

አሜሪካ የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በፈረንጆቹ ነሐሴ 14 በስዊዘርላንድ የተኩስ አቁም ንግግር እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረቧን ተከትሎ፤ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ “በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና የሠብዓዊ ርዳታ ለተቸገሩ ሁሉ እንዲደርስ” በንግግሩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ወዲያው ማሳወቃቸው ይታወሳል።

በገብጽ፣ በጂቡቲ፣ በኬንያ፣ በሳኡዲ አረቢያ እና በሌሎች አካላት ሁለቱን ተፋላሚዎች ለማደራደር የተደረገው ሙከራ ውጤታማ ሳይሆን ዘልቋል።

የሀገሪቱ ጦር በሀገር ከጂነት ከፈረጀው የፈጥኖ ደራሽ ሃይል ጋር ለመደራደር ፈቃደኝነት አላሳየም። የጄኔቫው ጉባዔ ሁለቱን አካላት በአንድ ክፍል ውስጥ ለማገናኘት ለወራት ከተሞከሩ ሙከራዎች ቀዳሚው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ከፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ ነኝ ቢልም፤ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመሩት ጦር ከተቆጣጠራቸው ስፍራዎች እንዲለቅ እና ሌሎች አካባቢዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ውግያ እንዲያቆም ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።

በተጨማሪም በድርድሩ አጀንዳዎች ዙርያ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገር እንደሚፈልግ ገልጿል።

ሮይተርስ እንደዘገበው ሱዳን ካሏት 18 ክልሎች ስምንቱን መቆጣጠር የቻለው የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ የሀገሪቱ ጦር ያቀረበውን ቅድመ ሁኔታ የመቀበል እድሉ ዝቅተኛ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች ለመደራደር ያሳዩት ፈቃደኝነት አንድ ርምጃ ነው ብሏል።

በጄኔቫ የሚካሄደው ድርድር በአሜሪካ እና ሳኡዲ መሪነት የሚደረግ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት፣ ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በታዛቢነት እንደሚታደሙ ተገልጿል።

15 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት 10 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንዲፈናቁሉ እና 10 ሺህ ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል።

በተጨማሪም ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግድያዎች የተስፋፉ ሲሆን በተለይም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በምዕራብ ዳርፉር የብሔር ጥቃት ፈጽሟል የሚል ክስ ይቀርብበታል።

አሜሪካ በቅርቡ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ድሜዳሜ ላይ መድረሷን ማሳወቋ ይታወሳል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You