በቅርቡ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ በብዙዎች ዘንድ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል። መንግሥት ያካሄደውን አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ያወጣው ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘርፈ ሁሉን አቀፍ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በመግለጫው አስታውቋል።
ከእነዚህ መካከል የሀገሪቱን የዕድገት ደረጃ እና ከቀሪው ዓለም ጋር ያላትን እያደገ የመጣ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑ በዋነኛነት ተጠቅሷል። የጥቁር ገበያ መስፋፋትን የሚቀንስ፤ ከፍተኛ የዋጋ ንረትን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የሚያስችል፤ በከበሩ ማዕድናት የሚደረግ ሰፊ የኮንትሮባንድ ንግድን የሚያስቀር፤ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ከባንክ ሥርዓት ውጭ ከሀገር እንዳይሸሽ የሚያደርግ መሆኑም ተጠቁሟል። የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚያሳደግ መሆኑም ተጠቅሷል። በርግጥ ይህ ማሻሻያ እነዚህን ሁሉ ትሩፋቶች ይዟል ? ስንል በፕላንና ልማት ሚንስቴር የልማት እቅድና የመንግሥት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ሥራ ክፍል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከሆኑት ከአቶ በረከት ፍስሃፅዮንን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ዋና አላማ ምንድን ነው ?
አቶ በረከት፡- የአሁንን ማሻሻያ ለማየት ከዚህ በፊት የነበሩትንም የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች መለስ ብሎ መቃኘት ይጠበቃል። ከዚህ በፊት ቀደም ብለው የነበሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓቶች ከፍተኛ መዛባቶችንና ስብራቶች የነበሩባቸው ናቸው። በዚህም የተነሳ ኢኮኖሚው ያጋጠሙትን መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት በርካታ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ተግባራዊ ሲደረጉ ቆይተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአስር ዓመት የልማት እቅድና የመጀመሪያው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል። በዛ ውስጥ በዋነኝነት የተለዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች የዘርፍ ምርትና ምርታማነትን የሚመለከቱና የኢንቨስትመንት ከባቢያዊ ሁኔታን ማሻሻልን የሚመለከቱት ነበሩ።
በወቅቱም በቀዳሚነት ትኩረት ተሰጥቷቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከያዛቸው ጉዳዮች መካካል በፊሲካል ሪፎርም የመንግሥትን የእዳ ጫና መቀነስ አንደኛው ነው። የመንግሥት ገቢ አስተዳደር ውጤታማ ማድረግ፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት ማረጋገጥ፤ በገንዘብ ፖሊሲ ውስጥም ወደ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ሽግግር ማድረግ የሚሉት ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የውጭ ምንዛሬ ተመን ውጤታማ እንዲሆን በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ መዛባቶችን ማረም የሚባሉት ተጠቃሾች ናቸው።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እነዚህን ሰፊ ጉዳዮችና ብዙ ዘርፎችን ያካተተ ሲሆን፤ አብዛኞቹን መተግበር የተቻለ ሲሆን አመርቂ ውጤትም ተመዝግቦባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ በዋነኝነት በተለያዩ ምክንያቶች ያልተከናወነው የውጭ ምንዛሬ ተመንን የተመለከተው ጉዳይ ብቻ ነበር። በአንጻሩ ዋነኛ ማነቆዎችን ለመፍታት መከናወን የነበረበት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል ነበር።
በመሆኑም አንደኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ሲጠናቀቅ ተከናውነው ውጤታማ የሆኑትን አጠናክሮ ለመቀጠል ያልተከናወኑትን ለመሥራት ትልቅ ድርሻ ያለው ነው። በተጨማሪም በኢኮኖሚ ውስጥ ያሉ መዛባቶችን ለመፍታት መወሰድ ካለባቸው ማሻሻያዎች መካከል አንዱ ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ ያለው የአሠራር ክፍተት ነበር። በአጭሩ አሁን የተወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በድንገት የተከሰተ ሳይሆን ቀደም ብሎ ሲወሰዱ ከነበሩት ጋር የሚያያዝ እና በሁለተኛው ሀገር በቀል ሪፎርም ማሻሻያ ለመከወን ቀድሞ በእቅድ የተያዘም ነው።
በአጠቃላይም የአሁኑ ማሻሻያና ከዚህ በፊት የተከናወኑትም በኢትዮጵያ ዕድገትን ለማፋጠን፤ የዋጋ ንረትን ለማርገብ፤ የፊስካል አቅምን ለማሳደግ፤ የወጪ ንግድንና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትና የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያው ምን ምን ፋይዳዎችን ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል ?
አቶ በረከት፡– ማሻሻያው በርካታ ጠቀሜታዎችን የሚያመጣ ነው። ከእነዚህም ውስጥ አንኳር የሆኑትን ብናነሳ የመንግሥትን የእዳ ጫና ለማቃለል ይረዳል። በገበያ ውስጥ የውጪ ምንዛሬ ሥርጭትን ፍትሃዊና ውጤታማ ለሆኑ ዘርፎች ብቻ እንዲውሉ ለማድረግ ያግዛል። በእዚህም በኢኮኖሚው የተሻለ አስተዋጽኦ ያላቸው ዘርፎች የተሻለ የውጪ ምንዛሬ እንዲያገኙ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይጠቅማል። በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ አጠቃላይ የውጪ ምንዛሬ ዋጋን በማስተካከል የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን ያጎለብታል። ይህንንም ተከትሎ የወጪ ምርትን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ የወጪ ንግድ ገቢን ያሳድጋል። በአንጻሩ ከውጪ የሚገቡ ውጤታማ ያልሆኑ የፍጆታ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ያደርጋል። በዚህ ሰንሰለት ውስጥ የሚኖሩትን የኢኮኖሚ ተዋናዮች በሙሉ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ይሆናል።
ከዚህም ባለፈ ሪፎርሙ አጠቃላይ እንደመሆኑ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የማሳደግ አቅም ይኖረዋል። በሀገር ውስጥ አቅም ሊተኩ የሚችሉ ምርቶችን ለማምረትም ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሰፊ እድል የሚከፍት በመሆኑ ለበርካቶች የሥራ እድል የሚፈጠር ይሆናል። እንደ ሀገር ገበያንና ውድድርን መሠረት ያደረገ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲፈጠርም የሚጠቅም ይሆናል። ትክክለኛውን ዋጋ ይዞ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማረጋገጥ ከእቅም ጋር የተመጣጠነ የወጪና የገቢ ንግድ እንዲኖር ያደርጋል። ተወዳዳሪ መሆን መቻል ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን የሚጠቅም ይሆናል።
ይህም የንግድ ሚዛን ጉድለትን ለመፍታትና የክፍያ ሚዛንን ለማስተካከል ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በጥቅሉ በግሉ ዘርፍ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ነፃ ኢኮኖሚ ዋናው ማረጋገጫው በገበያ የተመሠረተ ዋጋ መኖር ነው። በገበያ ውስጥ የተለያዩ ዋጋዎች አሉ። የነገረ ምርት ገበያ፤ የሸቀጥ ገበያ፣ የውጪ ምንዛሬ ገበያ እና የፋይናንስ ዘርፍ ገበያ ተብለው ይለያሉ። በዚህ ሂደት ሁሉ ማሻሻያው ዋጋ በፍላጎትና አቅርቦት የሚወሰን ሆኖ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የመንግሥትን የእዳ ጫና እንደሚቀንስ አንስተዋል ይህ በምን መልኩ ሊሆን ይችላል ?
አቶ በረከት፡– የእዳ ጫና የሚባለው ከዚህ በፊት የነበሩትንና በቀጣይ ኢኮኖሚው የሚፈልጋቸውን የልማት ፋይናንስ ፍላጎት የሚያካትት ነው። በማሻሻያ ውስጥ እንደተቀመጠው የእዳ ሽግሽግ ማለትም እዳ በዘላቂነት ከመፍታት አንጻር የተደረጉ ስምምነቶች አሉ። ይህም እዳውን በማሸጋሸግ የሚከፈልበት ጊዜ እንዲዘገይ ያደርጋል። ይህ አሁን ያለውን ጫና የሚያረግብ ሲሆን፤ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ምርትና ምርታማነትን እንዲሁም ተወዳዳሪነትን በማሳደግ የወጪ ንግድን የሚያበረታታና የንግድ ሚዛኑን የሚያስተካክል ይሆናል። ይህም ኢኮኖሚውን በማሳደግ የመንግሥት ገቢን በመጨመር እዳ የመክፈል አቅም እንዲኖር ይረዳል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አበዳሪዎች ትክክለኛ ገበያ እንዳለ ካወቁ የሚያበድሩት ገንዘብ ሊመለስላቸው እንደሚችል ስለሚያምኑ ለሌሎች ጉዳዮች እና በተጨማሪነት ለልማት የሚውል ፋይናንስ ለማግኘትም የሚቻልበት እድልን የሚፈጠር ይሆናል። ይህ ሲባል ሁሌ በብድር እንኖራለን ማለት ግን አይደለም። የሚገኘውን ጥሪት በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል ብድር ለመክፈል መቻልና፤ ከዚህም አልፎ በመቆጠብም ሌሎች የልማት ተግባራትን በራስ አቅም ለማከናወን መደላድል ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፡- ማሻሻያው ወደ ጎረቤት ሀገሮች የሚደረግ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቀነስ፤ ላኪዎችና አስመጪዎች የሸቀጦችን ዋጋ ያለ አግባብ ከፍ ወይም ዝቅ እንዳያደርጉ የሚኖረው ጠቀሜታ እንዴት ይታያል።
አቶ በረከት፡– በገበያ ውስጥ አንዱ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር የውጪ ምንዛሬ ተመን ነው። የውጪ ምንዛሬ ተመን መወሰን ያለበት ደግሞ በመደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ከሆነ የውጪያዊ አካላት ጣልቃ ገብነት አለ ማለት ነው። ከዚህ ቀደም ከውጪ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ የነበሩት ሥርዓቶች አምራቾችን የሚያበረታቱ አልነበሩም። በዚህም የተነሳ የውጪ ምንዛሬን በቀጥታ ለማግኘት ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገራት በተለይም ወደ ጎረቤት ሀገራት አምራቾች በማውጣት የሚሸጡበት አካሄድ ነበር። በተጨማሪ ሲተገበር የነበረው የውጪ ምንዛሬ ሥርዓት ትክክለኛውን የገበያ የዋጋ ተመን የሚያመላክት ባለመሆኑ የተሻለ ለማግኘት አማራጭ የሚያማትሩትም በርካቶች ናቸው።
አሁን በተወሰደው ርምጃ በገበያ ውስጥ የሚኖረው የውጪ ምንዛሬ ተመን በራሱ በገበያው የሚወሰን በመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ይሆናል። በእዚህም የገንዘብ ምጣኔው ተመጣጣኝ የሆነና ተወዳዳሪነትን የሚያንጸባርቅ መሆን ይችላል። ይህም አምራቾች ያመረቷቸውን የማዕድንም ሆነ ሌሎች ምርቶች የተለየ ጥቅም ስለማያገኙ በሀገር ውስጥ ገበያ ለመሸጥ ይበረታታሉ።
እስካሁን በነበረው ልምድ በውጭ ምንዛሪ የሚካሄድ ኢ-መደበኛ ገበያ እየተስፋፋ በመምጣቱ አብዛኛው የንግድ ማህበረሰብና የሀዋላ ተገልጋዮች በአብዛኛው በጥቁር ገበያ ሲገዙና ሲሸጡ ይስተዋላል። አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ ይህንን የገበያ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባና እንዲህ ዓይነቱን ኢ-መደበኛ አሠራር በማስቀረት ተወዳዳሪ፣ ግልጽና አመቺ ወደሆነ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መግባትን የሚያበረታታ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በማሻሻያው ለኑሮ ውድነት መደጎሚያ መንግሥት ከውጭ የሚገቡ የአንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በጊዜያዊነት ለመደጎም ወስኗል። ነገር ግን ማሻሻያው ህብረተሰቡን በዘላቂነት ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ምን ጥቅም ይኖራቸዋል?
አቶ በረከት፡- በመሠረቱ ማሻሻያው ሲደረግ ጥልቅ በመሆኑ ተጽእኖ ይደርስባቸዋል ተብለው የታሰቡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመታደግ ብዙ ተሰርቷል። የድርድሩም አካል ሆኖ ዝግጅት ተደርጎበታል። በዚህም ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞችን ተደራሽ የማድረግ፤ መሠረታዊ የሆኑ እንደ ነዳጅ፤ ማዳበሪያ፤ ዘይት መድኃኒት ያሉ ምርቶች ድጎማ የሚደረግባቸው ይሆናል። ለእዚህ የሚሆን በቂ ፋይናንስም የተዘጋጀ ሲሆን፤ በተጨማሪ መንግሥት የገቢ አቅምን በማሳደግ ተጽእኖ የሚደርስባቸውን ዜጎች ለመታደግ በየወቅቱ የሚሰራቸው በርካታ ሥራዎች ይኖራሉ። ይህም ማሻሻያውን ተከትሎ በገበያ ውስጥ የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የሚያስችል ይሆናል።
ይህም ሆኖ እንዲህ ዓይነት ትልልቅ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ሲወሰዱ በገበያ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። ለእዚህም በመንግሥት በኩል ማህበረሰቡ ለችግር እንዳይጋለጥ መሠረታዊ በሚባሉ ሸቀጦች ላይ የሚወሰዱ ተከታታይነት ያላቸው ቁጥጥሮችና ርምጃዎችም ይኖራሉ። በተለይም ከጉዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የማይኖራቸው የዋጋ ጭማሪዎች ላይ ጥብቅ ክትትል የሚደረግ ይሆናል።
ማሻሻያው የተደረገው እንደ ከዚህ ቀደሙ የውጪ ምንዛሬ መጠንን ማዳከም ሳይሆን፤ ገበያን መሠረት ያደረገ የውጪ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት መዘርጋት ነው። ይህም ማለት መንግሥት ዋጋ የሚተምንበት ሳይሆን ባንኮችና ደንበኞች በሚኖራቸው ግንኙነት የሚፈጠር የዋጋ ተመን ይኖራል ማለት ነው። ይህም ከነበረው ከተለመደው አካሄድ የተለየ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። በዚህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ጭማሪ ሊያሳዩ ይችላሉ።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች ምንነት ተለይቶ መታየት አለበት። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከከተሞች ውጭ የሚኖር ነው። የፍጆታው ዓይነትም በቀዳሚነት ራሱ የሚያመርታቸው ሲሆኑ፤ አንዳንድ በግብዓትነት የሚጠቀምባቸውም በስትራቴጂ የተያዙት ናቸው። በመሆኑም ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቀው ጭማሪ አብዛኛውን ዜጋ ለተጋነነ ችግር የሚያጋልጥ አይሆንም። ከዚህም በተጨማሪ አብዛኛው ሕዝብ እንደ ትምህርት ጤና ያሉ መሠረታዊ ነገሮችን በነፃ ተጠቃሚ መሆኑ ማሻሻያውን ተከትሎ ለሚፈጠር ለውጥ የመጋለጥ እድሉም ዝቅተኛ ነው። ይህም ሆኖ አብዛኛውን ሕዝብ የሚነኩ ጉዳዮችና ያንን ተከትሎ የሚከሰቱ ነገሮችን ለመቆጣጠር ዝግጅት ተደርጓል። በአንጻሩ ይፈጠራል ተብሎ የተሰጋው የአንዳንድ ምርቶች ዋጋ መጨመር የሀገር ውስጥ አምራቾችን የሚያበረታታ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች በማስቀጠል ረገድ የሚኖረው ጠቀሜታ ምንድን ነው?
አቶ በረከት፡– ከዚህ ቀደም ኢኮኖሚውን አንቀው የያዙ የውጪ ምንዛሬ አሠራር ሥርዓት ነበር። ይህንን አዲሱ ማሻሻያ በመሻገር ውጤታማ ለሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለሚኮንባቸው ዘርፎች ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል። ይህም ለሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። እዚህ ላይ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ሲገቡ ይዘዋቸው የሚመጡ እድሎችና መልካም አጋጣሚዎችም እንዳሉ መታወቅ አለበት። ኢንቨስትመንቱ አጠቃለይ ይነቃቃል። የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ውጤቶችን በግብዓትነት የሚጠቀሙም ይኖራሉ። ያለውን አቅም በአግባቡ በመጠቀም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ሂደትን የሚያበረታታም ይሆናል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ውጤታማ የሆኑ ባለ ሀብቶች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን፤ ከእነዚህ በፊትም ውጤታማ የሆነው አሠራር ውስጥ ያልነበሩ የሚገጥማቸው ችግር ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የሀገሪቱ የመሠረተ ልማትና ማህበራዊ ኢንቨስትመንት ጥራቱና ውጤታማነትን እንደጠበቀ እየተስተካከለ የሚቀጥል መሆኑ ነው።
በዚህ ሂደት የመንግሥት አቅም እየተጠናከረ ይመጣል። ይህንንም ተከትሎ የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የመንግሥት የማህበራዊና የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ሥራዎች የሚቀጥሉ ይሆናል። ለዚህም በሪፎርሙ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የሚደረግ ከፍተኛ መጠን የሚኖረው ፋይናንስ ይኖራል። ይህም አሁን ቃል ከተገባው ባለፈ ይህንን ስምምነት እየጠበቁ ካሉ ሌሎች አካላት የሚገኝ ነው። በመንግሥት በኩልም ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ሌሎች ምንጮች የሚያገኛቸውን ገቢዎች ለማሳደግ የሚሰሩ ጠንካራ ሥራዎች ይኖራሉ። በተጨማሪ የመንግሥት ወጪ በአግባቡ ተመርቶ ውጤታማ እንዲሆን በመንግሥት ወጪ አስተዳደር ላይም የሚወሰዱ ተከታታይነት ያላቸው ርምጃዎችም ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ማሻሻያ የብሔራዊ ባንክን ሚና የሚገዳደር አይሆንም ?
አቶ በረከት፡– የገበያው ዋጋ በባንኮችና በደንበኞች የሚወሰን ሲሆን የብሔራዊ ባንክ ሚና የሚኖረው ዋጋን የማረጋጋት ተግባር ብቻ ነው። ይህም የሚሆነው አንደኛ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ አለመረጋጋቶች ቢከሰቱ ካለው መጠባበቂያ በቂ የውጪ ምንዛሬ ወደ ገበያው በማስገባት እጥረቱን የሚታደግ ይሆናል። በተጨማሪ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖሩ መጋጋልና መቀዛቀዞችን ለማስተካከል በተዘዋዋሪ የገንዘብ ፖለሲ አማካይነት የሚወስዳቸው የተለያዩ ርምጃዎችም ይኖራሉ። እነዚህም የተረጋጋ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ በመፍጠር ትክክለኛ የዋጋ ተመን እንዲኖር የሚያስችሉ ይሆናል።
እንደ አጠቃላይ በውጭ ምንዛሪ ተመን ወይም በአገልግሎት ክፍያ ረገድ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም በጥብቅ የተከለከለ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ ዘዴዎችን፣ በተለይም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ በመጠቀምና እንደ አስፈላጊነቱ ከፋይናንስ ደህንነትና ሌሎች ሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር እነዚህን የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች ያከናውናል። ሕግን በሚተላለፉት ላይም አስተማሪ ርምጃ የሚወስድ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ማሻሻያው በውጭ አካላት ተጽእኖ የተደረገ ስለመሆኑ ይነገራል። ለዚህም ማሻሻያውን ተከትሎ ከአንዳንድ አበዳሪዎች እየተደረጉ ያሉ ድጋፍና ማበረታቻዎች ማሳያ ናቸው የሚል አሉ። ይህን እንዴት ያዩታል ? የተደረገውስ ማሻሻያ ወቅቱን የጠበቀ ነው?
አቶ በረከት፡– ሪፎርሙ የመጣው አጠቃላይ ሁሉን አቀፍ ሆኖ ነው። በሀገር በቀል ማሻሻያ «አንድ» ላይ የተጀመሩ በርካታ ሥራዎች ነበሩ። በሀገር በቀል ማሻሻያ «ሁለት» በእቅድ የተቀመጡ አሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢኮኖሚው ያለበትን ውስንነት ለመፍታት መወሰድ ካለባቸው ርምጃዎች መካከል አንዱ ይኸው ማሻሻያ ነው። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ስትጠቀምበት የነበረው የውጪ ምንዛሬ ዓይነት ሥርዓት ያላቸው ሀገራት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። በዓለም ላይ በአብዛኛው እየተተገበረ ያለውና ውጤታማ የሆነው አሁን በሀገራችን ወደ ትግበራ የገባው በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጪ ምንዛሬ ሥርዓት ነው። በመሆኑም ይህ ርምጃ ዘግይቷል ሊባል ይችላል፤ እንጂ ጊዜው አይደለም ለማለት የሚያስችል ሁኔታ የለም።
የውጪ ተጽእኖን በተመለከተም የተነሳው ሃሳብ ስህተት ነው። በዚህ ረገድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አለ። ድርድሩ ረጅም ጊዜ የወሰደ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው የዜጎችንና የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ ብዙ መፈተሽ የነበረባቸው ጉዳዮች ስለነበሩ እነሱን ለማጽዳት ነው። ለምሳሌ የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ አሁንም ወደ ውጪ የሚሄድ የካፒታል አካውንት በነበረበት እንዲቀጥል ተደርጓል። ይህ የተደረገው ከማሻሻያው ጋር ተያይዞ የውጪ ምንዛሬ ልውውጥ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽእኖ ከግምት በማስገባት የሀገር ጥቅምን በማስቀደም ነው።
በርግጥ በሪፎርሙ የተካተቱት ጉዳዮች ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ያልተለመዱ ናቸው። ይህም ሆኖ ሊደርሱ የሚችሉ ተጽእኖዎችን ለመፍታት በሚያስችል ሁኔታ የተዘጋጁ ናቸው። መንግሥት ከለውጡ በፊት ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶች ገጥመውት እንደነበር ይታወሳል። አሁን ላይ ግን በተለይም የእዳ ጫናውን በተወሰነ መልኩ ማቅለል ቢቻልም፤ አሁንም ያለው ቀላል የሚባል አይደለም። እነዚህ ተግዳሮቶች ለመሻገር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ የሚጠይቅ ይሆናል። ድርድሩ በጥንቃቄ በከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲከናወን የተደረገው ለዚህም ነው።
ባጠቃላይም ድርድሩ የሀገራችንን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ የተከናወነ ነው ለማለት ይቻላል። በውጤቱም በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ ስብራቶችን ለመጠገን የሚያስችል ይሆናል። በተጨማሪም የአሁኑ ጅምር በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠልም የሚያግዝ ይሆናል። በዚህ ረገድ ኢኮኖሚው እያደገና መዋቅራዊ ችግሮች እየተፈቱ ሲሄዱ፤ ተሳትፏችንም የሚጨምር በመሆኑ የመደራደር አቅማችንም ይጎለብታል።
አዲስ ዘመን፡- የተደረገው ማሻሻያ የገንዘብን አቅም የማዳከም ርምጃ ነው ይባላል። ይህንን እንዴት ያዩታል?
አቶ በረከት፡– ገንዘብን የማዳከም ርምጃ የሚባለው በዋነኝነት መንግሥት ከነበረው የውጪ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት የተለየ ክፍያ የሀገር ውስጥ ገንዘብን በሚያዳክም መልክ የሚወስንበት ሥርዓት ሲዘረጋ ነው። ማለትም በገበያ ውስጥ አቅርቦትንና ፍላጎትን መሠረት ሳያደርግ መወሰን ነው። አሁን የተደረገው በገበያ ላይ የተመሠረተ የዋጋ ተመን ማሻሻያ ሥርዓት ግን መንግሥት ገበያውን ክፍት በማድረግ የመቆጣጠር ሥራ ብቻ እንዲያከናውን የሚያደርገው ይሆናል። ተመኑ የሚወሰነው ግን በገበያ ውስጥ ባለው የውጪ ምንዛሬ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል በሚኖር ትስስር ይሆናል ማለት ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው በዚህ ሂደት ብሔራዊ ባንክ የሚኖረው የማረጋጋት ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት በቀጥታ ገብቶ የሚያስቀምጠው ተመን አይኖርም ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማሻሻያውን ተከትሎ በህብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠሩ ግርታዎችና መደናገሮች ለማስተካከል ምን ሊሰራ ታስቧል።
አቶ በረከት፡- ይመጣሉ የተባሉት ተጽእኖዎች በአንዳንድ አካላት እንደሚገለጹት የተጋነኑ አይደሉም። ሊከሰቱ የሚችሉት ጉዳዮች ቀድመው የተለዩና ቅድመ ዝግጅትም የተደረገባቸው ናቸው። የሚፈጠሩትን ተጽእኖዎች ለመከላከልም የሚወሰዱ ተከታታይ ርምጃዎች ይኖራሉ። በርግጥ ማሻሻያው ጥልቀት ያለውና መጠነ ሰፊ ጎዳዮችን የሚነካካም ነው። በአንጻሩ በርካታ መልካም እድሎችንም የያዘ ነው። በመሆኑም ስለማሻሻያው ለማወቅ የነበሩትንና ያሉትን በቀጣይም ሊከሰቱ የሚችሉትን ነገሮች በጥልቀት መረዳት ይጠበቃል። በመሆኑም ዜጎች መረጃዎችን ከተገቢው ምንጭ ይህን ሪፎርም ከሚያስፈጽሙ አካላት ብቻ ማግኘት ወይም ከእነሱ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ሀገርንና ሕዝብን በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ በዚህ ረገድ መንግሥት የሚወስዳቸውንም ሕግ የማስከበር ርምጃዎች ዜጎች በሚችሉት ሁሉ ሊደግፉት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ጊዜ እናመሰግናለን።
አቶ በረከት፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም