ሩሲያ አብዛኞቹን የጦር መርከቦቿን ያካተተ ልምምድ ጀመረች

ሩሲያ አብዛኞቹን የጦር መርከቦቿን ያካተተ ልምምድ ጀመረች።

ሩሲያ ባህር ኃይል አብዛኞቹን የጦር መርከቦቿን በመጠቀም በአርክቲክ፣ በፓሲፊክ እንዲሁም በባልቲክ እና በካስፒያን ባህሮች ልምምድ ማድረግ መጀመሯን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ትናንትና አስታውቋል።

ወታደራዊ ተንታኞች ሩሲያ በዓለም በጠንካራ የባህር ኃይል ከአሜሪካ እና ከቻይና ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጧታል። ሩሲያ በቂ የሚባል ኑክሌር ተሸካሚ ባህር ሰርጓጅ መርከቦችም ባለቤት ነች።

20 ሺ ወታደሮች እና 300 መርከቦችን የሚያካትተው የሩሲያ ልምምድ የባህር ኃይሉን ዝግጁነት እና አቅም በሁሉም ደረጃ ለመለካት እንደሚጠቅም ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።

ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ልምምዱ የጸረ-አውሮፕላን ሚሳይል፣ ከባድ መሣሪያ፣ የጸረ-ባህር ሰርጓጅ መርከብ መሣሪያ አጠቃቀም ጨምሮ 300 የውጊያ ልምምዶችን ያካትታል።

“የሩሲያ ባህር ኃይል የተለያዩ አደረጃጀቶች በሰሜን የልምምድ ቀጣናዎች፣ በፓሲፊክ እና በባልቲክ እንዲሁም በካስፒያን ባህር በታቀደው መሠረት ልምምድ ማካሄድ ጀምረዋል” ብሏል ሚኒስቴሩ።

ሚኒስቴሩ እንደገለጸው በዚህ ልምምድ 300 መርከቦች እና ጀልባዎች፣ ሰርጓጆች እና ደጋፊ መርከቦች፣ 50 የጦር ጀቶች እና ከ200 በላይ ወታደራዊ ቡድኖች እና ልዩ መሣሪያዎች በልምምዱ ይካተታሉ።

በጥቁር ባህር ያለው የሩሲያ የባህር ኃይል ጦር ፕሬዚደንት ፑቲን በሺዎች የሚቆጠር ጦር ወደ ዩክሬን ከላኩ ጀምሮ በልምምዶች ላይ ተሳትፎ አያውቅም።

ፕሬዚደንት ፑቲን የሩሲያ የባህር ኃይል ቀን ባለፈው ቅዳሜ እለት በተከበረበት ወቅት ዋሸንግተን ወደ ጀርመን የረጅም ርቀት ሚሳይል የምትልክ ከሆነ ሩሲያም ምዕራባውያንን ለመምታት በሚያስችል ርቀት ላይ ሚሳይል እንደምታስቀምጥ አሜሪካን አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ያለችውን ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ ብቻዋን እና ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ብዙ ወታደራዊ ልምምዶችን አካሂዳለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You