የሰው ልጅ አብዛኛውን ጊዜ በአካባቢው በሚመለከተው ነገር ማንነቱ እንደሚቀረጽ የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ። እናም ይህ የምናየው ነገር ቀስ በቀስ በአዕምሯችን ይቀረጻል። በጊዜ ሂደት ደግሞ እራሳችን የምንከውነው ተግባር እየሆነ ይመጣል።
ለዚህም ይመስላል አብዛኞቻችን ያሳደገን ማህበረሰብ ነጸብራቅ ነን የሚባለው። በቀጣይ ደግሞ እኛን ተክተው ለሚፈጠሩ ማህበረሰቦች እርሾ እንሆናለን። እንደዚህ እየሆነ የትውልድ ቅብብሎሽ ይቀጥላል።
ቢጠቅምም ባይጠቅም ደግነት ይሻላል ከክፋት እንዳለው ገጣሚ፤ ዛሬ በበጎነት በምንሰራው እያንዳንዷ ተግባር ለሌሎች መስታወት እየሆን ነው የምናልፈው።
የዛሬዋ ባለታሪካችን ወደ በጎ ሥራ እንድትገባ ምክንያት የሆናት ያሳደጋት ማህበረሰብ ነው። በአደገችበት አካባቢ አብሮ መብላትን፣ መረዳዳትን ስትመለከት በማደጓ በጎ ተግባርን ይዛው በማደግ ዛሬ ላይ የቀን ተቀን ተግባሯ አድርጋዋለች።
እራሷን ከማሳተፍ አልፋ ሌሎች እንዲሳተፉ በመጋበዝ በበጎ አድራጎት ሥራ በርካቶችን እየጠቀመች ትገኛለች።
የዛሬዋ ባለታሪካችን ወይዘሮ አፍራ አሕመድ ይባላሉ፤ ትውልድና እድገታቸው በድሬ ከተማ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት እዛው ድሬዳዋ ከተማ ነው።
‹‹የተወለድኩት በ1972 ዓ.ም ነው። ትምህርቴን እስከ 12ኛ ክፍል እዛው ድሬ ከተማ ነበር የተማርኩት። በትምህርቴ ጥሩ የምባል ዓይነት ተማሪ ብሆንም፣ እኛ አካባቢ ሴት ልጅ ቶሎ ስለምትዳር ተዳርኩኝ ›› ይላሉ።
በትዳርም ስድስት ልጆችን አፍርተዋል። ትምህርታቸውን በኮምፒውተር ሳይንስ በዲፕሎማ በማጠናቀቅ፤ ለሰባት ዓመት በሥራ ዓለም ቆይተዋል። አሁን ልጆቼ ቦታ ስለያዙ ሥራ አቁሜያለሁ የሚሉት ወይዘሮ አፍራ የራሳቸውን የግል ሥራ ለመሥራት እንደሚያቅዱ ይገልጻሉ።
ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥተው መኖር ከጀመሩ በኋላ በሚኖሩበት አካባቢ የተቸገሩትን በመርዳት የሚደርሳቸው አልነበርም። ከዛን እንደ ወረዳ በሚደረጉ የበጎ ተግባራት ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ለ14 ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እያገለገሉ ይገኛል። የበጎ አድራጎት ሥራ ከልጅነት ጀምሮ አብሯቸው ያደገ ተግባር እንደሆነም ይናገራሉ።
በልጅነታቸው በድሬዳዋ ከተማ በሚኖሩበት ወቅት በእድሜ ጠና ያሉ አሮጊቶች ሲታመሙ ሄደው በማስታመም ገላቸውን በማጠብ ይረዱ ነበር።
ይህ ባህሪያቸው ትዳር መስርተው አዲስ አበባ ከመጡም በኋላ አብሯቸው ቀጠለ። በአካባቢያቸው ሰው በሚታመምበት ወቅት፣ በማስታመም፣ ሴቶች ምጥ ሲይዛቸው ያላቸውን በማልበስ ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ድጋፍ ያደርጉ ነበር።
የወይዘሮ አፍራ እርዳታ በዚህ ብቻ አልተገደበም። ደብተር ለመግዛት አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች ደብተር በመግዛት፣ ለደብተር መያዣ ቦርሳ በመግዛት እና ከልጆቻቸው የተረፉ ልብሶች በመስጠት ይደግፉ ነበር። እንደዚህ ዓይነት ድጋፎች እያደረጉ በመጡ ቁጥር ልባቸው ለበጎ አድራጎት ሥራ ይበልጥ እየተሳበ መጣ።
ሰውን መርዳት በጣም ደስ የሚለኝና የተወለድኩበት ነው የሚሉት ወይዘሮ አፍራ፤ ይህን ሰው የመርዳት ተግባሬን ይፋ በሆነ መንገድ ለመሥራት በማሰብ ወረዳ ሄጄ ተመዘገብኩ ሲሉም ያስረዳሉ።
ሰውን መርዳት ቅንነት ነው፤ ሁለት ያለው አንዱን እንዲያካፍል ቁራንም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ስለዚህ ማንም ምንም ሳይገድበው ሌሎችን መርዳት አለበት ይላሉ።
ድሬዳዋ እያለሁ ብቻችንን አንበላም በማለት ትውስታቸውን ይናገራሉ። ‹‹እናም ይህ ልማድ ከውስጤ ሊወጣ አልቻለም። አዲስ አበባ ከመጣሁ አሁን 24 ዓመቴ ነው። የበጎ ፈቃድ ሥራ አብሮኝ ያደገ በመሆኑ አዲስ አበባም መጥቼ በዚሁ ተግባር ቀጠልኩ›› ይላሉ ወይዘሮ አፍራ።
በወቅቱ ወረዳ ላይ ተመዝግበው የበጎ አድራጎት ሥራ በመሥራት የሚያስተባብሩ ሴቶች ስለነበሩ ወይዘሮ አፍራ ከእነሱ ጋር ትሳተፍ ስለነበር እየተግባቡ መጡ። ከዛ በኋላ በበጎ ፈቃድ ሥራ በስፋት መሳተፍ ጀመሩ።
ወይዘሮ አፍራ በክፍለ ከተማው የቤት እጦት ላለባቸው ሰዎች ባለሀብቱን በማስተባበር እና ያላቸውን በማዋጣት የቤት እድሳት ሥራ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በወረዳ ደረጃ ይሳተፋሉ።
በቤት እጦት የሚቸገሩ አዲስ አበባ ላይ በጣም በርካታ ናቸው። ክረምት ሲመጣ ጎርፍ የሚገባባቸው፣ የሚያፈስ ቤት ያላቸው እና አቅመ ደካሞች ብዙ መሆናቸውን በመግለጽ ይህን በማየት ነው ወደዚህ ተግባር የገባሁት ይላሉ።
‹‹የቤት እድሳት በሚደረግበት ወቅት በማፍረስ ሥራ ላይ እሳተፋለሁ፤ ብሎኬት በማቀበልም እረዳለሁ። አንድ ሰው ቅንነት ከውስጡ ካለ፤ አንድ ነገር ለማድረግ የሚከብደው ነገር የለም ›› ይላሉ።
ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚያነሱት የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት ነው። ሥራው ሲጀመር አንዳንድ ሰዎች “ጀምረው ጭቃ አድርገው ሊተውቱ” በማለት አውርተው ነበር። ነገር ግን በጥቂት ጊዚያት ሊጠናቀቅ መቻሉ ለሁላችንም ትምህርት የሚሆን ነው። ሲሉ አንድ ነገር ከታሰበበት እንደማይከብድ ያስረዳሉ።
ለእናቶች የጡት ጫፍ ካንሰር በሽታ ምርመራ፣ ሕክምና ግንዛቤ በሚሰጥበት ወቅት በስፋት ተሳትፎ በማድረግ በርካታ ሴቶች፤ በራሳቸው ፈቃድ እንዲመረመሩና ግንዛቤ እንዲያገኙ አድርጋለች።
‹‹የበጎ አድራጎት ሥራ በመሥራቴ ተቆጥሮ የሚሰጠኝ ገንዘብ ባይኖርም፤ ማህበረሰቡን በመርዳቴ፤ በተለይም ሴቶች ከቤት ወጥተው እራሳቸው እንዲችሉ እና በዐሻራ ከመፈረም እንዲላቀቁ በማደረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ›› ይላሉ።
ሴቶችን ለመርዳት ከሚያደርጉት ጥረት አንዱ ትምህርት ያላገኙ ሴቶች መሠረት ትምህርት እንዲያገኙ ቅስቀሳ ማድረግም ይገኝበታል። ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሴቶች በማስተባበር በሥራ እንዲሳተፉ እና የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጠሩ ጥረት ማድረጋቸውም አልቀረም።
የበጎ አድራጎት ተግባራቸው በከተማው እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ሥራም ቀጥሏል። ወይዘሮ አፍራ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን፤ በኮሪደር ልማት ሥራ ላይ የሚሰሩ ሠራተኞችን እራት የማብላት ተግባርም ያከናውናሉ።
ይህ ሃሳብ እንዴት እንደመጣላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ አፍራ፤ አንድ ምሽት ዝም ብዬ አየር ለመቀበል ወጣ እንዳልኩ መንገድ ላይ የሚሰሩት ውሃ ሲያጠጡ ተመለከትኩኝ። እናም እነዚህ ሰዎች ምግብ ማብላት እንዳለብን ሃሳብ መጣልኝ። ከዛን ባለሀብቶችንም በማስተባበር እራት አበላን ይላሉ።
መሸት ሲል በመውጣት ከፒያሳ ሜክሲኮ ከሜክሲኮ እስከ ወሎ ሰፈር የሚሰሩትን በጥሩ ሁኔታ ማብላት ችለናል። እስካሁን ሁለት ጊዜ ማብላታቸውን በመግለጽ፤ ለመቀጠል እቅድ እንዳላቸው ይገልጻሉ።
አፍራና ጓደኞቿ ይህ ተግባር የሰሩት በራሳቸው ተነሳሽነት ነው። በዚህም ሄደው እነዚህን ሠራተኞች በመጠየቃቸው በጣም ደስተኛ ናቸው። ክፍለ ከተማውም በሰሩት ሥራ ምስጋና ተቸሯቸዋል።
በአረንጓዴ ልማት ችግኝ በመትከል፣ በየሶስት ወር ደም በመለገስ እና በሳምንት አንዴ አካባቢያቸውን በማጽዳት ሥራም ይሳተፋሉ።
ወይዘሮ አፍራ የልጆች እናት እንደመሆናቸው ልጅ መንከባከብ በጎ ሥራን ወጥቶ ከመሥራት አላገዳቸውም። ለልጆቻቸው ሞግዚት ብዙ ጊዜ የሚቀጥሩ ሲሆን፤ የባለቤታቸው እገዛ እና ማበረታቻም አልተለያቸውም።
‹‹ባለቤቴ ጥሩ ሥራ ነው በርቺ ይለኛል። በዓል በሚሆንበት ወቅት ደግሞ ዘይት፣ ዱቄት እና ሌሎች ነገሮችን በመያዝ ማእድ እናጋራለን›› ሲሉ ይገልጻሉ።
‹‹ለበጎ አድራጎት ሥራ ስወጣ ልጆቼ ሲመለከቱ በጣም ደስ ይላቸዋል። በተለይ አንድ የሕክምና ትምህርት የምትከታተል ልጅ አለችኝ እሷ “አንቺ ዛሬ የምትሰሪው ሥራ ለእኛ ነው የሚተርፈው፤ በዚህ ሥራሽ እኛ የትም አንወድቅም” ትለኛለች። ወደፊት ልጆቼ የእኔን አርአያ ይከተላሉ የሚል ተስፋ አለኝ።›› የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።
ወይዘሮ አፍራ የሕዳሴ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ለ13 ዓመታት ቦንድ ገዝተዋል። እሳቸው ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸውንም በዚህ ተግባር አሳትፈዋል።
ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ልጄ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወሰዶ ከፍተኛ ውጤት ስላመጣ ክፍለ ከተማ ጠርቶ ሽልማት ሰጠው። ሽልማቱን ተቀብለን ስንመለስ “ምን ላድርገው ብሩን? ቦንድ ልግዛበት?” ብሎ ጠየቀኝ። እንደውም ጥሩ ነገር ስለው እሱም ገዛ። ይህን ልምድ ልጆቼም ተጋርተውኛል ሲሉ ያስረዳሉ።
‹‹አጠገብ ላይ ሰው ተርቦ በር ዘግቶ ለብቻ መብላት ይከብዳል። አንዳንዴ እኮ ወጥ ሲሰራ ሽታው ጎረቤት እንዳይረብሽ በመሥጋት፣ አጣፍጦ ለመሥራት ይከብዳል። ነገር ግን እንደዚህ አካፍሎ መብላት ካለ የሥነ ልቦና ተፅእኖ አይኖርም። እናም ይህን ተግባር በማድረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ›› ይላሉ።
ወ/ሮ አፍራ እንደሚሉት ሥራዎች የሚሰጡት ከወረዳው በሚወርደው አቅጣጫ መሠረት ነው። በበርካታ ሥራዎች እንደመሳተፋቸው ለእያንዳንዱ አዲስ ለሚመጡ አቅጣጫዎች ፕሮግራም በመያዝ ሁሉንም ለማስኬድ ይጥራሉ። ቤት ማሳደስ ፣ መሠረተ ትምህርት ላይ፣ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ እና ሌሎች ነገሮችን ተራ በማስያዝ በቅድመ ያከናውናሉ።
የበጎ ፈቃድ ሥራ የህሊና እርካታ ከማስገኘቱም በላይ የበርካቶችንም ችግር እየቀረፈ የሚገኝ ሰናይ ተግባር ነው የሚሉት ወ/ሮ አፍራ በአንድ የምንኖር ሰዎች ያለንን አብረን ተካፍለን ብንበላ ወደ ጎዳና ወጥቶ የሚለምን ሰው ባልኖረ ነበር ሲሉ ያስረዳሉ።
እንደ ሀገር ሆነ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ምንም ነገር ሳይፈሩ እንደዚህ ዓይነት በጎ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ሊሰሩ ይገባል። ሴቶች በመሆናችንም ምንም የሚገድበን የለም ሲሉ ለሌሎች ሴት እህቶቻቸው መልዕክት ያስተላልፋሉ።
በቀጣይም አሁን የጀመሩትን የበገ አድራጎት ሥራ በማጠናከር፤ ጎዳና የወደቁ እናቶችና አባቶች ለመርዳት ሃሳብ አላቸው። በተጨማሪም የሕፃናት መዋያ በመክፈት ልጄን የት ላድርግ? እያሉ ለሚጨነቁ እናቶች መፍትሔ የመሆን ምኞች አላቸው።
የሕፃናት መዋያ ከፍታ በቅናሽ ዋጋ የምትሰራ ሴት አለች። እኔም በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ሕፃናት የሚውሉበትን ቦታ በማዘጋጀትና በመሥራት ፤ እናቶች ልጆቻቸውን ያለ ስጋት ትተው እንዲሄዱ እና ቀሪ ሥራቸውን እንዲሰሩ ማድረግ እፈልጋለሁ ሲሉ የወደፊት ዕቅዳቸውን ይገልጻሉ።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2016 ዓ.ም