በጎዳና ላይ አድጓል፤ ህይወቱን በጎዳና መርቷል። ዛሬ ለተመለከተው ጎዳና መተኛት ሳይሆን በጎዳና ላይ በእግሩ ተመላልሷል ለማለት አያስደፍርም። ተክለ ሰውነቱ፣ ግርማ ሞገሱ ከቢሮው ወንበር ላይ ተቀምጦ ላየው ያስደነግጣል። በምቾትና ድሎት ተቀማጥሎ ያደገ ይመስላል። መሆንና መምሰል ይለያያልና እሱም መሰለ እንጂ አልሆነም፤ እጅግ አስከፊና አሳዛኝ የህይወት ፈተናዎችን አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል የ”ህይወት እንዲህ ናት“ አምድ እንግዳችን የአምባሳደር ሆቴል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ተገኝ።
ልጅነት
ህጻኑ ወንድወሰን ጥር 15 ቀን 1965ዓ.ም ነበር ይህችን ምድር የተቀላቀለው። እትብቱ የተቀበረውም በቀድሞ ኢሉአባቦራ ክፍለሀገር ከመቱ ራቅ ብላ በምትገኘው የገጠር ከተማ አልጌ ውስጥ ነው። ይህቺ ቀን ለእናቱ ለወይዘሮ ልኬለሽ ደገፉ እና ለአባቱ ሃምሳለቃ ተገኝ በለጠ ልዩ ነበረች። ምክንያቱም የበኩር ልጅ አግኝተዋልና። እናት የቤት እመቤት፤ አባት የመንግስት ሰራተኛ ሆነው ቤተሰቡን ይመራሉ። ሆኖም ግን በአባቱ መሞት ምክንያት የቤቱ ገቢ ተቋረጠ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እናት ቤተሰቡን ለማኖር ሥራዎችን ለመስራት ተገደዱ።
ጠላ እየጠመቁና አረቄ እያወጡ ኑሮን ለማሸነፍ ይሯሯጡ ጀመር። ወንድወሰን በቤት ውስጥ ካሉት በእድሜ ከፍ ያለ በመሆኑ ኃላፊነት ተደቅኖበታል። እንጨት ከመልቀምና ውሃ ከመቅዳት አልፎ ምግብ ማብሰልም የእርሱ ስራ ሆነ። ያም ሆኖ ልጅ ያው ልጅ ነውና በተወለደበት ሰፈር በኦሮምኛ «ሰፈራ ዶቄ» በሚባለው ስፍራ እንደማንኛውም ልጅ ጭቃ አቡክቶ የተለያዩ ነገሮችን በመስራት ተጫውቷል።
ወንድወሰን በባህሪው ነገሮችን የሚፈራ ጭምት ልጅ ነበር። በተለይም ከሰዎች ጋር መጋጨትን በጣም ይፈራል፤ ከጸብ ራሱን ያሸሻል። ስለዚህ በእኩዮቹ ዘንድ ፈሪ ይባል እንደነበር ያስታውሳል። ነገሮችን አይቶ በፍጥነት መማር መቻሉና ለመተግበር መታተሩም አንዱ የሚለይበት ባህሪው ነው። በተለይ ስዕልና ቅርጻቅርጾችን በተለያየ ዲዛይን ማውጣት ላይ ማንም አይችለውም። በዚህም ብዙ ጊዜ ከትምህርት ቤት ሽልማት እንደተበረከተለት ያነሳል። ለጎረቤትም ታዛዥ ልጅ ነበር።
የልጅነት ፍላጎቱ ይህ ነው የሚባል አይደለም። ሆኖም አባቱ ከመሞታቸው በፊት እንዲሆንላቸው የሚፈልጉትን ይነግሩት ነበርና ያንን ለመሆን ይተጋ እንደነበር ያስታውሳል፤ ተምሮ ኮሌጅ ገብቶ ከፍተኛ የደመወዝ ተከፋይ መሆንና ቤተሰቡን መጦር አላማው ነበር። ሆኖም ግን ወንደሰን ከእናቱ ጋር የቆየው እስከ አስራ አንድ ዓመቱ ብቻ ነው። እናቱ ትዳር ሲመሰርቱ ከእንጀራ አባት ጋር አባት ብሎ መኖር ስለከበደው ወደ መቱ መኮብለሉን ይናገራል።
ባለታሪኩ፤ ከእናቱ እንዲለይ ሁለት ምክንያቶች መንስኤ መሆናቸውን ያነሳል። የመጀመሪያው የእናቱ ትዳር መመስረት ሲሆን፤ ሁለተኛው የአባቱ ዘመድ እርሳቸው ጋር ሆኖ እንዲማር መጎትጎታቸው ነው። በዚያ ላይ እርሳቸው ያሉበት ቦታ ከተማ ስለነበር ከተማ የመናፈቁ ጉጉትም ነበር።
ኑሮ በጎዳና
መቱ በደስታ እንደሚኖር አስቦ ቢጓዝም የጠበቀው ግን ተቃራኒ ነበር። በዘመድ ቤት ስቃይ ውስጥ ገባ። «እንጀራ እናት የሚለውን በሚገባ ያየሁበት ቤት ይህ ነው» ይላል ስቃዩን ሲያስታውስ። ምግብ በቀን አንዴ ነው የማገኘው ያውም ትርፍራፊ። በዚያ ላይ አቅሜን ያላገናዘበ የስራ ብዛት አስመረረው። ላስተምርህ ያሉትም ዘመድ የእጅ ሙያ አስተምረው የሰሌን ውጤቶችን ያሰሯቸውና ገንዘቡን ወደ ኪሳቸው ይከቱ ጀመር።
በቤት ውስጥ ከትምህርት መልስ ሁልጊዜ የሰሌን ሥራ ይሰራል፤ ፋታ አግኝቶ ሊያነብ ሲል እናቲቱ ሌላ ሥራ ትጭንበታለች። ስለዚህ የማጥኒያ ጊዜ የለም። ምሬት የዕለት ከዕለት ተግባር ሆነች። ታዲያ አንድ ቀን የአባቱ የብቻ ልጅ ወንድሙ በተመሳሳይ በእዛው ቤት ውስጥ ግፍ እየተፈጸመበት ይኖር ነበርና ከዚያ ቤት መውጣት አለብን ብለው ወሰኑ። «በእርግጥ ወቅቱ ድርቅ የተከሰተበት ጊዜ ነበር። ምግብ በቀላሉ አይገኝም። ስለዚህም እነርሱም ቢሆኑ ላልወለዱት ልጅ ይህንን ያህል መቸገር አልነበረባቸውም። ነገር ግን ሲናገሩ የነበረውን በመጠኑም ቢሆን ቢያደርጉልን ለጎዳና ህይወት አንዳረግም። በተለይ ለዘመዳችን ይህንን እንዲያውቁና ቢያንስ ምግብ እንድናገኝ ስንነግራቸው አለመፈጸማቸው ያሳዝነኛል። ስለዚህ አማራጫችን ነጻነትን ፍለጋ ጎዳና መወጣት ሆነ» ይላል ።
የወንደሰን ወንድም በእድሜ ከፍ ይላል፤ ጠንካራና ደፋርም ነው። ወንደሰን ግን ገና አላደገም፣ የቤትን ሙቀትና የውጪውን ቅዝቃዜ ለይቶ አያውቅም። በወንድሙ አደፋፋሪነት ግን ጣሪያቸውን ላስቲክ አድርገው ለመኖር ቆረጡ።
ከቤት ጠፍተው ሲወጡ ብርድልብሳቸውን፣ ደብተራቸውንና የለበሱትን ልብስ ብቻ ይዘው ቢሆንም ብርድልብሳቸው ግን ከአንድ ቀን በላይ አለበሱትም። የሚያስቀምጡበት ቦታ ስላጡ ደበቅን ብለው ትምህርት ቤት ሲሄዱ ተሰረቁ። ይህ ደግሞ ይበልጥ ብርዱን እንዳይቋቋሙት አድርጓቸው እንደነበር ያስታውሳል።
ወንድወሰን የጎዳና ትዝታውን ሲያነሳ « ድህነቴን የጠላሁበት፣ ማጣቴን የረገምኩበት ጊዜ ነበር ። ምክንያቱም የልጅነት ሰውነቴ ረሃቡን፣ ጥማቱን፣ ቅዝቃዜውን፣ ብርዱን፣ መከራውን ሁሉ… እንደምንም ቻል ማድረግ ተቸግሯል። ይህን በፅናትና በጥንካሬ እንዴት መቋቋም እንደሚችል ማሰብ አዳጋች ነበር» ይላል። ያም ሆኖ ግን ይሄንን መልመድ የግድ ይላል። በጎዳና ቆይታቸው ምን ሠዓት ላይ መተኛት፣ ምን ምልክት ሲሰጣቸው መንቃት፣ የተለያዩ የአየር ንብረቶችን እንዴት መቋቋም፣ እንዴት ከፍተኛውን የጎዳና ግዳጅ መወጣት እንዳለባቸውም ተማሩ።
የመጀመሪያ ጊዜ ቀኑ እየመሸ በመሄዱና ረሃቡ እየጸናባቸው በመምጣቱ ከስፖርት ካፌ ነበር የተራረፉ ዳቦዎችን ያገኙት። ሆኖም ለእነርሱ የነጻነት ጊዜ ነበረችና ተደስተዋል። ብርድልብሳቸውን ተከናንበውም ብርድ ሳይነካቸው አመሻሽተዋል። በጣም ከመሸ በኋላ ግን ሌላ ችግር እንዳለ ተረዱ። ለማደሪያ ማንም በረንዳውን አይፈቅድላቸውም። እንደውም ቀዝቃዛ ውሃ በተኙበት ይደፉባቸው እንደነበር አይረሳውም።
የጎዳና ህይወት በጣም ከሚፈትነው ነገር አንዱ ማደሪያ እንደሆነ የሚያነሳው ወንደሰን፤ በብዙ ነገር አንደሚቸገሩ ይናገራል። ከፖሊሶች፤ ከነባር የጎዳና ልጆች፤ ከበረንዳው ባለቤቶች፤ ጾታዊ ትንኮሳ ከሚያደርጉ አካላት ሁሉ ጋር ግብ ግብ ነው። እንደውም በአንድ ወቅት የተመሳሳይ ጾታ ጥቃት ሊደርስበት እንደነበረም ያስታውሳል። ከዚህ አልፎ ደግሞ ማንም ስለማያምናቸው ልብሳቸውንም ሆነ ደብተራቸውን የሚያስቀምጡበት ቦታ እንዳልነበራቸውም ይናገራል። ይህ በመሆኑም ለዓመታት ካርቶንና ላስቲክ እየለበሱ እንዳሳለፉ አይዘነጋውም።
እንግዳችን ችግር ውስጥ ቢሆንም ግማሽ ቀን እየሰራ ግማሽ ቀን ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ የነበረውን ትምህርቱን ይማር ነበር። ወንድሙ ግን ለመማር የሚያስችለው ሁኔታ ስላልነበረ አቋርጦ የድለላ ሥራ ላይ ተሰማርቷል። ወንድወሰን ለትምህርቱ ሲል ማንኛውንም ሥራ ይሰራል። በተለይ ሊስትሮና የመላላክ ሥራ በብዛት የሚሰራቸው አንደነበሩ ያስታውሳል። በሰው ቤት እየሄደም እንጨት ይፈልጣል፤ ልብስ ያጥባል። ሸክምም ሆነ ማንኛውንም የጉልበት ሥራ ገንዘብ እስካገኘበት ድረስ ይሰራል።
«በባዶ እግር መጓዝ ለእኔ ብርቅ አይደለም። እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ምንም አይነት ጫማን ለብሼ አላውቅም። በዚያ ላይ ልብሴም ተበጫጭቆ መቀመጫዬ እየታየ ነው ትምህርት ቤት የምገባው። ሆኖም በትምህርቴ በጣም ጎበዝ ስለነበርኩ ብዙዎች ይረዱኛል፤ በርታም የሚሉኝ መምህራን ነበሩ። ይህ ደግሞ ይበልጥ በጽናት ጎዳና ህይወትን እንድጋፈጠው አድርጎኛል» ይላል። የጎዳና ህይወትን ለመራቅ ሰዎች ጋር ይጠጋ የነበረው ባለታሪኩ፤ የማይመቹ ሲሆኑበት ግን ተመልሶ በዚያው ጎዳና ላይ ያሳልፍ እንደነበር ይናገራል።
«ጎዳና ህይወቴን አጠፋው ከምለው መካከል አንዱ ሌብነትን ለመልመድ ያደረኩት ጥረት ነው» የሚለው እንግዳችን፤ በልጅነቱ እንዲህ አይነት ነገር ሞክሮ ባያውቅም ወንድሙ ከገጠማቸው ጓደኞቹ የተማረውን እያለማመደው ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው ኪስ ገብቷል። ሆኖም ይህ ስራው ለስድስት ቀናት እስርና ግርፋት እንደዳረገው መቼም አይረሳውም።
«ጎዳና መካሪ አስተማሪ የሌለበት ቦታ በመሆኑ ሁሉ ነገር የተፈቀደ ይመስላል። አለማጨስ፣ አለመቃምና ሀሽሽና መሰል ነገሮችን አለመጠቀም ፋራ ያስብላል። ማንም ደግሞ ሊያስጠጋህ የሚችልበት ሁኔታ የለም። ስለዚህም ሁሉንም ለመሞከር ግዴታ ውስጥ ይከታል። እናም እኔ ብዙዎችን ነገሮች ሞክሬያቸዋለሁ» ይላል። ግን እንደማይጠቅሙት ከተረዳ በኋላ እንደተዋቸው ይናገራል።
«በጎዳና ሲኖር ያለችውን ቲሸርት ብርዱን ለመቋቋም ሲል ወጥሮ እግሩ ድረስ እንደሚለብሰው የሚናገረው ወንድወሰን፤ በዚያ ላይ እንዳንተኛ ለማድረግ ሲሉ ቀዝቃዛ ውሃ ሲደፉብን ብርዱ እንዴት አንጀታችን ገብቶ እንደሚያንዘፈዝፈን ዛሬ ድረስ ትዝ ይለኛል» ሲል ያስታውሳል። አንድ ቀን ቦይ ውስጥ ላስቲክ ለብሶ እንደተኛ ከሌላ አካባቢ የጣለ ዝናብ ያስከተለው ድንገተኛ ጎርፍ ወስዶት በስንት ትግል እንደተረፈ አጫውቶናል።
ትምህርት
አባቱ ለቤተክህነቱ ካላቸው ቅርበት የተነሳ በቤት ውስጥ ፊደላትንና ቁጥሮችን ጠንቅቀው ካስተማሩት በኋላ ነው መደበኛ ትምህርት ቤት የገባው። እናም ከአንድ እስከ አምስተኛ ክፍል በዚያው በትውልድ ቀዬው አልጌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረ። ከአምስት በኋላ ግን በእንግልት ነው ትምህርቱን የቀጠለው። መጀመሪያ መቱ ከተማ ላይ በጎዳና እያለ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ተማረ። ግን በዚህ ሰዓት አንባቢ ልጅ አልነበረም። ምክንያቱም ጊዜም ሆነ የሚያነብበት ቦታ የለውም። ስለዚህ በሚማረው ትምህርት ውጤታማ ለመሆን በክፍል የሚሰጠውን ትምህርት በሚገባ ይከታተላል። የቤት ሥራም ሲሰጥ ጎዳና ላይ መስራት ስለማይችል እዚያው ትምህርት ቤት ጨርሶ ይሄዳል። ይህ ጥረቱና ልፋቱ የስድስተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ፈተና ወስደው መቶ ካመጡትና ትምህርት ቤቱን ካስጠሩ አራት ልጆች መካከል አንዱ አድርጎታል።
የእናት ናፍቆት አላስችል ያለው ወንደወሰን እናቱን ፍለጋ ከትውልድ ቀዬአቸው ብቅ አለ። ነገር ግን ያሰበው አልተሳካም። እናቱ አግብታው የነበረው የእንጀራ አባቱ በመሞቱ ምክንያት ሌላ ሶስተኛ ሰው አግብታ አካባቢውንም ለቃ ሄዳለች። እርሱም ይህንን ሰምቶ እናቱን ፍለጋ አለችበት አመራ። ይህ ደግሞ ስድስተኛ ክፍልን ለስምንት ወር ያህል የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ጋር ሆኖ ለመከታተል እድል ፈጠረለት። ነገር ግን በአንድ አጋጣሚ ግጭት ተፈጠረና ከዚያ ለቆ ወጣ። እናቱንም ትቶ ወደ መቱ ተጓዘ። በዚያም የለመደውን የጎዳና ህይወት እየመራ ከስድስተኛ ክፍል ያቋረጠውን ትምህርት እስከ ዘጠኝ ቀጠለ። «ሳይደግስ አይጣላ» እንዲሉት አስረኛ ክፍል ሲገባ ገበየው ኤልያስ የተባለውን ሰው ተዋወቀ። በእርሱም ቤት ሁሉ ነገር ተሟልቶለት እስከ 11ኛ ክፍል ተማረ።
«ከጎዳና ህይወት ያላቀቀኝ፤ እንደእርሱ የረዳኝ አባት ማንም አልነበረም። ደግና የህይወቴ ቀያሽ መሀንዲስ ነው። ዛሬም ድረስ አባቴም ወንድሜም እርሱ ነው። ፍቅሩ የማያልቅ፤ ለጋስና ሰው ሆኜ ከሰዎች ተርታ እንድሰለፍ ያስተማረኝ ነው። ለዛሬ እዚህ መድረስ ወሳኝ ሰው ነው። በቃ ስለእርሱ ስናገር ቃላት ያጥረኛል። እኔን ሆኖ ያኖረኝ ነው ብል አይበዛበትም» ይላል ስለውለታው ሲናገር። ግን ምንያደርጋል 12ኛ ክፍልን እንኳን መቀጠል እንዳይችል ይህንን ሁሉ የሚያደርግለትን ባለውለታው ሰው ባጋጠመው ችግር ምክንያት ታሰረ። ጠንካራውም ተማሪም ሌላ ጭንቀት ላለመሆን ቤቱን ለቆ ከመቱ ወደ ጅማ ጉዞውን አደረገ። ወንድወሰን ማንኛውም ሰው ቤት በጥገኝነት ሲገባ ማንኛውንም ሥራ ይሰራ ነበር። ልብስ ማጠብም ሆነ ምግብ ማብሰል ለእርሱ መደበኛ ስራ ናቸው። ይህንን በሰውቤት በመስራት 12ኛ ክፍልን መከታተሉን ቀጠለ።
ጅማ ሲሄድ ዘመድ እንዳለው በማሰብና ነበር። ነገር ግን እዚያ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ አልተቀበለውም። መቱ በነበረበት ወቅት የሚያውቀው ፖሊስ ከአንዲት ሴት ጋር አስተዋውቆት ለጥቂት ጊዜ ቢቆይም እርሷን ተቋቁሞ ግን መማር እንዳቃተው ይናገራል። ደብተር እስኪርብቶ እንዲረዱት ለመጠየቅ ወረቀት ሲያዞር ግን ሁነኛ ሰው አጋጠመው። ታምራት ትባላለች፤ የልጆች እናት ናት፤ የልጅን ነገር ታውቃለችና ከልጆቿ እኩል ልታስተምረው ሰበሰበችው። እርሱም ልክ እንደቤት ሰራተኛ ያግዛታል። የጥናት ጊዜው እያነሰ የስራ ጊዜው እየበዛ በመሄዱና የፈተናዎቹም መደራረብ በትምህርቱ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ አልቀረም፤ ያሰበው ዩኒቨርሲቲ የመግባት ህልሙ ውጤት ባለማግኘቱ ሳይሳካ ቀረ። ከዚያም ጋምቤላ «አራ» የተባለ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሰራ ብዙም በትርፍ ሰዓቱ አጥንቶ ውጤቱን አሻሻለ። ከዚያ የሆቴልና ቱሪዝም ኮሌጅ ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድሮ በማለፉ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተምሮ በዲፕሎማ ተመረቀ።
ቀጥሎ ዲግሪውን ናሽናል አቬሽን ኮሌጅ ተማረ ፤ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ አገር በሚገኘው ሴንትራል ፊልድ ዩኒቨርሲቲ በሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት እየተማረ ይገኛል። የተለያዩ ሥልጠናዎችንም በተለያዩ አገራት እንዳገኘም አጫውቶናል።
ከ105 ወደ 70ሺ ብር
ጽኑው ወጣት ያልፈተነው ችግር፣ ያልሞከረው ስራ፣ ያልወጣና ያልወረደው የህይወት ጠመዝማዛ መንገድ የለም። ሁሉንም በድል ለማለፍ ግን አሁንም ጥረቱን ቀጥሏል። ከኮሌጅ ሲመረቅ በኢምፔሪያል ሆቴል ለተወሰኑ ጊዜያት የሰራ ሲሆን፤ በሆቴሉ ዘርፍ በደመወዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀጠረው ክራውን ሆቴል ነው። በሱፐርቫይዘርነት ደግሞ ፐርፕልካፌና ሬስቶራንት፤ ሬንቦ ሶል በሚባል የኮርያኖች ሬስቶራንት ውስጥ ለወራት ያህል ሰራ። ለኖተር ዳቦና ኬክ ቤትም እንዲሁም በተቆጣጣሪነት ሰርቷል። ቀጥሎ ጉዞውን ወደ ደቡብ ወሎ አደረገና «ጃሬ ሆቴል ስኩል ወይም ጃሬ የህጻናት መንደር» በሚባል ድርጅት ውስጥ የሙያ ትምህርት ለማስተማር በመምህርነት ተቀጠረ።
ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ተመሳሳይ ትምህርት የሚሰጥበት ኢማኑኤል የሚባል ትምህርት ቤት ስለነበር እየሰራ ለመማር ያስችለው ዘንድ አዲስ አበባ መጣ። የስልጠናና ፕሮግራም ዲፓርትመት ኃላፊ ሆኖ መስራት ቀጠለ። ከዚያ መምህርነቱን ትቶ ኢን ኤንድ አውት ሬስቶራንትና ሚያሚ ናይት ክለብ ውስጥ በዋና ሥራአስኪያጅነት ተቀጠረ። እያለ እያለ ኦዋሲስና ማራቶን ስፖርት ሬስቶራንቶች ላይ፣ በአዲስ አበባ ትልልቅ ሞሎች ተብለው የተደራጁ ሬስቶራንቶችንና ካፌዎች ውስጥ በብዛት ሰራ።
አቶ ወንድወሰን እንደሚለው፤ ደንበል ሲቲ ሴንተር ላይ ደንበል ዶም፤ ጌቱ ኮሜርሽያል ላይ ክላውድ ናይን፣ ፍሬንድ ሽፕ ላይ የፍሬንድሽፕ ካፌና ሬስቶራንቱን በማደራጀትም ሆነ በመምራት ዓመታትን አሳልፏል። ከዚያ ወደ ደቡብ ሱዳን ተጉዞም በኪዊንኦፍ ሼባ ሬስቶራንት ውስጥ በሥራስኪያጅነት ለአመት ያህል ቆይቷል። ሀይሌ ሪዞልት ገና እንደተከፈተ በምክትል ዋና ሥራስኪያጅነትም ሰርቷል። ወደ ጋምቤላ ሄዶ ደግሞ በአንድ ድርጅት ውስጥ የማማከር ብሎም በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሰርቷል።
አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ደግሞ በሪግል ገስት ሀውስ፣ የካፌ፣ ሬስቶራንትና ሆቴሎች ውስጥ ጎን ለጎን የማማከር አንዲሁም በሥራ አስኪያጅነት ይሰራ ነበር። ዛሬ ደግሞ በራሱ ድርጅት «ሰቨን ግሎሪ ኮልሰንተንሲ» አማካኝነት በኮንትራት የአምባሳደር ሆቴልን ዋና ሥራስኪያጅ ሆኖ እያገለገለ ነው። በቀን ሶስት ብር ከሀምሳ ከሚያገኝበት ስራ ወጥቶ ዛሬ በወር እስከ ሰባ ሺ ብር ተከፋይ ለመሆን በቅቷል። ይህም ሆኖ ገና መስራትና ማግኘት እንዳለበት ያስባል። ሰፊ ራዕይም ሰንቋል።
“በአሁኑ ወቅት እንደ አማዞን ዶት ኮም አይነት ሞባይል አፕሊኬሽን እየሞከርኩ በመሆኑ ስራውን መቶ በመቶ ሳጠናቅቅ ለአገሬ ብቻ ሳይሆን አለምን ሊሸፍን የሚችል ሥራ እሰራለሁ። በመጀመሪያ ግን ያለፍኩበት ህይወትን የሚመሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች የማግዝበት ይሆናል“ ብሏል።
የምወደውና የማከብረው አባቴ የዘራብኝን ሀሳብ መሆን ችያለሁ የሚለው እንግዳችን፤ ህልሜን እየኖርኩት ነው ብሎ እንደማያምንና በልጅነቱ ያሳለፈውን ድህነት እንዴት እንደሚበቀል እያሰበ እንደሆነም ነግሮናል። «ከተቀጣሪነት ወጥቼ ራሴን መቅጠር ብችልም ገና አሰብኩት ደረጃ አልደረስኩም። ገና ነኝ።» ይላል አቶ ወንድወሰን።
ያልተገደበ ፍቅር
አቶ ወንደወሰን በሥራ አለም በአንድ አጋጣሚ ከተዋወቃት እንስት አንድ ልጅ ወልዷል። አብረው ልጃቸውን ለማሳደግ ቢጥሩም መስማማት ባለመቻላቸው ከአንድ ዓመቱ ጀምሮ እስከ 11 ዓመቱ ድረስ እናትም አባትም ሆኖ በብቸኝነት አሳድጓል። ከዚያ ግን ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ የዛሬዋን ባለቤቱን እናት ማግኘቱን ይናገራል። ባለቤቱ መስማት የተሳናትና የጋምቤላዋ የአኝዋክ ብሔረሰብ ተወላጅ ናት።
ኢንተርኔት ካፌ ውስጥ ዓይኑ የገባችው የአኝዋክዋ ጉብል ከፊደላቱ ጋር በኪቦርዱ ላይ ቀርታ ኖሮ እርሷን ለማግኘት ይመላለስ ገባ። በወቅቱ ተራ ስትጠብቅ በመቆየቷና እርሱም ኮምፒውተሩን አለቅ በማለቱ ተናዳ በምልክት ቋንቋ አስተናጋጇን ስትጠይቃት አይቶ ነው መስማት የተሳናት መሆኗን ያወቀው። እናም ለጊዜው ቦታውን ለቆላት ወደ ቤቱ ቢያመራም ልቡ ግን ከዚያው ነበር። እርሷን በማሰብ ሳምንት አሳለፈ። አላስችል ሲለውም ዳግም ወደ ኢንተርኔት ካፌው ሄደና ስልክ ቁጥሩን አስቀመጠ። ከዚያም ማነው የደፈረኝ ስትል በቴክስት ማንነቱን ጠየቀችው።
ሊያገኛት እንደሚፈልግ ነግሯትና አሳምኗት ጓደኛሞች ሆኑ። መቼም ቢሆን አገባታለሁ ብሎ አስቦ ባያውቅም በድግግሞሽ ግንኙነታቸው ሳቢያ ፍቅሯ ከልቡ ገባ። ስለዚህ ብዙዎች ሊጠቀምባት ነው ቢሉም እርሱ የትዳር አጋሩ አደረጋት። ለጊዜው እርሷም ቢሆን በጥያቄው ተደናግጣ ነበር። ምክንያቱም የራሷ ደሴት ነበራት። እርሷን ማግባት ያለበት የጋምቤላ ልጅ ሊያውም እንደእርሷ መስማት የተሳነው ብቻ አድርጋ ታምናለች።
«ለእኔ አንቺ ምርጥና የአምላክ ሥጦታ ነሽ። ምንም አይነት የሚያስከፋሽ ነገር አላደርግም። ምክንያቱም በአንቺ ፍቅር ተይዥያለሁ። ስለዚህ እባክሽን አግቢኝ» ሲላት ባታምነውም በብዙ ጥረት እሺ አለችው። ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ የብሔረሰቡ ባህል እጅግ ይፈትነው ጀመር። ሆኖም ወዷታልና ችግሩን ዋጥ አድርጎ አለፈው።
«መዋደድ ብሔር፤ ቀለምና አካላዊ ጉዳት የሚያቆመው አይደለም። ይልቁንም የውስጥ ማንነት ታይቶበት የሚገነባ ነው» የሚለው ባለታሪኩ፤ ለእርሱ ምርጫው ማንነቷ በመሆኑ አገባት። ለወራት ያህል በቴክስትና በጽሁፍ ሲግባባ የነበረውን ቀየረና በእርሷ አጋዥነት የምልክት ቋንቋ ተለማመደ። ይህንን ሁሉ ማድረግ ቢቻለውም አንድ ነገር ግን ከበደው። ልጅ ይፈልጋሉ መውለድ ግን አቃታት። አራት ጊዜ ተጨናገፈባት። በዚህም ውስጧ በጣም ተጎዳ፤ በጣምም አዘነች። ይሁንና በብቸኛ ወንድ ልጁ ደስተኛ ሆና በቤት ውስጥ በሰላም እየኖሩ ነው።
መልዕክተ ወንደሰን
ከምድሪቱ ኦርቢት ለቅቆ ሰፊውን የህዋ ጠፈፍ መርገጥ የሚቻለው ታላቅ መሆንን አስቦ መስራት ሲቻል ነው ብሎ ያምናል። የጨረቃን ንሥራዊ ቀጠና ከፅኑ መንፈስ ጋር ማጣመርም እንደሚያስፈልግ ይገልጻል። ታላቅነት የመንፈስ ፅናት፣ ትልቁን ለመርገጥ የሚያስችል፤ ከትቢያ ጎዳና በብርታት የሚያነሳ ነው። ታላቅነት አይቻልምን ከራስ ውስጥ አሽቀንጥሮ ጥሎ በይቻላል መንፈስ መብረር ነው። ታላቅነት ከአስመራሪ የጎዳና ሕይወት ወደ ከፍታው ጫፍ ወደ ጥልቁ ህዋ መምዘግዘግ መቻል ነውና ይህንን ለማድረግ የጣረ ሁሉ ታላቅነቱን ያስመሰክራልና ይህንን ያድርግ መልዕክቱ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው