
እስራኤል በሄዝቦላ የሮኬት ጥቃት 12 ሰዎች መገደላቸውን ገለጸች።
በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው የጎላን ሀይት ውስጥ በሚገኝ የእግርኳስ ሜዳ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ 12 ሰዎች መገደላቸውን የገለጹት የእስራኤል ባለሥልጣናት ለጥቃቱ ሄዝቦላን ተጠያቂ አድርገዋል።
ባለሥልጣናቱ በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላ ላይ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል።
ሄዝቦላ ባለፈው ጥቅምት ወር የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለ ግዛት ለደረሰው ከባድ ጥቃት እጁ እንደሌለበት አስተባብሏል።
ጥቃቱ ከጋዛው ግጭት በትይዩ ያለውን ግጭት ያባባሰው ሲሆን በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል አጠቃላይ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ስጋት እንዲጨምር አድርጓል። የሮኬት ጥቃቱ የደረሰው እስራኤል በፈረንጆቹ 1967 ያካሄደችውን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ተከትሎ በያዘችው ጎላን ኃይት ውስጥ ዱሬዝ መንደር በሚገኝ የእግር ኳስ ሜዳ ላይ ነው።
ሄዝቦላ ባሰራጨው የጽሑፍ መግለጫ “እስላማዊ ቡድኑ ከክስተቱ ጋር በፍጹም የሚያገናኘው ነገር የለም፤ የሚቀርቡትን የሐሰት ክሶች አይቀበልም” ብሏል።
በእስራኤል እና ሊባኖስ ድንበር ያለው ግጭት እንዳይባባስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገች ያለችው አሜሪካ ጥቃቱን ዘግናኝ ስትል ያወገዘችው ሲሆን እስራኤል በኢራን ከሚደገፈው ሄዝቦላ ጋር በምታደርገው ውጊያ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደምታደርግም ገልጻለች።
“በሽብርኞች የሚካሄድን ማንኛውንም ጥቃት እናወግዛለን” ሲል የሩሲያው ታስ የዜና አገልግሎት የሩሲያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭን ጠቅሶ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር ሮኬቱ የተተኮሰው በደቡብ ሊባኖስ ቸዳ ከሚባለው መንደር ሰሜን በኩል ከሚገኝ ቦታ ነው ብሏል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሀጋሪ ሮኬቱ ኢራን ሠራሽ ፋራቅ-1 መሆኑ በምርመራ ተደርሶበታል ብለዋል። በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም