
በኢራን በተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ከ200 በላይ ሰዎች ታመው ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፥ ለማቀዝቀዣዎች የኤሌክትሪክ ፍጆታው ጨምሯል ተብሏል::
በኢራን ባንኮች፣ የመንግሥት ተቋማትና የፋይናንስ ገበያዎች ዝግ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በሀገሪቱ የተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከባድ የኅብረተሰብ ጤና ችግር እንዳይፈጥርና ኃይል ለመቆጠብ በሚል ነው ሁሉም የመንግሥትና የንግድ ተቋማት ዝግ ሆነው እንዲውሉ የተወሰነው።
በመዲናዋ ቴህራን ቅዳሜ እለት 42 ዲግሪ ሴልሺየስ የሆነ ሙቀት መመዝገቡን የኢራን ብሔራዊ የዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል።
የሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ መከላከል ቢሮ በከባድ ሙቀቱ ምክንያት 225 ሰዎች ለሕመም መዳረጋቸውና አፋጣኝ ሕክምና እንደሚሹ ነው ያስታወቀው።
በኢራን 10 ግዛቶች በትናንትናው እለት 45 ዲግሪ ሴልሺየስ የደረሰ ሙቀት ተመዝግቧል።
ከፓኪስታን እና አፍጋኒስታን ጋር በምትዋሰነው ደልጋን 49 ነጥብ 7 ዲግሪ ሴልሺየስ ሆኖ የተመዘገበው ሙቀትም ከፍተኛው መሆኑን የሀገሪቱ የሜቲዮሮሎጂ ድርጅት ገልጿል።
የሙቀት መጠኑ እየቀነሰ እንደሚሄድ ቢጠበቅም ኢራናውያን በቤት ውስጥ የአየር ማቀዝቀዣዎችን በመጠቀም ራሳቸውን እንዲጠብቁ ነው ያሳሰበው።
በከባዱ ሙቀት ምክንያት ለማቀዝቀዣዎች የሚውል የኤሌክትሪክ ፍጆታ ጨምሯል።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የተመዘገበው 78 ሺህ 106 ሜጋዋት የኃይል ፍጆታም ከፍተኛው ነው መባሉ ተዘግቧል።
በኢራን ባለፉት 50 ዓመታት የተመዘገበው ሙቀት በዓለማቀፍ ደረጃ ሙቀት ከሚጨምርበት በእጥፍ እንደሚልቅ የሀገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት ምክርቤት ይፋ ማድረጉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ቴህራን ባለፈው ዓመትም በሙቀት መጨመር ምክንያት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁለት የእረፍት ቀናት ማወጇ የሚታወስ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም