“በችግር ውስጥ ሆነን ያስመዘገብነው ውጤት ለከተማው ነዋሪና ለአልሚ ባለሀብቶች ተስፋ የሚሰጥ ነው”-አቶ ባዩህ አቡሀይ

አቶ ባዩህ አቡሀይ የጎንደር ከተማ ከንቲባ

የጎንደር ከተማ በ1632 ዓ.ም መመስራቷ ይነገራል:: አሁን ላይ በስድስት ክፍለ ከተማ፣ በ25 የከተማ ቀበሌ እና በ11 ቀበሌ በድምሩ በ36 ቀበሌ የተዋቀረች ናት:: አጠቃላይ የቆዳ ስፋቷም 31 ሺህ 400 ሄክታር ነው:: በዚህች ከተማ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንደሚኖርባት ይገመታል::

ጎንደር ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድ እና ለቱሪዝም የተመቸች ከተማ ብትሆንም፤ ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሲያስተጓጉሉ ቆይተዋል:: በአሁኑ ወቅት የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው::

አዲስ ዘመንም በዛሬው ወቅታዊ ዓምዱ ከጎንደር ከተማ ከንቲባ ጋር በከተማዋ አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን አስመልክቶ ቃለ ምልልስ አድርጓል:: ከከንቲባ ባዩህ አቡሀይ ጋር የተደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል:: መልካም ንባብ::

 አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የጎንደር ከተማ አጠቃላይ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ምን ይመስላል?

አቶ ባዩህ፡- ጎንደር ከተማ ለንግድና ለቱሪዝም የተመቸች ከተማ ናት:: እንደሚታወቀው በጎንደር ከተማ የፋሲል ቤተ መንግሥትን ጨምሮ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት የተመዘገቡ በርካታ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ይገኝባታል:: በዙሪያዋም ሊጎበኙ የሚችሉ የጣና ገዳማትና አብያተ ክርስቲያን እንዲሁም የሰሜን ፓርክ እና ሌሎች በርካታ ታሪካዊ ቦታዎች አሉ:: ለላሊበላና ለአክሱምም ማዕከል ሆና የምታገለግል ከተማ ናት:: የከተማዋ አካባቢ በኢንቨስትመንት ደረጃም በርካታ የሰብል ምርቶችና የቅባት እህሎች የሚመረትበት ነው::

እነዚህንና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን መሠረት በማድረግ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሲካሄድበት ቆይቷል:: ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት ግጭቶች እየተፈራረቁ የከተማዋን አጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አስተጓጉሏል:: በተለይ ደግሞ ኮቪድ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ቢሆንም ጎንደር ከተማ በቱሪዝም የተመሰረተች ከተማ እንደመሆኗ መጠን በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል::

በተጨማሪም የቅማንት አማራ የብሔረሰብ ግጭት ከተማዋ ብዙ ችግር ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል:: ከዚያም ባለፈ ከዓመታት በፊት የተካሄደው የህልውና ዘመቻው በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የከተማችንን የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንት፣ የንግድ እና የሰላም ሂደቱን ሲያስተጓጉል መቆየቱ የሚታወስ ነው::

ከህልውና ዘመቻ ማግስትም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከወርሃ ሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ክልሉ ላይ በተፈጠረው ግጭት የከተማዋ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ አስገብቶት ቆይቷል:: በከተማዋ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ወደነበረበት ለመመለስ በርካታ ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተናል::

በተለይም መከላከያ ሠራዊት፣ የአካባቢው የጸጥታ ኃይልና ማህበረሰቡ በሰሩት የቅንጅት ሥራ በከተማዋ አንጻራዊ ሰላም ከመስፈኑም ባለፈ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ከነበረበት መፋዘዝ ወጥተው ማንሰራራት ጀምረዋል::

ንግድንም በሚመለከት ጎንደር ከሲራራ ንግድ ጀምሮ የኮሪደር መውጫ ሆና ለዘመናት ትልቅ የንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወንባት ከተማ ነበረች:: በግጭቱ ባለሀብቱ እና ነጋዴው አካባቢያቸውን ትተው እንዲሰደዱ እንዲሁም ከወልቃይት እና በዙሪያው ካሉ አካባቢዎች ጋር ያለው የንግድ ትስስር እንዲተስተጓጎል ምክንያት ሆኖ ነበር::

ይሁን እንጂ አሁን እየተሠራ ባለው የሰላም ማስከበር ሥራ ባለሀብቶች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ እና ከወልቃይት እና በዙሪያው ካሉ አካባቢዎች ምርትና ሸቀጥ ወደ ከተማው እየገባ በመሆኑ የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ከነበረበት መፋዘዝ መውጣት የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል::

የግጭት ትርፉ የሀገርን እድገት ማቀጨጭ፣ ማክሰርና ማጥፋት ነው:: ይህንን ለመቀልበስ እንደከተማ ሰፊ ሥራ በመሥራታችን አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል:: በቀጣይ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ሙሉ ሰላም ለመቀየር ከፌዴራል ጀምሮ በሁሉም ደረጃዎች በርካታ ሥራዎችን እየሠራን ነው::

በስምንት ቀጣና ሕዝቡን በማወያየት እና የሰላም ካውንስል በማቋቋም ግጭቶች እና ችግሮች በውይይትና በድርድር እንዲፈቱ አቅጣጫ ተቀምጧል:: የተቀመጠውን አቅጣጫ ስኬታማ ለማድረግ ጫካ የገቡ አካላት ችግራቸውን ለውይይት እና ለድርድር በማቅረብ የከተማው ነዋሪ የተሟላ ሰላም አግኝቶ እጁን ወደ ልማት እንዲመልስ ማድረግ ይገባል::

እንደ ከተማ አስተዳደር ላለፉት ዓመታት ሕዝቡን ያማረሩ የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ከደሴ ከተማ እና ከዙፋን ችሎት ተሞክሮ በመውሰድ የከንቲባ ችሎት መድረክ ተጀምሮ ለረጅም ዓመታት የቆዩ ችግሮችን መፍታት ተችሏል::

ጎንደር ከተማ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ምቹ ከተማ በመሆኗ በቀጣይም የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደተሟላ ሰላም በመቀየር ሕዝቡን ያሳተፈ የሰላም ግንባታና የልማት ሥራዎች ትኩረት ሰጥተን እናከናውናለን::

አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ከማከናወን አንጻር የተሠሩ ሥራዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ባዩህ፡– የጎንደርና የአካባቢው ነዋሪ ለውጡን ተከትሎ ይመጣል የሚል በርካታ የልማት ጥያቄ ነበራቸው:: በከተማው በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጠሩ ግጭቶች በሚፈለገው ደረጃ ማልማት ባይቻልም በተጨባጭ ግን በአንድ በኩል ሰላም የማጽናት በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ የልማት ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን::

ከሚሰሩት የልማት ሥራዎች መካከል መንገድ አንዱ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት 22 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ አጠናቀናል:: በቀጣይ ዓመት ወደ አስፓልት በመቀየር ደረጃውን ለማሻሻል አቅደናል:: በተጨማሪም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ዘጠኝ ድልድዮች ገንብተን የማጠናቀቂያ ምዕራፉ ላይ ደርሰናል::

በከተማዋ የሚገኙት መንገዶች ከሰሜን ወደ ደቡብ የተዘረጉ በመሆናቸው ከምዕራብ ወደ ምስራቅ የሚያገናኙ መንገዶችና ድልድዮች አልነበሩም:: በዚህ ዓመት አቅደን እየሠራነው ያለው የመሠረተ ልማት ሥራ የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሊያሳልጡ የሚችሉ ናቸው:: በተለይ ግንባታቸው እየተጠናቀቀ የሚገኙት ዘጠኝ ድልድዮች የከተማዋን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሊያሳልጡ የሚችሉ ናቸው::

ጎንደር የምትታወቅበት የበዓላት ወቅት ሲመጡ የሚያጋጥመውን የመንገድ መጨናነቅ ሊቀርፉ የሚችሉ አማራጭ መንገዶች ተገንብተዋል:: በሌላ በኩል የከተማዋን ጽዳት እና ውበት ለማስጠበቅ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የቄራ ግንባታ የሲቪል ሥራው አልቆ የኤሌክትሮ መካኒካል ገጠማው እየተከናወነ ነው፤ በቅርብ ጊዜያት ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ ይበቃል ተ ብሎም ይጠበቃል::

በተጨማሪም ካለፉት የለውጥ ዓመታት ጀምሮ በርካታ ትላልቅ እና አነስተኛ የወጣት መናፈሻዎች፣ የገበያ ማዕከላት፣ መናኸሪያ፣ የጌጠኛ ውስጥ ለውስጥ መንገድ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው::

በየዓመቱ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የጌጠኛ ጠጠር መንገድ እየተሠራ ያለበት ሁኔታ አለ:: በቀጣይም ፕሮጀክት መጀመር ብቻ ሳይሆን ማጠናቀቅን ባሕል ለማድረግ በራሳችን አቅም በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት አቅደናል::

ከለውጡ ዓመታት በፊት ተጀምረው ሲጓተቱ የነበሩ ፕሮጀክቶች በተለይ ከአዝዞ አርበኞች አደባባይ የነበረው የአስፓልት መንገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ግንባታው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል::

በተጨማሪም ለከተማው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ትልቅ ፋይዳ አላቸው ተብሎ የሚገነቡ እንደ መገጭ ዓይነት ድልድዮች እና የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርን ሊቀርፉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች በፌዴራል መንግሥት ትኩረት ተሰጥቷቸው ግንባታቸው እየተከናወነ ይገኛል::

አዲስ ዘመን፡- የከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? በተለይ ምርትን በሀገር ውስጥ ከመተካት፣ የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት እና የሥራ እድል ከመፍጠር አንጻር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ምን ናቸው?

አቶ ባዩህ፡- ባለፉት ስድስት ዓመታት ጎንደርን የኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተማ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል:: ጎንደር እና አካባቢው በርካታ የቅባት እህሎች፣ ቅመማቅመም እና ሌሎች የሰብል ዓይነቶች በስፋት የሚመረትበት በመሆኑ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ እና ለእንስሳት ሀብት ልማት ምቹ አካባቢ ነው::

ባለፉት ዓመታት በክልሉ እና በከተማው አቅም አምስት የኢንዱስትሪ መንደሮችን ከልለናል:: ከነዚህ ውስጥ አራቱ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው ለባለሀብቶች ተላልፈዋል:: ኢንዱስትሪ መንደር ቁጥር አምስት ደግሞ ባለሀብቱ ካሳ እየከፈለ የሚወስደው እና እያስተላለፍን እንገኛለን:: በአምስቱም የኢንዱስትሪ መንደሮች 46 በቅድመ ግንባታ፣ 137 በግንባታ ላይ፣ ግንባታ ያጠናቀቁ 70፣ በምርት ላይ ያሉ 192 በአጠቃላይ 445 ፕሮጀክቶች ይገኛሉ:: ከመካከለኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ 192 ኢንዱስትሪዎች ሥራ ላይ የሚገኙ ናቸው::

ትኩረት ሰጥተን እየሰራንበት ያለው በርካታ ባለሀብቶችን መሳብ በመሆኑ በዚህ ዓመት ብቻ 116 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 349 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመስጠት 92 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ለ105 ባለሀብቶች ማስተላለፍ ችለናል::

በጎንደር ከተማ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው:: በተያዘው ዓመት ብቻ 27 ፕሮጀክቶችን ወደ ምርት ለማስገባት አቅደን 23ቱ ምርት ማምረት ጀምረዋል:: ሰባት ፕሮጀክቶች ደግሞ ማሽን ተከላ ላይ ያሉና በቅርቡ ለማስመረቅ ዝግጅት ላይ የሚገኙ ናቸው::

ኢንዱስትሪዎች እንደ ሀገር የሚገጥመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትን እንዲፈቱና ምርትን በሀገር ውስጥ እንዲተኩ ትኩረት አድርገን እየሰራን በመሆናችን በዚህ ዓመት ስምንት ኢንዱስትሪዎች 18 ሺህ 328 ቶን ምርትን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ 49 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት ችለዋል::

ተኪ ምርትንም በሚመለከት በተያዘው ዓመት ብቻ 12 ሺህ 799 ቶን ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት ታቅዶ 29 ሺህ 888 ቶን ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል:: ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ የከተማውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማሳላጥ ባለፈ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት፣ ተኪ ምርትን ለማምረትና የሥራ እድል ለመፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ:: በዚህ ዓመት ወደ ሥራ እየገቡ ባሉ ኢንዱስትሪዎች ብቻ ለአምስት ሺህ 71 ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሯል::

በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት ለወጣቶች የሥራ እድል ከመፍጠር፣ ምርትን በሀገር ውስጥ ከመተካት እና የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት አንጻር እንዲሁም ከተማው ካለው እድልና ከሚፈልገው የመልማት አቅም አንጻር ጥሩ ነው ተብሎ ባይወሰድም ካለው የጸጥታ ችግር አንጻር ያስመዘገበው ውጤት ለከተማው ነዋሪ እና ለአልሚ ባለሀብቶች ተስፋ የሚሰጥ ነው::

በከተማዋ የገጠመን ችግር የወጣቶች ሥራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ይህንን መቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎች ትኩረት ሰጥተን ከሰራንባቸው ዘርፎች የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ነው:: በተያዘው ዓመት 46 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንፈጥራለን ብለን 45 ሺህ 248 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችለናል::

አዲስ ዘመን፡- በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና መርሐግብር ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ባዩህ፡- እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች አንዱ የሌማት ትሩፋት ነው:: እኛም በከተማ ደረጃ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ወደ ተግባር ማስገባት ችለናል:: የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ጽሕፈት ቤት ብለን በአዲስ በማደራጀት ወደ ሥራ አስገብተናል:: በዚህም በመርሐ ግብሩ የከተማውን የምግብ ዋስትና በተለይ በሥጋ፣ በእንቁላል፣ በወተት እና በማር የተትረፈረፈ ምርት እንዲኖር ለማድረግ በተሠራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል::

ለአብነት ጽላተማርያም የዶሮ እርባታና ማቀነባበር ከቤቷ ጀምራ አሁን ላይ በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ዶሮዎችን ማርባት ችላለች:: በዚህም በከተማው የነበረውን የእንቁላል ዋጋ ከ15 ብር ወደ ዘጠኝ ብር እንዲወርድ ተደርጓል:: የእንቁላል ገበያ ከማረጋጋት ባለፈም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል ፈጥራለች:: ሌሎች በርካታ ወጣቶችም በዘርፉ ተሰማርተው የከተማውን የእንቁላል ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደጉት ይገኛል::

በተያዘው ዓመት 665 ነጥብ ስምንት ቶን ሥጋ ለማምረት ታቅዶ አንድ ሺህ 64 ነጥብ ስምንት ቶን ሥጋ ማምረት ተችሏል:: 23 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን እንቁላል ለማምረት ታቅዶ 30 ሚሊዮን እንቁላል ማምረት የቻልንበት ሁኔታ ተፈጥሯል::

የወተት ላምም ትኩረት ከተሰጠባቸው ዘርፎች መካከል ሲሆን፣ በርካታ ወጣቶች የራሳቸውን የምግብ ፍጆታ ከማረጋገጥ አልፈው ወደ ማቀነባበር እና ኢንቨስትመንት ተሸጋግረዋል:: በዓመቱ 54 ሺህ 237 ሊትር ወተት ለማምረት ታቅዶ 61 ሺህ 721 ሊትር ወተት ማምረት ተችሏል::

በንብ ማነብ ዘርፍም በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ወጣቶችን ወደ ሥራ እያስገባንበት ያለ ዘርፍ ነው:: በዚህም 358 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ 330 ነጥብ አራት ቶን የማር ምርት ማግኘት ችለናል::

በአጠቃላይ የከተማዋን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ሕዝቡንና አመራሩን ባሳተፈ መልኩ በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል:: ዘርፎችን በክላስተር ለማደራጀት 50 ሚሊዮን ብር ተመድቦ የዶሮ ክላስተር እየተገነባ ይገኛል:: የወተት ላምንም ወደ ክላስተር ለማምጣት መሬት ለይተን ለኮንትራክተር በማስረከብ ግንባታ ተጀምሯል::

ዘርፉ የሥራ እና የአመጋገብ ባሕልን መቀየር የሚያስችሉ ውጤቶች እየተገኙ በመሆኑ በሚቀጥሉት ዓመታትም ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን::

አረንጓዴ ዐሻራን በሚመለከት በ2016/17 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አራት ነጥብ 75 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል 475 ሄክታር መሬትን በችግኝ ለመሸፈን አቅደን እየሠራን እንገኛለን::

የችግኝ ተከላውን ለማከናወን ችግኝ የማፍላት፣ ቦታ የመለየት እና በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ስንሰራ ቆይተናል:: በ2016 በጀት ዓመት ሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ ሶስት ነጥብ 25 ሚሊዮን ችግኞችን ለተከላ ማዘጋጀት ችለናል::

ችግኞቹ የተዘጋጁት በከተማዋ በሚገኙ 463 የችግኝ ጣቢያዎች ሲሆን፣ ለተከላ የተዘጋጁት ችግኞች ሁለገብ መኖ፣ ፍራፍሬ፣ ቡና፣ ሀገር በቀል ዛፎች ናቸው:: የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ በተጨማሪ በጊዜያዊነት እና በቋሚነት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል::

ችግኝ መትከል ብቻ ግብ ባለመሆኑ ችግኞች ባለቤት ኑሯቸው ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው በትኩረት እየተሠራ በመሆኑ ጽድቀት መጠናቸውም ከዓመት ወደ ዓመት እየተሻሻለ ነው::

የአካባቢው ማህበረሰብ ችግኝ መትከል የሚያስገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳት ለ2016/17 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ለችግኞች ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲያደርጉ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ::

አዲስ ዘመን፡- የከተማው ነዋሪ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመፍታት አንጻር የተሠሩ ሥራዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ባዩህ፡- ላለፉት ዓመታት ሕዝቡን ካማረሩ ጉዳዮች አንዱ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው:: በተለይ ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ነው:: ይህንን ችግር ለመፍታት እንደ ከተማ በርካታ መድረኮችን አካሂደናል:: አመራሩም ሕዝቡን ያማረረውን ችግር በአጭር ጊዜ ለመፍታት የችሎት መድረክ እንዘረጋለን ብለን በገባነው ቃል መሠረት ከደሴ ከተማ እና ከዙፋን ችሎት ተሞክሮ በመውሰድ በሳምንት አንድ ቀን የሚካሔድ የከንቲባ ችሎት መድረክ ፈጥረናል::

በዚህም ረጅም ጊዜ የቆዩ የፍትህ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ችለናል:: ዜጎች ለዘመናት ሲመላለሱበት የነበረውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የከተማው ነዋሪ፣ አስፈጻሚዎች፣ ባለሙያዎች እና አመራሩ ባሉበት በተጨባጭ ምላሽና ፍትህ በመስጠት የከተማውን ነዋሪ ማስደሰት ተችሏል:: ከንቲባ ችሎት ለሕዝባችን ቃል የገባነው መድረክ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል::

አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ የተሟላ ሰላም ቢኖር ከዚህ በላይ ሥራዎችን ማከናወን ይቻል ነበር? በቀጣይስ በከተማዋ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ከማን ምን ይጠበቃል?

አቶ ባዩህ፡- ከተማዋ በችግር ውስጥ ሆናም የሚታዩና የሚጨበጡ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል:: ይሁን እንጂ ጎንደር ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለባት እና ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለው አበርክቶ ቀላል የሚባል አይደለም::

በሰላም እጦቱ የቱሪዝም ዘርፉን ብቻ ወስደን ብናይ በዓመት ግጭት ከመፈጠሩ በፊት በአንድ ዓመት ብቻ ከ160 ሺህ እስከ 200 ሺህ የሚሆኑ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ከተማዋን እንደሚጎበኙና በዚህም ከትኬት ሽያጭ ብቻ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በቀጥታ ይገኝ ነበር:: ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሲሰሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት በከተማዋ ኢኮኖሚ ላይ ፈሰስ ይሆን ነበር::

በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ግን በዘንድሮው ዓመት ማስተናገድ የቻለነው ሁለት ሺህ የሚሆኑ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ብቻ ነው:: የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችም በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል:: የጸጥታው መደፍረስ ባለፉት ዓመታት ለከተማዋ፣ ለክልልና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል:: በሌሎች ዘርፎችም ያሳደረው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው:: ብዙ ርቀት መጓዝ እንዳንችል ያደረገ ነው::

በየትኛውም መንገድ ግጭቶች የሚወስዱን የሀገርን ኢኮኖሚ ወደ ማቀጨጭ በመሆኑ በክልልና በከተማ ደረጃ ይህንን ለመቀልበስ ሰፊ ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተናል:: በከተማዋ አሁን የተገኘው አንጻራዊ ሰላም መከላከያ ሠራዊት እና የአካባቢው የጸጥታ ኃይል የሕይወት መሰዋዕትነት ጭምር ከፍለው ያመጡት ነው:: በሰላሙ መምጣት የሕዝቡም ድርሻ ቀላል የሚባል አይደለም:: አሁን ያገኘነውን አንጻራዊ ሰላም ወደተሟላ ሰላም ለመቀየር የሰላም ካውንስል ተቋቁሞ እየተሠራ ነው::

ግጭት ከችግር ላይ ችግር ከመጨመር ባለፈ የመፍትሔ አካል ሆኖ አያውቅም፤ ስለዚህም ችግሮች በውይይት እና በድርድር እንዲፈቱ መንግሥት፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን የመወጣት ኃላፊነት አለባቸው::

እኛ ለዘመናት ያላሸነፍነው እና ወደኋላ የቀረንበትን ድህነት ማሸነፍ የምንችለው የተሟላ ሰላም ስናገኝ በመሆኑ ጫካ የገቡ አካላትም እጃቸውን ለሰላም ሊዘረጉ ይገባል:: ለዘመናት ያላግባቡንን ችግሮች እንደሚፈታ ታምኖበት እንደ ሀገር የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየተሠራ ነው:: በዚህም ችግሮችን በንግግርና በውይይት መፍታት ስለሚቻል ሁሉም ችግሩን ወደ ጠረጴዛ በማቅረብ ጎንደር የመልማት እድሏን ያልተጠቀመች ከተማ ስለሆነች ሁላችንም የምንቆጭላት፣ የምንወዳት እና ታሪኳን አውቀን በጋራ የምንገነባት ከተማ ማድረግ ይጠበቅብናል::

ሰላም ከማንም አይመጣም:: ሰላም የሚጀምረው ከራስ ነው:: በከተማችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል::

አዲስ ዘመን፡- በ2017 በጀት ዓመት የተያዙ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ባዩህ፡– በ2017 በጀት ዓመት ዋናው የትኩረት አቅጣጫችን የሚሆነው የከተማዋን ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም መቀየር፣ የከተማዋን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ማነቃቃት፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ ከተማዋን ስማርት ሲቲ ማድረግ ነው::

በተለይ ደግሞ አሁን በአዲስ መልክ ወደሥራ እየገባንበት ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ በማጠናከር ከተማዋን ማስዋብ፣ አረንጓዴ መናፈሻ ቦታዎችን መገንባት፣ አገልግሎቶችን ዲጂታላዝድ ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራበት ዓመት ነው::

የልማት እና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ብቻችን የምናከናውነው ተግባር አይደለም፤፤ በመሆኑም ሕዝቡ ከጎናችን ሆኖ እንዲያግዘን ጥሪ አቀርባለሁ::

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን::

አቶ ባዩህ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ::

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You