የሐመር ብሔረሰብ በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን በዋናነት በዞኑ ውስጥ በሐመር ወረዳ ይኖራል። ሐመሮች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ‹‹ሐመር አፎ›› በማለት የሚጠሩ ሲሆን፣ ሌሎች ግን ‹‹ሐመርኛ›› ይሉታል። በኦሞአዊ የቋንቋ ቤተሰብ ሥር የሚመደበው ሲሆን የብሔረሰቡ አባላት ከራሳቸው ቋንቋ በተጨማሪ የበና፣ የአርቦሬ፣ የካራ እና የዳሰነች ብሔረሰቦች ቋንቋዎችን በሁለተኛ ደረጃ ይናገራሉ። የሐመር ቋንቋ ከንግግር ወይንም ከመግባቢያነት አልፎ የትምህርት ወይም የሥራ ቋንቋ ለመሆን አልበቃም።በ1999 ዓ.ም በተደረገ የሕዝብና ቤቶች የቆጠራ ውጤት መሠረትም የብሔረሰቡ ሕዝብ ብዛት 46ሺ532 መድረሱ ይታወቃል።
‹‹ሐመር›› የሚለው የብሔረሰቡ መጠሪያ ቃል በብሔረሰቡ ቋንቋ ‹‹በተራራ እና በድንጋይ መካከል የሚኖሩ፣ የተዋሃዱና የተቀላቀሉ ሕዝቦች›› የሚል ፍቺ እንዳለውና ይህም ትርጉም ታሪካዊ መሠረት እንደያዘ ከብሔረሰቡ አዛውንቶች የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሞ ዊኪፒዲያ የተሰኘ ድረ ገጽ ስለ ብሔረሰቡ ባወጣው መረጃ ላይ ገልጿል። ይህ ትውፊት ሐመሮች ከጥንት ዘመን አንስቶ በትላልቅና ሰንሰለታማ ተራሮች መካከል የሚገኙ የተቦረቦሩ ቋጥኞች ውስጥ ይኖሩ እንደነበር የሚያመላክት እንደሆነ የመረጃ ምንጩ የዕድሜ ባለፀጋዎች እንደሚናገሩ ጠቅሶ አትቷል።
የብሔረሰቡ አባላት ዋነኛ መተዳደሪያ ከብት እርባታ ሲሆን፣ ከዚህ ጐን ለጐን ንብ በማነብ እና በዝቅተኛ ደረጃ ደግሞ በቆሎና ማሽላ ለዕለት ፍጆታ በማምረት ኑሮአቸውን ይመራሉ።
የብሔረሰቡ ታሪካዊ አመጣጥ ጥንት ከ ‹‹ካራ››፣ ‹‹ኦሪ›› እና ‹‹መርሲ›› በመጡ የተለያዩ ማኀበራዊ ቡድኖች ውህደት የዛሬው የሐመር ብሔረሰብ እንደተገኘ ከብሔረሰቡ ታዋቂ ግለሰቦችና የሀገር ሽማግሌዎች የተገኘ አፍአዊ መረጃ ያስረዳል። ከእዚህ የትውፊት መረጃ እና ከላይ የተጠቀሱትን አራት መነሻ ሥፍራዎች መሠረት በማድረግ ብሔረሰቡ ውስጥ ስድስት ማኀበራዊ ቡድኖች መኖራቸውን ይናገራል።
‹‹ቶርቶሮ›› የሐመር ብሔረሰብ አባላት በዓመት አንድ ጊዜ አደባባይ በመውጣት የሚያከብሩት ባህላዊ በዓላቸው ነው። የሚከበረውም በሰኔ ወር መባቻ በእሸት ወቅት ነው።በዓሉም በድግስና በጭፈራ ይከበራል። የጭፈራው ዋነኛ ተዋናዮችም ያገቡ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አዛውንቶች ሲሆኑ ፣ ያላገቡ ወጣቶችና ኮረዶች ሚና ደግሞ ድግሱን በማዘጋጀትና በማስተናገድ ላይ ብቻ የተወሰነ ነው። ‹‹ኢቫንጋዲ ›› የሐመር ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ብቻ የሚሳትፉበት ባህላዊ ጭፈራ ነው። ጭፈራውም በየሦስት ቀን አንዴ እያሰለሰ በሐመር መንደሮች በምሽት ጨረቃ ይካሄዳል።
‹‹ኢቫንጋዲ›› በአዝመራ ወቅት በሥራ የደከመን አእምሮና አካል ለማዝ ናናት ሲባል የሚደረግ ባህላዊ ጭፈራ ሲሆን፣ የሐመር ወጣቶች ከማኀበራዊ ሕይወት ጋር የሚተዋወቁበት አዳዲስ ባህላዊ ዘፈኖችና ጭፈራ ሲሆን፣ የሐመር ወጣቶች ከማኀበራዊ ሕይወት ጋር የሚተዋወቁበት አዳዲስ ባህላዊ ዘፈኖችና የአጨፋፈር ስልቶችን የሚቀስሙበት አጋጣሚ ነው። ከእዚህ በተጨማሪ ሐመሮች የተለያዩ አጋጣሚዎችን ምክንያት በማድረግ የሚጫወቱት ‹‹ኤሬ›› የተባለ ባህላዊ ጨዋታ አላቸው። ኤሬ ወደ ሌላ አካባቢ ወይም ወደ ዘመቻ ለመሄድ ሲታሰብ በፉከራ መልክ የሚከወን ባህላዊ ጨዋታ ነው።
ሀመሮች ለየት ያለ ለጋብቻ የማጨት ስርዓት አላቸው። ይህ የማጨት ስርዓት የሚከናወነው ከብት በመዝለል ሲሆን በብሔረሰቡ ቋንቋ “እኩሊ ቡላ” ብለው ይጠሩታል። በብሄረሰቡ ዘንድ አንድ ወጣት ለጋብቻ ሲደርስ መጀመሪያ “ቦኩ” የሚባል ዱላ ዘመድ በተሰበሰበበት በመውሰድ ከብት ሊዘል መሆኑን በየአካባቢው ላሉ ዘመዶቹ ይናገራል። ለመዝለል ሳምንት ሲቀረው ወጣቶች እና ሽማግሌዎች ባር (ዳስ) ይሰራሉ። ሴቶች የድግስ እህል ይፈጫሉ። ወጣቶች ይጨፍራሉ።
ወጣቱ ከብት በሚዘልበት ቀን ዘመድ አዝማድ ከየቦታው ተሰብስበው ይጨፍራሉ፤ ይበላል፤ ይጠጣል። ሴት ዘመዶቹ ጀርባቸውን በመገረፍ ለወጣቱ ያላቸውን ፍቅር እና ደስታቸውን ይገልፃሉ (ይህ አሁን አሁን እየቀረ መጥቷል)። ወጣቱም ከ20 እስከ 30 በሚደርሱ የተደረደሩ ከብቶች ጀርባ ላይ በመመላለስ ብቃቱን ያሳያል። ከዚህን ቀን ጀምሮ ወጣቱ “እኩሊ ቡላ” (ከብት የዘለለ) ተብሎ የሚያገባት እስክትታጭለት ድረስ ከማር ፣ ወተት እና ስጋ ውጪ እህል አይመገብም።
የእያንዳንዱ ብሔረሰብ አብሮ የመኖር ጥበብ ባህልን እንደ አገር ብንጠቀምበት፤ ተቻችሎ ለመኖር፣ ለመከባበር፣ ለአንድነት እና ለሰላም እንዲሁም ፍትሃዊነትን ለማምጣት ይጠቅማል። አገራችን ኢትዮ ጵያ ከሰባ ስድስት በላይ የሆኑ ብሔር ብሔረሶች በሰላም የሚኖሩባት እንዲሁም ህዝቦቿ ያለ ምንም ዘርና ቋንቋ ልዩነት ተጋብ ተው እና ተዋልደዉ ያቆሟት ውህድ የብሔረሰቦች አገር ናት ።አሁን ባለን በት ወቅት እዚህም እዚያም የሚነሱ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች ፣ዋልታ ረገጥ የሆኑ አስተሳሰቦች እንዲሁም እኔ እና የእኔ ብቻ ከሚል ግለኝነት ለመውጣት ከሐመሮች ባህል ብዙ ልንማር ይገባናል።
አንደኛው የሌላውን መብት እያከ በረ፣ እየተቻቻለ እና የወንድማማች መንፈስን እያዳበረ በፍቅር ለፍ ቅር መኖር እንደሚቻል ካሉን ወር ቃማ ባህል እና እሴት ካላቸው ብሔረሰብ የሐመር ባህል አንዱ ማሳያም ነው። እኛም ያሉንን ባህላዊ እሴቶቻችንን በመጠቀም ለአገር አንድነት እና ሰላም መጠቀም ይገባል እንላለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
አብርሃም ተወልደ