ኪነ ጥበብ ለአንድ ሀገር ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል። የህዝቦችን ቀደምት ታሪክ፣ ማንነትንና አብሮነትን በመስበክ የአንድ ሀገር ህዝቦችን የጋራ የሆነ ስነ ልቦና እንዲኖራቸው የማድረግ አቅም አለው። ስለ ልዩነትና ዘረኝነት የሚሰራ ከሆነም ችግሩ በዛው ልክ አስቸጋሪና ውስብስብ መሆኑን የሚናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር መምህር አቶ ምንያህል በንቲ ይናገራል።
በተለይ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሀገርና በህዝብ ላይ ለውጥ የማምጣት ሚናው የጎላ ነው። ወገንን በማስተባበር ለወገን መድረስ ይችላል። ህዝብን በከፍተኛ ሁኔታ የማነቃነቅና የመቀስቀስ ጉልበት አለው። ለችግሮቻችን በጋራ እንድንቆም የማድረግ ጉልበት አለው። የኪነ ጥበብ ሥራዎች ድንበር የላቸውም። የሁሉንም ስሜት መያዝና ሥራዎችንም ዘር፣ ሃይማኖት ሳይለዩ የሰውን ስሜት ሰርስሮ የመግባት አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን ያብራራሉ።
የቴአትር መምህሩ እንደሚሉት ኪነ ጥበብ ከፍተኛ ተሰሚነት አለው። በማህበረሰቡ ላይ ያሉንን መልካም ነገሮች በኪነ ጥበብ በማጠንከር ህዝቡን አስተባብሮ ወደ አንድነት ለማምጣት ይረዳል። የሚያዋድዱንና የሚያፋቅሩን ነገሮች ላይ ሥራ ቢሰራ ለሀገር አንድነት ጠቀሜታ አለው። በአርት ማህበረሰቡን ወደ አንድነት ማምጣት ይቻላል። የሃይማኖት የብሄር ክፍፍሎች እንዳይመጡ ይከላከላል።
በየክልሎች ያሉ ባህላዊ የእርቅ አፈታት ሥርዓቶቻችን ማራኪ በሆነ መን ገድ ብናቀርባቸው ማህበረሰቡ ይማር ባቸዋል። የማስተማር አቅማቸውም ትልቅ ነው የሚሉት መምህር ምንያህል ቴአትር ማህበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ ክፉ ሀሳቦችን ማጥፋት ይችላል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ላይ የመጣውን መፈናቀልና አለመተማመን ለመመለስ ኪነጥበብ ትልቅና ዋነኛ መንገድ መሆኑን ነው የሚጠቅሱት።
“በኛ ሀገር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በነበረው የህዝብ መፈናቀል ላይ የሚጠበቅባቸውን ያህል ሥራ አልሰሩም” የሚሉት መምህሩ በምሳሌነት ያነሱት አሜሪ ካኖችን ነው። የአሜሪካኖች ‹‹የፊልም ደራሲዎች ብዙ ልዩነቶች አሏቸው። ነገር ግን በሀገራቸው ጉዳይ አንድ›› ናቸው። የሀገራቸውን ትልቅነት በኪነ ጥበባቸው አሳይተዋል። በኛ ሀገርም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ስለሀገራችን መስበክ ይኖርባቸዋል። ኪነ ጥበብን መሰረት አድርጎ ህዝብ ላይ ከተሰራ የምናያቸው የእርስ በርስ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ ስደትና የተለያዩ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ እንደሚቻል ይናገራል።
‹‹ቴአትር ልማት›› ነው። በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮች መቅረፍ መቻል ነው። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብዙ ጥናታዊ ፁሑፎች አሉ። መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ወደ ፊልም ቢቀየሩ ህብረተሰባችንን ብዙ ማስተማር ይችላሉ። በአሁኑ ጊዜ የማህበረሰባችን ችግር የመፈናቀል ብቻ አይደለም፤ የሥራ እጥነት፣ የፈለጉት ቦታ ሂዶ ያለመስራትና የነፃነት ችግርም ነው። እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚቻለው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም ፈትሸው መስራት ሲችሉ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ምንያህል ኪነ ጥበብ የማይፈታዉ ችግር የለም ሲሉ ይገልፃሉ። በንጉሱና በደርግ ጊዜ ኪነ ጥበቡ ትልቅ ቦታ ነበረው። ደርግ የሶሻሊዝምን አስተሳሰብ ወደ ህብረተሰቡ ለማስረፅ ሙዚቃንና ግጥምን እንደ ዋና መሳሪያነት ተጠቅሞበታል።በዚህም ውጤታማ ነበር ይላሉ።
በተለይ ደግሞ የንጉሱን አገዛዝ ይቃወሙ የነበሩ ሰዎች ተቃውሟቸውን የሚገልፁት በኪነ ጥበብ ነው። የሀገር አስተዳዳሪዎችም ኪነ ጥበብን በመጠቀም በህዝብ ከፍተኛ የሆነ ተቀባይነትን ማግኘት ችለዋል። መንግሥታቸውንም በሚገባ ሁኔታ ለህዝብ አስተዋውቀውበታል። ፍቅር እስከመቃብር በወቅቱ የነበረውን የፊውዳል ሥርዓት ለመቃወም ሲባል በፍቅር አምሳል ተመስሎ የተከፈለ ህይወትን ነው የሚያሳየን። እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሀሳባቸውን በግጥም፣ በቴአትር ድርሰት የሥርዓቱን አገዛዝ ይቃወሙ ነበር። ጥሩም ይሁን መጥፎ ሥርዓትን መቀየር ችሏል። ይህ የኪነ ጥበብ አቅም ነው። ብዙ ችግሮችንም በሙዚቃና በመጣጥፍ መፍታት ተችሏል። አሁንም ለኪነ ጥበብ ቦታ በመስጠት የችግሮቻችን ሀሳብ ማፈላለጊያ ማድረግ እንደሚቻል ይገልፃል።
አሁን ለኪነ ጥበቡ ቦታ አልተሰጠውም የሚሉት መምህር ምንያህል፤ ይህ ሁኔታም በማህበራዊ ኑሯችን ችግር እየፈጠረብን ይገኛል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከሉ እንደበፊቱ የሀገራችንን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት አይሰራም። ያለው የፖለቲካ ስርዓት እንዳያንሰራራ አድርጎታል። አርት አንድ ሀገርን የመገን ባትና የማፍረስ አቅም አለው። ብዙ ሀገሮች ለአርቱ ትኩረት በመስጠታቸው አንድ ነታቸውን ማጠንከር ችለዋል። የሀገራቸው የኢኮኖሚ ማማ እንዲሆን አድርገዋል። ሀገራቸውን ለማስተዋወቅና ትልቅ ቦታ ለማድረስ በቅተዋል።
አቶ ምንያህል ይህን አሉ “ለኪነ ጥበቡ ትኩረት ባለመስጠታችን ብዙ ከስረናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ ችግሮች ከኪነ ጥበቡ ጋር ግንኙነት አላቸው። የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ደግሞ ለብርና ለዝና መስራታቸውን ትተው ለማህበረሰቡ ጥቅምና ህይወት መስራት ቢችሉ ሀገራ ችንን መለወጥ ይቻላል። ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚለው አስተሳሰብ አንድ ወቅት በኪነ ጥበብ በመቀንቀኑ በሰው አዕምሮ ውስጥ ማስረፅ ተችሏል። ሙዚቀኞቻችን የሚያዘጋጁት የሙዚቃ ድግስ ቁርስና ምሳ ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም፤ከዚህ በዘለለ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ተመልሰው ቁርስና ምሳቸውን መብላት እንዲችሉ የሚያደርግ ሥራን መስራት አለባቸው።”
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሚሰሯቸው ሥራዎች መጠንቀቅ እንዳለባቸው አቶ ምንያህል ይናገራሉ። “በሀገራችን የሚሰሩ ሥራዎች እኛን የሚገልፁ አይደሉም። የእኛን ማህበረሰብ ኑሮ ማንፀባረቅ አይችሉም። የኛ ማህበራዊ ኑሮ ጠንካራ ተዋዶና ተከባብሮ ሙስሊሙና ክርስትያኑ ሃይማኖትና ብሄር ሳይገድበው አብሮ የሚኖር ነው። የተቸገሩትን የምንረዳ። አርት ደግሞ ይህን መንገሪያ መንገድ ነው። ነገር ግን ፊልሞቻችን የማንኖረውን ነው የሚያሳዩን። ማንነታችንን አያሳዩንም። ይህ ሁኔታ ችግሮቻችንን ከመፍታት ይልቅ ችግር እያመጣብን ነው“ ሲሉ ይተቻሉ።
ያለንን መልካም ነገር በአግባቡ መጠቀም ብንችል በአሁኑ ጊዜ ኪነጥበብ አድማጭም ተቀባይም እንዳለው ይናገራሉ። በአርት ዙሪያ የሚሰሩ ሚዲያዎች ተስፋፍተዋል። ኪነ ጥበባችን ትክክለኛውን የሀገራችንን ታሪክና ኢትዮጵያዊነትን ማስተዋወቅ መቻል አለበት። የምንሰማው ታሪካችን በጣም አጭርና የትንሽ ጊዜ ዓመት ነው። ኪነጥበቡን ተጠቅመን የተዛባ ታሪካችንን ማስተካከል ችግሩን እንደሚያቀል ይናገ ራል።
አርቲስት ኢሳያስ በለጠ በበኩሉ ሁሉም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በመጀመሪያ ሀገራቸውን ማስቀደም እንዳለባቸው ይገልጻል። ሀገርን ታሳቢ ተደርጎ የተሰራ ሥራ ሰላም አለው። ከሀገር በፊት የራስን ጥቅም ማስቀደም ለሀገር ሰላም ሳይሆን ውድቀት ነው። በተለይ ደግሞ አሁን ያለንበት ወቅት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሀገራቸው የሚሰሩበት ጊዜ መሆን እንዳለበት ይናገራል። ሁሉም የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከምን ጊዜውም በላይ ለሀገራ ችን ያስፈልጓታል። ሁሉም ባለሙያ ራሱን አሳልፎ መስጠት አለበት። የኪነ ጥበብ ሰዎች መስራት ከቻሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። የምንሰራው ሥራዎችም ዘመን ተሻጋሪና ትውልድን ማስተማር የሚችሉ መሆን አለባቸው ።
የኪነ ጥበብ ባለሙያው አንድ ሆኖ ለአንድ አላማ መስራት አለበት የሚለው አርቲስት ኢሳያስ አሁን ያለው የኪነጥበብ ሥራዎች አዲስ አበባን ብቻ ማዕከል ያደረጉ ናቸው። ነገር ግን ለውጥ ለማምጣትና ትውልዱን ለማስተማር በገጠርና በመላው ሀገራችን እየተዘዋወሩ መስራት ይኖርባቸዋል። በተለይ ደግሞ ባለሙያዎች ገንዘብን ትኩረት አድርገው ከመስራት መውጣት አለባቸው። በዚህ ወቅት እየተሰሩ ያሉ ድራማዎችና ዘፈኖች አንድነታችንን የሚያጠናክሩ አይደሉም። በሀገራችን ከመቶ ዘጠና በላይ ሲኒማ ቤቶች አሉ። ነገር ግን ትኩረታቸው ገንዘብ ላይ ብቻ ነው። ሀገርንና ትውልድን ታሳቢ አድርጎ መስራት ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ያስረዳል።
የዘርፉ ባለሙያዎች ኪነ ጥበብ ትልቅ ጉልበት እንዳለው አምነው ሀገርን አንድ በሚያደርግ ሥራ ላይ መረባረብ ይኖርባቸዋል። በተያዘው በክረምቱ ወቅት ሙያቸውን በመጠቀም ጎዳና ላይ የወደ ቁትን ማንሳት፣ ስለ አንድነትና መቻቻል መስበክና ማስተማር ቢቻል ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አስገንዝቧል።ኪነጥበብ ጉልበቷ ጠንካራ ውጤቷም ኃያል ነውና።
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
ሞገስ ፀጋዬ