2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ ዛሬ ይጀመራል

በዘመናዊው ኦሊምፒክ ጠንሳሽነታቸው ‹‹የኦሊምፒክ አባት›› የተሰኙት ፒየር ደ ኩበርቲን ሀገር ፈረንሳይ 33ኛውን ኦሊምፒያድ ዛሬ በድምቀት ታስጀምራለች፡፡ ከ100 ዓመታት በኋላ ለሶስተኛ ጊዜ የአስተናጋጅነት ዕድልን ያገኘችው ፓሪስ፤ ታላቁን ውድድር ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ የመክፈቻ መርሃግብሩን ከስታዲየም ውጪ ለማካሄድ አስባለች። አስደናቂ የተባለው ይህ የውድድር ማስጀመሪያ በፓሪስ ሰሜናዊ ክፍል የተንጣለለውና ዘወትር የመዝናኛ ጀልባዎች በሚንሸራሸሩበት ሴን ወንዝ ላይ የሚከናወን ሲሆን፤ ተሳታፊ ሀገራትም ባንዲራቸውን ይዘው የሚታዩት በተዘጋጁላቸው 94 ጀልባዎች ላይ ሆነው ነው፡፡

ታላላቅ የእግር ኳስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታዎች፣ ሁለተኛው የዓለም ትልቁ የጎዳና ሩጫ የፓሪስ ማራቶን፣ ፈታኙ የብስክሌት ግልቢያ ‹‹ቱር ደ ፍራንስ››፣ ዝነኛው የሜዳ ቴኒስ ‹‹ፍሬንች ኦፕን››፣ የኦሊምፒክን ደረጃ በሚያሟሉት የዋና ገንዳዎች የሚያስተናግዷቸው ቻምፒዮናዎች፣ የፈረስ ግልቢያ፣ የራግቢ እና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች ወትሮም ፓሪስ ላይ ከ‹‹ኤፍልስ›› ማማ ስር የሚከወኑ ታላላቅ ስፖርታዊ ሁነቶች ናቸው። አሁን ደግሞ ውቧ የመዝናኛ ከተማ የዓለም ትልቁን የስፖርት ውድድር ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ታስተናግዳለች፡፡

የስፖርታዊ ውድድሮች ሁሉ በኩር ለሆነው ኦሊምፒክም ሀገሪቷ 9 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያደረገች ሲሆን፤ ከስፖርት ቱሪዝም እንዲሁም ከውድድሩ ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ እስከ 12 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች ተብሎም ይጠበቃል። በሀገሪቷ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እንዲሁም በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባኽ የሚመራው የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ሲታደሙ፤ ሴሊን ዲዎን እና ሌዲ ጋጋን የመሳሰሉ የሙዚቃው ዓለም ከዋከብት በድምጻቸው ያደምቁታል፡፡ 300ሺ የሚሆኑ ሰዎች በፓሪስ ተገኝተው ታሪካዊውን ዝግጅት ሲመለከቱ፤ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ በመላው ዓለም በቴሌቪዥን መስኮት ይከታተላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከ206 ሀገራት የተውጣጡ ከ10ሺ በላይ ስፖርተኞች (በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ስር የሚወዳደሩ ስደተኛ አትሌቶችን ጨምሮ) ለባንዲራቸው ክብር ይፋለማሉ፡፡ በ35ቱ የማዘውተሪያ ስፍራዎችም በ32 የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮቻቸውን ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ዓመት በብቸኝነት ኦሊምፒክ ላይ የተካተተው የውድድር ‹‹ብሬክ›› የተባለው የዳንስ ዓይነት ሲሆን፤ በኦሊምፒክ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የሴቶችና የወንዶች ተሳትፎ እኩል ሆኖ የተመዘገበበትም ነው፡፡

ፈረንሳይ ታሪኳንና ባህሏን በምታንጸባርቅበት በዚህ ውድድር ላይ አሸናፊ አትሌቶች የሚያጠልቁት ሜዳሊያዎች ታዋቂው የኤፍል ታወር በተገነባበት የብረት ዓይነት ቅንጣት የተዘጋጀና ከጀርባውም ምስሉ ያረፈበት ነው፡፡ በአጠቃላይም 329 የወርቅ ሜዳሊያዎች አሸናፊ አትሌቶችን በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለአሸናፊ አትሌቶች እንደየደረጃቸው ሜዳሊያ የሚያበረክት ቢሆንም፤ ዘንድሮ በመምና የሜዳ ተግባራት አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች 50ሺ ዶላር የሚሸልም የዓለም አትሌቲክስ የመጀመሪያው የስፖርት ማህበር ይሆናል፡፡

የኪነጥበብ፣ የስፖርትና የመዝናኛ ከተማ የሆነችው ፈረንሳይ ኦሊምፒኩን ተከትሎ የገነባችው ብቸኛው የማዘውተሪያ ስፍራ ዘመናዊው የውሃ ስፖርቶች ማዕከል ብቻ ነው፡፡ ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ የሚገኙት በተለያዩ አካባቢዎች ይሁን እንጂ እያንዳንዳቸው ከኦሊምፒክ መንደሩ ያላቸው ርቀት በአማካይ 5 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ በመሆኑም ደጋፊዎች ከአንዱ የማዘውተሪያ ስፍራ ወደሌላኛው ለማቅናት በእርምጃ፣ በብስክሌት አሊያም በተዘረጋው የከተማ መጓጓዣዎች በቀላሉ መጠቀም ይችላሉ፡፡

የውድድሮች ሁሉ ቁንጮው ኦሊምፒክ መክፈቻ ውን ዛሬ ያድርግ እንጂ በአንዳንድ ስፖርቶች ቀናትን አስቀድሞ ነው ውድድር ማካሄድ የተጀመረው። ኢትዮጵያ የምትጠበቅበትና በመድረኩ እጅግ ትኩረት ሳቢ የሆነው የአትሌቲክስ ውድድር ደግሞ ከቀናት በኋላ ይጀመራል፡፡ 11 ዕለታትን በሚሸፍነው አትሌቲክስ 48 ውድድሮች ሲደረጉ፤ ከ2ሺ በላይ የሚሆኑ አትሌቶች ለ 144 ሜዳሊያዎች ሊፎካከሩ ተዘጋጅተዋል፡፡ የመም እና የሜዳ ተግባራት ፉክክሮች በምሽት የሚከናወኑ ሲሆን፤ የጎዳና ሩጫዎች ደግሞ ጠዋት ላይ የሚደረጉ መሆናቸውን የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል፡፡ አብዛኛዎቹ ውድድሮችም የሚደረጉት በፓሪስ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘውና ከ80 ሺህ በላይ ደጋፊዎችን በሚይዘው የፓሪስ ስታዲየም ነው፡፡ የዓለም ዋንጫን ጨምሮ የአውሮፓ ቻምፒዮና እና ሌሎች ውድድሮችን ያስተናገደው ስታዲየሙ በታወቀበት ድምቀቱ ኦሊምፒክንም ያካሂዳል፡፡

በተወዳጁ የእግር ኳስ ስፖርት 16 ሀገራት በአራት ምድብ ተከፍለው የሚወዳደሩ ሲሆን፤ ጊኒ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ እና ማሊ፣ በሴቶች ደግሞ ዛምቢያ እና ናይጄሪያ አፍሪካን የሚወክሉ ቡድኖች ናቸው፡፡ ጨዋታዎቹም በሀገሪቱ ትልቁ የእግር ኳስ ክለብ በሆነው ፓሪስ ሴንት ዠርማ ስቴድየም ፓርክ ደ ፕሪንስን ጨምሮ በ7 የተለያዩ ስታዲየሞች የሚከናወኑ ይሆናል፡፡ በ‹‹ፍሬንች ኦፕን›› የሜዳ ቴኒስ ውድድሮች የሚታወቀው ሜዳ ተፈጥሯዊ ሁኔታውን ሳይለቅ ከዋክብቱን ያስተናግዳሉ፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You