በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገ ነው

  • ኮሚቴ ተዋቅሮ ተጨማሪ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ ተጀምሯል

አዲስ አበባ፡- በጎፋ ዞን ከተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተረፉና ከአካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖችን ኮሚቴ በማቋቋም ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡ ከ400 መቶ ኩንታል በላይ የሚሆን እህል መቅረቡንም ተመላክቷል፡፡

የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ፣ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ ከትናንት በስቲያ ረፋድ አካባቢ በተከሰተው የመሬት መሸራተት አደጋ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ 229 በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

የፌዴራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር 400 መቶ ኩንታል በላይ የሚሆን እህል፣ አልባሳት፣ መመገቢያና ማብሰያ ቁሳቁሶችን የማቅረብ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የአስቸኳይ አደጋ ጊዜ መልሶ ማቋቋሚያ ኮሚቴ ተቋቁሞ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በአካባቢው በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የመሬት ናዳ በአንድ የቤተሰብ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ እነሱን ለማትረፍ በወጡት የአካባቢ ነዋሪዎች፣ የፀጥታ አካላት እና የቀበሌ አመራሮች ላይ ተጨማሪ የመሬት መሸራተት አደጋ በመከሰቱ የሟቾች ቁጥር ከፍ ማለቱን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በአካባቢው የመሬት መንሸራተት አደጋ በተደጋጋሚ እንደሚከሰት የገለጹት ወይዘሮ ሰናይት፤ በዚህኛው አደጋ በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

በአደጋው ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውና በሕይወት የተገኙ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ሰናይት ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ከአደጋው የተረፉና የተፈናቀሉ ወገኖችን በአካባቢው በሚገኙ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች በጊዜያዊነት የማስጠለልና የዕለት ደራሽ ምግብ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

የተጎዱ ዜጎችን መደገፍና የነፍስ አድን ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ ሰናይት፤ በአካባቢው ተጨማሪ ጉዳት እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲደረግም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የሟቾች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት አስከሬን የመፈለጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ወይዘሮ ሰናይት ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ እና ከአጎራባች ክልሎች እና ዞኖች የተውጣጡ ባለሙያዎች በሥፍራው በመገኘት ለተጎጂዎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

Recommended For You