ዲዛይነር ለመሆን የተገኘችበት ቤተሰብ መነሻ እንደሆነ ታነሳለች :: ‹‹ ገባይል ፎር ኦል ›› የተሰኘ የፋሽን ዲዛይን መስራች፣ ዲዛይነርና ዳይሬክተር ናት:: የፋሽን ዲዛይን ልብሶችን ከመሥራት ባሻገር የሀገራዊነት ስሜትን የሚያንጸባርቁ ውበትን ወጣትነትን የሚገልጹ ሃሳቦቿን የምታሳርፍባቸውን ሥራዎቿን ወደ ገበያው ይዛ ቀርባለች::
ዲዛይነር መሆን የልጅነት ፍላጎቷ በመሆኑ አሁን ያለችበት ደረጃ ለመድረስ ቀላል የማይባሉ መንገዶችን አልፋ አሁን የደረሰችበት ላይ ትገኛለች:: በዛሬው የሴቶች ገጽ ላይ ሙያዋን በመጠቀም መልዕክት ማስተላለፍ የሚችሉ ልብሶች ከምትሰራ እና የራሷን የፋሽን ዲዛይን ብራንድ ገንብታ በሥራ ላይ ከምትገኝ ዲዛይነር ጋር ቆይታ አድርገናል:: መልካም ንባብ …
ገባይል አሰግድ ትባላለች:: የስሟ ትርጓሜም ሕዝባዊት የብዙ የሆነች የሚል ነው:: ሥራዎቿንም በስሟ ስትሰይመው አላማው ብዙዎች ጋር መድረስ የሚችሉ ልብሶችን ሰርቶ ለማቅረብ ነው:: ‹‹ በባህሪዬ ለሀበሻ ልብሶች ቅርብ ነኝ ፤ ነገር ግን የሀበሻ ልብሶች የበዓላት ወቅትን ብቻ ጠብቀው ነው የሚለበሱት የሚለውን ሃሳብ አልስማማበትም ›› የምትለው ገባይል የምትሰራቸው ልብሶች ሰዎች የሀበሻ ልብስን ለሥራ፤ ለመዝናኛ ቀናት እና በፈለጉት ሁነት እና ቦታ በነፃነት እንዲጠቀሙበት ትፈልጋለች::
ገባይል ወደ ፋሽን የተሳበችበትን አጋጣሚ ስትገልጽ ‹‹እናቴ በቤት ውስጥ የተለያዩ ልብሶችን ትሰራ ነበር:: አያቴም 10 ልጆች ስለነበሯት በራሷ መስፊያ ማሽን የተለያዩ ልብሶችን ትሰራላቸው ነበር::›› በተጨማሪም ገባይል የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በተከታተለችበት የናዝሬት አንደኛ ደረጃ የሴቶች ትምህርት ቤት ራሱን የቻለ የእጅ ሥራ ትምህርት ነበር:: በዚህ ሰዓት ገባይል ሥዕል የእጅ ሥራ ክህሎትን በይበልጥ እንድትለምደው እና ፍላጎቱ እንዲያድርባት ሆነ:: ታዲያ በልጅነት እድሜዋ ለመጫወቻነት የሚገዙላትን አሻንጉሊቶች ቤት ውስጥ ያገኘችውን ጨርቅ እየቀደደች ፣ እየለካችና እየቆረጠች ለአሻንጉሊቶቿ ልብሶችን ትሰራለች::
የፋሽን ዲዛይን ፍላጎት ያደረባት ገባይል ይበልጥ እንድታውቀው የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤት ገብታ መማርን ፈለገች፤ ነገር ግን ትምህርቷን ጭራሽ እንዳትተወው ስጋት ያደረባቸው እናት በዚህ እድሜ ወደ ፋሽን ማዘንበሏን አልወደዱትም ነበር:: ገባይል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ምህንድስና ትምህርትን መማር ጀመረች:: የምትማረው ትምህርት ትኩረት የሚጠይቅ እና የፋታ ጊዜ የማይሰጥ ቢሆንም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም የራሷን ልብሶች በምትፈልገው መንገድ ዲዛይን በማድረግ የፋሽን ዲዛይን ክህሎቷን በምትለብሳቸው ልብሶች ላይ ታንጸባርቅ ነበር::
የመካኒካል ምህንድስና አራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለች ለፋሽን ዲዛይን ያላትን ፍላጎት የተረዳው ወንድሟ የፋሽን ዲዛይን ትምህርትን እንድትማር አገዛት እሷም ቀን ቀን በረዳት መካኒክነት ማታ ደግሞ ፋሽን ዲዛይን መማሯን ቀጠለች:: የፋሽን ዲዛይን የአንድ ዓመት ስልጠናዋን ስታጠናቅቅ በረዳት መካኒክነት ለስድስት ወር ያክል ጊዜ ሰራች:: የመካኒካል ምህንድስና ትምህርት ቀላል የሚባል አይደለም የምትለው ገባይል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ስታጠናቅቅ በትምህርት ክፍሉ ከተመረቁ ስምንት ሴቶች ውስጥ አንዷ ነበረች::
‹‹የፋሽን ትምህርት ቤት እንደገባሁ አስብ የነበረው ቶሎ ዲዛይነር መሆን ነበር:: ነገር ግን ሥዕል መሳል ጨርቅ መቁረጥ እንዲሁም መስፋት ዲዛይነር አያስብልም የእነዚህ ሁሉ ክህሎቶች ድምር ዲዛይነር የሚለውን እንደሚፈጥር ተረድቻለሁ:: ›› በማለት የነበራትን የትምህርት ቆይታ ታስታውሳለች:: ትምህርቷን እንደጨረሰች ታላቅ ወንድሟ በገዛላት ማሽን ይበልጥ የራሷን ሥራዎች እንድትሰራ እና ችሎታዋን እንድታሳድግ ረዳት:: ከመመረቋ በፊትም በቅርቧ ላሉ ጓደኞች እና ወዳጆቿ የተለያዩ ልብሶችን በመሥራት ቢዝነሷን ጀመረች::
ገባይል የምህንድና ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤት ከተዋወቀቻት ጓደኛዋ ጋር ሃሳባቸውን እና የወሰዱትን ትምህርት እንዴት ወደ ገበያ እንቀይረው በሚል ተማከሩ ፤ ከቤተሰቦቻቸው ባገኙት መነሻ ገንዘብም የራሳቸውን ሱቅ መለያ ስም አልያም ብራንድ አውጥተው ቀጥታ ወደ ሥራ ገቡ:: ይህም ገባይል የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን በጨረሰች ማግስት ነበር:: ‹‹የተለያዩ የልብስ ትእዛዞችን በራሳችን እየተቀበልን እንሰራ ነበር:: የምናውቅ የመሰሉን ነገር ግን ብዙ የማናውቃቸውን በንግድ ሥራ የሚያጋጥሙ ሁነቶችን አስተናግደናል ተምረንበታል::›› የምትለው ገባይል ደንበኞችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው ፣ የታዘዟቸውን ምርቶች ጊዜውን ጠብቆ በጥራት ማድረስ፣ ገበያው ላይ ለመቆየት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ፣ ዋጋ ማውጣት ለተከራዩበት ሱቅ ከፍተኛ ክፍያ መጠየቅ እና ጓደኝነትና ቢዝነስን አብሮ ማስኬድ ከተፈተኑባቸው ጉዳዮች ውስጥ መሆኑን ታነሳለች::
በጣም ጥሩ የሚባሉ የሕይወት ልምዶች ከባድ የሚባሉት ጊዜያት ናቸው የምትለው ወጣቷ ዲዛይነር ከጓደኛዋ ጋር በነበራት የሥራ ቆይታ ብዙ መማሯን ትናገራለች:: ‹‹ከቤተሰብ ተበድረን ስለነበር ሥራውን የጀመርነው ለተከራየንበት ሱቅ የምንከፍለውን ክፍያ በፍጹም ከቤተሰብ አልጠየቅንም ባናተርፍም ግን የመጀመሪያውን ፈተና ተወጥተነዋል ብዬ አስባለሁ::›› ትላለች:: ሥራውን ለመጀመር የመረጡት የሥራ ቦታ ከፍተኛ ክፍያ መጠየቃቸው ፣ የራሳቸውን ደንበኞች ሳይገነቡ መጀመራቸው እንደ ፈተና የሚነሱ መሆናቸውን ጠቅሳለች::
በዚህ ሥራ ውስጥ አንድ ዓመት ያክል ጊዜ ከሰሩ በኋላ ቢዝነሱ አንድ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ቢሆንም የሁለት ሰዎች እይታ የሚንጸባረቅበት በመሆኑ በሥራቸው መሀል የሌሎች ጉዳዮች ግፊትም ተጨምሮበት በሃሳብ አለመስማማት እንደነበር ገባይል ታስታውሳለች:: ሥራቸው መቀጠል ባለመቻሉ ያሏትን ደንበኞች እና ሙያዋን ይዛ ከቤቷ መሥራት ጀመረች:: ‹‹ አሁን ባለንበት ኢኮኖሚ አብሮ መሥራትን እጅግ በጣም እደግፋለሁ፤ መተጋገዝ ይኖራል ነገር ግን አብሮ መሥራት ሕጋዊ መንገድን የተከተለ በሰነድ ማስረጃ የተደገፈ መሆን አለበት:: ›› ስትል ትገልጻለች::
በተጨማሪም በጓደኝነት ውስጥ የተጀመረ ማንኛውም ሥራ የታለመለትን ውጤት እንዲያመጣ ሥራው ከጓደኝነት መብለጥ አለበት የሚል ሃሳብ አላት:: ይህም በጉርብትናው አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን ሥራው ግን እንዲቀጥል ያስችላል ስትል ትገልጻለች::
‹‹እንደተመረቅኩ ሥራውን ስጀምር ቤተሰቦቼ በዙርያዬ ያለ ሰው ሊመክረኝ ወይም ይከብድሻል ተብዬ ነበር:: ነገር ግን ሁሉንም ነገር ከሰው አንማረውም፤ ራሳችን ሞክረን ወይ ወድቀን እስካልተማርነው ድረስ አምነን አንቀበለውም:: በሥራ ውስጥ ደግሞ ውድቀት ያለ ነገር ነው::›› የምትለው ገባይል በዙርያዋ መልካም የሚባሉ ድጋፎችን በማግኘቷ በቤተሰቦቿ ዘንድ ይበልጥ እንድትሰራ ድጋፍን ማግኘቷን በመንፈሳዊ ሕይወቷ ያላት ጥንካሬም እንደጠቀማት ትናገራለች::
ገባይል የፋሽን ዲዛይን ሥራ ከቤቷ ለመጀመር ስታስብ ሌላ ከባድ ነገር በሕይወቷ አስተናገደች ፤ እሱም የአባቷ ማረፍ ነበር:: ‹‹ በወጣትነት እድሜያችን የሚያስደስተን ነገር በጣም ውስን ነው ቤተሰብ ፣ ጓደኛ ጥቂት ነው በመሆኑም አባቴን ማጣቴ እና የደረሰብኝ ኪሳራ እንደ ወጣት እጅግ በጣም ከብዶኝ ነበር::›› ትላለች::
በዚያን ወቅት አፍሪካን ሞዛይክ የተሰኘ በየዓመቱ ለፋሽን ዲዛይነሮች የሚሰጥ የስልጠና ፕሮግራም ይፋ ሲሆን ስልጠናው ብዙ ዲዛይነሮች የሚፈልጉት ቢሆንም ገባይል በሰዓቱ ይህን ስልጠና ለመውሰድም ሆነ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለመግባት የስሜት ዝግጁነት አልነበራትም:: ‹‹ ለወላጆቼ ብቸኛ ሴት ልጅ ስሆን ከአባቴ ጋር በጣም ጥብቅ ግንኙነት ነበረኝ፤ በመሆኑም የአባቴን ህልፈት መቀበል አቅቶኝ ነበር ፤ ስልጠናውንም ልወስድ የቻልኩት በእናቴ ግፊት ነው::›› ስትል ሁኔታውን ትገልጻለች::
የአፍሪካን ሞዛይክ ስልጠና የወሰዱ ዲዛይነሮች የራሳቸውን ሃሳብ የሚያንጸባርቁበት የሃሳብ ንድፍና የእጅ ሥራዎቻቸውን ውጤት እንዲያቀርቡ በስልጠናው ማብቂያ ላይ ይደረጋል:: ገባይል የአባቷን ህልፈት ተከትሎ የጭንቀት ስሜትን ለተወሰኑ ጊዜያት አስተናግዳ ያለፈች ሲሆን በዙርያዋም ከዚህ ስሜት መውጣት ያልቻሉ አለፍ ሲልም ራሳቸውን እስከ ማጥፋት ድረስ የደረሱ ሰዎች ነበሩ:: ‹‹ ስለ አዕምሮ ጤና የነበረኝ አመለካከት ልክ እንደ ሌላው ሰው ከሃይማኖታዊ ነገር ጋር የተገናኘ ነበር:: አዕምሮ እንደ ማንኛውም ሰውነታችን ክፍል ታክሞ መዳን የሚችል ነው:: ሰዎች እንደመሆናችን በተለያየ የሕይወት መንገድ ውስጥ እንሰበራለን፤ ነገር ግን አንገጣጠምም ማለት አይደለም:: የአዕምሮ ጤናን በሕክምና ከሰዎች ጋር በማውራት እና ከራሳችን ሌላ እድል በመስጠት ማሸነፍ እንችላለን::›› በማለት ከደረሰባት ችግር የወጣችበትን ዘዴ ትናገራለች::
ገባይልም ይህን የጭንቀት ወቅት ከሥራ ጋር የተገናኙ ስልጠናዎችን በመውሰድ ሥራዋ ላይ በማተኮር እና በሥራ በመወጠር ከዚህ የጭንቀት ስሜት መውጣት ችላለች:: ሰዎች ሁልግዜም እንደ አዲስ የሚያስተናግዱት የማይለምዱት ስሜት ተብሎ የሚወሰደው በሕይወታቸው ውስጥ ቦታ የሚሰጡት የሚወዱትን ሰው ማጣት ነው:: ገባይል ሀዘንን የምናስተናግድበት መንገድ ማየት ይገባል ትላለች ‹‹ሀዘን አምስት ሂደቶች አሉት፤ የመጀመሪያው ድንጋጤ ነው:: ከዚያም ንዴት ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ እውነታውን መካድ አልያም መቀበል አለመፈለግ ፤ ሌሎች ሰዎች ላይ መጠቆም ፤ አልያም ተጠያቂ ማድረግ ሲሆን ድብርት ውስጥ መግባት ከዚያም አለፍ ሲልም ሁኔታውን ወደ መቀበል ይደርሳል:: የብዙ ሰዎች ችግር ግን ከእነዚህ ሂደቶች ላይ በአንዱ በጣም በመቆየት ራሳቸውን ወደ መጉዳት ጥሩ የማይባል የባህሪ ለውጥ ሲያመጡ እናይባቸዋለን::›› በማለት ያለፈችበት የድባቴ እና የጭንቀት ወቅት ታስታውሰዋለች::
ገባይል ስለ አዕምሮ ጤና ጥናት ካደረገች በኋላም ‹‹ከድባቴ ጀርባ ያሉ ውብ ልቦች የሚል መጠሪያ ያለው›› ሥራዎቿን ይዛ ቀረበች:: በአፍሪካን ሞዛይክ ላይ ይዛ የቀረበችው ስብስብም በጀርመን ሀገር በርሊን የፋሽን ሳምንት ‹‹ኒዮ የፋሽን መድረክ›› ላይ ኢትዮጵያን ወክላ ሥራዎቿን ይዛ የመቅረብ እድሉን አገኘች:: በዚያም የአዕምሮ ጤናን በፋሽን ዲዛይን ለመግለጽ የሞከረችበት መንገድ አድናቆትን አግኝቶ የበርሊን እና እንግሊዝ ሀገር ዓለም አቀፍ ጋዜጦች ላይ ሽፋን ተሰጠው::
ገባይል ይህን እድል ያገኘችው ባላት ነገር የራሷን ሥራ በጀመረችበት ወቅት ነበር:: ‹‹በዚህ ሥራ የተማርኩት ወጣት ስንሆን ከፍላጎታችን እና መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የምናደርገው ግብግብ ያልተገባ ጊዜ እንድናጠፋ ያደርገናል:: ያለንበትን ሁኔታ ስንቀበል ግን እድሎችን መድረኮችን እናገኛለን::›› ስትል ሁኔታዎችን መረዳት ያለውን ጠቀሜታ ታስረዳለች::
ገባይል የራሷን ሥራ ለመሥራት ወስና በመኖሪያ ቤቷ እናቷ ትሰራ በነበረበት ሱቅ ውስጥ ሥራዎቿን እንደ አዲስ ጀመረች:: ሥራዎቿን በተለያዩ የማህበራዊ ገጾች ላይ በማስተዋወቅ በየጊዜው ብራንዷን ሃሳቧን የምታንጸባርቅበት ልብሶችን መሥራት እና ለገበያ ማውጣት የተለያዩ የፋሽን ትርኢቶች ላይ ሥራዎቿን ይዛ ብቅ ትላለች::
‹‹ገባይል ፎር ኦል›› ብላ የሰየመችውን ሥራዎቿን ስትገልጻቸው ቀለል ያለ ነገር ግን ውበትና ግርማ ሞገስን የተላበሱ በማለት ትገልጻቸዋለች:: የድሮ ፋሽኖች ይስቡኛል የምትለው ገባይል አያቷ በነበሩበት ዘመን ይለብሷቸው የነበሩ በብር ፣ በነሃስ እንዲሁም ጥሩ ኢኮኖሚ ያላቸው እንስቶች ደግሞ በወርቅ ጭምር የተጌጡ ልብሶችን ይለብሱ እንደነበር ታስታውለች::
እሷም ከዚህ በመነሳት በሸማኔ በተሠራው የፈትል ጨርቅ ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ እንስቶች በአንገታቸው፣ በእጃቸው ላይ የሚያደርጓቸውን ማጌጫዎች በማከል ልብሱ የተለየ ውበት እንዲሰጥ አድርጋ ትሰራለች:: ጌጣጌጦቹን ከአክሱም ፣ ከላሊበላ የምታገኛቸው ሲሆን በምትፈልገው መንገድ ዲዛይን በማድረግ ጌጣጌጦቹን በልብሶቹ ላይ ትጠቀምበታለች:: መነሻው ከአያቷ የሆነው የዚህ ዲዛይን ስያሜም ‹‹እማዬ የወረደች ቀሚስ::›› የሚል ነበር:: ‹‹ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን ግብዓት እዚሁ በሀገራችን የተመረተ እንዲሆን ነው የምንፈልገው አብዛኛዎቹ ልብሶችም ሽመና ናቸው::›› ትላለች::
ገባይል የምትሰራቸውን ልብሶች ቀለል ያሉ እና ውበትን የሚያጎናጽፉ በማለት ትገልጻቸዋለች:: እነዚህንም ልብሶች ለመሥራት በዋናነት የሀገር ባህል ልብሶች የሚሰሩባቸውን ግብዓቶች ትጠቀማለች:: ምንም እንኳን የምትጠቀመው የሀበሻ ፈትል ጨርቅን ቢሆንም አሠራሩ ከተለመደው የሀበሻ ልብስ የተለየ በመሆኑ ሰዎች ጋር ለማስተዋወቅ በምትገኝባቸው መድረኮች እና ዝግጅቶች ላይ እራሷ ለብሳው ትሄዳለች:: በዚያም ሰዎች እንድትሰራላቸው ይጠይቋታል፤ በዚህ መንገድ ሰዎች ጋር እንዲደርስ የተለያዩ ሞዴሎችን በመጠቀም በማህበራዊ ገጽ ሥራዎቿን ታስተዋውቃለች:: ለሌላ ሰው የሰራችውን አይተው ወደ እርሷ የሚመጡ ደንበኞችም እንዳሉ ታነሳለች::
በራሳቸው ሥራ ውስጥ ላሉ እና ማንኛውንም የራሳቸውን ሥራ መጀመር ለሚፈልጉ ወጣቶችም ገባይል ሁለት ሃሳቦች አሏት ‹‹የራስ ሥራ ውጤቱ በፍጥነት ላይታይበት ይችላል:: ስለዚህ በጣም ትዕግስተኛ መሆን ያስፈልጋል:: ሌላኛው ደግሞ ሁሌም ራስን ከሰው ጋር ማወዳደር እጅግ በጣም የሚገል በመሆኑ ራሳችንን ካለፈው የእኛ ማንነት ጋር እያወዳደርን ሁሌም አዲስ ነገር ለመማርና ራስን ለማሻሻል በመሞከር ውስጥ ማለፍ ይገባል::›› ትላለች::
ገባይል በአሁኑ ወቅት ሶስት ሠራተኞችን ይዛ እየሠራች ትገኛለች:: የወደፊት እቅዷ ምርቶቿን በተለያዩ ሰዎች የልኬት መጠን ሰርታ በማዘጋጀት ሰዎች ወደ ሱቋ መጥተው ጊዜ ሳያጠፉ የወደዱትን ልብስ ለክተው ይዘው የሚሄዱበትን መንገድ መፍጠር ፣ ቅርንጫፎችን መክፈት እና ሥራዎቿ ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ዓለም አቀፍ ገበያዎች ላይ እንዲገኙ ማድረግ የወደፊት ህልሟ ነው::
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም