ፈር ቀዳጁ ኦሊምፒያኖች አሰልጣኝ- ንጉሴ ሮባ

ውጤታማው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የድል ታሪኩ የሚጀምረው በውጪ ሀገር ዜጋ አሰልጣኝ ነው። በስዊድናዊው የኢትዮጵያውያኖች የኦሊምፒክ አሰልጣኝ ኦኔ ኔስካነን የጀመረው ጉዞ በሀገር ውስጥ አሰልጣኞች ተተክቶ በደማቅ ታሪክ መቀጠል ከጀመረም ዘለግ ያሉ ዓመታት ተቆጥረዋል።

በኦሊምፒክ መድረክ ልምድና እውቀትን ቀምረው ለሀገራቸው ስኬት ሲጥሩ ከቆዩ ቀደምት አሰልጣኞች መካከል ደግሞ ግንባር ቀደሙ ንጉሴ ሮባ ናቸው። 25 ዓመታትን ባስቆጠረው የአሰልጣኝነት ህይወታቸውም በርካታ ስመጥር አትሌቶችን በማፍራት የሀገራቸው ባንዲራ እንዲውለበለብ አድርገዋል። ጥቂት ቀናት ብቻ የቀሩትን የ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ ተከትሎም በዛሬው የስፖርት ማህደር አምድ ታላቁን አሰልጣኝ እናስታውሳለን።

በ1933 ዓ.ም ጅግጅጋ የተወለዱት አሰልጣኝ ንጉሴ በሐረር እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተሞች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የተፈሪ መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ንግድ ስራ ኮሌጅን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ በዲፕሎማ በመመረቅ በአንድ የግል ኩባንያ ውስጥ ይሰሩ ነበር። በ1949 ዓ.ም ግን የሚሰሩበት ኩባንያ ባለቤት የሆኑት ሰው አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ወጣቱ ንጉሴ በፀሐፊነት እንዲቀጠሩ አደረጉ።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ በአጭር ርቀት፣ እግር ኳስ(የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አማካይና አጥቂ ተጫዋች) እና በቦክስ ስፖርቶች ተሳታፊ እንዲሁም ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆናቸው በጽህፈት ቤቱ በተቀጠሩበት ዓመት በተለያዩ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ እውቅናን ማትረፍ ቻሉ። በወቅቱ በሚደረጉ ውድድሮች የታወቁ አትሌቶችን ጭምር በማሸነፋቸውም ለሜልቦርን ኦሊምፒክ ሊመረጡ ቻሉ። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት በዚህ ኦሊምፒክ ሀገራቸውን ከወከሉት ብሄራዊ ቡድን አባላት መካከል አንዱ በመሆን በቢሾፍቱ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተው በ100 እና 200 ሜትር ተወዳደሩ። ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ የውድድር ልምድ ስለሌላቸው ውጤት ማስመዝገብ አልቻሉም። ከአራት ዓመት በኋላም በተመሳሳይ የሮም ኦሊምፒክ ላይ በአትሌቲክስ ሀገራቸውን ወክለዋል።

ንጉሴ ከሜልቦርን መልስ ወደቀድሞ ስራቸው ቢመለሱም ኮንፌዴሬሽኑ እንደቀድሞው ደመወዝ ሊከፍላቸው ባለመቻሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት መምህርነት በመቀጠር እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ ማገልገላቸውን በታሪካቸው ዙሪያ የተፃፉ የተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ በቼኮዝላቫኪያ የትምህርት ዕድል በማግኘት የአካል ማሰልጠኛና ስፖርት ትምህርት የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ከስድስት ዓመታት በኋላም ወደሀገራቸው በመመለስ በኢትዮጵያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን በአትሌቲክስ ስፖርት ባለሙያ ሆነው ለዘጠኝ ዓመታት ሰርተዋል። ኮንፌዴሬሽኑ ኋላ ላይ ወደ ኮሚሽንነት ሲቀየርም የተመሰገኑበትን ሥራ አከናውነዋል።

ከስፖርት አመራርነት ባለፈ በስልጠናውም ይሳተፉ የነበሩት ንጉሴ ሮባ በ1968ቱ የሜክሲኮ ኦሊምፒክ በአስመራ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ከስዊድናዊው ዋና አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን ጋር በመሆን በስልጠናው ቆይተዋል። ወጣቱ አሰልጣኝ ንጉሴ ሳይንሳዊ አሰለጣጠንን ተግባራዊ በማድረጋቸውም ተሳትፎው አጠራጣሪ በነበረው 4ኛው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ በ10ሺ ሜትር የብር እና በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ተመልሷል። በአሰልጣኝነት ዘመናቸውም እንደ ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር የመሰሉ አትሌቶችን ለስኬታማነት በማበቃትም ስማቸው ይነሳል።

ምሩፅ በሙኒክ ኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ፣ ኢትዮጵያም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በመሆን በደቡብ አፍሪካዊያን ላይ የሚፈጸመውን በደል ተቃውማ ራሷን ከውድድሩ ባገለለችበት የሞንትሪል ኦሊምፒክ እንዲሁም ምሩጽ በ5ሺ እና 10 ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን ባገኘበት የሞስኮ ኦሊምፒኮችም ንጉሴ ሮባ በዋና አሰልጣኝነት ብሄራዊ ቡድኑን መርተዋል። ቀጣዮቹ የሎስአንጀለስ እና የሴኡል ኦሊምፒኮች ላይ ኢትዮጵያ ባትሳተፍም ባርሴሎና ላይ ግን በቡድን መሪነትና አሰልጣኝነት ተሳትፈዋል። በአጠቃላይ የአሰልጣኝነት ግልጋሎታቸውም ሻምበል አበበ ቢቂላን ጨምሮ በማሞ ወልዴ፣ መሐመድ ከድር፣ እሸቱ ቱራ፣ በላይነህ ዴንሳሞ እና አበበ መኮንን የመሳሰሉ አንጋፋ እንዲሁም በርካታ ምርጥ ሴት አትሌቶችን ማፍራት ችለዋል።

ማርሽ ቀያሪው ምሩጽ ይፍጠር የወርቅ ጫማ መሸለሙ እንዲሁም በላይነህ ዴንሳሞ በማራቶን የዓለም ክብረወሰንን ለመስበሩም የአንጋፋው አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ሳይንሳዊ ዘዴን የተከተለ አሰለጣጠን ከፍተኛ ድርሻ አለው። ከኢትዮጵያዊያን ባለፈም ሌሎች አፍሪካዊያን አትሌቶችንም ማሰልጠን ችለዋል። በውጤታማ ስልጠናቸውም የጥቁር አባይ ኒሻን ሲሸለሙ፤ በላይነህ ዴንሳሞ ክብረወሰን እንዲሰብር ምክንያት በመሆናቸው በሮተርዳም ማራቶን አውቶሞቢል ተበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም ከዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የዓለም አትሌቲክስ እና ሌሎች ተቋማት የምስክር ወረቀቶችና ዲፕሎማዎችንም አግኝተዋል።

በሩብ ክፍለ ዘመን የአሰልጣኝነት ቆይታቸው ከምርጥ አትሌቶች ባለፈ እንደ እነ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ያሉ በኦሊምፒክና በዓለም ቻምፒዮና ገናና ስም ያተረፉ አሰልጣኞችንም በማፍራትና ልምዳቸውን በማካፈል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በስኬት ጎዳና እንዲቀጥል አድርገዋል። የአንድ ወንድና አራት ሴት ልጆች አባት የነበሩት አሰልጣን ንጉሴ ሮባ ባደረባቸው ህመም በ1985ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር ግን ስማቸው ህያው ሆኖ ይታወሳል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You