ለ117ኛ ጊዜ ደም በመለገስ የበርካቶችን ሕይወት የታደገችው ነርስ

በዓለማችን ሆነ በሀገራችን በሚኖሩበት የሕይወት ዘመን በአጋጣሚ ወይም በራሳቸው ተነሳሽነት ሌሎችን የመርዳት ትልቅ ባህል ያላቸው በርካታ ግለሰቦች እንዳሉ አስረጂ አያስፈልገውም። በዛው ልክ ደግሞ ለመርዳት እና በጎ ነገር ለማድረግ አቅም ኖሯቸው በቸልተኝነት ወይም፣ በፍላጎት ማጣት ምክንያት ይህቺን ዓለም የሚሰናበቱ በርካቶችም እንደሆኑ እሙን ነው።

የሰው ልጅ እንደመሆናችን ሌሎችን ለመርዳት የግድ በሚሊዬን የሚቆጠር ብርና ወርቅ ያለን ሰዎች መሆን አይጠበቅብንም። ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው የሚል ዘመን የማይሽረው ብሂል እንዳለን ሁሉ፤ በተለያዩ መንገዶች ሌሎችን መርዳት እንድንችል ተፈጥሮ የለገሰችን ትልቅ ጸጋ አለ።

ደም መለገስ ደግሞ ተፈጥሮ ከቸረችን ስጦታዎች ሁሉ የማይቋረጥ ስጦታ ነው። ይህን የተፈጥሮ ስጦታ ተጠቅመው ለበርካታ ሰዎች ዳግም በሕይወት ለመኖር ምክንያት የሆኑት ሲስተር አሰጋሽ ጎሳ ደግሞ አንዷ ናቸው።

ሲስተር አሰጋሽ ጎሳ ይባላሉ። በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ስለ ደም ልገሳ ትምህርትና ቅስቀሳ የሚሰጡ ባለሙያ ናቸው። ለወላጆቻቸው አራተኛ ልጅ ሲሆኑ ፤ትውልድ እና እድገታቸው በድሮ ስሙ አርሲ ክፍለ ሀገር አሰላ ከተማ ነው። የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በእዛው አሰላ ከተማ መሆኑንም ሲስተሯ ይገልጻሉ።

የትምህርት አቀባበላቸው መሀከለኛ ከሚባሉ ተማሪዎች መሆኑን የሚያስረዱት ሲስተር አሰጋሽ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት ወደ ነርሲግ ሙያ ለመግባት ሃሳብ ባይኖራቸውም በአካባቢያቸው አንዳንድ ሳቢ ምክንያቶች እንደነበሩ ያነሳሉ።

ወደ ነርሲግ ሙያ እንዴት እንደገቡ የሚናገሩት ሲስተር አሰጋሽ፤ በመጀመሪያ አባታቸው የጤና ባለሙያ በመሆን በጤና ተቋም እንደሚሰሩ በመግለጽ፤ በአቅራቢያቸው ጤና ተቋም ስለነበር እዛ የሚሰሩት ነርሶች የሚለብሱት ልብስን ሲመለከቱ የፈጠረባቸው ስሜት ወደ ነርስ ሙያ እንደተሳቡ ይናገራሉ።

በዚህ ሁኔታ የህክምና ባለሙያዎችን እያዩ ማደጋቸው ወደ ሙያው ለመግባት በአዕምሯቸው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን የሚገልጹት የህክምና ባለሙያዋ፤ ወለጋ ነርሲንግ ኮሌጅ ገብተው ትምህርታቸውን እንደተከታተሉ ያስረዳሉ።

በዙሪያችን ያሉ ሰዎች በቀን ተቀን እንቅስቃሴያችን የምንመለከታቸው ተግባራት ወደ ክፉም ሆነ ወደ ደግነት እንድንገባ ተጽእኖ እንደሚያደርጉ ሁሉ፤ ሲስተር አሰጋሽም ወደ በጎ አድራጎት እንዲገቡ ትልቁን ሚና የተጫወቱት እናት እና አባታቸው ናቸው።

‹‹እናቴ ጾም በሚያዝበት ወቅት በአካባቢው ያሉ የጎረቤት ሴቶች ትረዳለች። ጾም በሚፈታበት ወቅትም ለጎረቤት ሴቶች ቅቤ ወስዳ ትቀባቸው ነበር። አባቴ ጎሳው ይባላል ጥሩ ስነ ምግባር ያለው አባት ነው። እድገቴ በእንደዚህ አይነት ቤተሰብ ውስጥ መሆኑ ተጽእኖ አሳድሮብኛል›› ይላሉ።

ወደ ደም ልገሳ ተግባር የገቡበት መንገድ

ወደ ደም ልገሳ ተግባር እንዲገቡ የገፋቸው በስራቸው አጋጣሚያ ያጋጠማቸው ክስተት እንደነበር የሚያስታውሱት ሲስተር አሰጋሽ፤ በደም ባንክ ውስጥ በሚሰሩበት ወቅት አንድ አባወራ ሚስቱ ታማ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ገብታ ስለነበር፤ ደም ስላስፈለጋት ለባለቤቱ በሚሰጣት ደም ምትክ ደም እንዲለገስ ተጠየቀ።

በዛን ወቅት አባወራው ከክፍለ ሀገር ስለመጣ የምትክ ደም ሊሰጥ የሚችል የቅርብ ዘመድ እንኳን በዙሪያው አልነበረም። ያ አባወራ በጣም ውጥረት ውስጥ ከመግባቱ የተነሳ ከሆስፒታሉ እየሮጠ ወደ ደም ባንክ ሲመጣ ደክሞት ስለነበር እያለከለ ነበር የመጣው። ሚስቴ፣ የልጆቼ እናት ልትሞትብኝ ነው ወይም እኔ ደም ልለግስና እሷ ኖራ እኔ ልሙት የሚል ተማጽኖ አሰማ። ሲስተር አሰጋሽ ውስጣቸው ተነካ።

የአባወራው ጭንቀት ውስጣቸው ገባ። ለሚስቱና ለቤተሰቡ ያለው ፍቅር እና እርሱ ሞቶም ቢሆን ባለቤቱን ለማዳን ሲያደርግ የነበረው ጥረት እስከዛሬ አይረሳቸውም። ‹‹ያ ሰው ደክሞት እያለከለከ ነው ወደ ደም ባንክ የደረሰው። በዛ ላይ ከክፍለ ሀገር ነው የመጣው። በዙሪያው ምንም ዘመድ ስለሌለው ምግብ እንኳን በልቶ ላይሆን ይችላል። ምናልባት ደሙን ይዞ ሲሄድ እራሱን ስቶ ሊወድቅ ይችላል ››የሚሉት ሲስተር አሰጋሽ፤ ይህ ሰው ደም እንዲለግስ ማድረግ ወንጀል ነው በማለት ይገልጻሉ።

ምናልባት ከተማ ውስጥ የሚኖር ሰው ቢሆን እሱ መለገስ ባይችል እንኳን በዙሪያ ያለ ሰው ወንድም ሆነ እህት ወይም ጎረቤት መጥቶ እንዲለግስ ማድረግ ይቻላል። ይህ ሰው ከገጠር ነው የመጣው፤ባለቤቱን የሚያስታምማት እሱ ብቻ ነው። እንዳጋጣሚ ሆኖ በወቅቱ በሥራ ቦታው ተረኛ የነበርኩት እኔ ነበርኩና በጣም ስላሳዘነኝ እኔ ልስጥ አልኩና ሰጠሁ። አባወራው የተጠየቀው ሁለት ዩውኒት ደም ስለነበር አንድ ዩኒት ደም ከራሳቸው በመለገስ አንዱን ዩኒት ደም ደግሞ ለማግኘት መፍትሄ መፈለግ ጀመሩ።

‹‹በዛን ወቅት ከቦታ ቦታ በመሄድ የደም ልገሳ ቅስቃሳ በማድረግ ደም የምንሰበስብ ስለሆነ አንዱን ዩኒት ደም እኔ ከሰጠሁት በኋላ፤ አንዱን ደግሞ በቅስቀሳ ወቅት ከሚሰበሰበው ደም እንደምተካ ነግሬ፤ሴትዮዋ ደም እንድታገኝ አደረግኩ›› ይላሉ።

በወቅቱ በክፍያ ደም የሚለግሱ ሰዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ባለሙያዋ‹‹ እኔ እሰጣለሁ ተቀማጭ ደም አለኝ››እያሉ ደም የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለማስማማት የሚጥሩ እንዳሉም ያነሳሉ።

እነዛ ሰዎች የጤንነታቸው ሁኔታ ስለማይታወቅ አንድ ሰው ከነዛ ሰዎች ደም ከገዛ በኋላ ተቀባይነት የማይኖርበት አጋጣሚ ብዙ እንደሆነም ሲስተር አሰጋሽ ያስረዳሉ።

እናም በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ተቸግረው ሲመጡ ተረኛ ከሆኑ ደም የሚለግሱበት አጋጣሚ የበዛ እንደነበር ይናገራሉ። አንድ ሰው ደም የሚለግሰው የመጀመሪያውን ከለገሰ በኋላ ሦስት ወር ሲሞላው መሆኑንም ያስረዳሉ።

ነገር ግን እሳቸው በወቅቱ ኮምፒውተር ስላልነበር በሁለት ወር ውስጥ እንኳን የሚሰጡበት ሁኔታ ነበር። አሁን ኮምፒውተር ስላለ በኮምፒውተር ይመዘገባል። አንድ ሰው ደም ለግሶ ሦስት ወር ካልሞላው ኮምፒውተሩ አይቀበልም ሲሉ ያስረዳሉ።

‹‹የዛን ወቅት ሦስት ወር ሳይሞላኝ ደም የምለግስ ቢሆንም፤ እግዚአብሔር ይመስገን ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰብኝም። ደግሞም ደም በሚለገስበት ወቅት የደም መጠኔ፣ ክብደቴ ስለሚለካ እና ምርመራዎች ስለሚደረግልኝም ጉዳት አልደረሰብኝም›› ይላሉ።

‹‹ያ አባወራ ነው ደም እንድስጥ መነሻ የሆነኝ። ከዚህ በፊት የደም እጥረት አጋጥሞት ደም የለገስኩለት ዘመድም ሆነ ጓደኛ ስላልነበረኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ደም የለገስኩት ለዛ አባወራ ሚስት ነው››የሚሉት ሲስተር አሰጋሽ፤ ለአባወራው ሚስት ደም ሲለግሱም ገና ደም ባንክ የተቀጠሩበት ወቅት እንደነበር ይናገራሉ።

‹‹የአባወራው ሚስት ምን ደረጃ እንደደረሰች አላወኩም። ምናልባት ጊዜ አጥቶ ይሁን፤ ወይም ማመስገን እንዳለበት ባለማወቅ ምክንያት ይሁን አባወራውም ተመልሶ መጥቶ የደረሰበትን ደረጃ አልነገረኝም። ነገር ግን እኔ በዋናነት የሚያስደስተኝ እኔ በለገስኩት ደም የሰው ሕይወት መትረፉ ነው›› በማለት ይገልጻሉ።

ሲስተር አሰጋሽ እንደሚሉት፤ አንድ ሰው ደም ተለግሶለት ሕይወቱ ተርፎ፤ ደምባንክ መጥቶ የማመስገን ልምድ የለም። አጋጥሟቸውም አያውቅም። ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ እንደ ሀገር ደም ለመለገስ ፍርሀት አለ። ይህንኑ ከግንዛቤ በማስገባት ሰዎች ደም እንዲለግሱ የቅስቀሳና የግንዛቤ ትምህርት እንደሚሰጡ ይናገራሉ።

በደም ባንክ የተለያዩ የደም አይነቶች አሉ የሚሉት ሲስተር አሰጋሽ፤ ሆስፒታሉ በሚጠይቀው የደም አይነት ደምባንክ ይሰጣል። በዛ ምትክ ነው በዙሪያው ያሉ ሰዎች እንዲለግሱ ይደረጋል። አንድ ሰው የደም እጥረት አጋጥሞት በዙሪያው ያሉ ሰዎች ደም እንዲለግሱ ሲደረግ፤ ተመሳሳይ እንዲሆን አይጠበቅበትም።

ሲስተር አሰጋሽ ደም መለገስ የጀመሩት ከ1984 ዓ.ም በደም ባንክ አገልግሎት ሥራ መሥራት ከጀመሩበት ሰሞን አንስቶ ሲሆን፤ አሁን ላይ ለ 117ተኛ ጊዜ ደም ለግሰዋል። በ2010 ዓ.ም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 19ኛውን የጤና ጉባኤ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ባካሄደበት ወቅት፤ ለ66 ጊዜ ደም በመለገስ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የላቀ ተሸላሚ በማለት ሽልማት ሰጥቷቸዋል።

በ2013 ዓ.ም የቀድሞ ጤና ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ሊያ ታደሰ ሲስተር አሰጋሽ ለ80 ጊዜ ደም በመለገስ በሴት ደም ለጋሾች መሃከል ክብረወሰን ማስመዝገባቸውን አስመልክቶ የምስጋና እና የእንኳን ደስ አለሽ መልእክት አስተላልፈው ነበር።

ሌሎች የበጎ አድራጎት ሥራዎች

በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ የግንዛቤ ትምህርት መስጠት እና ሰዎች ደም እንዲለግሱ የንቅናቄ ሥራ ይሠራሉ። ሌላው በስፋት ደም ሊለግሱ የሚችሉ አካባቢዎች በመለየት ደም እንዲለግሱ የማድረግ ሥራ ይሠራሉ።

‹‹ ደም ከመለገስ ውጪ በተለያዩ አጋጣሚዎች በመንገድ ስንቀሳቀስ እኔ ወደምሄድበት አቅጣጫ እቃ ተሸክመው የሚሄዱ አቅመ ደካሞችን ስመለከት የያዙትን እቃ በመሸከም እረዳቸዋሉ›› ይላሉ። የበጎ አድራጎት ሥራቸው በዚሁ አልተገደበም። በሚኖሩበት አካባቢ አንዳንዴ ለተቸገሩ ግለሰቦች ልብስ እና ገንዘብ በመስጠት የሚረዱ መሆኑንም ያነሳሉ።

አንድ ሰው በአንድ ጊዜ የሚለግሰው ደም በደም እጥረት ለተቸገሩ ለሦስት ሰዎች ያገለግላል። አንድ ደም የሚለግስ ሰው ምንም እንከን ሳይገጥመው በተወሰኑ ደቂቃዎች ተነስቶ ወደ ሥራው ሊመለስ ይችላል። ነገር ግን ይህን ለማድረግ ችላ በመባሉ፤ በግንዛቤ እጥረት እና ፍረሃት በደም እጥረት ምክንያት በርካታ ሰዎች ይችን ምድር ዳግም ላለማየት ይሰናበታሉ።

ምናልባት እነዚህ ሰዎች የእነሱን እጅ የሚመለከት ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ሀገርን በእውቀታቸው የሚረዱ እና በበጎ ፈቃደኝነት የሚያሳድጉት ልጅ ሊኖር ይችላል። ቤተሰቦቻቸውን እና ሀገራቸውን ይረዳሉ ተብሎ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸውም ሊሆኑ ይችላሉ።

እነዚህ ግለሰቦች ሲቀጠፉ ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ጎረቤት ደረጃው እያደገ ሲመጣም ሀገር ይጎዳል። ‹‹ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ደም ስለግስ ነው የቆየሁት። እኔ አንዴ የምሰጠው አንድ ዩኒት ደም ለሦስት ሰዎች ያገለግላል። በዚህም ከእግዚአብሄር በታች የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ማዳን ችያለው›› ሲሉ ያስረዳሉ።

መጠነኛ የደም መፍሰስ ላጋጣማቸው ‹‹ፕላዝማ ››፤ ለሚደሙ ደግሞ የሚደማውን ደም ለማቆም ‹‹ፕሌትሌት›› ይሰጣል። በተጨማሪም ቀይ የደም ሴል ለማያመርቱ የሚሰጥ ደም አለ ሲሉ ያስረዳሉ።

በዚህም ደም ልገሳ ተግባራቸው ለበርካቶች መድረሳቸውን የሚገልጹት ሲስተር አሰጋሽ፤ ‹‹አንዴ የሰጠሁት ደም ለሦስት ሰው የሚደርስ ከሆነ 117 ጊዜ የሰጠሁት ደም በርካቶችን መታደግ እንደቻለ በቀላሉ መረዳት ይቻላል›› ይላሉ።

አንድ ሰው ደም ሲለግስ ምርመራ ተደርጎለት በክብደቱ መጠን 350 ዩኒት ወይም 450 ዩኒት ነው የሚወሰደው። ከ350 ዩኒት በላይ የሚወሰድ ደም በሚለግሰው ግለሰብ ደም ውስጥ ጥሩ የአይረን መጠን ካለ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

ደም ከሰውነታችን ሲወጣ ይረጋል። ደሙ ቀጣይ ለሚሰጠው ግለሰብ ጋር እስከሚደርስ ድረስ ነፍስ እንዲኖረው እና እንዳይረጋ የሚያደርግ ንጥረ ነገር ከደም ከረጢቱ ጋር አንድ ላይ ታሽጎ ይመጣል። ስለዚህ 350 ዩኒቱ ወይም 450 ዩኒቱ በሙሉ ደም አይደለም ሲሉ ያስረዳሉ።

ደም መለገስ የሚያስከትለው ጉዳት ይኖር ይሆን ?

ደም መለገስ ጉዳት የለውም ሲሉ የሚያስረዱት ሲስተር አሰጋሽ፤ ደም በሰውነት ውስጥ አይጠራቀምም፤ከወራት በኋላ ይሞታል ፤በቦታው ሌላ ደም ይተካል። ‹‹እኛ ግን በምንለግሰው ደም የሦስት ሰዎችን ሕይወት እንታደጋለን›› ሲሉ ይናገራሉ።

በደም ውስጥ ያሉ ህዋሳት ስለሚሞቱ ደም ጊዜው ሲደርስ በሽንት እና በላብ የሚወገድ ነው። አብሯቸው ዘላለም የሚቀመጥ የሚመስላቸው ሰዎች እንዳሉም ይገልጻሉ።

የካንሰር ታማሚዎች፣ የመኪና አደጋ የገጠማቸው ፣ እናቶች እና ሎሎች በርካታ ደም የሚፈልጉ አካላት ስላሉ ሁልጊዜም ደም የሚለግሰው ሰው ማሰብ ያለበት እነሱን ከግምት ማስገባት አስፈላጊ ነገር መሆኑን ይመክራሉ።

‹‹በሕይወታችን ቆይታችን ምን እንደምንሆን አናውቅም። ስለዚህ በምድር ቆይታችን ከራሳችን አልፈን ለሌላ ሰው መኖር ትልቅ በጎ ተግባራ ነው ››ሲሉ ይናገራሉ።

ደም መለገስ ደግሞ ሰው በመሆናችን ብቻ የምናደርገው በጎ ሥራ ነው የሚሉት ሲስተር አሰጋሽ፤ ስለዚህ ማንም ሰው እድሜው ከ18 እስከ 65 የሆነ፣ ክብደቱ ከ45 ኪሎ በላይ፣ሌላ የጤና ችግር የሌለበት እና የማታጠባ ሴት ከሆነች ደም መለግስ ይችላሉ ሲሉ ያስረዳሉ። በነገራች ላይ ከ18 እድሜ ክልል በላይ የሚባለው በሕገመንግሥቱ የተቀመጠውን አንድ ሰው በራሱ የመወሰን አቅም መሰረት በማድረግ ነው እንጂ የ16 እና 17 ልጅም በወላጆቹ ፈቃድ መለገስ ይችላል ይላሉ።

‹‹ደግሞ አንድ ሰው ደም ለመለገስ ሲመጣ የደም ግፊት ሆነ ሌላ በሽታ ካለበት ተመርምሮ ነው የሚሰጠው እንጂ ለመለገስ ስለመጣ ብቻ ደም እንዲለግስ አይደረግም ››ይላሉ።

‹‹ከደም ግፊት ጋር ተያይዞ የተሳሳተ ግንዛቤ አለ። ደም ግፊት ማለት ብዙ ደም አለን ማለት አይደለም። በአጋጣሚ በ2010 ዓ.ም በሰኔው ፍንዳታ ወቅት ደም ግፊት ስለነበረባቸው በተሳሳተ ግንዛቤ ብዙ ደም ነው ያለኝ በማለት ደም ለመለገስ አስበው አንድ ግለሰብ ከጋምቤላ ድረስ መጥተው ነበር። ነገር ግን የደም ግፊት ስለነበረባቸው መለገስ እንደማይቻል ተነግሯቸዋል›› ሲሉ ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

እኒህ ሰው‹‹ ኧረ እኔ ብዙ ደም አለኝ መለገስ እችላለው በማለት ከኛ ጋር በዙ ተከራከሩ። አይ የደም ግፊት በሽታ ስላለበዎት መለገስ አይችሉም ብለን ነገርናቸው። በመጨረሻም ሁኔታውን ተረድተው ወደ መጡበት ተመለሱ››ሲሉ አጫውተውናል።

ሲስተር አሰጋሽ እንደሚመክሩት ሰዎች ጤናማ በሆኑበት ወቅት ስለደም ልገሳ አውቀው ቢለግሱ መልካም ነው። ደግሞም ደም መለገስ ከድንገተኛ የልብ ህመም፣ ከአይረን ክምችት፣ ከስኳር እና ኮልስትሮል ይታደጋል ሲሉ ደም መለገስ የሚሰጠውን ጥቅም ያስረዳሉ።

አንድ ሰው የልብ ህምም ኖሮበት ተመርምሮ እስካላወቀ ዝምብሎ ማጅራቴን ያዘኝ እንዲህ አደረገኝ እያለ እቤቱ ይቀመጣል። ደም ለመለገስ አንድ ግለሰብ ሲመጣ እኛ የልብ አመታቱን እንመረምርና ችግር ካለ ሌላ ጊዜ እንዲመጣ እናደርጋለን ይላሉ ሲስተር አሰጋሽ።

ደም በሚለግሱበት ወቅት የደም አይነታቸውን፣ የኤች አይቪ፣ የጉበት እና የሌሎች በሽታዎች ምርመራ ተደርጎ ውጤት የሚነገር ስለሆነ ደም የሚለግሱ ሰዎች በዚህም ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉ ይናገራሉ።

ደም በመለገስ የተገኘ ጥቅም

ቀደም ሲል ደም የሚለግሱ ሰዎች ጥቂት ስለነበሩ በእይታ ብቻ ይታወቁ እንደነበር የሚናገሩት ሲስተር አሰጋሽ፤ በተደረጉልን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች አሁን በርካታ ሰዎች ደም በመለገስ ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ። ደም የምለግሰው በየሦስት ወር አንድ ጊዜ ሲሆን፤ በአንድ ዓመት አራት ጊዜ በመደበኛነት እለግሳለሁ ሲሉ ሲስተር አሰጋሽ ያስረዳሉ።

ደም መለገስ ከኮልስትሮል፣ ከድንገተኛ የልብ ህመም እና ሌሎች በሽታዎች ይታደጋል። ሲስተሯ ለረጅም ዓመታት ደም በመለገሳቸው ከእነዚህ በሽታዎች ነጻ ሊሆኑ ችለዋል። ከምንም በላይ ደግሞ ደም በመለገስ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት መዳን ምክንያት በመሆናቸው፤ ከፍተኛ የህሊና እርካታ እንደሚሰማቸው ያስረዳሉ።

ገጠመኞች

አንዳንዴ ደም ልገሳ ሲባል ዝምብሎ የሚቀዳ ወይም በፋብሪካ የሚመረት የሚመስላቸው አሉ። አንድ አባወራ ሚስታቸው በወሊድ ምክንያት ብዙ ደም ፈሷት ስለነበር፤ እሳቸው እንዲሰጡ ሲጠየቅ ‹‹ሁለታችንንም ልትገሉን ነው ወይ ልጆቼን ሌላ ሚስት አግብቼ አሳድጋቸዋለሁ›› ያሉትን አባት እንደማይረሷቸው ይገልጻሉ።

ሌላውኛው ገጠመኝ ደግሞ አንድ እናት ሁለት ዩኒት ደም ያስፈልጋቸዋል፤ አንደኛውን ሴት ልጃቸው እንድትሰጥ ሌላኛውን ደግሞ ወንድሟ እንዲሰጥ ተብሎ መጡ።

ወንዱ ለመስጠት በጣም ስለፈራ የደም ግፊቱ ጨመረ፤በጣም ተጨናነቀ። እንደዛ ሲሆን እህቱ ሁለተኛውን እኔ ጨምሬ ልስጥ አለችን። የሴቷ ጥንካሬ ያስደስታል። ብዙ ጊዜ ሴቶች ደም ለመለገስ የተሰጡ ይመስላል የሚሉት ነርሷ፤‹‹ ብዙ ጊዜ ወንዶች ሲጠየቁ ላስብበት፣ ዝግጁ አይደለሁም ይላሉ። ነገር ግን ሴቶች ወደያውኑ ነው የሚወስኑት›› ይላሉ።

ሌላኛውን አሳዛኝ ገጠመኛቸውን የሚናገሩት ሲስተር አሰጋሽ፤ አንድ አባት ሚስቱ ወለደችና ለተወለደው ሕፃን ደም መቀየር አስፈልጎ ስለነበር ሚስቱ አራስ ስለሆነች መስጠት ስለማትችል፤ አባትየው እንዲሰጥ ይጠየቃል ። ሰውየውም ይሄድና ወላጅ እናቱን ያማክራል። እናቱም የሚሞት ስለመሰላቸው ‹‹አንተ ብትኖር ሌላ ልጅ መውለድ ትችላለህ፤ደም መስጠት የለብህም ›› ብለው ስለመከሩት እሱም ሳይሰጥ ቀረ ። በኋላ ላይ ስንሰማ ልጁ ማረፉን ሰማን ይላሉ።

አርአያነታቸውን የተከተሉ

‹‹የኔን አርአያ የተከተሉ ብዙዎች አሉ። ቤተሰቦቼ፣ እህቶቼ እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ደም መለገስን እንደባህል የወሰዱ አሉ። ፎቶግራፎቼ ደም ባንክ ተሰቅለው ሲመለከት አንቺ ይህን ያህል ጊዜ እስከምትለግሺ እኔ የትነበርኩ ብሎ የተቆጨ እና ከዛ በኋላ በቋሚነት ደም በመለገስ ለበርካታ ጊዜ የለገሰ እና አሁንም እየለገሰ የሚገኝ ሰው አውቃለሁ›› ሲሉ ይናገራሉ።

የእሳቸውን አርአያነት በመከተል ለ92 ጊዜ ደም የለገሰ አለ። አርአያነታቸው በቤተሰብ ውስጥም ቀጥሏል። አንዲት ሴት ልጅ አለችኝ የሚሉት ሲስተር አሰጋሽ፤ እሷም በቅርቡ ለ14 ጊዜ ደም እንደለገሰች ይገልጻሉ።

ደም የመለገስ ልምድ አሁን ላይ

ሲሰተር አሰጋሽ እንደሚናገሩት አሁን ላይ ደም የመለገስ ተግባር በጣም እያደገ መጥቷል። በፊት ለዘመዳቸው እንኳን ደም ለመስጠት በጣም የሚያስቸግሩ ሰዎች አሁን ከራሳቸው አልፈው በበጎ ፈቃደኝነት ደም የሚለግሱ ሰዎች ብዙ ናቸው ሲሉ በማሳያነት ያነሳሉ።

ባህሉ እያደገ ቢመጣም አሁንም የደምና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎት የሚፈለገውን ያህል አልደረሰም። የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ጥናት እንደሀገር የደም ለጋሾች ቁጥር ገና አንድ በመቶ እንኳ አልደረሰም ። በኢትዮጵያ 120 ሚሊዮን ሰው የሚኖር ቢሆንም፤ ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር ገና አንድ ሚሊዮን እንኳን አልደረሰም ሲሉ ያስረዳሉ።

አንዳንዴ መርፌ ፈርተው ደም የማይለግሱ ሰዎች አሉ። ‹‹ሰው ጦር ሜዳ ይሄድ የለ እንደ›› የሚሉት ሲስተር አሰጋሽ፤ ‹‹እኛ ሰላም ወጥተን እንድንገባ አንድ ወታደር ነፍስ እስከመስጠት ከደረሰ በሰላም ሀገር ቁጭ ብለን ደም መለገስ ትልቅ ጉዳይ ሊሆንብን አይገባም›› ይላሉ።

ልባችን ቅን ከሆነ አንድ መርፌ ብቻ ተወግተን ደም አጥቶ ለመሞት የተቃረበን ሰው ማዳን እንደምንችል ማሰብ ይገባናል። አይደለም መርፌ ነፍሴን እሰጥለታለሁ የምንላቸው ሰዎች አሉ። ሌሎችንም እንደዛ ማየት መልካም ነው የሚሉት ሲስተር አሰጋሽ ሁሉም ሰው በተቻለው አቅም ደም እንዲለግስ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ።

አንዳንዶች ደግሞ በውፍረት እና በቅጥነት የሚመስላቸው አሉ። ‹‹አጥንት ስትፈልጉ እንመጣለን›› የሚሉ መኖራቸውን ያነሳሉ። እኛ ደግሞ ስጋ አይደለም የምንፈልገው የሚሉት ሲስተር አሰጋሽ፤ የሁሉም ሰው ደም ክቡር በመሆኑ ደም ለመስጠት ለሚመጡ ሁሉ ክብር እንሰጣለን ሲሉ ይናገራሉ።

ወንጀል ሰርተው ቅጣት እንዲቀልላቸው ከዚህ በፊት ደም የለገሱትን ወረቀት ለማጻፍ የሚመጡ እና የትምህርት እድል ወደ ውጭ ሀገራት በሚያገኙበት ወቅት ለማጻፍ የሚመጡ እንዳሉ ያነሳሉ። ደም መስጠት በዚህ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያስቀምጣሉ።

ቀጣይ እቅድ

ሲስተር አሰጋሽ ለ117ኛ ጊዜ ደም የለገሱት የዓለም ደም ለጋሾች ቀን በጅማ ከተማ በሚከበርበት ወቅት ሲሆን፤ በቀጣይም እድሜያቸው እስከሚያግዳቸው ድረስ ደም ለመለገስ ዝግጁ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You