‹‹የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለተለያዩ አገልግሎቶች ምቹ የማድረግ አንዱ ሞዴል ነው›› በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)

ከተሞች ለአንድ ሀገር እድገት ሰፊ ሚና እንዳላቸው ይታመናል:: የአንድን ሀገር እድገት ወይም ልማት ሊወስኑ የሚችሉ የልማት ሞተሮች በመባልም ይታወቃሉ። የየትኛውም የለማ አገር የልማት ምንጭ ከተሞች ስለመሆናቸውም ይጠቀሳል።

ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በቅድሚያ ከተሞቹ ራሳቸው በአግባቡ ሲለሙ ነው:: ለከተሞች ልማት ደግሞ መሠረተ ልማት፣ ፕላንና በአግባቡ መምራት ላይ በትኩረት መሠራት እንዳለበት የከተማ ልማት ባለሙያዎች ይመክራሉ::

የኢትዮጵያ ከተሞች በፍጥነት እየተስፋፉም እያደጉም ስለመሆናቸው ይገለጻል፤ የከተሞች መስፋፋትና ማደግ እንዲሁም የከተሜነት በፍጥነት እየተስፋፋ መምጣት በከተሞች መሠረተ ልማቶች ላይ አተኩሮ መሥራትን የግድ ይላል:: መሠረተ ልማቱ በአግባቡ እንዲመራ ማድረግ ላይም መሠራት ይኖርበታል:: ዜጎች ከከተሞች ትሩፋት መጠቀም እንዲችሉ ከተሞች በፕላን ሊመሩ እንደሚገባም የከተማ ልማት ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ከተሞች አይቀሬ ለሆነው ከተሜነት ዝግጅት አድርገው መጠበቅ እንዳለባቸውም ያመለክታሉ:: በተለይ አዳዲስ የከተማ ማዕከላት ከምሥረታቸው ጀምሮ በእቅድ መመራት ይችሉ ዘንድ ዝግጁ ሆነው መጠበቅ እንዳለባቸውም ያሳስባሉ።

በከተማና ከተሜነት እንዲሁም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት ላይ ያነጋገርናቸው በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየታየ ያለው የከተሜነት መስፋፋት ዓለም ላይ ከሚታየውም ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ:: ይህ ከተሜነት በእቅድ ካልተመራ ለትውልድ ትልቅ ፈተና ሊሆን ይችላል ሲሉም አስገንዝበዋል::

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ግብርና መር አሁን ደግሞ የማኑፋክቸሪንግ ወይም ከተማ መር የልማት አቅጣጫ በመያዝ እየለማች መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከተሞች የሀገሪቱን የልማት አቅጣጫ የሚያመላክቱ ናቸው ። በመሆኑም በሀገር ልማትና ዕድገት ላይ የከተሞች ሚና ሰፊ ድርሻ አለው ይላሉ።

ዳንኤል (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ የከተሞች ምጣኔ 25 በመቶ አካባቢ ደርሷል ተብሎ ይገመታል። የከተሜነት መስፋፋት ፍጥነቱም አምስት ነጥብ አራት በመቶ ነው። ይህም ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የከተሞች እድገት ካለባቸው ሀገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ያደርጋታል:: በመሆኑም ይህ ፈጣን የከተሜነት እድገት በአግባቡ መመራት እንዳለበት አመልክተዋል:: በአግባቡ ካልተመራ ግን ከተሞቹ የሥራ አጥነት ችግር፣ የመሠረተ ልማት እጥረት የሚከሰትባቸው እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል።

ከተሞቹ በፕላን ከተመሩ፣ የመኖሪያ፣ የመነገጃ፣ የማኑፋክቸሪንግና የሥራ ፈጠራ ማዕከላት ይሆናሉ። እነዚህ ከተሞች የኢትዮጵያን ብልፅግና እና ልማት ወደ ፊት ሊወስኑ የሚችሉ ስለሆኑ በአግባቡ ሊመሩ ይገባል። አሁን እየተካሄዱ ያሉት የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴዎች ከተሞቹን በአግባቡ ለመምራት የመሥራት መገለጫዎች ናቸው።

ዳንኤል (ዶ/ር) እንዳብራሩት፤ ከተሞች የፈጠራ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የተለያዩ ፈጠራዎች ማዕከላት ተብለው ይወሰዳሉ፤ ንፁሕ አካባቢ መሆን አለባቸው፤ እግረኛ በነፃነት የሚንቀሳቀስባቸው፣ ወንጀለኛ የሌለባቸው፣ ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆኑ ይጠበቃል::

ደረጃቸውን ጠብቀው ማደግም አለባቸው። ደረጃውን የጠበቀ መንገድ፣ የመብራት ዝርጋታ፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራ፣ የአረንጓዴ ስፍራ፣ የቱሪስት መስሕቦች፣ የመናፈሻ ስፍራዎች ለከተሞች ያስፈልጋሉ። ከዚህ አኳያ የሚሠሩ ሥራዎች ለመጪው ትውልድ ጭምር የሚሆን ከተማን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ደረጃቸውና ሥነውበታቸው ተጠብቆ መገንባት ይኖርባቸዋል።

የመሬት አጠቃቀምም በአግባቡ እና በሥርዓት መመራት እንዳለበትም ያመላከታሉ። መንገዱን፣ መናፈሻ ስፍራውን፣ የንግድ ቦታውን ቅይጥ ቦታዎችን በአጠቃላይ የታሰበውን የትምህርት፣ የመዝናኛ፣ የሃይማኖት ስፍራዎችን በሙሉ ማኅበራዊ፣ አካባቢያዊ፣ ሕጋዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ባሕላዊ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ በማስገባት በፕላን መምራት ያሻል።

ከዚህ አኳያ ሲታይ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለእዚህ ዝግጁ ለማድረግ የሚከናወን አንዱ ጎልቶ የሚታይ ሞዴል ነው ሲሉ ዳንኤል (ዶ/ር) አስታውቀዋል:: አዲስ አበባ በኮሪደር ልማቱ በድጋሚ እየለማች መሆኗን ገልጸዋል::

በኮሪደር ልማቱ ተገቢ የሆኑ የተሽከርካሪ መንገዶች፣ የእግረኛ መሄጃዎች፣ የፍሳሽ እና የቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች፣ የንፁሕ መጠጥ ውሃ መስመር፣ የመብራትና የቴሌ መስመሮች በሙሉ በተናበበ መልኩ እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል:: የኮሪደር ልማቱ ዘላቂ የሆነ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ፕላን እንዲመጣ አድርጓል ብለዋል።

በኮሪደሩ በግራና ቀኝ ደግሞ ኪነ ሕንፃ ጥበባቸው የተጠበቀ የሚያምሩ ሕንፃዎች እንዲመጡ፣ ቅይጥ የሆነ እና በአንድ ሕንፃ ሁሉም አገልግሎት ያለበት ሞዴል ተግባራዊ መሆን ጀምሯል ይላሉ። ቢሮ ያለበትና እዚያው የሚሠራበት፣ የሚነገድበት፣ የሚኖርበት የሚለው ሀሳብ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹የኮሪደር ልማት የከተማ ዲዛይን አንዱ ሞዴል ነው። ሌሎች ሀገራትም ይሄንን ተግባራዊ አድርገዋል›› ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከተሞችን ዳግም ማልማት የሚለው ሀሳብ የተጀመረው በእንግሊዝ ሀገር በተካሄደው የኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት በተለይም በ1850 ዓ.ም ነው። በወቅቱ የኮሪደር ልማት ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል የፋብሪካ ምርትን በአግባቡ ማጓጓዝ፣ የአካባቢን ፅዳት ማስጠበቅ፣ የከተማ ውበት ማስጠበቅ የሚሉት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል::

የሀገራችን ኮሪደር ልማት የከተማ ሰው በነፃነት የሚንቀሳቀስበት፣ የሚኖርበት፣ የሚዝናናበት፣ የቱሪዝም መስሕብ እና የውበት ከተማ እንዲሆን እና ዘላቂ የሆነ ልማትን ለማረጋገጥ የመጣ የልማት ሞዴል መሆኑን አስታውቀዋል። ሞዴሉን በሌሎች ከተሞችም ላይ በተመሳሳይ በመተግበር ከተሞችን የልማት ማዕከላት ማድረግ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል። ተገቢ የቤት አቅርቦት የተሟላባቸው ከተሞችንም ከመፍጠር አንጻር መንግሥት የፋይናንስ ተቋማትንም በማገናኘት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዳንኤል (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፤ በ1900 ዓ.ም አካባቢ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሲመሠረት ሚናስ የሚባል የመጀመሪያው አርመናዊ ማስተር አርክቴክት ከተማዋን በፕላን ለመሥራት ጥረቶች አድርጓል። ሰፈሮችን የማፍረስ እንቅስቃሴዎችም ነበሩ። በጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅትም እንዲሁ አዲስ አበባ የፈረንሳይ እና የጣሊያን አርክቴክቶች ሲፈራረቁባት ነበር::

መዲናዋን ዳግም የማልማት ጥያቄ የከተማ አስተዳደሩንና የፌዴራል መንግሥቱን አመራር ውሳኔና ቁርጠኝነትን የጠየቀ መሆኑን ጠቅሰዋል:: ከምሥረታዋ ችግር የነበረባትን እና ያለ ፕላን ያደገችውን አዲስ አበባ የመጣችበትን አካሄድ ለመቀየር ውሳኔ በማሳለፍ ሕግና ሥርዓትን እንደገና በማሰብ ዳግም እየለማች መሆኑን ጠቁመዋል። ከተማዋ አሁን ይበል በሚያሰኝ ደረጃ ላይ ትገኛለች ሲሉም ጠቅሰው፣ ይሄንንም በማጠናከር ለሚቀጥለው ትውልድ ጭምር የመኖሪያ፣ የመነገጃ፣ የማምረቻ፣ የሥራ ፈጠራ፣ የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ዋና ከተማ፤ የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ከተማ መሆኗ ከሌሎች ከተሞች ልዩ ባሕሪ እንዲኖራት ማድረጉን ገልጸዋል:: በዓለም ካሉት አራት ከተሞች አንዷ የዲፕሎማቲክ ከተማም ናት ያሉት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ይሄ ሁሉ ትሩፋት እያላት ከዚህ ሁሉ መጠቀም የሚያስችላትን ደረጃ ሳታሟላ ቆይታለች ብለዋል። ይሄንን ግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ አበባ ዳግም እየለማች መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ሌሎችም ጥሩ ምሳሌ በምትሆንበት ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከተማዋ የፕላን ጉድለት አለባት:: ፕላኑን የማስተግበር ጉድለትም አለ። ወደ ሀገሪቱ ሌሎች ከተሞች በሚኬድበት ጊዜም ፕላን ይዘጋጃል፤ ነገር ግን መሬት ወርዶ ተፈፃሚ አይሆንም። አንዳንዱ ፕላን ደግሞ ያለጊዜ ይመጣል። ከተማን በእቅድ እና በፕላን በመምራት የ10፣ የ20፣ የ30 ዓመታት በቂ የኃይል እና የውሃ አቅርቦት፣ በቂ ትምህርት ቤት፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ ጤና ተቋማት፣ የመናፈሻ እንዲሁም የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች መገንባት ያስፈልጋል።

እስካሁን ባለው አካሄድ አዲስ አበባ በቂ ውሃ የላትም፤ የኃይል አቅርቦት እጥረትም ነበረባት። የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመናፈሻ ስፍራዎች፣ የልጆች መናፈሻ ስፍራዎች እጥረት አለ። ይህንን ከግምት በማስገባትም አሁን በኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መሄጃ ክፍት ስፍራዎች፣ የብስክሌት መሄጃዎች፣ በየቦታው ባሉ ኪስ ቦታዎች ዛፎችን በመትከል እና አረንጓዴን ስፍራዎችን የመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ሲሉ ያብራራሉ።

የመብራት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ጨምሮ ሌሎችም ሰፋፊ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰው፣ እነዚህን ሁሉ ችግሮች በመለየት በዘርፍ ደረጃ የከተማ አስተዳደሩም ይሄንን በመሥራት አሁን በግልጽ የታየውን ለውጥ እያመጣ ይገኛል ብለዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲም በዚህ ላይ ባለው ተሳትፎ ፕሮጀክቶችን በብቃት ሠርቶ አስረክቧል ሲሉም ዳንኤል (ዶ/ር) ይናገራሉ። የኮሪደር ልማቱ ሥራ ላይ ሲጠናቀቅም አዲስ አበባ ውብ፣ የፈጠራ ማዕከል፣ የቱሪዝም፣ የማኑፋክቸሪንግ ከተማ ምንጭ እንደምትሆን ጠቁመዋል::

በከተማ ፕላን በከተማ ውስጥ ያለውን አጠቃላይ የመሬት አጠቃቀም በአግባቡና በሥርዓት መምራት ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል:: በሌሎች ሀገሮች አቻ ከተሞች ያለውን ሁኔታ በንፅፅር ሲገልጹም የደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ የሆነችው ሴኡል ከተማ በአብነት አንስተዋል:: ሴኡል ከፍተኛ ጥግጊት ያላት ከተማ ናት ያሉት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ 10 በመቶ ክፍት የመኖሪያ ቤቶች እንዳላትም ጠቁመዋል:: ይህም ወደ ከተሜነት የሚገባው ሰው የመኖሪያ ቤት እንዳይቸገር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። የእኛም ከተሞች ከፊት ለፊት የሚመጣውን ከተሜነት በሚሸከም መልኩ ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ዳንኤል እንዳብራሩት (ዶ/ር) አሁን በከተማዋ በኮሪደር ልማቱ እየተከናወነ ያለው ተግባር ከተሞች እንዴት ውበታቸውን አጉልተው ማሳየት እንደሚችሉ ማሳያ ነው። በኮሪደር ልማቱ በአዲስ አበባ እየታዩ ያሉትን እነዚህ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እንዲሰፉ ማድረግ ያስፈልጋል፣ በአንዳንድ የክልል ከተሞች የኮሪደር መጀመሩን ጠቅሰው፣ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውቀዋል::

በዚህም ሕዝቡ ከከተሞቹ ትሩፋት እንዲጠቀም ማድረግ እንደሚቻል አስታውቀዋል፤ ከተሞቹ እንዲያድጉ፣ የሥራ ፈጠራ ማዕከላት፣ የመናፈሻ ማዕከላት እንዲሆኑ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል:: ይሄንን አጠናክሮ መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረው፣ የሀገሪቱን ልማት፣ እድገት እና ብልፅግና ለማረጋገጥ በፕላን ላይ የተመሠረተ ከተማ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ዳንኤል (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ ስለሀገሪቱ ከተሞች በትክክል ማሰብ የሚገባበት ጊዜ (The right time to think pink) አሁን ነው። ጉድለት አለ፤ ከተሞች በፕላን እየተመሩ አይደለም። ዘላቂ የሆነ የመሬት አጠቃቀም በፕላን በማዘጋጀት መሬትን ለታሰበው ዓላማ በማዋል የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ በአግባቡ ሊሠራ ይገባል። ይህንን ሁኔታ አዲስ አበባ ላይ የፕላኑ አካል እንዲሆን ለማድረግ ማስተካከያ እየተሠራ ነው።

የፕላን ችግር ያለበትን ሁኔታ ለማረም የኮሪደር ልማቱ ሕግና ደንብ በማምጣት የከተማው ካቢኔም የፕላኑ አካል እንዲሆን በማድረግ የአዲስ አበባ የአስረኛ ፕላን ትግበራ አንዱ አካል መደረጉን አስታውቀዋል።

ማኅበረሰቡ እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከተሞችን ለማስዋብ፣ ከተሞች የሥራ ማዕከላት፣ የውበት፣ የቱሪዝም ማዕከላት እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ መንቃት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል። አሁን በየከተሞቻችን የሚታየው ደካማ አካሄድ ለመቀየር ራዕይ እና ፕላንን ተግባራዊ በማድረግ ከተሞቹን በማልማት ላይ መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል:: ለእዚህም ከሳጥን ውጪ በማሰብ ስማርት ከተሞችን መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል::

በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበው፣ በሌሎችም ከተሞች ሁለተኛ፣ ሦስተኛ ዋና ከተማ እየተባለ ሁሉም ከተሞች የቱሪዝም፣ የንግድ፣ የማምረቻ፣ የመናፈሻ ማዕከላት በመሆን የየራሳቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You