በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በአትሌት ደራርቱ ቱሉ ተሰይሞ በሱሉልታ የተገነባው የስፖርት ማሠልጠኛ እና የምርምር ኢንስቲትዩት ትናንት በይፋ ተመርቆ ወደ ሥራ ገባ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳና ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ኢንስቲትዩቱን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በጀግናዋ አትሌት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የተሰየመው ኢንስቲትዩት የግንባታ ሥራው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ለማስፋፋትና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንዳስገነባው ተጠቁሟል።
ከፍተኛ በጀት ወጥቶበት የተገነባው ይህ የስፖርት ማዕከል ዘመናዊና ደረጃውን ጠብቆ መገንባቱም ተገልጿል። አቶ ሽመልስ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ክልሉ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት ትልቅ ሥፍራ እንዳለው በማስታወስ በጀግናዋና ፈር ቀዳጇ አትሌት ደራርቱ ቱሉ የተሰየመው ለእንቁዋ አትሌት እና ላለፈው ታሪክ ብቻ ሳይሆን ክልሉ በአትሌቲክስ ላይ ያለውን ድርሻ ለማሳየት እንዲሁም ምርጥ ስፖርተኞችን ለማፍራ በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል።
“የደራርቱን ስም እኛ አሁን የምናነሳው ሳይሆን ሁሌም የሚኖርና ለዘላለም የተጻፈ ነው። በአትሌቲክሱ ችግር ውስጥ ሆና በጠንካራ ሥራና ውጤት ታሪክ በመሥራት የመጀመርያ ሴት ጥቁር የኦሊምፒክ የ 10ሺህ ሜትር ባለድል በመሆን የተጻፈ ስም” ያሉት አቶ ሽመልስ፣ በኢንስቲትዩቱ የሚሠለጥኑ ተተኪ አትሌቶች የእሷን አርአያ ተከትሎ ውጤታማና ሀገርን ማስጠራት እንዲችሉ በማድረግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ በስሟ በመሰየሙ ትልቅ ደስታ እንደተሰማት የገለፀችው የቀድሞዋ ኮከብና የአሁኗ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ፣ የክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ “ለሀገር ሰርተሻል ይገባሻል” ብሎ በስሟ ኢንስቲትዩቱን በመሰየሙ ልባዊ ምስጋናዋን አቅርባለች። “ባገኘው እድልና እውቀት ሕዝብን ማገልገል አለብን፣ ሁሌም ዝቅ ብለን ደከመን ሰለቸን ሳንል ሕዝባችንን ማገልገል ይኖርብናል” በማለትም ተናግራለች።
የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በኢትዮጵያ ከተካሄደ ረጅም ዓመት እንደሆነ የጠቆመችው ደራርቱ፣ ይህም የሆነው በአህጉሪቱ እንደዚህ ዓይነት የስፖርት ሥልጠና እና ምርምር ማእከል አለመኖር አንዱ ምክንያት ነው ብላለች። አሁን ግን ኢትዮጵያ ማንኛውንም ትልቅ ውድድር ማዘጋጀት ትችላለችና ይህንን ዘመናዊና ትልቅ ኢንስቲትዩት ሁሉም ሰው ሊጠብቀውና ሊያሳድገው እንደሚገባ ተናግራለች።
የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማትዮስ ሰቦቃ በበኩላቸው፣ የክሉሉ መንግሥት ለስፖርት ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት ትልቅ በጀት መድቦ ዘመናዊውን እንስቲትዩት ማሠራቱን ተናግረዋል። ተቋሙ በትልቅነቱና ባካታተቸው ፋሲሊቲዎች እንደ ሀገር ትልቅ በመሆኑ በሥልጠናና ምርምር ለስፖርቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የማይተካ መሆኑንም ጠቁመዋል። የሀገሪቱን ስፖርት ለማሳደግ እንዲሁም ስብራቱን ለመጠገን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም አክለዋል።
የኢንስቲትዩቱ ግንባታ ሥራ በ2008 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ በ16 የስፖርት ዓይነቶች ከ800 በላይ ስፖርተኞችን ተቀብሎ የማሠልጠን አቅም እንዳለው ተጠቁማል፡፡ እንደ ሀገር የሚታየውን የሥልጠናና ምርምር ማዕከላት ችግር እንደሚያቃልልም ተጠቅሷል። ለግንባታው ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ታውቋል።
የኦሊምፒክና የፊፋን ደረጃ ጠብቆ የተገነባው ይህ ኢንስቲትዩት በውስጡ 196 የስፖርተኞች ማደሪያ ክፍል፣ 2 የአስተዳደር መኖሪያ ቤቶች፣ 80 የአሠልጣኞች መኖሪያ፣ 24 የመማሪያ ክፍሎች፣ 2 የጥናትና ምርምር ክፍሎች፣ ዘመናዊ ጂምናዝየም፣ 3 የእግር ኳስ ሜዳ፣ 1 የሩጫ መም፣ 2 የእጅ ኳስ ሜዳ፣ 4 የቅርጫት ኳስ ሜዳ፣ 6 የመረብ ኳስ ሜዳ፣ 6 የሜዳ ቴኒስ፣ 2 የውሃ መዋኛ ገንዳ፣ 5200 ሰው መያዝ የሚችል አዳራሽ፣ 250 ሰው የሚያስተናግድ ዘመናዊ አዳራሽ፣ 4 የቦክስ ሪንጎች፣ ክሊኒክና የመዝናኛ ክፍሎች አሉት።
ተቋሙ ከ350 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን ስፖርቱንም በሳይንሳዊ መንገድ በመምራት የገቢ ማስገኛ ምንጭ ሆኖ ዘርፉ ከመንግሥት ድጎማ ተላቆ እራሱን እንዲችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተነግሯል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም