በከበሩ ማዕድናት የበለጸገችው ኢትዮጵያ እንደ ኦፓል፣ ኢምራልድና የመሳሰሉ ማእድናትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ታገኛለች። ይሁንና ማእድናቱ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበት መንገድ ሀገሪቱን በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ አዳላደረጋትም። ከኢትዮጵያ ይልቅ ማእድናቱን በጥሬው የሚቀበሉ ሀገሮችና ሕገወጦች የበለጠ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይገለጻል።
እነዚህ ማዕድናትም በተለምዶ ከወርቅ ያነሰ ዋጋ እንዳላቸው ተደርገው ይቆጠራሉ፤ እንደ ሀገርም ብዙ ትኩረት ሳይሰጣቸው እንደቆዩ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ብዙዎች እንደሚሉት ዘርፉ ገና ብዙ ያልተሠራበት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ የሚፈልግ ነው። ሌሎች ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበትና ችግሮቹን ለመፍታትም ብዙ መሥራትን የሚጠይቅ ነው። በዚህም ምክንያት በዘርፉ ተሠማርተው እየሠሩ ያሉ ጥቂት ተቋማትም ቢሆኑ በሚፈለገው ልክ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም።
በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ የማቅረብ የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸው ተቋማት መካከል የኦርቢት ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አንዱነው። አቶ ቴዎድሮስ ስንታየሁ የኦርቢት ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ከተመሠረተ ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በከበሩ ማዕድናትና ሌሎች የኢንዱስትሪ ማዕድናት አነስተኛ ፍለጋ እና ማውጣት ሥራ ተሠማርቶ እየሠራ ነው። ድርጅቱ ከ15 ዓመት በፊት የወሎ ደላንታ የኦፓል ማዕድን መገኘትን ምክንያት በማድረግ ማዕድን ላይ እሴት የመጨመር ሥራ ጀምሯል። በሀገሪቱም የመጀመሪያው የማዕድን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወሰዶ በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር የሚሠራ ብቸኛ የግል ድርጅት ነው። ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል።
የወሎ ኦፓል ለመጀመሪያ ጊዜ ለመላው ዓለም በማስተዋወቅ በአሜሪካና በአውሮፓ ገበያ እንዲቀርብ ያደረገ መሆኑን አቶ ቴዎድሮስ ጠቅሰው፣ ይህን ኦፓል እሴት በመጨመር ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች በመላው ዓለምና በአፍሪካ ገበያ እንዲቀርቡ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። ምርቱን ለአሜሪካ ፣ ለኤዥያ፣ ለጀርመን ፣ ለጃፓን፣ ለቻይና እና ለሌሎች ለሀገራትም ያቀርባል፡፡
ድርጅቱ ሥራውን ሲጀመር በኦፓል ማዕድን መሆኑን አቶ ቴዎድሮስ ሲያስታውሱ፤ የኦፓል መገኘትን ተከትሎ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በጣም ብዙ የከበሩ ማዕድናት ተገኝተዋል፤ በመገኘትም ላይ ናቸው። ድርጅቱም በእነዚህ ማዕድናት ላይ ይሠራል ሲሉ ገልጸዋል። ማዕድናቱ የተገኙባቸው ቦታዎች ድረስ ሄዶ በማረጋገጥ እና በአንዳንዶቹ ማዕድናት ላይም ከባህላዊ አምራቾች ጋር ማምረትን ጨምሮ ማዕድናቱን በማስመጣት እሴት በመጨመር /ፕሮሰስ በማድረግ/ እንደሚሠራ ያመላክታሉ።
ድርጅቱ አሁን ላይ በርካታ የከበሩ ማዕድናት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ሲገልጹ፤ ‹‹አሁን በሀገራችን ዋና ዋና ከሚባሉት የከበሩ ማእድናት መካከል በጥራት ደረጃው የሚታወቀው ኤመራልድ ማእድን ተገኝቷል። ኤመራልድ በዓለም ላይ ኮሎምቢያ እና በአፍሪካ ደግሞ በእነዛምቢያ ብቻ የሚመርት ነበር። በእኛ ሀገር ደግሞ ከሻኪሶ አካባቢ የሚመጣ ኤመራልድ፣ ከኮሎምቢያው ኤመራልድ የሚወዳደር (የሚበልጥ) መሆኑ ተረጋግጧል። ከትግራይ ክልል የተገኘው ሳፋየር ማዕድንም እንዲሁ በጣም ተፈላጊ ነው›› ይላሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ በወሎ ጥቁር የሚባል አፓል አለ። አሁን ላሊበላ አካባቢ የተገኘው ይህ ጥቁር ኦፓል በዓለም ላይ በአውስትራሊያ ብቻ ይመረታል። ይህንንም በተመለከተ ከማዕድን ሚኒስቴር እና ከአንድ የውጭ ዩኒቨርሲቲና ላብራቶሪ ጋር በመተባበር ጥናት እንዲካሄድ ተደርጎ የላሊበላ ኦፓል ጥቁር ኦፓል ተብሎ በዓለም ላይ ሁለተኛ ግኝት ሆኗል።
በሰሜን ሸዋና አፋር አካባቢም ፋየር ኦፓል የሚባል የተለየ አይነት ባህሪ ያለው የኦፓል አይነት መገኘቱንም ጠቁመዋል። በአሜሪካ ብቻ ይገኝ የነበረው ‹ሰን ስቶን› የተሰኘ የተለየ አይነት ባህሪ ያለው የከበረ ማዕድን በአፋር ክልል መገኘቱንም ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ የማእድኑ ሁለተኛዋ መገኛ ሆናለች ብለዋል። እነዚህ የከበሩ ማእድናት በሀገሪቱ ከሚገኙት የከበሩ ማእድናት ከብዙ በጥቂቱ ናቸው።
‹‹የከበሩት ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር የመጀመሪያዎቹ ስለሆንን እኛ ራሳችንን እንደ መሞከሪያ ነው ያየነው፤ ሕጎች እና የተለያዩ ነገሮች የወጡት በኛ ምክንያት ›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ድርጅታቸው ባለው አቅም ልክ እንዳይሠራ ያደረጉ ዛሬም ድረስ ያልተፈቱ ብዙ ችግሮች እንዳሉበትም አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ዋናው የችግር ምንጭ እንደ ሀገር የሀብቱ ባለቤት መሆናችን አለማወቃችን ነው። ለዚህም መነሻ ምክንያቱ ደግሞ አንደኛ የከበሩ ማዕደናቱ ሀብት ተብለው አይታሰቡም ነበር። ሁለተኛው ጥቅማቸው ያን ያህል አይታወቅም፤ ትኩረት አልተሰጠው ነበር። ሦስተኛው እሴት የመጨመሩ ሂደት ባለቤት የለውም።
የከበሩ ማእድናት ሥራ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አውቆት እንደሌሎች ኢንዱስትሪዎች የሚመራ አልነበረም ሲሉ ጠቅሰው፣ የማዕድን ሚኒስቴር በሚገባ ተረድቶት በባለቤትነት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እየመራው አይደለም በማለት ጠቁመዋል። አሁንም ድረስ የዘለቀው ችግር ባለቤት የሌለው ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው በማለት፤ ‹‹የሀብቱ ባለቤት መሆናችንን አለማወቃችን እና ሀብቱ መኖሩን ካወቅን በኋላ እንዴትና በምን መልኩ መጠቀም እንዳለብን አለማወቃችን የሁሉም ችግር መነሻ ነው›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ድርጅቱ በተለይ እሴት መጨመሩ ላይ ያለውን አቅም በሙሉ ሳይጠቀም 15 በመቶ ያህል በማይሞላ አቅሙ እየሠራ መሆኑንም ይገልጻሉ። አቶ ቴዎድሮስ እንደተናገሩት፤ ‹‹ከ 100 ሰው በላይ መቅጠር የሚችሉ ማሽነሪዎች እና መሣሪያዎችን ይዘን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እንዳንሠራ ሆነናል። ያሉንን ሠራተኞች ላለመበተን ብለን ለዓመታት እየታገልን ነው፡፡›› ይላሉ።
እሳቸው እንዳመለከቱት፤ እንደ ድርጅት አንዱ ትልቁ ችግር ሆኖ የሚነሳው ደረሰኝ አለማግኘት ነው። የ 10 እና የ20 ሚሊዮን ብር ማዕድን ተገዝቶ ደረሰኝ የለውም፤ ማወራረድም አይቻልም። ለአብነትም በዓመቱ መጨረሻ የ 10 እና የ20 ሚሊዮን ብር ጥሬ እቃ ተገዝቶ፤ 30 እና 40 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ማዕድን ወደውጭ ቢላክ ለጥሬ እቃ ውጭ የሆነውን ገንዘብ የምናወራርድበት ደረሰኝ የለም። በዚህ ምክንያት መሥራት አልተቻለም። ይህንን ችግር በተለያየ ጊዜ ለማሳወቅ የተሞከረ ቢሆንም መፍትሔ አላገኘም።
አሁን ላይ ከማዕድን ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጦች ዘርፍ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ በመጠናቀቁ ተስፋ ስለመኖሩ ተናግረዋል። ስትራቴጂው ተግባራዊ ሲደረግ ችግሮች ይፈታሉ የሚል እምነትም አላቸው። ሁለተኛው ተስፋም ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ባለሥልጣን ጋር በመሆን ኦፓልና ኤመራልድን በመሳሰሉት በተወሰኑት ማዕድናት ላይ ብሔራዊ ደረጃ እየወጣ መሆኑ ነው። አቶ ቴዎድሮስ እነዚህ ሁሉ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ሲገባ የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚቻል እምነታቸው ነው፡፡
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ማብራሪያ፤ የከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች የሚለዩት ለየት ያሉ ባሕርያት አሉት። የሚጠቀመው በጣም ቀላል ውድ ያልሆነ ቴክኖሎጂ ነው። ከማሽነሪዎቹ የተወሰኑት ለጊዜው በሀገር ውስጥ ላይሰሩ ይችላሉ እንጂ፣ አብዛኛዎቹ በሀገር ውስጥ መመረት የሚችሉ ናቸው። ከውጭ እናምጣ ብንልም ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉና ዋጋቸውም እርካሽ ነው።
ለዘርፉ ትልቁ ግብዓት ተብለው ከሚታሰቡት መሠረታዊ ነገሮች አንደኛው የሠለጠነ የሰው ኃይል ሲሆን፤ ሁለተኛው የጥሬ እቃ አቅርቦት ነው። እንደሚታወቀው ሀገሪቱ ብዙ ወጣት የሰው ኃይል ያላት እንደመሆኗ በአጭር ጊዜ ሥልጠና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ይቻላል፡፡
‹‹እኛ ለሠራተኞቻችን በሠጠናቸው የአጭር ጊዜ ሥልጠና ብቁ ሠራተኞች አፍርተን በእነርሱ የተሠሩ ሥራዎች ለውጭ ገበያ እያቀረብን ነው። ቻይናና ህንድን በመሳሰሉ ሀገራት ከተመረቱ ምርቶች ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ማቅረብ የቻልነው እኛው በሰጠነው ሥልጠና ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
በተለይ ይህ ዘርፍ ለየት የሚያደርገው የሌላ ሀገር እገዛ ሳይፈለግ በኛው አቅም ሌሎችንም አሠልጥኖና አብቅቶ ችሎታው እንዲኖራቸው በአጭር ጊዜ በራስ አቅም ትልቅ ኢንዱስትሪ መገንባት የሚቻል መሆኑ ላይ ነው ሲሉም አቶ ቴዎድሮስ ይገልጻሉ፤ በዚህ ላይ የተሠራው ሥራ የከበሩ ማእድናትን ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹የብዙዎቹ የከበሩ ድንጋዮች ዋጋ ከወርቅ በላይ ነው። እኛ በተለመዶ የምናውቀው ወርቅን ብቻ ስለሆነ እንጂ ኦፓልን ጨምሮ ሌሎች የከበሩ ማእድናት ከወርቅ በላይ ዋጋ የሚያወጡ ናቸው ›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ፤ በዘርፉ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባትም ከፍተኛ የሥራ እድል መፍጠር ይቻላል። እያንዳንዱ የከበረ ማዕድን በሰው እጅ እሴት ሊጨመርበት /ፕሮሰስ ሊደረግ/ ይችላል። በኦፓል ብቻ እንኳን በአንድ ዓመት ውስጥ ለብዙ ሺዎች የሥራ እድል መፍጠር ይቻላል። ምክንያቱም እንደ ሀገር ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሬ ኦፓል ኤክስፖርት እየተደረገ ነው። በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ ብቸኛ ኦፓል ምርት አቅራቢ ኢትዮጵያ ስትሆን፣ በቂ ክምችትም አላት። የ2015 የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ 53 ሺ ጥሬ ኦፓል ለዓለም ገበያ መላኩን ያመለክታል፤ ይህም ምን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ኦፓል በሀገሪቱ እንዳለ ይጠቁማል።
‹‹ለውጭ ገበያ የሚላከው ኦፓል እሴት ቢጨመርበት የሚፈጥረው የሥራ እድልና የሚያመጣው ገቢ ከፍተኛ ነው፤ በዚህም ብቸኛ መሆናችን ከተወዳዳሪነት አንጻር አንዱ ልጠቀምበት የሚገባ መልካም አጋጣሚ ነው›› ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ ይገልጻሉ። የከበሩ ማእድናትን በአግባቡ እያስተዳደርን አይደለም በማለት ሲያስረዱ፤ በሕገወጥ መንገድና በሕጋዊ ሽፋን ወደ ውጭ እንደሚላክ ጠቁመዋል። ይህ ቢስተካከል ደግሞ ኢትዮጵያ ብቸኛ የሀብቱ ምንጭ በመሆኗ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ምርቱን ገበያው በሚፈለገው ልክ ማቅረብ ይቻላል ሲሉ አስገንዘበዋል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት፤ ምርቱ ለዓለም ገበያ መቅረብ የሚችለው ደረጃው ሲረጋገጥ ነው። መስፈርቱን አሟልቶ ደረጃውን ጠብቆ ለገበያ ካልቀረበ ገበያ ላይ ተቀባይነት አያገኝም። የኢትዮጵያ ምርቶች ገበያው ውስጥ ተቀባይነት እንዳላቸው ዋናው አንዱ ማሳያ አሜሪካና አውሮፓ መሆኑ ነው።
በዚህ ኢንዱስትሪ ላይ ዋና ተብለው ለብዙ ዓመታት የሚቆጠሩት ጀርመኖች ናቸው። ዛሬም በዓለም ላይ የጀርመን የከበሩ ማዕድናት ቀራጺዎች ዋና ተብለው የሚታሰቡ ናቸው። ለጀርመን ገበያም ምርታችንን እናቀርባለን። ጀርመን ገበያ አገኘን ማለት ደግሞ የምርቱ ጥራት ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል። ይህም የመጀመሪያ ኢትዮጵያ ኦፓል በብዛት የምታመርት መሆኑ ተወዳዳሪነቱን ቀላል ያደርገዋል። ሌላው ደግሞ እስካሁን ባልተደራጀና ባልታገዘ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳን ተወዳዳሪ ሆኖ መሸጥ መቻሉ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን፣ ስፔንና በመሳሳሉት ሀገሮች ምርቶቻችን ተደራሽ ሆነዋል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ለሀገር ውስጥ ገበያ ደግሞ ብዙ ወርቅና ብር የማይጠቀሙ ቀለል ያሉ የፋሽን ጌጣጌጦችን /የፋሽን ጆለሪ/ ለቱሪስት በሚሆኑ በተለያየ መልኩ ወደ ጌጣጌጥነት በመቀየር ለመሸጫ ሱቆች እያቀረቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከበሩት ማዕድናት ዙሪያ ያለው የኢትዮጵያውያን ግንዛቤም እየጨመረ መምጣቱን አቶ ቴዎድሮስ ጠቅሰዋል። ሌሎች ሰዎችም በዘርፉ ገብተው እየሠሩ ሲሆን፤ አበረታች ለውጥ እየታየ ነው ይላሉ። በሌላ መልኩም በዲጂታል ፕላትፎርሙ ላይ በተወሰነ መልኩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጸው፤ ነገሮች ሲስተካከሉ ደግሞ ዲጂታል ፕላትፎርሙን ለመጠቀም ዝግጅት መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
ዘርፉ ካለበት የደረሰኝ ችግር በተጨማሪ ብዙ ካፒታል የሚፈልግ እንደመሆኑ የብድርና የድጋፍ አገልግሎት የለውም ሲሉም አቶ ቴዎድሮስ አመልክተዋል፤ በሚገባ ስለማይታወቅም የፋይናንስ ተቋማት በቀላሉ የሚደገፉት እንዳልሆነም ተናግረዋል። ድርጅቱ 30 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ሲሆን ፤ በቀጣይም በዘር የሚስተዋሉ ችግሮች ሲቀረፉ ለብዙዎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
በከበሩት ማዕድናት ዘርፍ በርካታ እውቀትና ዝግጁነት እንዳለው ጠቅሰው፣ ልማቱን በስፋት ለማካሄድ ግን ችግሮች እስኪቀረፉ በትዕግስት እየጠበቀ ነው ብለዋል። ብዙ ሰዎች ማሰልጠን የሚችል አቅምና በዚያው ልክ ገበያ እንዳለውም ይገልጻሉ። ‹‹ማዕድኑ ከሚወጣበት አንስቶ እስከ ገበያ ያለውን የእሴት ሰንሰለት በሙሉ በደንብ አድርገን እናውቃለን የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ እሴት ከመጨመር ባሻገር በብርና በወርቅ የተሠራ ጌጣጌጥ ለውጭ ሀገር ገበያና ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡
አቶ ቴዎድሮስ እንዳብራሩት፤ እነዚህ ችግሮች ከተፈቱ አንደኛው የማዕድናት መቅረጽና ፕሮስስ ማድረጉን ድርጅቱ ብዙ የሰው ኃይል በመቅጠር ባለው አቅም ልክ እየሠራ ትልቅ በሆነ የምርት ሂደት ሥራውን ይሠራል። ማዕድኑን በጥሬ ከመሸጥ ይልቅ እሴት ጨምሮ በጌጣጌጥ መልኩ ሠርቶ መሸጥ የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል፤ እነዚህን ሥራዎች ለመሥራት ዝግጅቱን አጠናቀዋል። በቀጣይም በርካቶችን በማሠልጠንና ትላልቅ ሥራዎችን በመስራት ከድርጅቱ ባለፈ ለሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ተጨማሪ አቅም መሆን እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም