
የሃውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር አካባቢ የደቀኑት ስጋት በአጠቃላይ የዓለም ንግድ ሥርዓት ላይ እክል ፈጥሯል፡
ግዙፉ የባሕር ሎጂስቲክ አገልግሎት ማርስክ አፍሪካ፣ እስያ እና አውሮፓ በዚህ ችግር ምክንያት እየተፈተኑ እንደሚገኙ ድርጅቱ ተናግሯል፡፡
በእስራኤልና ሐማስ መካከል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ከአሜሪካና እስራኤል ጋር ግንኙነት ባላቸው የንግድ መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የፈጸሙት ሀውቲዎች፤ እስራኤል ከጋዛ እስከምትወጣ ድረስ ጥቃት ማድረሳቸውን እንደሚቀጥሉ መዛታቸውን ተከትሎ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የንግድ መርቦች የደኅንነት ስጋት አጥልቶባቸዋል፡፡
በቀጣናው ለደኅንነት አስተማማኝ ሁኔታ ባለመኖሩ አማራጭ መተላለፊያዎችን ለመጠቀም ተገደናል ያለው ማርስክ ይህም ውጭዎችን እንዲጨምር በማድረጉ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ንረት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ነው ያነሳው፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ ወደ አውሮፓ በሚያሻግረው ስዊዝ ቦይ እና ወደ ባብ ኤል መንደብ መተላለፊያ ለመድረስ በሚደረገው ጉዞ ላይ ስጋቶች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ወደ ሩቅ ምሥራቅ እና እስያ መተላለፊያዎች ላይ ተመሳሳይ እክሎች እንደሚያጋጥሙት ነው የመርከብ ድርጅቱ ያስታወቀው፡፡
በዚህ የተነሳም የመርከቦቹን የመጫን አቅም ከ15 እስከ 20 በመቶ እንዲቀንስ በማድረግ የሀውቲዎችን ጥቃት ሽሽት ተጨማሪ ጊዜ እና ወጪ በሚጠይቀው አፍሪካን ኬፕ በተባለ መተላለፊያ በመጠቀም እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ ዋነኛ የምርት ምንጭ እንደሆነ በሚነገርለት እስያ እየተስፋፋ የመጣው የደኅንነት ስጋት በቀጣይ በንግድ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ችግር ከማስከተሉ በፊት መፍትሔ እንዲበጅለት መጠየቁን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
የዓለም 30 በመቶ የንግድ ኮንቴነሮች በሚተላለፉበት ቀይ ባሕር ካሳለፍነው መጋቢት ወር ጀምሮ በባብ ኤል መንደብ እና በስዊዝ ካናል የሚተላለፉ መርከቦች በግማሽ ቀንሰዋል፡፡
በነዚህ ሁለት መተላለፊያዎች በዓመት ከ30ሺ – 50 ሺ መርከቦች ይተላለፋሉ፤ 12 በመቶ የዓለም ንግድ ፣ 15 በመቶ የዓለም ነዳጅ ምርት ፣ የእስያ እና አውሮፓ 40 በመቶ ንግድ በነዚህ መስመሮች የሚተላለፍ ነው፡፡
በአጠቃላይ ሁለቱ አሕጉሮች ብቻ እስከ 700 ቢሊዮን ዶላር ድረስ የሚወጣ የንግድ ሸቀጦቻቸውን ስጋት ላይ በወደቀው መስመር ያሳልፋሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም