‹‹በቡና ግብይት በላኪውና በአቅራቢው መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ እንሰራለን›› -ዶክተር አዱኛ ደበላ የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር

ቡና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እየተጫወተ ያለው ሚና በእጅጉ ከፍተኛ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከሚታወቁ የሀገር ውስጥ ምርቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል፡፡ 50 በመቶ የሚሆነውንም የሀገር ኢኮኖሚ የሚሸፍን ምርት ነው፡፡

ታዲያ ይህ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘው የቡና ምርት ዕድገት እንዲጨምር ምን አይነት አሰራሮች ተቀርጸው እየተሰሩ ነው? በቀጥታ ትስስር የግብይት ስርዓት በአቅራቢና ላኪዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች እንዴት እየተፈቱ ነው? በቡና እና ሻይ ግብይት ወቅት በሚፈጠሩ አለመግባባቶች በዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ እንዳይጎዳ ምን አሰራሮች ተቀምጠዋል? በሚሉና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ከዶክተር አዱኛ ደበላ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ምንባብ!፡፡

አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምን አቅዶ ምን አሳካ?

ዶክተር አዱኛ፡- የቡና እና ሻይ ግብይትን ለማከናወን ብሎም በሂደቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለይቶ በማውጣት ልማቱን ማሳደግ አስፈላጊ ስለሆነ ባለስልጣኑ ኃላፊነት ተሰጥቶት እየሰራ ነው። ከዚህ አንጻር ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ስትራቴጂክ ዕቅድ በመቅረጽ ልማቱና ግብይቱ ላይ ያሉ ችግሮች ምንድ ናቸው? እንዴትስ እንቀርፋቸዋለን በሚል መነሻ የ15 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድና ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ስራዎች እየተሰሩ ነው።

ይህም በግብይቱ ውስጥ ያለው ችግር ልማቱን አንቆ የያዘ፤ አልፎ ተርፎም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ስላልሆነ ቡናውን ሜዳ ላይ የሚደፋበት ዘመን ነበር። በዋናነት የግብይት ስርዓቱ በጣም የተንዛዛ፤ እሴት የማይጨምር እና ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነበር። ይህን በማስቀረት የግብይት ስርዓቱን በማሳጠር በልማቱ እና በግብይቱ ላይ ለውጥ ሊመጣ ይገባል በሚል እሳቤ ማሻሻያ ተሰርቷል። በሪፎርሙ የተለያዩ የግብይት አማራጮች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል።

ከዚህ በፊት አርሶ አደሩ ቡናውን ማሳው ላይ ይሸጥ ነበር። አርሶ አደሩ ለአቅራቢው ከሸጠ በኋላ አቅራቢው ወደ ምርት ገበያ ወስዶ ይሸጣል። ላኪው ከምርት ገበያ ገዝቶ ለውጭ ገበያ ያቀርባል። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች አማራጮች እንዲኖሩ በማሻሻያው ላይ በደንብ ተመላክቷል። በዚህም አርሶ አደሩ አምርቶ ቀጥታ ወደ ውጭ እንዲልክ፤ ከላኪ ጋር መረካከብ የሚችልበት መንገድና ሌሎች በርካታ አማራጮች መጥተዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተጀመረው ጥራትን ማሻሻል፤ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ፤ ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት መጨመር እና ተጠቃሚነትን ማጉላት ትኩረት ተሰጥቶታል። ከዚህ አንጻር ቡና አርሶ አደሩን ብሎም ሀገርን መጥቀም እንዲችል ተደርጎ እየተሰራ ነው።

አዲስ ዘመን፡– የቡና ግብይት ስርዓቱ እንዲያጥር መደረጉ ምን ጥቅም አስገኘ ?

ዶክተር አዱኛ፡- የግብይት ስርዓቱን ማሳጠር ብቻ ሳይሆን ከአንድ ኪሎ ቡና ዝቅተኛ ዋጋ ህዳግ ማስተካከል አስፈላጊ ነበር። ምክንያቱም ቡና ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ 10 ዶላር ከተሸጠ ላኪው በአምስት ዶላር እሸጣለሁ ሊል ይችላል። ስለዚህ የፈለገውን ያህል የቡና መጠን ያለጥራት ብንልክ የምንፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አንችልም። ይህን ለማሳጠር በ2011 ዓ.ም በሪፎርም የግብይት ስርዓቱ ካጠረ በኋላ 2013 ዓ.ም ዝቅተኛ የዋጋ ህዳግ እዲወሰንና አይነቱ ደረጃ እንዲኖረው ተደርጓል።

ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ሊሙ ቡና ደረጃ ሁለት የታጠበ በስድስት ዶላር የሚሸጥ ከሆነ በአማካይ መሸጥ ያለበት ከዘጠኝ እስከ ስድስት ዶላር ነው። ከዚያ በታች መሸጥ የለበትም በማለት ማዕቀፍ ተቀምጦለታል። ስለዚህ ላኪዎች ከገዥዎቻቸው ጋር ኮንትራት የሚገቡት ባለስልጣኑ በሚያወጣው የዋጋ ህዳግ ነው።

ወደ ውጭ የሚላከው የቡና ምርት አይነት ኮሜርሻል፤ ስፔሻሊቲ የሚባል ነው። ኮሜርሻል ማለት ደረጃው የወረደ በኒዮርክ ገበያ ላይ በጨረታ የሚሸጥ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ቡና የሚሸጠው የብራዚል ቡና ከተሸጠ በኋላ ነው። ለብራዚል ቡና ዋጋ ከተቆረጠ በኋላ ለኢትዮጵያ ቡና ሲቀነስ 20 እና 15 ተብሎ በልዩነት ይሸጣል።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ቡና በብራዚል የቡና ዋጋ ላይ ተንተርሶና እና ጥገኛ ሆኖ እንዲሸጥ የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነውʔ

ዶክተር አዱኛ፡- ይህ ጥያቄ የባለስጣኑ ሆኖ ለምን በብራዚል ቡና ላይ ተመርኩዞ ይሸጣል፤ የራሳችን ዋጋ ሊኖረን ይገባል በማለት ኮሜርሻል የሚባሉት ደረጃ አራትና አምስት መጠናቸውን በመቀነስ በዋናነት ስፔሻሊቲ ቡና ላይ በመስራት ኒዮርክ ገበያ ላይ ከብራዚል ቡና ጋር እኩል መወዳደር እንዲችል ማሻሻያ ተደርጓል። ስለሆነም የስፔሻሊቲ ቡናን ድርሻ ከፍ ለማድረግ በ2014 ዓ.ም የስፔሻሊቲ ቡናን ‹ፐርሰንቴጅ› ከ30 በመቶ ወደ 60 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል። የኮሜርሻሉ ከ70 በመቶ ወደ 40 በመቶ እንዲወርድ ተደርጓል። ይህ በመደረጉ በ2014 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

ስለዚህ በየጊዜው አሰራሩን በማሻሻል የግብይት አሰራሩ ሲስተካከል ወደ ውጭ የሚላከው የቡና መጠን ከፍ ሲል የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እያደገ መጥቷል። ስለሆነም አሁን ላይ በቡና ግብይቱ ላይ ያሉ ችግሮች እየተፈቱ ነው። ልማቱ ላይ ያሉ ችግሮች ደግሞ እንደ ሀገር የቡና መገኛና ለሌሎች ሀገራት ቡና የሰጠች ሀገር ሆና እያለ ነገር ግን የምርት መጠኑ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ዝቅተኛ ነው። ለዚህ ደግሞ አንዱ እና ዋናው ችግር የአረጁ ቡናዎች በስፋት መኖር ነው።

የአረጁ ቡናዎች ካልተነሱና ካልተቀየሩ በስተቀር ምርትና ምርታማነት እንደማያድግ በመረዳት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ መቶ መቶ ሺ ሄክታር ላይ ያሉ የአረጁ ቡናዎችን የማንሳትና በአዲስ የመትከል ስራ እየተሰራ ነው። በተሰራው ስራ የስፔሻሊቲ ቡና መጠን ከፍ ተደርጓል። በልማቱ ዘርፍ ምርትና ምርታማቱ ላይ ያሉ ችግሮችን የመቅረፍ ስራ ተከናውኗል። ስለዚህ እንዲህ እየተስተካከለ በ2017 ዓ.ም አንድ ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እናገኛለን ብለን አቅደን እየሰራን ነው። ይህንንም ለማሳካት ባለፉት ሶስት አራት ዓመታት ሰፋፊ ስራዎች በባለስልጣኑ ተከናውነዋል።

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ሶስት ዓመታት የተሰራው ስራ ኢትዮጵያ ካለት ታሪካዊ የቡና ስምና አቅም አንጻር ከሌሎች ሀገራት ጋር እንዳትወዳደር ያላደረጋት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ ነው ይባላልና በዚህ ላይ የእርሶ ምላሽ ምንድን ነው?

ዶክተር አዱኛ፡- እውነት ለመናገር ከዚህ በፊት ቡና ሻይና ቅመማቅመም በግብርና ሚኒስቴር በአንድ ዳይሬክተር ስር የነበረ ሲሆን ይህም በልማቱ ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር። ስለዚህ ግብይቱ ለንግድ ሚኒስቴር ልማቱን ለግብርና ሚኒስቴር የተሰጠ ነበር። ስለሆነም አሁን ላይ በአንድ ተቋም እንዲመራ መደረጉ በመንግስት በኩል ትኩረት መሰጠቱን ያሳያል። የራሱ በጀት ተመድቦለት፤ አዋጅ፤ ደንብ፤ መመሪያ ወጥቶለት ከልማት እስከ ግብይት የእሴት ሰንሰለቱን ተከትሎ የጥራት ደረጃውን ለማሳደግ በሚገባ እንዲሰራበት በአንድ ተቋም መመራቱ በመንግስት በኩል ትኩረት መሰጠቱን ያሳያል።

በተጨማሪ ከዚህ በፊት ቡና ላይ ችግሮች የነበሩ ሲሆን የውጭ ድርጅቶችና አንዳንድ ተቋማት በፈንድ ለመደገፍ ይቸገሩ ነበር። ዛሬ ላይ ችግሩ ተቀርፎ በርካታ ፕሮጀክቶች በቡና እና ሻይ ላይ እየተሰሩ ነው። ስለዚህ መንግስት ከሚበጀተው በጀት በተጨማሪ እስከ ታች ባለው መዋቅር ከስልጠና ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ነው። ዘርፉን መደገፍ የሚችሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂ እዲታገዙ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ስለዚህም ከምንግዜውም በላይ ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱን መረዳት ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- የቡና ግብይት በባህሪው ብዙ ሰንሰለቶችን የሚያልፍ እንደመሆኑ መጠን ለስርቆት የሚዳረግበት ዕድል ሰፊ ነውና ችግሩን ለመቅረፍ ምን ተሰርቷል? በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በአግባቡ ከመተግበር አኳያ ያለው ልምድ ምንድን ነው?

ዶክተር አዱኛ፡- እውነት ለመናገር በቡና ግብይት ላይ አሁንም ፈተናዎች አሉ። ሆኖም ግን እንደ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ፈተናውን ለመከላከል የተደረገው የግብይት ስርዓቱ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ማድረግ ነው። ስለዚህ አንድ ቡና ከጅማ ሲነሳ ሲስተም ውስጥ ገብቶ ወደየት እንደሚሄድ፤ የትኛው መጋዝን እንደሚገባ፤ መቼ አዲስ አበባ እንደሚደርስ ሲስተም ላይ ይታያል። እስከ አሰራሩ ድረስ ሲስተሙን ተከትሎ ይመጣል። አዲስ አበባ ሲደርስም ወደ ተፈቀደለት መጋዘን ብቻ መግባት አለበት። ነገር ግን አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ ወደ ሌላ ቦታ የሚወስድበት ሁኔታ ታይቷል።

ይህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥም በአዋጁ የተቀመጠው አንድ ቡና የጫነ መኪና ከተፈቀደለት መስመር ከወጣ እንዲወረስ ይደረጋል የሚል ነው። ስለዚህ ከአዲስ አበባ ፖሲስና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው። ከመስመር የወጡና ከተፈቀደላቸው መጋዘን ውጭ ሲያራግፉ የተገኙት ሙሉ በሙሉ ተይዘው እንዲወረሱ ተደርጓል። በዚህ ዓመት በአንድ ጊዜ ብቻ እስከ 13 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቡና እንዲወረስ ተደርጓል። አልፎ አልፎ እንዲህና መሰል ችግሮች ይፈጠራሉ። ከባለስልጣኑ ኬላ ሰራተኞች ጭምር እየተመሳጠሩ ቸግሮች የሚፈጠሩበት ሁኔታ አለ።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር ክትትል በማድረግ 11 የሚደርሱ የኬላ ሰራተኞች ላይ በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ በቁጥጥር እንዲውሉ ተደርጓል። ስለዚህ ስርቆቱን መቶ በመቶ ቀርፈናል አንልም፤ ሆኖም ግን ቴክኖሎጂ በማበልጸግ ቡና የት እንደሚደርስ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግበት ስርዓት ተፈጥሯል።

ቡና ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ ሲላክ የሚቀሽብበት እና ሹፌሮች የሚታገቱበት ሁኔታ ነበር። ነገር ግን ከሶስት ዓመት ወዲህ ቡና ሙሉ በሙሉ ወደ ኮቴነር ተቀይሯል። ይህም በባቡር እንዲላክ እየተደረገ ነው። 98 በመቶ የሚሆነው ቡና ወደ ውጭ ገበያ ሲቀርብ የሚጓጓዘው በባቡር ነው። ስለዚህ ቅሸባ የሚባል ነገር ሙሉ በሙሉ ቀርቷል። አልፎ አልፎ ባቡሩ እንከን ሲገጥመው ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ጅቡቲ ድረስ ታጅቦ ይላካል። ስለዚህ ችግሩ ያለው ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ሳይሆን አዲስ አበባ እስኪደርስ ድረስ ነው። ይህንም በከፍተኛ ጥንቃቄ ክትትል እየተደረበት ነው።

አዲስ ዘመን፡- የቀጥታ ትስስር ግብይት ሲተገበር ምን አይነት አሰራር አለው? በግብይቱ ውስጥ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ጭምር የድለላ ስራ እንደሚሰሩ ቅሬታ ይነሳልና አሰራሩ በግልጽ ያስቀመጠው ምንድን ነው?

ዶክተር አዱኛ፡- አንድ ስራ ሲሰራ ያለ አሰራር ስርዓት አይከናወንም። አንድ የአሰራር ስርዓት ሲዘረጋ አዋጅ፤ ደንብና መመሪያ ይኖረዋል። ስለዚህ የአሰራር ስርዓት ሳይኖረው ወደ ስራ ሊገባ አይችልም። በ2013 ዓ.ም ወደ ቀጥታ ትስስር የተገባው ትስስሩን ማስተዳደር የሚቻልበት መመሪያ ቁጥር 02/2013 የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ነው። በዚህ መመሪያ እያንዳንዱ አሰራር በግልጽ ተዘርዝሯል።

አቅራቢው ከፈለገ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሸጥ ይችላል። ካልፈለገ ደግሞ በቀጥታ ትስስር መገበያየት ይችላል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ቡና ላኪው ጋር በዋጋ፤ በመጠንና በደረጃ መስማማት መቻል አለባቸው። ስለዚህ ተስማምተው ሲመጡ በውልና ማስረጃ ከጸደቀና ከተፈራረሙ በኋላ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያንን ፊርማ ወስዶ በማጽደቅ ተግባራዊነቱን ይከታተላል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቡና ደረጃን የሚያወጣ ከሆነ ላኪው በዕለቱ ክፍያ ፈጽሞ መረከብ እንዳለበት መመሪያው በግልጽ ያስቀምጣል። ላኪና አቅራቢው ደግሞ በስምምነት ስለሚሰሩ ብር ባልተቀበለት አቅራቢው ተቀብያለው ብሎ ሊሸኝ ስለሚችል መስሪያ ቤቱ ከቡና አቅራቢው ተረክቦ ለላኪው ሲሸኝ ግልጽ አድርጎ ይሸኛል። አንዳንድ አቅራቢ እኔ ምርቱ እንዲሸኝ ፈልጌ እንጂ ብር አልተቀበልኩም ብሎ ‹‹ስሊፕ›› ይዞ መጥቶ ቅሬታ ያቀርባል። እነዚህንና መሰል ችግሮች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተገቢው መንገድ በመለየት የማጥራት ስራ ይሰራል።

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ላይ ቅሬታ ካለ ነጻ የጥቆማ ሳጥን ስላለ ጥቆማ መስጠት ይቻላል። ከዛ ውጭ ደግሞ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ክፍል ስላለ ቀርበው ቅሬታና ጥቆማ መስጠት ይችላሉ። ችግር በሚፈጥሩ ሰራተኞች ላይ ክትትል በማድረግ ብልሹ አሰራር ውስጥ ገብተው ከተገኙ ርምጃ ይወስዳል።

አዲስ ዘመን፡- በርካታ ቡና አቅራቢዎች በተረካቢ ኩባንያዎች ማጭበርበር ሲደርስባቸው ይታያል። ለአብነትም ዲዳ ሆራ ቡርቃ ትሬዲንግ የብዙ ቡና አቅራቢዎችን ገንዘብ አልከፈለም፤ ባለስልጣኑ እነዚህንና መሰል የቡና ግብይት ችግሮችን በምን መልኩ እየፈታ ነው?

ዶክተር አዱኛ፡- ዲዳ ሆራ ትሬዲንግ ላይ ያለውን ችግር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚያየው ጉዳይ ነው። ዲዳ ሆራ ቡርቃ ትሬዲንግ የሚል መጠሪያ ያለው ቡና ላኪ በፌደራል ፖሊስ ክትትል እየተደረገበት ነው። የፌዴራል ፖሊስ ክትትል ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን ላኪው ወደ ሌላ ምርት ግዥ ውስጥ እንዳይገባና በእጁ ያሉ ሀብቶችን እዳይሸጥ እንደ ተቋም በእጁ ላይ ያለ እዳ ሳይከፍል ወደ ሌላ ስራ እንዳይገባ እንዲሁም በእጁ ላይ ያለውን ቡና ወደ ውጭ እንዳይልክ ክትትል እየተደረገበት ነው።

በላኪና በአቅራቢዎች መካከል ይህ አይነት ችግር ሲመጣ ሁለቱን ወገኖች በማገናኘት ችግሩን እንዲፈታ እናደርጋለን። በዚህ ሳቢያ ችግር ውስጥ ገብተናል የሚሉ አቅራቢና ላኪዎች ካሉ ስም ዝርዝራቸውን በመያዝ ሁሉንም ወገኖች በማገናኘት ችግሩ እንዲፈታ ይደረጋል።

አዲስ ዘመን፡- ከግብይት ጋር በተያያዘ በተለይም ቡና ላኪዎች ለአቅራቢዎች ብር መመለስ ባለመቻላቸው የአቅራቢዎች ሀብትና ንብረት በባንክ ታግዶ እስከ መሸጥ እየደረሰ ነው፤ ይህ የቡና ልማትንና ግብይት የሚጎዳ ስለሆነ ችግሩን ለመቅረፍ ምን ታስቧል?

ዶክተር አዱኛ፡- እንደ አሰራር ቡና አቅራቢው ለላኪው ባስረከበበት ወቅት ገንዘባቸውን መረከብ አለባቸው የሚል ነው። ነገር ግን በመካከላቸው ተስማምተው በሚያደርጉት የሁለትዮሽ ስምምነት እያደረ ችግር እየፈጠረ ነው። ስለዘህ አቅራቢዎች አንድ ዓመት ከሞላው በኋላ በመምጣት እከሌ የሚባል ቡና ላኪ ምርት አቅርቤ ብር አልከፈለኝም ብለው ቅሬታ ያቀርባሉ። የቡና ግብይት መመሪያው የሚለው ቡና በተረካከቡ በሶስተኛው ቀን ቅሬታቸው ለባለስልጣኑ ማቅረብ ይችላሉ። ባሰስልጣኑ ቅሬታውን እንዳገኘ ላኪውንና አቅራቢውን በመጥራት ተወያይተው ገንዘቡ እንዲከፈል የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ካልሆነ ላኪው ወደ ሌላ አይነት ግብይት እንዳይሸጋገር የያዘው ምርት በአስቸኳይ ተሽጦ እንዲከፍል የማድረግ ስልጣን አለው።

በሌላ በኩል ደግሞ ላኪው ቡና ከአርሶ አደር ገዝቶ ለአቅራቢው አዘግይቶ እንዳይከፍል ‹‹አድቫንስ ፔይመንት›› ይሰጣል። አቅራቢ ይህን ክፍያ ከወሰደና በብሩ ከገዛ በኋላ ለሌላ ሰው ቢሸጥ ተጠያቂ ይደረጋል። የቀጥታ ትስስር ጽንሰ ሀሳብ ለአንድ ዓመትና ሁለት ዓመት ስምምነት ያለው አቅራቢና ላኪ ቤተሰባዊ ትስስር እንዲፈጥር ነው። ነገር ግን አቅራቢው ገንዘቡን ከወሰደ በኋላ ላኪው ከባንክ የተበደረው ስለሆነ ወለድ ይቆጥርበታል። በብሩ ገዝቶ ለላኪው ማቅረብ ሲገባው ለሌላ ሰው የሚሸጥበት ሁኔታ አለ። ስለሆነም ሁለቱንም ከማስታረቅ አንጻር በዚህ ዓመት ጥሩ ስራ ተሰርቷል። ይህ ዓይነት ችግር ከባለፈው ዓመት የመጣ ችግር እንጂ በዚህ ዓመት የመጣ አይደለም።

አዲስ ዘመን፡– በምርት ገበያ ባለው ግብይት ብር በወቅቱ ይከፈለን ነበር፤ በቡና እና ሻይ የቀጥታ ትስስር ግብይት ግን ላኪዎች በቶሎ ብር አይከፍሉምና የግብይት ስርዓቱ አደጋ ደቅኖብናል የሚሉ ቅሬታዎች አሉ። የእርሶ ምላሽ ምንድ ነው?

ዶክተር አዱኛ፡- የቀጥታ ትስስር ግብይትና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አማራጭ ገበያዎች ናቸው። ነጋዴው በሚያዋጣው መንገድ ምርቱን መሸጥ ይችላል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አልተዘጋም የቀጥታ ትስስር ግብይት አስገዳጅ ሳይሆን አማራጭ የገበያ ስርዓት ነው። ስለዚህ በምርት ገበያ በኩል ግብይት አከናውናለሁ የሚል አቅራቢ መሄድ ይችላል፤ ቀጥታ ትስስርም እንዲሁ ነው። ሁለቱም አቅራቢና ላኪን የሚያገናኙ መዋቅሮች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የቀጥታ ትስስር ግብይት ላይ የመጋዘን ኪራይ፤ የደላላ፤ የጫኝና አውራጅ ክፍያ የለበትም። አምስት ፐርሰንት ጭማሪ አለው። በሁለተኛ ደረጃ እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ወጭ ይቆጥባል። ስለዚህ አማራጩ የራሱ ስለሆነ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስገዳጅ ወይም ባለስልጣኑ አስገዳጅ ነው የሚል ነገር የለውም።

አዲስ ዘመን፡- የግብይት ስርዓቱ አማራጭ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ግብይት ዋጋ ባለስልጣኑ ስለሚያወጣ ዋጋው በራሱ ልዩነት ስላለው አማራጭ የሚለውን የግብይት ስርዓት ዝግ አያደርገውም?

ዶክተር አዱኛ፡- የቀጥታ ትስስር በምርት ገበያ ላይ አምስት በመቶ ጭማሪ ከፍለው እንዲገዙ የተቋሙ አዋጅ ይፈቅዳል። ለምሳሌ ምርት ገበያ ላይ ቡና በፈረሱላ አራት ሺ ብር ከሆነ የቀጥታ ትስስር እስከ አራት ሺ 200 ድረስ መገበያየትን ዕድል ይሰጣል። ስለዚህ አመላካች (reference license) ስለሚያስፈልግ ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ታይቶ ተመሳክሮ ወደ ሀገር ይመጣል። በየሳምንቱ የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ሊሙ ደረጃ ሁለት ይህ ነው ተብሎ ሲቀርብ እንደ ዋና የዋጋ ማመልከቻ ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ይሰጣል። በምርት ገበያ አራት ሺ ብር ከተባለ የቀጥታ ትስስር አዋጁ ሲደመር አምስት ፐርሰንት ስለሰጠው ተጠቃሚ ነው።

የቀጥታ ትስስር ምርት ገበያ ላይ የማመላከቻ ዋጋ (reference price) ስለሚያስፈልግ ከዓለም አቀፍ የቡና ገበያ ላይ ያለውን ዋጋ በመውሰድና በማመሳከር በየሳምንቱ ለምርት ገበያ ዋጋ ይቆረጣል። ስለዚህ በምርት ገበያና በቀጥታ ትስስር የሚገበያዩበት ብቻ ሳይሆን አሜሪካ፤ አውሮፓና ሌሎች ሀገራት ላይ ያሉ ገዥዎች ጭምር ከላኪ ጋር ድርድር ውስጥ ይገባሉ። አንድ ሰው ሶስት አራት መቶ ኬሻ ቡና ይሸጣል፤ በዚህ ሁለት መቶ ብር ልዩነት ካለው በአንድ መኪና ምን አይት የዋጋ ልዩነት እንዳለው መገመት አያዳግትም።

አዲስ ዘመን፡– ባለስልጣኑ በተለያዩ የቡና አምራች አካባቢዎች የሚከፍታቸው የቡና ቅምሻና ሰርተፊኬሽን ማዕከላት የጅማ ማዕከልን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ለስራ ምቹ እንዳልሆኑ ቅሬታ ይነሳል። በሌላ በኩል ደግሞ የኢትጵያ ምርት ገበያ ሰፋፊ መጋዘኖችና የቅምሻ ማዕከላት በቀጥታ ትስስሩ ምክንያት ስራ አቁመዋልና በአንድ ሀገር ላይ ሁለት ወጭ ማውጣቱ የሀብት ብክነት አይሆንም?

ዶክተር አዱኛ፡- በደቡብ ምዕራብ በኩል የሚመጡት ቡና ላኪዎች ጅማ ላይ በሌላ በኩልም ሀዋሳ ላይ ማዕከል ተከፍቶ አገልግሎት እየሰጡ ነው። መጀመሪያ ሲከፈት በዋናነት የታሰበው የቀጥታ ትስስር ግብይት ቡና ለመቅመስ ብቻ ሳይሆን ለመሸኘት ጭምር ነው። ቀጥታ ከጅማ ወይም ከሀዋሳ ወደ ጅቡቲ መላክ ያስችላል። ስለዚህ ማዕከላቱ የተቋቋሙት ይህን ከማሳለጥ አኳያ ነው። ጅማ ላይ ከበደሌ፤ መቱ፤ ጅማ፤ ቦንጋ፤ ቴፒ፤ ሚዛንና መሰል አካባዎች ይመጣል። ይህ ሁሉ ሲመጣ በርካታ ምርት ስለሆነ የቦታ መጨናነቅ ይከሰታል። አሁን ላይ ጅማ ላይ ጫና የሚፈጥር ስለሆነ በደሌ፤ መቱና ቦንጋ የቅምሻና ሰርተፊኬሽን ማዕከል ተቋቁሟል። ስለዚህ ጅማ ላይ መጨናነቅ የለም። በሌላ በኩልም ማዕከሉ ያለበት ቦታ ምቹ አልነበረም።

የሀገር ሀብትን በአግባቡ ከመጠቀም አንጻር ስምምነት ላይ ተደርሷል። ቡና አቅራቢ ሳይጉላላ ወደ ሚቀርበው ሰርተፊኬሽን ማዕከል በመሸኘት ከበደሌ ወደ ጅቡቲ እንዲላክ በማድረግ ወደ አዲስ አበባ የማይመጣበትን መንገድ እንዲመቻች ተደርጓል። በምርት ገበያ ያሉ የቅምሻ ግብዓቶች ለመጠቀም ግብርና ሚኒስቴር እና ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ ሆነው ከምርት ገበያ ጋር በጋራ በመሆን በትብር ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ 252 ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቧል። ከዚህ ቡና ተረፈ ምርት ተብሎ ለሀገር ውስጥ ገበያ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ይቀርባልና ምን ያህል ቡና ለምርት ገበያ ቀረበ?

ዶክተር አዱኛ፡- ደረቅ ቡናም ሆነ የታጠበ ቡና ወደ መጋዘን ሲገባ ስንት ፐርሰንት ወደ ውጭ ይላካል፤ ስንት ፐርሰንት ደግሞ ሀገር ውስጥ ይቀራል የሚል አሰራር ‹ካልኩሌሽን› አለ። በዚያ መሰረት አንድ ላኪ አስር ቶን ቡና ወደ መጋዘኑ ካስገባ ከዛ ውስጥ ቢያንስ ከ10 እስከ 20 በመቶ ይወገዳል። ይወገዳል ማለት ግን የተበላሸ ቡና ነው ማለት ሳይሆን ደረጃ አንድ፤ ሁለት፤ ሶስት እያለ የሚወጣ ነው። ደረጃ አንድ ተብሎ ኮንትራት ከተፈራረመ በኋላ ደረጃ ሁለት መላክ አይችልም።

ላኪው ወደ ውጪ ከሚልከው ተረፈ ምርት ወደ ምርት ገበያ ማስገባት አለበት። አሁን ላይ የመጣው የሱዳን ገበያ ዩጂ የሚባል ግብይት አለ። የሚወገደው ቡና ማለትም ተረፈ ምርት ቡና ድጋሚ ከሁለት ጊዜ በላይ ይበጠርና የተሻለ ቡና ይወጣለታል። ስለዚህ የተሻለው ቡና ዩጂ ይባላል። ይህም ወደ ሱዳን ስለሚሸጥ ለሀገር ውስጥ ለምርት ገበያ የሚቀርበው መጠን ይቀንሳል።

ወደ ምርት ገበያ ሲመጣ የሚወገደው ላይ ሲጣራ መጠኑ ይቀንሳል። ይህም ወደ ምርት ገበያ የሚሄደው ተረፈ ምርት የሚቀንሰው ወደ ሱዳን ስለሚሸጥ ነው። ከዚያ የተረፈው ግን ማንኛውም ቡና ላኪ ነጋዴ ወደ ምርት ገበያ ማስገባት አለበት። ይህ ካልሆነ ግን የትም ሄዶ የሚሸጥበት አግባብ የለም። ከዛ በኋላ የሚቀረው ጥቁር ቡና ነው። ይህ ቡና በአዋጁ እንደተቀመጠው መቃጠል አለበት ይላል። ስለዚህ የኤክስፖርት መጋዘን ውስጥ ያለ ወይም የተወገደ ነው ወይም ደግሞ ጥቁር ቡና ነው። ስለዚህ ጥቁር ቡናው ወደ ምርት ገበያ የሚላክ ሳይሆን በጤና ላይ እክል ስለሚያመጣ የሚቃጠል ነው። ይህ በአዋጁ በግልጽ ተቀምጧል። በመሆኑም ምርት ገበያ ገብቶ የማይሸጥ ከሆነ በየመጋዘኖቹ ወርዶ ማየትን ይጠይቃል። በዚህ ዙሪያ ከምርት ገበያ ጋር በጋራ እየሰራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- በሚቃጠል ተረፈ ምርት ሰበብ ላኪዎች ወደ ምርት ገበያ ማስገባት ሲገባቸው በሕገ ወጥ መንገድ ወደ መርካቶ ገበያ የሚወስዱበት ዕድል አይፈጥርም?

ዶክተር አዱኛ፡- ማንኛውም ቡና ሲሸኝ በባለስልጣኑ እውቅና ነው። ስለሆነም ከአንድ መጋዘን ሲወጣ ተሸኝቶ ነው። ላኪው ሳይሸኝ ይዞ ከወጣ እንደ ኮንትሮባንድ ይያዛል። ሳይሸኝ ከመጋዘን ወጥቶ አይንቀሳቀስም። የሚወገደው ተረፈ ምርትም ቢሆን ወደ ምርት ገበያ ሲላክ በሽኝት ነው። ስለዚህ ያለመሸኛ የቡና ምርት አይንቀሳቀስም።

አዲስ ዘመን:- በቡና ግብይት ውስጥ እንደ ሀገር ያለን አቅምን መሰረት በማድረግ እሴት ጨምሮ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ባለስልጣኑ ምን እየሰራ ነው? ከዚህ በፊት ያለው ልምድ ምን ይመስላል?

ዶክተር አዱኛ:- በዋናነት እሴት ጨምረንበት ተቆልቶና ተፈጭቶ ወደ ውጭ ለመላክ የአሰራር ስርዓት ያስፈልጋል። ስለዚህ መመሪያና ምቹ የአሰራር ስርዓት መፍጠር አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ደንብና መመሪያ ከማዘጋጀት አኳያ ስራው አልቆ ወደ ስራ ተገብቷል። በዚህም ቡና የሚልኩ አካላት ቁጥር እየጨመረ ነው። በተጨማሪም በሀገር ውስጥም እሴት የተጨመረበት ቡና በውጭ ምንዛሬ መሸጥ የሚችልበት ዕድል ተፈጥሯል። ሆኖም ግን በዋናነት እንደማነቆ ሆኖ እያስቸገረ ያለው ዓለም ዓቀፍ ገበያ ውስጥ የተቆላና የተፈጨ ቡና ከትላልቅ ቡና አምራች ሀገራት ጋር ለመወዳደር ችግሮች አሉ። ትላልቅ ቡና ገዥዎች ቡና የሚፈልጉት በጥሬው ነው።

ስለዚህ ጥሬ ቡና በመግዛት ከሌላ ቡና ጋር በመቀላቀል የሚቆሉበትና የሚፈጩበት ሁኔታ አለ። እሱን መከልከል የሚቻለው የራሳችን መለያ ‹ብራንድ› ሲኖር ነው።

ስለዚህ የራስ የሆነ ብራንድ በመፍጠር እና በመጠቀም በተለያዩ ሀገራት የሚሸጠው ቡና የኢትዮጵያ ቡና ሆኖ እንዲቀጥል ከሌላ ሀገር ጋር እዳይቀላቀል የማድረግ ስራ መሰራትን ይጠይቃል። ቻይና በአሁኑ ወቅት እስከ 25 ሺ ቶን ቡና ከኢትዮጵያ ቡና የምትገዛ ሀገር ናት። ነገር ግን የኢትዮጵያ ቡና ‹ብራንድ› እንዲሆን ከቻይና ጋር የጋራ የሆነ ስምምነት በመፍጠር ማላመድ አስፈላጊ ነው። ካለን የቡና ምርት አቅም አንጻር ገና ይቀረናል። ነገር ግን ጅምር ስራዎች ስላሉ መመሪያ ማዘጋጀትና ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር እና የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲሻሻል ማድረግ ላይ እየተሰራበት ነው።

አዲስ ዘመን፡– የቡና፤ የሻይና ቅመማቅመም ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ከባለስልጣኑ ጀምሮ ዘርፉ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ከማሳደግ አኳያ ምን እየተሰራ ነው?

ዶክተር አዱኛ፡- እንደ ተቋም የራሱ የሆነ እቅድ አለው። ስለሆነም ከሌሎች ተቋማት ይለያል ብለን የምናስበው የክልል፤ የፌደራል ዕቅድ የሚባል ነገር የለም። ሁሉም አንድ ላይ በመሆን ከክልሎች ጋር በጋራ ይታቀዳል። ይህንም እስከታችኛው መዋቅር ድረስ እየተሰራበት ነው። በየአምስት ዓመቱ መከናወን ያለባቸው ጉዳዮች ላይ በግልጽ በማመላከት ከክልሎች ጋር የጋራ ተደርጎ እየተሰራ ነው። በየዓመቱ የሚታቀደው እቅድ ከ15 ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ የሚቀዳ ነው። ቡናን የሚያቀርቡ የአምራች ማህበር፤ ዩኔኖች እና መሰል አደረጃጀቶች አሉ። ስለዚህ በስልጠና እና መሰል ጉዳዮች ላይ የመደገፍ ስራ ይሰራል። በተለይ በግብይ ስርዓቱ ላይ ያሉትን አንዳንድ ክፍተቶች በጋራ በመስራት እየታረሙ ነው። ሀገራዊ ለውጡ በተቋሙ ብቻ ሳይሆን ከአርሶ አደሩ ጀምሮ እስከ ላኪው ድረስ የሚሳተፍ ባለድርሻ አካላት ተፈጥሯል።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር በሻይና ቅመማቅመም ትልቅ አቅም እንዳለ ይነገራልና አቅሙን በተገቢው ሁኔታ ከመጠቀም ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ዶክተር አዱኛ፡- እውነት ለመናገር ቡና ላይ በተሰራው ልክ በሻይና በቅመማቅመም ላይ ብዙም አልተሰራም። ሆኖም ግን ቡና ላይ የተገኘውን ስኬት በሻይና ቅማቅመም ላይ መድገም ያስፈልጋል። የቅመማቅመም ግብይትና ጥራት ቁጥጥር መመሪያ ተዘጋጅቶና ጸድቆ ወደ ስራ ገብቷል። በዚህ መሰረት ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ የተላከው ከባለፈው ዓመት የበለጠ ነው። በቅመማቅመም እንደ ሀገር ካለው አቅም አንጻር ወደ ውጭ የተላከው ከ50 በመቶ አይበልጥም። አሁን ላይ ወደ ውጭ የሚላኩት የቅመም አይነቶች 21 አይነቶች ናቸው። 16 ለሚሆኑት የጥራት ደረጃቸው ምን መሆን አለበት፤ እንዴት ነው የሚመረቱት የሚሉና መሰል ጉዳዮች ላይ ሙሉ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ በመገባቱ ከባለፈው ዓመት የተሻለ እንዲሆን አድርጓል።

ቅመማቅመም የሚመረተው እንደ ሀገር አርሶ አደር ማሳ ላይ ቁጥ ቁጥ በሆነ መንገድ ነው። ነገር ግን በኢንቨስትመንት ደረጃ መመረት አለበት። ለዚህም ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ብዙዎቹን የማሰልጠን ስራ ተሰርቷል። የቅመማ ቅመም ማህበር የገበያ ትስስር በመፍጠር ግብይቱን ማሳደግ የሚችልበትን ሁኔታ ኔዘርላንድ ከሚገኝ ግብረ ሰናይ ድርጅት ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። ሰፊ አቅም አለ። አዳዲስ እንደ ሮዝመሪ ያሉ ቅመማቅመሞች ወደ ግብይት የገቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ስለዚህ ዘርፉን ለማሳደግ ብዙ ስራዎች መስራት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ትብብር የሚሻ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

ዶክተር አዱኛ፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።

በሞገስ ተስፋ

Recommended For You