የገበያ ትስስር የሚፈልጉት የሌማት ትሩፋቱ ትሩፋቶች

በሌማት ትሩፋት አማካይነት የቤተሰብ የምግብ ሥርዓትን ለማሟላት የተጀመረው መርሐ ግብር የቤተሰብን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የማኅበረሰቡን ፍላጎት ወደ መመለስ እየተሸጋገረ ይገኛል። የመገናኛ ብዙኃን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ መርሐ ግብሩ በተጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቤተሰብ ደረጃ ወደ ልማቱ የገቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንቁላል፣ ወተትና የወተት ተዋፅዖዎች፣ አትክልት፣ ዶሮ ባለው ውስን ቦታ ላይ እያለሙ የቤተሰባቸውን የተመጣጠነ ምግብ ፍላጎት መመለስ እየቻሉ ከመሆኑ በተጨማሪ ምርቶቹን ለገበያ ማቅረብ ጀምረዋል። ተደራጅተው እያለሙ የሚገኙትም እንዲሁ ውጤታማ መሆናቸው እየተገለጸ ነው።

የሌማት ትሩፋቱን ትሩፋቶች ማጣጣም እየተቻለ ነው። የእንቁላል ምርታማነት ከፍተኛ እየሆነ ስለመምጣቱ ገበያውም ያመለክታል። በአንድ ወቅት ዋጋው ሰማይ ወጥቶ የነበረው እንቁላል መርሐ ግብሩ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ፤ በስፋት ከመገኘቱ በተጨማሪ የአንድ አንቁላል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን አይተናል፤ የአንድ እንቁላል ዋጋ ከአስራ አራት ብር ወደ ሰባትና ስምንት ከወረደበት ሁኔታም መረዳት የሚቻለው ይህንኑ ነው።

የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ አንዱ መሣሪያ ምርታማነትን መጨመር ስለመሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ። ይህ ሲደረግ ዋጋን ባለበት ማቆም መቻል ነው በአብዛኛው የሚታየው። በእንቁላል ላይ የታየው ግን ዋጋ ባለበት አይደለም እንዲቆም ያደረገው፤ ወደ ቀድሞ ዋጋው ነው የተመለሰው። ይህ የልማቱ ትልቅ ስኬት ነው። ይህን ስኬት ጠብቆ ማስቀጠል ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ለምርቱ ተጨማሪ ገበያዎችን ማፈላለግ የግድ ይላል። አለበለዚያ ምርታማነቱ በምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል።

በአንድ ወቅት በቆሎ በስፋት ይመረት እንደነበር አስታውሳለሁ። ምርቱን የሚገዛው እያጣ አርሶ አደሩም ይቸገር እንደነበር በእዚያው ወቅት የወጡ መረጃዎች ይጠቁሙም ነበር። በግዜው ችግሩን የተገነዘበው መንግሥት ሁለት ሥራዎችን ሠርቷል። አሁን ግን ለያዝነው ጉዳይ የሚጠቅሙትን አማራጮች እጠቅሳለሁ። በዚያን ወቅት ምን ያህል ለውጥ እንዳመጣ ባላውቅም የኅብረተሰቡን የአመጋገብ ባሕል መቀየር ላይ ለመሥራት ተሞክሯል። ከበቆሎ የተለያዩ የምግብ አይነቶች ሊሠሩ እንደሚችሉ በመገናኛ ብዙኃን/ በቴሌቪዥን/ ጭምር አዘጋጃጀቱን የተመለከተ መረጃ ይተላለፍ ነበር። ምርቱን አከማችቶ በመያዝ እንደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም ላሉት ተቋማት ይሸጥም ነበር።

እንቁላልን ስለመመገብ ፋይዳ ኅብረተሰቡን በማስተማር በተመጣጠነ ምግብ፣ አልሚውን በዋጋ መጥቀም ይቻላል። የሌማት ትሩፋት አንዱ ዋና ዓላማም ይሄው ነው። የእንቁላል ምርቱ ተሰባስቦ ሰፊ ገበያ ወደአለበት አካባቢ እንዲቀርብ ማድረግ፣ አንደ ኬክ ቤቶች ካሉት ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር ያስፈልጋል። እንቁላሉ ለገበያ እስከሚውል ድረስ ለብልሽት እንዳይዳረግ የሚያስችሉ እንደ ፍሪጅ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠርም ሌላው የልማቱ ቀጣይነት ማረጋገጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ጉዳይ ነው።

እነዚህን ተግባራት ሊሠሩ እንደሚገባቸው ባልታሰበበት ሁኔታ ምርቶቹን ለቤተሰብ አገልግሎት በማዋልና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ብቻ በማቅረብ ልማቱን ብዙ ርቀት ማድረስና አልሚዎቹንም ማኅበረሰቡንም ሀገርንም ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ አይቻልም።

በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የተሰማሩ አካላት የሥጋ ዶሮ ልማቱንም እንደሚያካሂዱ ከመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ተረድቻለሁ። እርባታው ግን አሁንም በዓላትን ታሳቢ ያደረገ ነው። የሥጋ ዶሮ በብዛት የሚፈለገው በበዓል ወቅት እንደመሆኑ አልሚዎቹ የያዙት አቅጣጫ የተሳሳተ አይደለም። በቀጣይ ምርታማነቱ እየሰፋ እንዲሄድ ለማድረግ ግን ተጨማሪ ገበያ መፈለግ ያስፈልጋል።

አንዱ ገበያ ሊሆን የሚችለው የኅብረተሰቡን የዶሮ አመጋገብ ባሕል መቀየር ላይ መሥራት ይሆናል። ዶሮ ከተለመደው መንገድ ውጪ ለምግብነት እንዲውል ማድረግ ላይ መሠራትም ይኖርበታል። ይህን ሥራ እነሱ ባይሠሩትም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት መሥራት ይኖርባቸዋል። የተመጣጠነ ምግብ ለመመገብም ሆነ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዶሮ በስፋት ሊበላ የሚችልበትን መንገድ መፈለግ ይገባል።

ዶሮ በአዘቦት ቀን ለምግብነት እንዲውል ማድረግ ላይ ቢሠራ የዶሮ ፍላጎት እንዲጨምር ማድረግ ይቻላል። ይህ ደግሞ በቅድሚያ የአመጋገብ ባሕል ለውጥ ማድረግ ላይ በስፋት መሥራትን ይጠይቃል። የአመጋገብ ባሕል መቀየር ላይ በተለይ ከዶሮ አኳያ በትኩረት መሠራት እንደሚኖርበት የሚጠቁሙ አልሚዎችም እየታዩ ናቸው። የሚመለከታቸው የሥነ ምግብ ባለሙያዎችም ይሁኑ ሌሎች ይህን ማድረግ ባለባቸው ወቅት ላይ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል።

ዶሮ ከዓመት በዓልና የተለዩ ዝግጅቶችም ባሻገር ለምግብነት ሊውል በሚችልበት መንገድ ላይ ቢሠራ በላተኛውም ዶሮ አርቢውም ተጠቃሚ መሆን ይቻላሉ። አመጋገባችን የምግብ ሥርዓቱን የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የበኩሉን አስተዋፅዖ ሊያበረክት ይችላል።

እኛ ዶሮ የምንመገብበት መንገድ ብዙ ወጪን ይጠይቃል፤ ብዙ ሽንኩርት፣ ዘይት፣ ቅቤ ፣ ቅመማ ቅመም፣ ወዘተ ያስፈልጋል፤ ዓመት በዓልን ታሳቢ ያደረገ ስለሆነም ፓኬጁ ብዙ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ በአዘቦት ቀን ቀለል ባለ መልኩ ዶሮ ሊበላ በሚችልበት መንገድ ላይ መሥራት ያስፈልጋል።

በሌሎች ሀገሮች ዶሮ ወጥ አይታወቅም፤ ዶሮ ግን በስፋት ይበላል። በሀገራችንም ዶሮ በአሮስቶና በመሳሰሉት መንገዶች ለምግብነት እንደሚውል ይታወቃል። ዶሮ በስፋት ሊበላ የሚችልበትን መንገድ በመቀየስ፣ በማስተዋወቅና አሠራሩንም በማሳየት የልማቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ አስተዋፅዖ ማድረግ ይቻላል።

በወተት ምርት በኩልም ጥሩ ጥሩ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆናቸው የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ይጠቁማሉ፤ የመስክ ምልክታዎችም እያረጋገጡ ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎችና ክልሎች ተመረተ የሚባለው የወተት መጠን ሲታሰብ ፣ ዓመታዊ የግለሰብ የወተት ፍጆታ በጣም ዝቅተኛ ለሆነባት ኢትዮጵያ ታላቅ የምሥራች እየመጣ ነው ማለት ይቻላል። ምንም እንኳ በዋና ዋና ከተሞች በወተት ዋጋ ላይ ቅናሽ ባይታይም፣ የምርት መጠኑ በቀጣዮቹ ዓመታት ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስ አንደሚችል መገመት የሚያስችሉ ሁኔታዎች አሉ።

በወተት ሀብት ልማት የተሠማሩ ወገኖች የተሻሻሉ የወተት ላሞች ዝርያዎችን በመጠቀም ወተት በብዛት እያመረቱ ይገኛሉ። አንዳንዶች የቤተሰብ ፍጆታቸውን ሞልተው ለገበያ እያቀረቡ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ በድርጅት ደረጃ የወተት ልማት ውስጥ ገብተዋል።

ምርታቸውንም በየአካባቢያቸው ለሚገኝ ማኅበረሰብ ከማቅረብ በተጨማሪ በራሳቸው የወተት ተዋፅዖዎችን በማዘጋጀት ለገበያ የሚያቀርቡበት ሁኔታ ይታያል። እነዚህም አልሚዎች ከሚያገኙት ወተት በተጨማሪ በእርባታውም በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። እንደ ከብት እርባታው ሁሉ የወተት ልማቱ ትሩፋትም ብዙ ነው፤ ወተትና የወተት ተዋፅዖዎችን ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ጥጆች ይሸጣሉ፤ ጊደሮቹ ደግሞ ቀጣዮቹ የወተት ላሞቻቸው ናቸው።

ይህ ልማት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በእጅጉ ሊሰፋ እንደሚችል አልሚዎቹ ጠቁመው፣ ምርታቸውን የሚያቀርቡበት ሰፊ ገበያ ከወዲሁ እንዲፈለግላቸውም እየጠየቁ ይገኛሉ። ከቤተሰብና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ያለፈ የወተት ምርት እየታየ መሆኑ ይገለጻል። ይህ ምርት ቅቤም አይብም ሊወጣለት ስለሚችል ለብልሽት የመዳረግ ዕድል ባይኖረውም የወተት ምርቱን ቶሎ ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር በወተት ልማቱ የጨቅላ እድሜያቸው የወተት ተዋፅዖዎች ማምረቻዎችን ከማሰብ ያወጣቸዋል።

አልሚዎቹ የሚጠቀሙት በወተቱ ወይስ በቅቤና አይቡ ነው የሚለው እየታየ ልማቱን አጠናክረው መቀጠል የሚያስችላቸው ገበያ ቢመቻችላቸው ወይም እነሱ ተደራጅተው በቴክኖሎጂ ተጠቅመው ምርታቸውን ራቅ ወደ አሉ ገበያዎች የሚያደርሱበት ሁኔታ ቢፈጠር ልማቱ የገበያ ጉዳይ ሳያሳስበው መቀጠል ይችላል፤ ባሉባቸው አካባቢዎች የአግሮ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች ቢቋቋሙላቸው የልማት ትሩፋቱን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ ይቻላል።

በሁሉም የሌማት ቱሩፋቱ ሥራዎች ጥሩ አፈጻጸም እየታየ ነው። ዜጎች በጠባብ ቦታ ላይ ለቤተሰብም ለገበያም የሚፈለጉ ምርቶችን ማምረት እየቻሉ ናቸው። ሥራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እየሆነም ይገኛል። አሁንም ይበልጥ እንዲሰፋ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል። ይሄ ጥያቄ ውስጥ አይገባም።

ልማቱን ሊያሰፉ የሚችሉ የተለያዩ መንገዶች እንዳሉ ይታወቃል፤ ከእነዚህ መካከልም ጥሩ ገበያ፣ የአመጋገብ ባሕል መቀየር፣ የአግሮ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ ምርቶች ሳይበላሹ እንዲቆዩ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም ላይ ቢሠራ ልማቱ ብዙ ርቀት ማድረስ ይቻላል።

እስመለአለም

አዲስ ዘመን ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You