በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዓመት በርካታ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን ከነዚህም መካከል በእድሜ እርከን የሚካሄዱ የአዋቂዎች፣ የማሰልጠኛ ማዕከላት፣ የፕሮጀክቶች እና የወጣት ውድድሮች ይጠቀሳሉ። እነዚህ ውድድሮች ላይ በየጊዜው የሚነሳና መነጋገሪያ የሆነው የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ ነው። ይህም ለስፖርቱ አዳጋች እየሆነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕክምና ክፍል ባለሙያ ዶክተር አያሌው ጥላሁን በዚህ አሳሳቢ የስፖርቱ ፈተና ዙሪያ እንደሚናገሩት፣ የእድሜ እርከን ውድድሮች (U-20 እና U-18) ለአትሌቲክስ እድገትና በቀጣይነት ተተኪዎችን ለማፍራት መሰረታዊ ነው። እዚህ ላይ የሚሰራው ስራ በተገቢው መልኩ ካልተመራ እና ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት የማይቻል ከሆነ በአትሌቲክስ ስፖርት የሚደርስ ስብራትና ጉዳት ከባድ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተተኪዎች ላይ የሚሰራው ስራ ዝቅተኛ እንደሆነና ተተኪዎች እየጠፉ እንደሆነና ያሉትን አትሌቶች ብቻ እንደ ነገሩ እየተወዳደሩ ይገኛሉ።
የፌዴሬሽኑን የሕክምና ክፍል 2013 ላይ ተቀላቅለው እየሰሩ የሚገኙት ዶክተር አያሌው እንደሚያስረዱት፣ የ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች በየ ዓመቱ ይካሂዳሉ። በስራው ላይ በቆዩባቸው ሶስቱንም ዓመታት በእድሜ ማጣራት ላይ ስራዎችን የሰሩ ሲሆን እድሜን ለመለየት ሁሉም ማዕከላት፣ ክለቦችና ፕሮጀክቶች አትሌቶችን የውድድር ቦታ ድረስ ይዞ በመምጣት ማጣራት ተደርጎ ተገቢ አትሌት እንዲወዳደር ይደረግ ነበረ።
ከመጀመሪያው ዓመት ማለትም ከ2013 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም በተደረገው ማጣራት 90 ከመቶ የሚሆኑ አትሌቶች ከእድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ ጉዳይ ከውድድር ውጪ ሆነዋል። ይህ በጉልህ የሚታይና ችግሩ ሲከሰት ተረድቶ የሚያምን ክለብ አለመኖሩንም ዶክተር አያሌው ያስረዳሉ። በፌዴሬሽኑም በኩሉ ውድድሮችን ከእድሜ ተገቢነት ጋር ተያይዞ እንዲሰረዙም ለማድረግ ቆራጥነት አይታይም። በተጨማሪም ለችግሩ መከሰት ምክንያት የሆኑትን ውድድሮች በተገቢው መልኩ የማይገመገም በመሆኑ ችግሮቹ ሲጠራቀሙ እና በዚህም ምክንያት ክስና አላስፈላጊ ስድቦች ሲበዙ ክለቦችና የሚመለከታቸው አካላት እድሜን አስመርምረው እንዲመጡ ቅጽ ይለክላቸው ጀመረ።
በ2016 ዓ.ም እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ እድሜን በሕጋዊና ተገቢ የሕክምና ማዕከል አስመርምረው እንዲመጡ ጠንካራ ማሳሰቢያ የተሰጠ ቢሆንም የተደረገው ነገር እጅግ አሳፋሪ እና ከዚህ ቀደምም የባሰ ነው ይላሉ ዶክተር አያሌው። በተለይ የሜዳ ተግባራት አትሌቶች በሙሉ በሚባል ደረጃ ከ20 ዓመት በታች አትሌትን ለማግኘት እንደሚከብድና ሌሎችም ላይ የታየው ይሄው እንደሆን ያብራራሉ። ከአሰልጣኞች ጋር የቴክኒክ ስብሰባ ሲደረግ ስለ ጉዳዩ ሲወራ የሚክድ አሰልጣኝ ባይኖርም ተግባራዊ ማድረግ ላይ እጅ ያጥራቸዋል። ኢትዮጵያ ብዙ እውቀት ያላቸው የአትሌቲክስ አሰልጣኞች ቢኖሯትም አብዛኞቹ በእድሜና ሌሎች ችግሮች ላይ ከመስራት ይልቅ ለችግሩ መባባስ ሚና አላቸው።
ዶክተር አያሌው አክለውም፣ በኢትዮጵያ 37 የአትሌቲክስ ክለቦች የሚገኙ ሲሆን አንዳቸውም የወጣቶች ፕሮጀክት ባይኖራቸውም በወጣቶች ውድድር ላይ ይሳተፋሉ። እነሱ ጋር የሚታየው ችግር አሁን ወደ አካዳሚው እና ጥሩነሽ ማሰልጠኛ በመሄዱ አራቱም ማዕከላት ክለቦችን እንደሚያወዳድሩም ይናገራሉ። አሰላ ላይ በተካሂደው የማዕከላት ውድድር ላይ የታየው ችግር ሃዋሳም እንደተደገመና ውጪ የሚሮጡ አትሌቶች በማዕከላት እና ከ 20 ዓመት በታች ውድድር መምጣት ጀምረዋል።
በዓለም አቀፉ ተቋም ፌዴሬሽኑ በእድሜ ጉዳይ ተወጥሮ እንደተያዘና ከዚህ ቀደም 14 አትሌቶች ከእድሜ ተገቢነት ጋር በተገናኘ እንደተያዘባቸው ለማሳየነት ይጠቅሳሉ። ሃዋሳ በተካሄደው የ20 ዓመት በታች ውድድርም ችግሩ ጎልቶ በመታየቱ ቀጣይ ቀጣይ የፔሩ ሊማው የወጣቶች ውድድር ተሳትፎም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ከመድረኩ ለዚህ ተብሎ የሚመረጥ ወጣት አትሌት በትክክለኛ እድሜ ላይና በመስፈርቱ መሰረት ለመምረጥ የሚያቸገር መሆኑንም ያ መላክታሉ።
ሁሉም ባለድርሻ አካል በችግሩ ውስጥ የተዘፈቀ በመሆኑ ሀገር ከፍተኛ ባለሙያዎቿን ይዛ ቁጭ ብላ ችግሩ የቱ ጋር ነው? እና ወደ ፊት ምን መደረግ ይኖርበታል? የሚለውን በመወያየት አዲስ ስርዓትን መጀመር ያስፈልጋልም ይላሉ። ለዚህም የወጣቶችን ውድድርን በማቆም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን፣ ባለሙያዎችን ሌሎችን ያካተተና ጥናት በማዘጋጀት እና የሚያስተምር ስርዓትን መፍጠር ይገባል።
የትምህርት እና ስልጠና፣ የውድድርና ተሳትፎ መስመሩም ግንኙነት መፈተሽ ይፈልጋል። የአራቱም ዓመት ጥናት እና ማስረጃ መኖሩንም ጠቅሰው፣ ከዚህ የሚበልጥ አጀንዳ መኖር የለበትም ይላሉ። ለችግሩ መፈጠር የሁሉም እጅ ያለበትን በመሆኑ እከሌ እከሌ ሳይባል ቁጭ ብለን ልንወያይ ይገባልም ብለዋል።
በሃዋሳ የኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መቅደስ ማሞ በበኩላቸው፣ የእድሜ ዶፒንግ ላይ ጥናት ለመስራት ሃሳቡ ቢኖርም ያልተሳካው የፋይናንስና እቅድ ማጽደቅ እጥረት በመኖሩ እንደሆና ይናገራሉ። አትሌቲክሱን የሚገድለው የእድሜ ማጭበርበር እንደሆነ ከፌዴሬሽኑ የሕክምና ክፍል ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ያስታውሳሉ። ችግሩ የት እንዳለ ለመለየት እና መፍትሄውን ለማመላከት ጥናትና ምርምር መደረግ እንደሚኖርበትም አክለዋል።
በተጨማሪም የእድሜ ተገቢነት (ኤጅ ዶፒንግን) የሚቆጣጠር አካል (ተቋም) ቢኖርና ተጋግዞ ቁጥጥሩ ቢጠናከር የተሻለ ሳይንሳዊ እንደሚሆን ያነሳሉ። ይህም ስጋት እየሆነ የመጣውን የእድሜ ጉዳይን በዘላቂነት ሊፈታ ይችላል። ይሄንን የሚያበረታታና የጥናትና ምርምር ክፍል ከዩኒቨርሲቲና ከባለሙያዎች ተውጣቶ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማሳተፍ ቢቻል መፍትሔ ለማግኘት ይረዳል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም